Get Mystery Box with random crypto!

የስብዕና ልህቀት

የቴሌግራም ቻናል አርማ human_intelligence — የስብዕና ልህቀት
የቴሌግራም ቻናል አርማ human_intelligence — የስብዕና ልህቀት
የሰርጥ አድራሻ: @human_intelligence
ምድቦች: መዝናኛዎች
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 89.04K
የሰርጥ መግለጫ

በዚህ ቻናል
⚡ህይወትን የሚያንፁ የስነ-ልቦና ምክሮች
⚡መሳጭ የፍቅር ታሪኮች እና ወጎች
⚡ጥልቅ ማህበራዊ እና ፍልስፍናዊ እይታዎች
⚡ውብ የጥበብ ስራዎች
በፅሁፍ እና በድምፅ/Audio ይቀርባሉ።
#ሼር በማድረግ ወዶጅዎን የዚህ የእውቀት እና የጥበብ ድግስ ታዳሚ እንዲሆኑ ይጋብዙ።

Ratings & Reviews

4.00

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

2

3 stars

0

2 stars

0

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 8

2023-03-20 22:09:05 ኤፒክቲተስ- 2

ክስቶችን እንደ አፈጣጠራቸው ይቀበሏቸው

ነገሮች የእርስዎን መሻትና ፍላጎት ብቻ ተከትለው እንዲከናወኑ አይጠብቁ፤  ነገሮችን እንደ አፈጣጠራቸው ይቀበሏቸው፡፡ በዚህ መንገድ ብቻ ሰላም የሚቻል ይሆናል፡፡

ሁኔታዎች የእኛን ምኞትና ጥባቆት ለማሟላት ብቻ አይከናወኑም፡፡ ክስተቶች የሚከናወኑት በራሳቸው ተፈጥሯዊ መንገድ ነው፡፡ ሰዎች የሚያደርጉትን የሚያደርጉት በራሳቸው መንገድ፣ ጸባይ ነው፡፡
የሚያገኙትን ነገር ይቀበሉ፡፡

ከሐሳዊ ስቃይ ለመዳን ዓይንዎን ይክፈቱ፤ ነገሮችን በተፈጥሯዊ ማንነታቸው ብቻ ይገንዘቧቸው፡፡ የሚያስደስቱዎትን፤ ጥገኛ የሆኑባቸውን ነገሮች፤ የሚያደንቋቸውን ሰዎች ልብ ብለው ያንሰላስሏቸው እስቲ፡፡ የነገሮቹ ተፈጥሮአዊ ስሪትና ክንውን እርስዎ ለነገሮቹ ካለዎት ግምት ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡

@Human_Intelligence
848 views19:09
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-20 20:27:07 ኤፒክቲተስ-1

አቅምዎን ይወቁ

ደስታ እና ነጻነት ሊቆጣጠሯቸው የሚችሏቸውና የማይችሏቸውን ነገሮች ከመለየት ይጀምራሉ፡፡ የተወሰኑ ነገሮች በእኛ የቁጥጥር ማዕቀፍ ውስጥ ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ናቸው፡፡
ይህን መሠረታዊ መርህ በቅጡ ሲገነዘቡና ሊያዝዟቸው የሚችሏቸውን ነገሮች፤ ሊያዟቸው ከማይችሏቸው መለየት ሲችሉ ብቻ ስክነትና ውጤታማነት የሚደረስበት ይሆናል፡፡
እኛን ምቾት የሚነሱን ምኞቶቻችን፣ ጉጉቶቻችን፣ የግል ሐሳቦቻችን በእኛ ቁጥጥር ውስጥ ናቸው፡፡ ልናዝዛቸው እንችላለን፡፡ ልንጨነቅባቸውም ይገባል፡፡ ምክንያቱም በትክክል ልናዝዛቸው የምንችለው እነሱን ብቻ ስለሆነ፡፡ በውስጣችን በሚላመለሱ ዕረፍት በሚነሱን ጉዳዮች ላይ ለመወሰን ዘወትር ምርጫዎች አሉን፡፡

