Get Mystery Box with random crypto!

#ህይወት_ፈተና_ነው በጣም ከምወዳቸው ጥቅሶች አንዱ “ህይወት ፈተና ነው። ፈተና ባይሆን ኖሮማ በ | የስብዕና ልህቀት

#ህይወት_ፈተና_ነው

በጣም ከምወዳቸው ጥቅሶች አንዱ “ህይወት ፈተና ነው። ፈተና ባይሆን ኖሮማ በእያንዳንዱ ሁኔታ የት መሄድ፤ ምን ማድረግ እንዳለብን ይነገረን ነበር።” ይላል። ይህን ወርቃማ ጥቅስ ባሰብኩ ቁጥር በህይወት ውስጥ ሁሉን ማካበድ እንደሌለብኝ ይሰማኛል።

ህይወትንና በውስጧ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን እንደፈተና ማየት ስትጀምር የሚያጋጥሙህን ችግሮች ለማደግ እንደሚረዱ እድሎች መመልከት ትጀምራለህ። ተከታታይ ችግሮች፣ ተደራራቢ ሀላፊነቶችና  የማይታለፉ የሚመስሉ ጉዳዩች ጭምር ከነገሮቹ በላይ እንድትሆን ለመፈተን የሚቀርቡ እድሎች ይሆናሉ። ነገር ግን በተቃራኒው የሚያጋጥሙህን ጉዳዮች ሁሉ እንደ የሞት ሽረት ትግል የምትመለከታቸው ከሆነ ህይወት ኮሮኮንች መንገድ ይሆንብሀል። “ደስተኛ የምሆነው ሁሉም ነገሮች የተስተካከሉ ሲሆኑ ብቻ ነው!” ብለህ ትደመድማለህ። የሚያሳዝነው ሁሉም ነገሮች የተስተካከሉ የሚሆኑት ከስንት አንዴ ነው።

ነገሮች አስቸጋሪ ሲሆኑ ለሙከራ ያክል ይህን መንገድ ሞክረው። ምናልባት የሚያስቸግር ወንድም ወይም የሚያስጨንቅ አለቃ ይኖርሀል። ለሙከራ ያክል የሚያጋጥምህን ሁኔታ “ችግር” ከማለት “ፈተና” ብለህ ጥራው። በሁኔታው ከመናደድ ከሁኔታው መማር የምትችለውን ነገር ፈልግ። “ይህ ነገር በህይወቴ ለምን ተከሰተ?” እንዴት በተለየ መንገድ ልመለከተው እችላለሁ? የሆነ አይነት ፈተና ይሆን?” ብለህ ራስህን ጠይቅ።

ይህንን ስትራቴጂ ከሞከርክ ለነገሮች የሚኖርህ ምላሽ ሲለወጥ አይተህ መገረምህ አይቀርም። "ጊዜ ያጥረኛል" በሚል ሀሳብ እቸገር ነበር። ሁሉንም ነገሮች ለማከናወን እሯሯጣለሁ። የፕሮግራሜ መጣበብ፣ መስሪያ ቤቴን፣ ቤተሰቤን በአጠቃላይ ጊዜዬን እየተሻሙ የመሰሉኝን ነገሮች ሁሉ እወቅሳለሁ። ከዛ ድንገት ብልጭ አለልኝ። ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልገው አንዳንዱን ነገር በደንብ መስራት ሳይሆን የሚችሉትን ያክል ሰርቶ የቀረውን “ስራው ያውጣው!” ብሎ መተው መቻል ነው። በሌላ አነጋገር ችግሮችን እንደፈተና ማየት ስጀምር በፊት በጣም ያሳስቡኝ የነበሩትን ችግሮች በቀላሉ መወጣት ችያለሁ። ይሁን እንጂ አሁንም አልፎ አልፎ ጊዜ እያጠረኝ እንደምቸገር ግን አልክድም።

ቀላሉን ነገር አታካብድ መፅሐፍ
ዶ/ር ሪቻርድ ካርሰን ትርጉም ከዶ/ር ዮናስ ላቀው

@Human_Intelligence