Get Mystery Box with random crypto!

ወግ ብቻ

የቴሌግራም ቻናል አርማ wegoch — ወግ ብቻ
የቴሌግራም ቻናል አርማ wegoch — ወግ ብቻ
የሰርጥ አድራሻ: @wegoch
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 21.12K
የሰርጥ መግለጫ

✔በየቀኑ ምርጥ ምርጥ የጥበብ ስራዎችን ለማግኘት የቻነላችን ተከታይ ስለሆኑ እናመሰግናለን።
✔ @getem @serenity13
✔ @wegoch @Words19
✔ @seiloch
✔ @zefenbicha
Creator @lula_al_greeko

Ratings & Reviews

4.33

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

2

4 stars

0

3 stars

1

2 stars

0

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች

2023-07-06 07:22:05 [ማነቂያ]

የሰኔ ጢንፍ የሚያበሰብሰው፣ አቋምና ማገሩ መጋለጥ የጀመረ የጭቃ ግድግዳቸውን ተደግፎ ከካፊያው ጋር የሚመጣውን ቅዝቃዜ ሽሽት ከእድሜ ብዛት መነሾ የሳሳ ኮሌታው የተበዘበዘ ሸሚዙን ከአንገቱ አጣብቆ ኩርምት ብሏል። እናቱን ጥበቃ!

እሷ እንደሁልጊዜው ሁሉ "የትልቅ ሰው ወሬ ልናወራ ስለሆነ ውጭ ቆይ! ጎሽ የ'ኔ ልጅ!" በማለት ነበር በሩን ከውስጥ የቀረቀረችበት።

እናቱ በየዕለቱ ከተለያዩ ወንዶች ጋር ምን እንደምታወራ አያውቅም። ቢያውቅም አይገባውም። ብቻ ወሬአቸው ቶሎ እንዲያልቅ ከደጃፍ ተቀምጦ እላዩ ላይ የሚፈረፈረውን ወደ መፍረሱ የተጠጋውን የግድግዳ አፈር እያራገፈ በተቻለው ሁሉ በእንቅልፍ ላለመውደቅ እየታገለ ይጠብቃታል።

በርግጥ የሆነ ቀን ግን ብርዱ በጣም ሲብስበት የፒያሳ ጎዳና ተዳዳሪ ውሾች ዛቻ ሲፀናበት "እማ ጨለማውን ፈራሁት ወሬአችሁን አልሰማባችሁም አስገቢኝ” ብሏት ያውቃል።

ለዚህ እሮሮው ከእናቱ ያገኘው መልስ ግን "ወንድ ልጅ አይደለህ ለምን ትፈራለህ…" የሚል ነበር። አንዳንዴ ሳስበው ወንድ መሆን መረገም ይመስለኛል!! ወንድ መሆን በራሱ ጫንቃ የሚያደነድን የሚመስላቸው ብዙ አውቃለሁ። ወንድነት ፍዳን ከመቀበል ጋር ያለውን አወንታዊ ቁርኝት የሚያሳስበው ማግኘት እምብዛም ነው!

በርግጥ በእሷም ፍርድ የለ! ምን ታድርገው! ገላዋን ለጎረምሳ የስካር ማብረጃ መስዋዕት ካላቀረበች እሷንም ልጇንም አድፍጦ የሚጠብቃቸው ከርሳም ርሃብ ይበላቸዋል።

እዚህ መሸት ሲል አዳኝና ታዳኝ፣ ገጸባህርይ እና ድርሰት፣ ንጋትና ምሽት፣ ገሃነምና ገነት፣ ገዥና ሻጭ የሚገዙበትን ገንዘብ የሚሸጡትን እቃ ይዘው በድንግዝግዙ ይገናኛሉ።

የገዢው መድረሻ ከደቂቃዎች ሀሴት የሻጭም ዋጋ ወስፋትን ገሎ ከማደር አልፎ አያውቅም። እዚህ ህይወት ዛሬን ተንፈስ ስለማለት ጠግቦ ስለማደር እንጂ ነገን ስለመድረስ አይደለችም።

እዚህ እናትነት በአደባባይ ለሽያጭ ይቀርባል፣ እህትነት ይሸቀጣል። አባትነት ይረክሳል፣ ወንድምነትም እንዲሁ። ሁሉም ለስሜቱና ለሆዱ ብቻ፤ ትግሉ፣ መፍጨርጨሩ፣ ሳንጃ መሞሻለቁ፣ ቡጢ መሰናዘሩ፣ ይሉኝታን መጣሉ… ዛሬን ይተርፉ ዘንድ ብቻ ነው። እዚህ ሁሉም የሚሰዋለት የየግል ጥም አለው። ይህ ዶሮ ማነቂያ ነው!