የሰውነት አካላችን መጠንና ሁኔታ፣ የምንወለድበት ቤተሰብ የሐብት መጠንና የድህነት ሁኔታ የመሳሰሉት ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ያሉ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ከእኛ አቅም በላይ ስለሆኑ ልንጨነቅባቸው የተገባ አይሆንም፡፡ ልንቆጣጠራቸው፤ ልናዝዛቸው የማንችላቸውን ነገሮች ለመዳኘት መሞከር ትርፉ ዕረፍት የለሽነትን መከናነብ ብቻ ነው፡፡
አስታውሱ - በእኛ የማዘዝ ሥልጣን ውስጥ ያሉ ነገሮች አስቀድሞውኑም በተፈጥሮ ስልተ ሥሪት ያለ ገደብ፣ ያለከልካይ መዳፎቻችን ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ያሉ ነገሮች፤ በሌሎች የሚወሰኑ፤ ተለዋዋጭና የማያስተማምኑ ናቸው፡፡ በድጋሜ አስታውሱ በተፈጥሮአዊ ቅኝታቸው ከእናንተ የማዘዝ ኃይል ውጭ የሆኑ ነገሮችን ለመቆጣጠር፣ ለመዳኘት፣ የራስ ለማድረግ መሞከር ትርፉ ብስጩ፣ ስሕተት ፈላጊ እና ነጭናጫ ሰው መሆን ይሆናል፡፡


@Human_Intelligence
1.8K viewsedited  17:27
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-18 20:22:51 እንደምን አናፍር ፣ እናፍራለን እንጂ
( ዓለማየሁ ገላጋይ )

፨፨፨

አንዳንዴ እንዲህ ማሰብ ጥሩ ነው...
" ሰው ማለት በዛሬና በነገ መካከል የሚዘል ተጫዋች ነው፣ " ይላሉ ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ። እኛን ሳይጨምር የሰው ልጅ ታሪክ ይሄው ነው ። በዛሬ እና በነገ መካከል መዝለል ነው ። በ'እኛ ሀገር ፣ የዛሬ' ጌታ 'ነገ' አይደለም 'ትናንት' ነው ። ዛሬ ያለውን ነገ በሚኖረው ሳይሆን፣ ዛሬ የደረሰውን በትናንት ዳኝነት በመመዘን እንከፋፈላለን ፊታችን ወደ ነገ ሳይሆን ፣ ወደ ትናንት ነው ። ነገ'ን ያላየ "ትውልዱን" አይሰራም...

ወላጆቻችን "ትናንትን"ን ሲመለከቱ ያለ ዕቅድ ተወለድን ። እኛም ወላጆቻችን ትኩረታችንን ወስደውብን ያላሰብናቸው ተወላጆቻችንን እሥራችን አገኘናቸው ። ወፍ እንኳን ጎጆ የምትሰራው ዕንቁላል መጣል ስታስብ ነው ። የእኛ ጎጆ የሚቀለሰው "ትናንት" ለተባለው የገማ እንቁላል መንከባከቢያ ነው ። የትውልድ ቅብብላችን ባዶ ጭንቅላት እና ባዶ መሬት የሆነው ፊታችን ወደ ኋላ ስለዞረ ነው ።



ኑሮአችን፣ ሕይወት ማቆያችን፣ መሸጋገሪያ መንገዳችን ሁሉ ራሳችንን ለሌሎች ሰዎች ስለ መተዋችን ማረጋገጫዎቻችን ናቸው ። የምንለብሰው፣ የምንጎርሰው የሌሎች ሕዝቦችን በስራ የተጠመቀ ላብ ነው ። እንደ ቅማል፣ እንደ ትኋን፣ እንደ ጥገኛ ትል የተፈጠርነው የሌሎችን ደም ለመምጠጥ ነው? የትኛውን የዓመት ልብስ በማሰብ እና በመሥራት ከወንን?
አንዳንዴ እንደዚህ ማሰብ ጥሩ ነው...
...መጉረስ እና መልበስ የመርከብን ያህል ገዝፎ ከፊታችን ቢገተርም፣ እሱን ተላልፈን፣ ትናንት ላይ እናተኩራለን ። ከዛሬ መሪዎች በላይ በትናንት የትናንት አከናዋኞች መዝገባችንን ሞልተዋል ። ያላየናቸው ትውልዶች በ'የ አደባባዩ ተርመስምሰዋል ።

...የሰው ልጅ ሁሉ ጭራ ነን ሰውነታችን የሚያጠራጥረን፤ የሰው ልጅ ከፍታው ሥር ነን፤ የድቅታው ምሳሌዎች ፣ የታጥቦ ጭቃነቱ ማሳያዎች ነን! የሰው ልጅ ዘወር ብሎ ሲያየን፣ የኋላው ማፈሪያዎች ነን! ጥሎ ያለፈውን እንኖራለን፤ ግጦ የጣለውን እናነሳለን፤ ለብሶ የጨረሰውን ለክብር እንደርባለን ። ምንም የሚያኮራ ነገር የለብንም ።...
አንዳንዴ እንዲህ ማሰብ ፈውስ ነው ..



