Get Mystery Box with random crypto!

ኤፒክቲተስ-1 አቅምዎን ይወቁ ደስታ እና ነጻነት ሊቆጣጠሯቸው የሚችሏቸውና የማይችሏቸውን ነገሮች | የስብዕና ልህቀት

ኤፒክቲተስ-1

አቅምዎን ይወቁ

ደስታ እና ነጻነት ሊቆጣጠሯቸው የሚችሏቸውና የማይችሏቸውን ነገሮች ከመለየት ይጀምራሉ፡፡ የተወሰኑ ነገሮች በእኛ የቁጥጥር ማዕቀፍ ውስጥ ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ናቸው፡፡
ይህን መሠረታዊ መርህ በቅጡ ሲገነዘቡና ሊያዝዟቸው የሚችሏቸውን ነገሮች፤ ሊያዟቸው ከማይችሏቸው መለየት ሲችሉ ብቻ ስክነትና ውጤታማነት የሚደረስበት ይሆናል፡፡
እኛን ምቾት የሚነሱን ምኞቶቻችን፣ ጉጉቶቻችን፣ የግል ሐሳቦቻችን በእኛ ቁጥጥር ውስጥ ናቸው፡፡ ልናዝዛቸው እንችላለን፡፡ ልንጨነቅባቸውም ይገባል፡፡ ምክንያቱም በትክክል ልናዝዛቸው የምንችለው እነሱን ብቻ ስለሆነ፡፡ በውስጣችን በሚላመለሱ ዕረፍት በሚነሱን ጉዳዮች ላይ ለመወሰን ዘወትር ምርጫዎች አሉን፡፡

የሰውነት አካላችን መጠንና ሁኔታ፣ የምንወለድበት ቤተሰብ የሐብት መጠንና የድህነት ሁኔታ የመሳሰሉት ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ያሉ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ከእኛ አቅም በላይ ስለሆኑ ልንጨነቅባቸው የተገባ አይሆንም፡፡ ልንቆጣጠራቸው፤ ልናዝዛቸው የማንችላቸውን ነገሮች ለመዳኘት መሞከር ትርፉ ዕረፍት የለሽነትን መከናነብ ብቻ ነው፡፡
አስታውሱ - በእኛ የማዘዝ ሥልጣን ውስጥ ያሉ ነገሮች አስቀድሞውኑም በተፈጥሮ ስልተ ሥሪት ያለ ገደብ፣ ያለከልካይ መዳፎቻችን ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ያሉ ነገሮች፤ በሌሎች የሚወሰኑ፤ ተለዋዋጭና የማያስተማምኑ ናቸው፡፡ በድጋሜ አስታውሱ በተፈጥሮአዊ ቅኝታቸው ከእናንተ የማዘዝ ኃይል ውጭ የሆኑ ነገሮችን ለመቆጣጠር፣ ለመዳኘት፣ የራስ ለማድረግ መሞከር ትርፉ ብስጩ፣ ስሕተት ፈላጊ እና ነጭናጫ ሰው መሆን ይሆናል፡፡


@Human_Intelligence