በረድፍ ተደጋግፈው የተሰደሩት ጠባብ ገላ መሸቀጫ ቤቶች የእነሱን ቤት ጨምሮ መጋረጃቸውን ከውጭ አድርገው በውሽንፍር እያውለበለቡ ከውስጥ ተቀርቅረዋል። የአልጋዎች መንሰጣሰጥና በወሲብ የሚቃትቱ ድምፆች ሰፈዋል።

እንግዲህ
የመጋረጃቸው ከውጭ ሆኖ በሩ ከውስጥ መቀርቀር ቤቱ በወሲብ ፈረስ እየተጋለበ ስለመሆኑ ምልክት መሆኑ ነው። ማንም አንቀጽና ገጽ ጠቅሶ ያላወጀው ግና ሁሉም የሚያወቀው ምልክት። ገዥና ሻጭ፣ ኢላማና ፍላፃ የሚግባቡበት እጅግ የረቀቀ ምልክት።

ቀስ እያለ
ካፊያን ውሽንፍር አመሻሽን ወድቅት ተስፋን ሀዘን ተካቸው። አልፎ አልፎ እየተሯሯጡ ከሚያልፉ የውሻ መንጋ በቀር በሰፈሩ ብቅ የሚል አይታይም። የሰፈሩን ሰርጣሰርጥ ቅያሱንም ሁሉ እንደ መቃብር ቤት ያለ ጭርታ ከበበው። ከላይ ጎርፉ እያንከባለለ የሚያመጣቸው የለስላሳ ጠርሙሶች እየተንገጫገጩ አረፋ እየደፈቁ ከቤታቸው ፊት በሚገኝ ቦይ ስር ያልፉ ጀመር። የህይወቱ ማለዳ ልጅነቱ እየተንገጫገጨ ያለፈ መሰለው…

“አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣አራት…”

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Tamiru temesgen
1.1K viewsPapi, 04:22
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-07-05 10:29:58 Fifty shades of him
'
'
አለሜ የምለው እርሱ "የኔ ጨረቃ " ብሎ ያለኝ ለታ ስሸሻት የኖርኳት የምጠላት ጨረቃ ፊት እስክቆም ድረስ የአምስተኛ ክፍል ሳይንስ መምህራችን "ፀሃይ ትልቋ ኮከብ ናት .... ጨረቃ ደግሞ ከእርሷ ብርሃን ትሰበስባለች "ካሉን ቀን ጀምሮ ብርሃን መስረቋ አናዶኝ ጨረቃን ጠምጄ ያዝኳት።

ስንቴቴ "የዛሬው ብርሃንስ ጤፍ ያስለቅማል" በተባለለት ምሽት ሰማይ ኮርኒስ ላይ የተንጠለጠለች የብርሃን ኳስ ፅልመቱ ላይ የተንሰራፋች ለታ፣ እርሷን ለመሸሽ ስሮጥ አምጪ የተባልኩትን የታናሽ እህቴን ወተት ንጬ ቅቤ ወጣለት።
እናቴም የተቀበለችኝን የወተት እቃ ከፍታ እያየች "ብራ ጨረቃ እየጠበቀማ የሚያበር ጋኔል ሰፍሮብሻል" ስትል የምሮጠው ጨረቃ ወለል ስላለች መሰላት እንጂ ከእርሷ እየሸሸሁ እንደሆነ አታውቅም ነበር።