"በእከሌነቴ እኮራለሁ!" ያለ ውስጡ የተከማቸው ወራዳነት ነው ። ከጠይምነታችን በላይ እኛን አንድ የሚያደርገን የሰው ልጅ ሁሉ ማፈሪያነታችን ነው። በሚያሳፍር ኮርቶ መገኘት እብደት ነው። የሚወቀስ እንጂ የሚያኮራ ወላጅ የለንም፤ የሚረገም እንጂ፣ የሚወደስ ብሔር የለንም፣ የምናፍርበት እንጂ፣ የምንኮራበት ወንዝ የለንም...ቅብብሎሻችን ወቀሳ እና ውርደት ነው ።

...አንዳንዴ እንዲህ ማሰብ ደግ ነው...

እንኮራለን ባህልም እንለዋለን ። በበሬ ማረስ፣ ሣር አጭዶ ማበጠሪያ መስፋት፣ እኽል በድንጋይ ወፍጮ ሰልቆ ማገንፋት፣ ሥጋ ጥሬውን መብላት...እንዴት አደባባይ የሚሰጣ ኩራት እንደሚሆን ግራ ያጋባል ። ዘፈኖቻችን እና ውዝዋዜዎቻችንን የምንደሰትባቸው በልምድ ስለ'ተጣቡን እንጂ፣ ጥበብ ስለሆኑ አይደለም ። የሰው ልጅ በአንድ ወቅት የነበረበት ዛሬም የመገኘታችንን ውርደት እንደ ቅርስ ቆጥረን "እንሞትለታለን!" እንላለን ። "በዛሬ እና በነገ" ሳይሆን፣ በዛሬ እና በትናንት መካከል የምንዘልል ተጫዋች መሆናችን እና ወደፊት እንዳናይ መጋረዳችንን "ውርስ" አድርገን በማስቀጠል ላይ ነን ።

...አንዳንዴ...

፨፨፨

ምንጭ ከፍትሕ መጽሔት ላይ የተቀነጨበ
ዓለማየሁ ገላጋይ

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
2.3K viewsedited  17:22
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-07 20:52:20 የተካደ ትውልድ
(በእውቀቱ ስዩም)
የተካደ ትውልድ
አይዞህ  ባይ የሌለው
ታዳጊ የሌለው
ወይ ጠባቂ መላክ፥ ወይ አበጀ የሚለው
ደርሶ ከቀንበሩ ፥የማይገላግለው፤

የተካደ ትውልድ

አብዝቶ የጾመ፥ ተግቶ የጸለየ
ጥቂት መና ሳይሆን፥ ጥይት  ሲዘንብ ያየ
እድሜ ይፍታህ ተብሎ፥ የተወለደ ለት
አምባሩ ካቴና፥ ማተቡ ሰንሰለት፤

ምቾትን የማያውቅ፥ ረፍት የተቀማ
አልጋው ያጋም እሾህ፥ መኝታው የሳማ፤

የተካደ ትውልድ

ሞቶ እንኳን ሬሳው፥ አይላላለት ቀንበር
በዘብ እጅ ተገድሎ ፥ በሹም የሚቀበር
ከጡት አስጥል በላይ፥ ኑሮ የመረረው
እንዳይሄድ ጎዳናው ፥ የተደናገረው
ድል ያልሰመረለት ፥ትግል ሳይቸግረው።

የተካደ ትውልድ
በስጋ በነፍሱ
በቀልቡ በገላው
ከቶ ምንድን ይሆን?
ምንድን ይሆን መላው?

#በእውቀቱ_ስዩም

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
1.7K viewsedited  17:52
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-05 13:40:39 #ህይወት_ፈተና_ነው

በጣም ከምወዳቸው ጥቅሶች አንዱ “ህይወት ፈተና ነው። ፈተና ባይሆን ኖሮማ በእያንዳንዱ ሁኔታ የት መሄድ፤ ምን ማድረግ እንዳለብን ይነገረን ነበር።” ይላል። ይህን ወርቃማ ጥቅስ ባሰብኩ ቁጥር በህይወት ውስጥ ሁሉን ማካበድ እንደሌለብኝ ይሰማኛል።

ህይወትንና በውስጧ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን እንደፈተና ማየት ስትጀምር የሚያጋጥሙህን ችግሮች ለማደግ እንደሚረዱ እድሎች መመልከት ትጀምራለህ። ተከታታይ ችግሮች፣ ተደራራቢ ሀላፊነቶችና  የማይታለፉ የሚመስሉ ጉዳዩች ጭምር ከነገሮቹ በላይ እንድትሆን ለመፈተን የሚቀርቡ እድሎች ይሆናሉ። ነገር ግን በተቃራኒው የሚያጋጥሙህን ጉዳዮች ሁሉ እንደ የሞት ሽረት ትግል የምትመለከታቸው ከሆነ ህይወት ኮሮኮንች መንገድ ይሆንብሀል። “ደስተኛ የምሆነው ሁሉም ነገሮች የተስተካከሉ ሲሆኑ ብቻ ነው!” ብለህ ትደመድማለህ። የሚያሳዝነው ሁሉም ነገሮች የተስተካከሉ የሚሆኑት ከስንት አንዴ ነው።

ነገሮች አስቸጋሪ ሲሆኑ ለሙከራ ያክል ይህን መንገድ ሞክረው። ምናልባት የሚያስቸግር ወንድም ወይም የሚያስጨንቅ አለቃ ይኖርሀል። ለሙከራ ያክል የሚያጋጥምህን ሁኔታ “ችግር” ከማለት “ፈተና” ብለህ ጥራው። በሁኔታው ከመናደድ ከሁኔታው መማር የምትችለውን ነገር ፈልግ። “ይህ ነገር በህይወቴ ለምን ተከሰተ?” እንዴት በተለየ መንገድ ልመለከተው እችላለሁ? የሆነ አይነት ፈተና ይሆን?” ብለህ ራስህን ጠይቅ።

ይህንን ስትራቴጂ ከሞከርክ ለነገሮች የሚኖርህ ምላሽ ሲለወጥ አይተህ መገረምህ አይቀርም። "ጊዜ ያጥረኛል" በሚል ሀሳብ እቸገር ነበር። ሁሉንም ነገሮች ለማከናወን እሯሯጣለሁ። የፕሮግራሜ መጣበብ፣ መስሪያ ቤቴን፣ ቤተሰቤን በአጠቃላይ ጊዜዬን እየተሻሙ የመሰሉኝን ነገሮች ሁሉ እወቅሳለሁ። ከዛ ድንገት ብልጭ አለልኝ። ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልገው አንዳንዱን ነገር በደንብ መስራት ሳይሆን የሚችሉትን ያክል ሰርቶ የቀረውን “ስራው ያውጣው!” ብሎ መተው መቻል ነው። በሌላ አነጋገር ችግሮችን እንደፈተና ማየት ስጀምር በፊት በጣም ያሳስቡኝ የነበሩትን ችግሮች በቀላሉ መወጣት ችያለሁ። ይሁን እንጂ አሁንም አልፎ አልፎ ጊዜ እያጠረኝ እንደምቸገር ግን አልክድም።

ቀላሉን ነገር አታካብድ መፅሐፍ
ዶ/ር ሪቻርድ ካርሰን ትርጉም ከዶ/ር ዮናስ ላቀው

@Human_Intelligence
2.5K views10:40
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-03 20:26:23 ከሰው ጋር አብሮነት አለኝ?

“በአብዛኛው ማሕበራ ልምምዳችሁ በስራ፣ በጓደኝነትም ሆነ በፍቅር ግንኙነት አብሯችሁ ካለ ሰው ጋር ካላችሁ ልዩነት ይልቅ አንድ አይነትነት ከበዛ እና ለወዲፊትም አብሮ የመቀጠል ጉጉትና ፍላጎት እንዳላችሁ ከተሰማችሁ በእርግጥ ጤናማ ናችሁ፡፡ ይህ ሁኔታ በአንድ ግንኙነት ላይ ወይም በአንድ መስክ ላይ ፍሬያማ እስከምንሆን ድረስ ለረጅም ጊዜ የመቆየት ብቃታችንን አመልካች ነው፡፡ በገባንበት ቦታም ሆነ ግንኙነት ውስጥ የሚጎላው ልዩነታችንና አለመስማማታችን ከሆነ ባለን የሰው-ለሰው ግንኙነት ወይም ማሕበራ ብልህነት ላይ መስራት እንዳለብን ጠቋሚ ሊሆን ይችላል፡፡”

ከመፍትሄ ሃሳብ ጋር ሲብራራ፡-

ምናልባት ሕይወታችሁን በዚህ ሁኔታ ላይ ካገኛችሁት በመጀመሪያ ማድረግ ያለባችሁ ይህ ሁኔታ ለምን እንደተከሰተ መንስኤውን ማግኘት ነው፡፡

