Get Mystery Box with random crypto!

ከሰው ጋር አብሮነት አለኝ? “በአብዛኛው ማሕበራ ልምምዳችሁ በስራ፣ በጓደኝነትም ሆነ በፍቅር ግን | የስብዕና ልህቀት

ከሰው ጋር አብሮነት አለኝ?

“በአብዛኛው ማሕበራ ልምምዳችሁ በስራ፣ በጓደኝነትም ሆነ በፍቅር ግንኙነት አብሯችሁ ካለ ሰው ጋር ካላችሁ ልዩነት ይልቅ አንድ አይነትነት ከበዛ እና ለወዲፊትም አብሮ የመቀጠል ጉጉትና ፍላጎት እንዳላችሁ ከተሰማችሁ በእርግጥ ጤናማ ናችሁ፡፡ ይህ ሁኔታ በአንድ ግንኙነት ላይ ወይም በአንድ መስክ ላይ ፍሬያማ እስከምንሆን ድረስ ለረጅም ጊዜ የመቆየት ብቃታችንን አመልካች ነው፡፡ በገባንበት ቦታም ሆነ ግንኙነት ውስጥ የሚጎላው ልዩነታችንና አለመስማማታችን ከሆነ ባለን የሰው-ለሰው ግንኙነት ወይም ማሕበራ ብልህነት ላይ መስራት እንዳለብን ጠቋሚ ሊሆን ይችላል፡፡”

ከመፍትሄ ሃሳብ ጋር ሲብራራ፡-

ምናልባት ሕይወታችሁን በዚህ ሁኔታ ላይ ካገኛችሁት በመጀመሪያ ማድረግ ያለባችሁ ይህ ሁኔታ ለምን እንደተከሰተ መንስኤውን ማግኘት ነው፡፡

ከማሕበራዊ ግንኙነት ውጪ መኖር አንችልም፡፡ ስለሆነም በሁኔታው የመብሰላችን ጉዳይ እጅጉን አንገብጋቢ ነው፡፡ ያለንን ማሕበራ ኑሮ ወይም የሰው-ለሰው ግንኙነት ከሚወስኑ ሁኔታዎች አንዱ የራሳችን ምልከታ ነው፡፡ ሰዎችን፣ የሰዎችን ንግግር፣ የሰዎችን ተግባር፣ ሕብረተሰቡን እና በዙሪያችን የሚከናወነውን የምናይበት ምልከታና እይታ ለምንሰጠው ምላሽ ወሳኝ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ ሲዛባ ከሰዎች ጋር ውለን፣ አድረን መክረም ስለማንችል የጀመርናቸውንም ነገሮች የማስቀጠል እድሉንና አቅሙንም ይወስደዋል፡፡ ማሕበራዊ ግንኙነታችንን የተረጋጋ ማድረግን ከፈለግን የሚከተሉት ልምምዶች ማሰብና መተግበር እንችላለን፡፡


1. የሁኔታዎችን ድግግሞሽ ማጤን

ሁል ጊዜ አስቸጋሪ ሰዎችን የመጋፈጣችን አይቀሬነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሄድንበት ስፍራ ሁሉ፣ ከሁሉም ሰው ጋር ችግር የሚፈጠር ከሆነ ግን በመጀመሪያ ችግሩ እኔው ጋር ሊሆን የመቻሉን ጉዳይ መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡

ምንም ቢሆን ሁሉም ሰው ክፉ ሰው እንደሆንኩኝ፣ አስቸጋሪ ሰው እንደሆንኩኝ፣ የማልመች ሰው እንደሆንኩኝ . . . ሊያየኝና ሊቆጥረኝ አይችልም፡፡ ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ ግን በእርግጥም እንደዚያ የመሆኔን ጉዳይ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ምናልባት እንደዚያ እንዳልሆንኩኝ እርግጠኛነቱ ካለኝና እኔ እየመሰለኝ ከሆነ ደግሞ የአመለካከቴን ጤናማነት ማጤንና እዚያ ላይ መስራት አስፈላጊ ነው፡፡

2. ራስን መቀየርን ማስቀደም

ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት አስቸጋሪ የሆነ ሲመስለን በአብዛኛው የሚቀናን ሰውንና ስፍራን መቀየር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ጊዜያዊ መፍትሄ ቢሰጠንም ዘላቂ መፍትሄ ግን አያመጣም፡፡

ስፍራንና ሰውን ከመቀያየር በፊት በቅድሚያ ራስን መቀየር የተሻ ነው፡፡ መቀየር የማንችለውን የሰውን ሁኔታ ለመቀየር ከምንታገል፣ መቀየር የምንችለውን ራሳችንን መቀየር ይቀላል፣ ተመራጭም ነው፡፡ ሰዎችን ለመቀየርና ለመለወጥ ከታገልን በኋላ ተቀየሩም አልተቀየሩም ነገ ከእኛ ሲሄዱ፣ ሌሎች መቀየር የምንፈልጋቸው ሰዎችን እንተካለን፡፡ ራሳችንን ከለወጥን ግን የተለወጠ ማንነት ይዘን እንሄዳለን፣ ከራሳችን መለየት አንችልምና::

3. በማበራዊ እና በስሜት ብልህነት መብሰል

ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት የሰመረና ቀጣይ እንዲሆን ካስፈለገ ከላይ የጠቀስናቸውን፣ የሁኔታዎችን ድግግሞሽ በማጤን ራስን የመመልከትን እንዲሁም  ሰዎችን ለመቀየር ከመታገል ይልቅ ራስን መቀየርን ማስቀደም ከመለማመድ ባሻገር በጥበብ እየበሰልን እና እያደግን የመሄዳችንን ጉዳይ እውን ማድረግ መልካም ነው፡፡

ይህንን የማድረጊያው ቀላሉ መንገድ የማሕበራዊ እና የስሜት ብልህነታችንን በማሳደግ መቀጠል ነው፡፡ በአጭሩ በአካባቢያችን ከሚገኙ አስቸጋሪ ሰዎች ተሽሎ የመገኘትን ሁኔታ ማዳበር ማለት ነው፡፡

ተፈጸመ!    
 
ዶ/ር እዮብ ማሞ
@Human_Intelligence