የኋላ ኋላ የጠመድኳት ጨረቃ መልሳ ጠምዳኝ ነው መሠል የሃምሌ ጭጋግ በጋረደው ምሽት መሃል አግኝቶኝ "ቤት ሄደን ጃኬት ደርቤ ልሸኝሽ " ያለኝን የሰፈሬን ጎረምሳ ተከትዬ ቤቱ ደርሰን ጃኬት ይደርባል ብዬ ስጠብቅ ልብሱን ሁሉ አውልቆ ርቃኑን ወደ ቆምኩበት መጥቶ ወተቴን ተቀብሎኝ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦ ልብሴን ሲያወላልቅ እንደበግ እየተነዳሁለት የሆነው ሁሉ ሆኖ " አይዞሽ" እያለኝ አስሬ እንደምንም ለባብሼ ከቤቱ ስንወጣ ቀና ብዬ ሳይ፣ ቅድም የጋረዳትን ጭጋግ ገፍፋ የወጣች ሙሉ ጨረቃ ቁልቁል ስታየኝ አየኋት። የያዘኝን እጁን መንጭቄ በጉያዬ መኻል ያለውን ህመም ችዬ እየተደነቃቀፍኩ ለመሮጥ ስንቧቸር በብሩህ ጨረቃ ቀናት የማይነሳሳ ሴትነቴን በደመና ተከልላ ያታለለችኝ ሙሉ ጨረቃ ላስታውሰው እንኳ ለማልሻው ደብዛዛ ሰው ድንግሌን እንደሸለመች፣ ከእኔ እንዳስነጠቀችብኝም እያሰብኩ ነበር።

እና "የኔ ጨረቃ " ያለኝ ቀን ዘመናት በመሃላችን በኩርፊያ ያለፉት እኔና እርሷ ማዶ ለማዶ ፊት ለፊት ተፋጠጥን። አልጠላኋትም የዛን ቀን አልሸሸኋትም ያን ማታ ብቻ ግን እርሷን ሆንኩላት፤ እኔንም የሆነች መሰለኝ።

በእኔና በእርሱ መካከል የነበረው የቦታ ርቀት በዘመን ሁሉ የሚሰፈር ይመስለኝ ነበር። በቃ እርሱን የማቀርብበት ከእርሱ የምገናኝበት ምንም መንገድ የለም ብዬ ተስፋ ከቆረጥኩ ብሰነብትም አለሜ አፍ አውጥቶ "አንተያይም ተስፋ ቁረጪ" ሲለኝ ቅስሜ ደቅቆ ተሰበረ።

ገላዬ የናፍቆት ብርድ ያቆራመተው ነው። በእርሱ መታቀፍ በእርሱ መነካት ብቻ ይፈልግ ነበር። ጭኔ ላይ ያቆጠቆጡ ጥቃቅን ፀጉራት ሲቆሙ ይታወቀኛል፣የጡቴ ጫፎች ሲሾሉ ይታወቀኛል ፣ ብሽሽቴን ሲሞቀኝ ይታወቀኛል፣ ገላዬን የኔ ያልሆነ ያህል ልመቆጣጠር ሲያቅተኝ።

እየሩስዓለሜ ነበር። ሰርክ ዕለት ልሳለመው የማልመው ነክቼው ልፈወስ ዳብሼው ካለ እና ከሚመጣው ነገር ሁሉ ልነፃበት የምፈልገው።

ዳስሼው ከቅዱስነቱ ቅንጣት ቆንጥሬ ዘመኔን ሁሉ በደጄ የሚፈስ የቅባ መውደዱን ዘይት ነፍሴን እንዲያረሰርስ፤ ከአላፊ አግዳሚው መሃል ጨርቁን ጨብጬ ልፈወስ ....