ከማሕበራዊ ግንኙነት ውጪ መኖር አንችልም፡፡ ስለሆነም በሁኔታው የመብሰላችን ጉዳይ እጅጉን አንገብጋቢ ነው፡፡ ያለንን ማሕበራ ኑሮ ወይም የሰው-ለሰው ግንኙነት ከሚወስኑ ሁኔታዎች አንዱ የራሳችን ምልከታ ነው፡፡ ሰዎችን፣ የሰዎችን ንግግር፣ የሰዎችን ተግባር፣ ሕብረተሰቡን እና በዙሪያችን የሚከናወነውን የምናይበት ምልከታና እይታ ለምንሰጠው ምላሽ ወሳኝ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ ሲዛባ ከሰዎች ጋር ውለን፣ አድረን መክረም ስለማንችል የጀመርናቸውንም ነገሮች የማስቀጠል እድሉንና አቅሙንም ይወስደዋል፡፡ ማሕበራዊ ግንኙነታችንን የተረጋጋ ማድረግን ከፈለግን የሚከተሉት ልምምዶች ማሰብና መተግበር እንችላለን፡፡


1. የሁኔታዎችን ድግግሞሽ ማጤን

ሁል ጊዜ አስቸጋሪ ሰዎችን የመጋፈጣችን አይቀሬነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሄድንበት ስፍራ ሁሉ፣ ከሁሉም ሰው ጋር ችግር የሚፈጠር ከሆነ ግን በመጀመሪያ ችግሩ እኔው ጋር ሊሆን የመቻሉን ጉዳይ መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡

ምንም ቢሆን ሁሉም ሰው ክፉ ሰው እንደሆንኩኝ፣ አስቸጋሪ ሰው እንደሆንኩኝ፣ የማልመች ሰው እንደሆንኩኝ . . . ሊያየኝና ሊቆጥረኝ አይችልም፡፡ ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ ግን በእርግጥም እንደዚያ የመሆኔን ጉዳይ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ምናልባት እንደዚያ እንዳልሆንኩኝ እርግጠኛነቱ ካለኝና እኔ እየመሰለኝ ከሆነ ደግሞ የአመለካከቴን ጤናማነት ማጤንና እዚያ ላይ መስራት አስፈላጊ ነው፡፡

2. ራስን መቀየርን ማስቀደም

ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት አስቸጋሪ የሆነ ሲመስለን በአብዛኛው የሚቀናን ሰውንና ስፍራን መቀየር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ጊዜያዊ መፍትሄ ቢሰጠንም ዘላቂ መፍትሄ ግን አያመጣም፡፡

ስፍራንና ሰውን ከመቀያየር በፊት በቅድሚያ ራስን መቀየር የተሻ ነው፡፡ መቀየር የማንችለውን የሰውን ሁኔታ ለመቀየር ከምንታገል፣ መቀየር የምንችለውን ራሳችንን መቀየር ይቀላል፣ ተመራጭም ነው፡፡ ሰዎችን ለመቀየርና ለመለወጥ ከታገልን በኋላ ተቀየሩም አልተቀየሩም ነገ ከእኛ ሲሄዱ፣ ሌሎች መቀየር የምንፈልጋቸው ሰዎችን እንተካለን፡፡ ራሳችንን ከለወጥን ግን የተለወጠ ማንነት ይዘን እንሄዳለን፣ ከራሳችን መለየት አንችልምና::

3. በማበራዊ እና በስሜት ብልህነት መብሰል

ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት የሰመረና ቀጣይ እንዲሆን ካስፈለገ ከላይ የጠቀስናቸውን፣ የሁኔታዎችን ድግግሞሽ በማጤን ራስን የመመልከትን እንዲሁም  ሰዎችን ለመቀየር ከመታገል ይልቅ ራስን መቀየርን ማስቀደም ከመለማመድ ባሻገር በጥበብ እየበሰልን እና እያደግን የመሄዳችንን ጉዳይ እውን ማድረግ መልካም ነው፡፡

ይህንን የማድረጊያው ቀላሉ መንገድ የማሕበራዊ እና የስሜት ብልህነታችንን በማሳደግ መቀጠል ነው፡፡ በአጭሩ በአካባቢያችን ከሚገኙ አስቸጋሪ ሰዎች ተሽሎ የመገኘትን ሁኔታ ማዳበር ማለት ነው፡፡

ተፈጸመ!    
 
