Get Mystery Box with random crypto!

እንደምን አናፍር ፣ እናፍራለን እንጂ ( ዓለማየሁ ገላጋይ ) ፨፨፨ አንዳንዴ እንዲህ ማሰብ ጥሩ | የስብዕና ልህቀት

እንደምን አናፍር ፣ እናፍራለን እንጂ
( ዓለማየሁ ገላጋይ )

፨፨፨

አንዳንዴ እንዲህ ማሰብ ጥሩ ነው...
" ሰው ማለት በዛሬና በነገ መካከል የሚዘል ተጫዋች ነው፣ " ይላሉ ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ። እኛን ሳይጨምር የሰው ልጅ ታሪክ ይሄው ነው ። በዛሬ እና በነገ መካከል መዝለል ነው ። በ'እኛ ሀገር ፣ የዛሬ' ጌታ 'ነገ' አይደለም 'ትናንት' ነው ። ዛሬ ያለውን ነገ በሚኖረው ሳይሆን፣ ዛሬ የደረሰውን በትናንት ዳኝነት በመመዘን እንከፋፈላለን ፊታችን ወደ ነገ ሳይሆን ፣ ወደ ትናንት ነው ። ነገ'ን ያላየ "ትውልዱን" አይሰራም...

ወላጆቻችን "ትናንትን"ን ሲመለከቱ ያለ ዕቅድ ተወለድን ። እኛም ወላጆቻችን ትኩረታችንን ወስደውብን ያላሰብናቸው ተወላጆቻችንን እሥራችን አገኘናቸው ። ወፍ እንኳን ጎጆ የምትሰራው ዕንቁላል መጣል ስታስብ ነው ። የእኛ ጎጆ የሚቀለሰው "ትናንት" ለተባለው የገማ እንቁላል መንከባከቢያ ነው ። የትውልድ ቅብብላችን ባዶ ጭንቅላት እና ባዶ መሬት የሆነው ፊታችን ወደ ኋላ ስለዞረ ነው ።



ኑሮአችን፣ ሕይወት ማቆያችን፣ መሸጋገሪያ መንገዳችን ሁሉ ራሳችንን ለሌሎች ሰዎች ስለ መተዋችን ማረጋገጫዎቻችን ናቸው ። የምንለብሰው፣ የምንጎርሰው የሌሎች ሕዝቦችን በስራ የተጠመቀ ላብ ነው ። እንደ ቅማል፣ እንደ ትኋን፣ እንደ ጥገኛ ትል የተፈጠርነው የሌሎችን ደም ለመምጠጥ ነው? የትኛውን የዓመት ልብስ በማሰብ እና በመሥራት ከወንን?
አንዳንዴ እንደዚህ ማሰብ ጥሩ ነው...
...መጉረስ እና መልበስ የመርከብን ያህል ገዝፎ ከፊታችን ቢገተርም፣ እሱን ተላልፈን፣ ትናንት ላይ እናተኩራለን ። ከዛሬ መሪዎች በላይ በትናንት የትናንት አከናዋኞች መዝገባችንን ሞልተዋል ። ያላየናቸው ትውልዶች በ'የ አደባባዩ ተርመስምሰዋል ።

...የሰው ልጅ ሁሉ ጭራ ነን ሰውነታችን የሚያጠራጥረን፤ የሰው ልጅ ከፍታው ሥር ነን፤ የድቅታው ምሳሌዎች ፣ የታጥቦ ጭቃነቱ ማሳያዎች ነን! የሰው ልጅ ዘወር ብሎ ሲያየን፣ የኋላው ማፈሪያዎች ነን! ጥሎ ያለፈውን እንኖራለን፤ ግጦ የጣለውን እናነሳለን፤ ለብሶ የጨረሰውን ለክብር እንደርባለን ። ምንም የሚያኮራ ነገር የለብንም ።...
አንዳንዴ እንዲህ ማሰብ ፈውስ ነው ..



"በእከሌነቴ እኮራለሁ!" ያለ ውስጡ የተከማቸው ወራዳነት ነው ። ከጠይምነታችን በላይ እኛን አንድ የሚያደርገን የሰው ልጅ ሁሉ ማፈሪያነታችን ነው። በሚያሳፍር ኮርቶ መገኘት እብደት ነው። የሚወቀስ እንጂ የሚያኮራ ወላጅ የለንም፤ የሚረገም እንጂ፣ የሚወደስ ብሔር የለንም፣ የምናፍርበት እንጂ፣ የምንኮራበት ወንዝ የለንም...ቅብብሎሻችን ወቀሳ እና ውርደት ነው ።

...አንዳንዴ እንዲህ ማሰብ ደግ ነው...

እንኮራለን ባህልም እንለዋለን ። በበሬ ማረስ፣ ሣር አጭዶ ማበጠሪያ መስፋት፣ እኽል በድንጋይ ወፍጮ ሰልቆ ማገንፋት፣ ሥጋ ጥሬውን መብላት...እንዴት አደባባይ የሚሰጣ ኩራት እንደሚሆን ግራ ያጋባል ። ዘፈኖቻችን እና ውዝዋዜዎቻችንን የምንደሰትባቸው በልምድ ስለ'ተጣቡን እንጂ፣ ጥበብ ስለሆኑ አይደለም ። የሰው ልጅ በአንድ ወቅት የነበረበት ዛሬም የመገኘታችንን ውርደት እንደ ቅርስ ቆጥረን "እንሞትለታለን!" እንላለን ። "በዛሬ እና በነገ" ሳይሆን፣ በዛሬ እና በትናንት መካከል የምንዘልል ተጫዋች መሆናችን እና ወደፊት እንዳናይ መጋረዳችንን "ውርስ" አድርገን በማስቀጠል ላይ ነን ።

...አንዳንዴ...

፨፨፨

ምንጭ ከፍትሕ መጽሔት ላይ የተቀነጨበ
ዓለማየሁ ገላጋይ

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence