Get Mystery Box with random crypto!

የልማድ ምስጢር ብዙ ሰዎች እንዲህ ሲሉ ይደመጣሉ፡- “በአንድ አሳብ፣ ንግግር ወይም ጽሑፍ እነሳሳ | የስብዕና ልህቀት

የልማድ ምስጢር

ብዙ ሰዎች እንዲህ ሲሉ ይደመጣሉ፡- “በአንድ አሳብ፣ ንግግር ወይም ጽሑፍ እነሳሳና አንድ ነገር እጀምራለሁ፣ ነገር ግን ብዙ ሳይቆይ አቆመዋለሁ”፡፡ ይህ ችግር የብዙ ሰዎች ችግር ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በርካታ ማሰብና መለማመድ የሚገቡን እውነታዎች ቢኖሩም መሰረታዊውና ዋናው ግን በመነሳሳት፣ በዲሲፕሊን፣ በድግግሞሽና በልማድ መካከል ያለውን ግንኙነትና ልዩነት ማወቅ ነው፡

መነሳሳት የሚገናኘው አንድን ጤና ቢስ ነገር ለማቆም ወይም አንድን መልካም ነገር ለማድረግ ካለን የመፈለግ ስሜት ጋር ነው፡፡

ዲሲፕሊን የሚገናኘው መቆም የፈለግነውን ነገር ለማቆም ወይም ማድረግ የፈለግነውን ነገር ለማድረግ ራስን ከማስገደድ ጋር ነው፡፡

ድግግሞሽ የሚገናኘው ማቆም በፈለግነው ወይም መጀመር በፈለግነው ነገር አንጻር ራሳችንን እየተቆጣጠርንና ዲሲፕሊን እያደረግን አንድን ነገር ካለማቆም ከመደጋገም ጋር ነው፡፡

ልማድ የሚገናኘው ምንም ሳናስብበት፣ ሳንጨነቅና ሳንገደድ አንድን ነገር ለማቆም ወይም ለማድረግ ካለን ብቃት ጋር ነው፡፡ አንድ ልምምዳችን ወደ ልማድ ደረጃ መድረሱን የምናውቀው ያንን ነገር ለማድረግ ምንም አይነት የሚቀሰቅሰን (መነሳሳት) ወይም የሚጫነን (ዲሲፕሊን) ነገር ሳይኖር ማድረግ ስንጀምር ነው፡፡

ማንኛውም ሰው አንድን መልካም ልምምድ ወደ ልማድ ደረጃ እስከሚያደርሰው ድረስ ስኬታማነቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ስለዚህም፣ በመነሳሳት የተጀመረን ነገር ወደ ዲሲፕሊን ደረጃ ማድረስ አስፈላጊ ነው፡፡ ራሳችንን ወደመጫንና ዲሲፕሊን ያደረግንበትን ነገር ደግሞ ልማድ እስኪሆን ድረስ መደጋገም አስፈላጊ ነው፡፡

ሁል ጊዜ በመነሳሳት የሚሰራ ሰው መነሳሳቱ ሲያቆም እሱም ያቆማል፡፡ ሁል ጊዜ በዲሲፕሊን ላይ የሚደገፍ ሰው አንድ ቀን ራስን መጫንና ማስገደድ ይሰለቸውና ወይም ዲሲፕሊን የሚደርገው ሰው ወይም ሁኔታ ሲያቆም አንድ ቀን ያቆማል፡፡ ከዲሲፕሊን ደረጃ አልፎ አንድን ነገር እስኪለምደው ድረስ ድግግሞሽ ደረጃ የዘለቀ ሰው ወደ ልማድ ቀጠና ያልፋል፡፡ በልማድ የሚሰራ ሰው ራስ-ሰር (Automatic) ስልት ውስጥ ስለገባ ሁኔታው ዝም ወደሚፈስለት ደረጃ ያልፋል - ውጤቱም ልህቀትና ስኬት ይባላል፡፡

ለምሳሌ፣ ጠዋት ስትነሳ ማንም ሳያስታውስህና ማስታወሻ ደወል ሳታደርግ የምታደርጋቸውን ነገሮች አስባቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ልማድ ደረጃ የደረሱ ስለሆነ ለማስታወስ፣ ለመነሳሳትና ለማድረግ ምንም አድካሚ አይደሉም፡፡

በሕይወትህ ስኬታማ መሆን የምትፈልግበትን ነገር ለይና በዚያ ጉዳይ ላይ በመነሳሳት ጀምረህ፣ ወደ ራስን ማስገደደ (ዲሲፕሊን) በማለፍ ልማድ እስኪሆን ድረስ መደጋገም የግድ ነው፡፡ አንድን ነገር ጀምረህ የምታቆመው ነገሩ ልማድ እስኪሆን ስላልተነሳሰህና ራስህን ዲሲፕሊን ስላላደረከው ነው፡፡ በሕይወትህ ማቆም ያቀተህ አጉል ነገር ሁሉ አስበው፣ ልማድ እስኪሆን ስለደጋገምከው ነው፡፡ ጤና ቢስም ነገር እኮ ለዚያ ነገር ተነሳስተን ጀምረነውና ደጋግመነው ነው የልማድን አቅም ያገኘው፡፡

እንደገና ልድገመውና፣ ልማድን ለመጀመር መነሳሳት አስፈላጊ ነው፡፡ መነሳሳት ግን ራስን ዲሲፕሊን ማድረግ ደረጃ ካለደረሰና ወደ እንቅስቃሴ ካልተለወጠ የትም አይሄድም፡፡ ማንኛውም እንቅስቃሴ ደግሞ ወደ ድግግሞሽ ካልዘለቀ ልማድ አይሆንም፡፡

ዶ/ር እዮብ ማሞ
@Human_Intelligence
@Human_Intelligence