ዶ/ር እዮብ ማሞ
@Human_Intelligence
2.1K views17:26
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-03 19:21:05 ድሆች ነን! በድህነት የተነሳ ብዙ ነገራችንን ያጣን አሳዛኝ ድሆች ነን።

ለማጣታችን ብዙ ሰበብ መደርደር እንችላለን። አገዛዞቻችን ግን ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው። በዘመናት መሓከል ወደ መንበር የወጡ የኢትዮጵያ መሪዎች የሚያበጁት ስርኣት የንጥቂያ ነው። ዜጎች በጭካኔ እንዲበዘበዙ ሆነዋል።

በነገስታት ዘመን፥ ገበሬዎች ጭሰኛ ሆነው የድካማቸውን ውጤት መሳፍንቱ በልተዋል። አምራቾች በገዛ ሃገራቸው ባይተዋር ተደርገው ልፋታቸውን ሌሎች ጠግበውበታል። ገበሬው ገባር ነበር!

ደርግ ገበሬውን ከጭሰኝነት አላቅቄያለሁ ቢልም በተራው አስገባሪ ሆኗል። ሰዎች በገዛ ድካማቸው ያመረቱትን በነፃነት እንዳይሸምቱ ገደብን አበጅቷል። በሰበብ አስባብ የዜጎችን ሃብት ቀምቷል።

ኢህአዴግ እና ብልፅግና "ከቀደሙት እሻላለሁ" ቢሉም ነገራቸው ተመሳሳይ ነው። ሆነ ብለው ኢንፍሌሽን በመፍጠር ዜጎችን ይመዘብራሉ። የገንዘብን የመግዛት አቅም በማሽመድመድ የራሳቸውን ኔት ወርክ ያበለጥጋሉ።

በሐገራችን ወደ መንበር የሚወጡት ሁሉ ቀማኞች ናቸው።

ዜጎች በገዛ ንብረታቸው ላይ ነፃነት የላቸውም።

መንግስት ያስፈለገው ለዜጎች ዋስትና እንዲሰጥ ቢሆንም እኛ ለዚህ አልታደልንም።

ያለ ነፃነት ከድህነት መውጣት አይቻልም! "መብታችንን ስጡን፥ ዳቧችንን እኛው እንጋግራለን" ማለት መጀመር አለብን !


@Tfanos

@Human_Intelligence
2.5K viewsedited  16:21
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-02-27 20:22:44 ሶስቱ የጤናማ ሕይወት ምልክቶች!

ሕይወታችሁ ጤናማ ሂደት ላይ መሆኑን ለማወቅ ከፈለጋችሁ መጠየቅ ከምትችሏቸው ወሳኝ ጥያቄች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

1. የውስጥ ብርታት አለኝ?

ማታ እቤታችሁ ስትገቡ ምንም እንኳን ከቀኑ ስራና ውሎ የተነሳ አካላችሁ ቢደክምም፣ የስሜትና የስነ-ልቦና ጥንካሬ እንዳላችሁ ከተሰማችሁ በእርግጥ ጤናማ ናችሁ፡፡

አያችሁ አንዳንድ ሰዎች እኮ ምንም ነገር ሳያሰሩ እንኳን ውስጣቸው ይዝላል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ የሆነ የተዛባ ነገር እንዳለ አመላካች ነው፡፡

2. የነገ ተስፋ አለኝ?

ከዛሬው የኑሮም ሆነ ሌሎች የሕይወታችሁ ሁኔታዎች የነገው እንደሚሻል ተስፋውም ሆነ ለዚያ የመስራት አቅሙ እንዳላችሁ ከተሰማችሁ በእርግጥ ጤናማ ናችሁ፡፡

ምንም እንኳን አሁን የምንኖረው ኑሮ ለእኛ የሚመጥን እንዳልሆነና እንኖረዋለን ብለን ቀድሞ ስናስበው የነበረው አይነት ባይሆንም፣ ዋናው ቁም ነገር ነገን ስናስብ ወደ ለውጥ እየሄድን እንደሆነ የማሰባችን ጉዳይ ነው፡፡ ያንን ማድረግ እስማንችል ድረስ ከጨለመብን፣ የሆነ መስተካከል ያለበት ሁኔታ እንዳለ ጠቋሚ ነው፡፡  

3. ከሰው ጋር አብሮነት አለኝ?

በአብዛኛው ማሕበራ ልምምዳችሁ በስራ፣ በጓደኝነትም ሆነ በፍቅር ግንኙነት አብሯችሁ ካለ ሰው ጋር ካላችሁ ልዩነት ይልቅ አንድ አይነትነት ከበዛ እና ለወዲፊትም አብሮ የመቀጠል ጉጉትና ፍላጎት እንዳላችሁ ከተሰማችሁ በእርግጥ ጤናማ ናችሁ፡፡

ይህ ሁኔታ በአንድ ግንኙነት ላይ ወይም በአንድ መስክ ላይ ፍሬያማ እስከምንሆን ድረስ ለረጅም ጊዜ የመቆየት ብቃታችንን አመልካች ነው፡፡ በገባንበት ቦታም ሆነ ግንኙነት ውስጥ የሚጎላው ልዩነታችንና አለመስማማታችን ከሆነ ባለን የሰው-ለሰው ግንኙነት ወይም ማሕበራ ብልህነት ላይ መስራት እንዳለብን ጠቋሚ ሊሆን ይችላል፡፡

እነዚህ ሶስት ልምምዶች ከዛሬው ባሻገር አልፋችሁ ወደ ተሻለ ነገር እንዳትዘልቁ የሚያደርጉ ነገሮችን ከላይ ከላዩ እንድትቀርፉ የሚያግዙ ጠቋሚች ናቸው፡፡

ዶ/ር እዮብ ማሞ
@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
1.8K views17:22
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-02-14 07:28:52 የልማድ ምስጢር

ብዙ ሰዎች እንዲህ ሲሉ ይደመጣሉ፡- “በአንድ አሳብ፣ ንግግር ወይም ጽሑፍ እነሳሳና አንድ ነገር እጀምራለሁ፣ ነገር ግን ብዙ ሳይቆይ አቆመዋለሁ”፡፡ ይህ ችግር የብዙ ሰዎች ችግር ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በርካታ ማሰብና መለማመድ የሚገቡን እውነታዎች ቢኖሩም መሰረታዊውና ዋናው ግን በመነሳሳት፣ በዲሲፕሊን፣ በድግግሞሽና በልማድ መካከል ያለውን ግንኙነትና ልዩነት ማወቅ ነው፡

መነሳሳት የሚገናኘው አንድን ጤና ቢስ ነገር ለማቆም ወይም አንድን መልካም ነገር ለማድረግ ካለን የመፈለግ ስሜት ጋር ነው፡፡

ዲሲፕሊን የሚገናኘው መቆም የፈለግነውን ነገር ለማቆም ወይም ማድረግ የፈለግነውን ነገር ለማድረግ ራስን ከማስገደድ ጋር ነው፡፡

ድግግሞሽ የሚገናኘው ማቆም በፈለግነው ወይም መጀመር በፈለግነው ነገር አንጻር ራሳችንን እየተቆጣጠርንና ዲሲፕሊን እያደረግን አንድን ነገር ካለማቆም ከመደጋገም ጋር ነው፡፡

ልማድ የሚገናኘው ምንም ሳናስብበት፣ ሳንጨነቅና ሳንገደድ አንድን ነገር ለማቆም ወይም ለማድረግ ካለን ብቃት ጋር ነው፡፡ አንድ ልምምዳችን ወደ ልማድ ደረጃ መድረሱን የምናውቀው ያንን ነገር ለማድረግ ምንም አይነት የሚቀሰቅሰን (መነሳሳት) ወይም የሚጫነን (ዲሲፕሊን) ነገር ሳይኖር ማድረግ ስንጀምር ነው፡፡

ማንኛውም ሰው አንድን መልካም ልምምድ ወደ ልማድ ደረጃ እስከሚያደርሰው ድረስ ስኬታማነቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ስለዚህም፣ በመነሳሳት የተጀመረን ነገር ወደ ዲሲፕሊን ደረጃ ማድረስ አስፈላጊ ነው፡፡ ራሳችንን ወደመጫንና ዲሲፕሊን ያደረግንበትን ነገር ደግሞ ልማድ እስኪሆን ድረስ መደጋገም አስፈላጊ ነው፡፡

ሁል ጊዜ በመነሳሳት የሚሰራ ሰው መነሳሳቱ ሲያቆም እሱም ያቆማል፡፡ ሁል ጊዜ በዲሲፕሊን ላይ የሚደገፍ ሰው አንድ ቀን ራስን መጫንና ማስገደድ ይሰለቸውና ወይም ዲሲፕሊን የሚደርገው ሰው ወይም ሁኔታ ሲያቆም አንድ ቀን ያቆማል፡፡ ከዲሲፕሊን ደረጃ አልፎ አንድን ነገር እስኪለምደው ድረስ ድግግሞሽ ደረጃ የዘለቀ ሰው ወደ ልማድ ቀጠና ያልፋል፡፡ በልማድ የሚሰራ ሰው ራስ-ሰር (Automatic) ስልት ውስጥ ስለገባ ሁኔታው ዝም ወደሚፈስለት ደረጃ ያልፋል - ውጤቱም ልህቀትና ስኬት ይባላል፡፡

ለምሳሌ፣ ጠዋት ስትነሳ ማንም ሳያስታውስህና ማስታወሻ ደወል ሳታደርግ የምታደርጋቸውን ነገሮች አስባቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ልማድ ደረጃ የደረሱ ስለሆነ ለማስታወስ፣ ለመነሳሳትና ለማድረግ ምንም አድካሚ አይደሉም፡፡

በሕይወትህ ስኬታማ መሆን የምትፈልግበትን ነገር ለይና በዚያ ጉዳይ ላይ በመነሳሳት ጀምረህ፣ ወደ ራስን ማስገደደ (ዲሲፕሊን) በማለፍ ልማድ እስኪሆን ድረስ መደጋገም የግድ ነው፡፡ አንድን ነገር ጀምረህ የምታቆመው ነገሩ ልማድ እስኪሆን ስላልተነሳሰህና ራስህን ዲሲፕሊን ስላላደረከው ነው፡፡ በሕይወትህ ማቆም ያቀተህ አጉል ነገር ሁሉ አስበው፣ ልማድ እስኪሆን ስለደጋገምከው ነው፡፡ ጤና ቢስም ነገር እኮ ለዚያ ነገር ተነሳስተን ጀምረነውና ደጋግመነው ነው የልማድን አቅም ያገኘው፡፡

እንደገና ልድገመውና፣ ልማድን ለመጀመር መነሳሳት አስፈላጊ ነው፡፡ መነሳሳት ግን ራስን ዲሲፕሊን ማድረግ ደረጃ ካለደረሰና ወደ እንቅስቃሴ ካልተለወጠ የትም አይሄድም፡፡ ማንኛውም እንቅስቃሴ ደግሞ ወደ ድግግሞሽ ካልዘለቀ ልማድ አይሆንም፡፡

ዶ/ር እዮብ ማሞ
@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
2.9K viewsedited  04:28
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-02-12 21:39:24 እንዴት ንጉስ መሆን ይቻላል-ማኪያቬሊ

ወደ ላይ መውጣት ከፈለግክ የግድ የበታቾችህን መጨፍለቅ ይኖርብሃልን? ስኬት የሚመጣው ሰዎችን በማታለል እና በክፋት ውስጥ ብቻ ነውን?

ስለምንድን ነው በአብዛኛው ዘርፍ ላይ ከላይ የሚሆኑ ባለ ስልጣናት ወይም አለቆች የእብደት ጠባይ ያላቸው?
የዲፕሎማቱ እና ፈላስፋው ማኪያቬሊ መጽሐፍ የሆነው The Prince ለዚህ መልስ አለው። ይህ አጭር መጽሐፍ እንዴት ምርጥ እና ስኬታማ መሪ እንደምትሆን ያሳይሃል፡፡ ምርጥ መሪ ማለት መልካም መሪ የሚል ቀጥተኛ ትርጓሜ የለውም፡፡ ምርጥ መሪ በምንም አይነት መንገድ ስልጣኑን የሚያስጠብቅ መሪ ነው። ይህ መሪ ያጭበረብራል፣ ይሰርቃል፣ ህዝቡን ያታልላል ሆኖም በመጨረሻ የሀገሪቷን ሰላም እና ደህንነት በሚገባ ያስጠብቃል፡፡ የራሱን የስልጣን ዘመን ያራዝማል፡፡

በመጽሐፉ ውስጥ እነዚህን ምክሮች እናገኛቸዋለን፡፡
“በማታለል የምታገኘውን ነገር ኃይል በመጠቀም ለማሸነፍ አትሞክር”

“ፍቅር እና ፍርሃት በአንድ ሊኖሩ ስለማይችሉ... ከመወደድ ይልቅ መፈራትን ምረጥ”

“በንጉስህ ላይ ከተኮስክ ላለመሳትህ እርግጠኛ ሁን”

አሁን ላይ ማኪያቬሊ ይህን መጽሐፍ ባለ ስልጣኖች ላይ ለመሳለቅ የጻፈው ይሁን አልያም አቋራጭ የስልጣንን መንገድ ሊያሳየን፤ እርግጠኛ ሆነን መናገር አንችልም፡፡ ሆኖም የThe art of war ጸሐፊ - ሰን ዘ'ም ሆነ ማኪያቬሊ ስልጣን - በጭካኔ፣ በኃይል እና በማታለል እንደሚገኝ አሳይተውናል።

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
1.2K views18:39
ክፈት / አስተያየት ይስጡ