"ካለሽበት የምመጣበት መንገድ ጠቧል" ሲለኝ ለመዓከ ገብሬል አባቴ በእለተ ቀኑ ነግሬው፣ "በግራም በቀኝም የለኝ ካላንተ የማስቸግረው" ብዬ ከቅፅሩ ተንበርክኬ የደጁን ጠጠር ዘግኜ ነጠላዬ ጫፍ የቋጠርኩት፣ ቤቴ ስመለስ ጎረቤቴ ለሣምንቱ ሰባት ቀናት ሁለት ጡት ያላቸው ሶስት ጀበናዎች አፈራርቃ የምትካድም፣ የፋጤና ከድጃን ቀናት የምታከብር፣ በአርሲዋ እመቤት ምትምል ባለውቃቢ ደግ ሴት የገብሬል ቡና ካልጠጣሽ ብላ ስትበቅተኝ፣ እንደታቦት ቀን እየቆጠረች ከምታወጣቸው ፍንጀሎቿ በአንዱ ያፈላችውን ቡና አቀብላኝ ...ምን አስተከዘሽ ብትለኝ "የምወደው ሰው የሰው ሃገር ቀረብኝ " ብያት እጆቿን ወደ ላይ ዘርግታ መአት አይነት መለዓክ፣ መአት አይነት መላይካ እየጠራች በአማርኛ በኦሮምኛ ተማፅኖዋን ስታንበለብል
"በየአፍ መፍቻቸው ይሆን የምትፀልይላቸው?" እያልኩ እየሰማዃት.....

የማግሁትን ቡና ሲኒውን ላቀብላት ከተቀመጥኩበት ስነሳ ነጠላዬ ጫፍ ከተቋጠሩ የገብሬል ጊቢ ጠጠሮች መሃል አንዲቷ ጊርጊራዋ ላይ ድንገት ተፈትታ ብትወድቅ ከእጣን ማጨሻዋ ላይ ሃምራዊ ጢስ ሲንቦለቦል አየሁ ...በሰፈሩ ቀድሞ ያልነበረ ጣዕመ አልባስጥሮስ ጠረን ሸተተኝ። ይህም ለመምጣቱ ምልክት ሆኖኝ መላዕክት መላይካዎቹ ጭላንጭል ተስፋ ቢያሳዩኝ ታላቁ ፀገመ እንዳለው ተስፋ መቀነት ሆነኝ።

አመታት እንደቀናት አልፈው "ካለሽበት የምመጣበት መንገዱ ሁሉ ቁልፍ ነው" ያለኝ አለሜ ሃገር ቤት ድረስ መጣ። ግን የሌላ ሰው ሆኖ ከሌላ ሰው በፍቅር ከንፎ ያለሁበት ከተማ ውስጥ ተገኘ።

ይህን ሳውቅ "ምን ከከፍታ ሆነው ወደ ታች ቢወረውሩት እርሱ እንደሁ እንደ ላባ ነው ተችሏቸውም አይሰብሩት" ብዬ የታባልኩለት ልቤ እንክት ብሎ ወደ እልፍ ቅንጣቶች ደቀቀ። እንባዬ በጉንጬ መም ነድሎ እንደ ጤግሮስ ዥረት ሆነ።

ደውሎ "ላግኝሽ" አለኝ
ግን ላገኘው አቅም አነሰኝ .... ናፍቆቴ ዘመን ተሻግሮ መጥቶልኝ ከኔ ከተማ ላገኘው ጉልበቴ ከዳኝ ላገኘው ወኔዬ ጠፋ የሰው መሆኑን ስሰማ።

የሚሰሙኝን ስሜቶች ስም ልሰጥ ስጥር ከረምኩኝ ቅናት ነው? ፍቅር ነው? በእርሷና በእርሱ የሚሰማኝ ይህ ነገር ምቀኝነት ነው? እያልኩኝ.... ሌት ተቀን ስብከነከን እህህ ብዬ ከረምኩኝ።

አንድ ቀን መልክት ደረሰኝ
"በዚህ ፀባይሽ ሳላገኝሽ ልሄድ ነው።"
"መች?" አልኩት መለስኩና "ዛሬ" አለኝ......ይሄኔ አንጀቴ ተላወሰ ጥፋተኝነት ተሰማኝ "ከማንስ ጋር ቢሆን ምን አለ አንዴ እንኳ ባየው ?" እያልኩኝ ፀፀት እንደጦስ ዶሮ አርባ ዘጠኝ ጊዜ ሲዞረኝ ቤት ገባሁ። በረንዳ ወጣሁ። ምጥ እንደያዛት ድርስ እርጉዝ ስንቆራጠጥ ቆይቼ ድንገት ወደ ላይ ቀና ብል ጨረቃ ከአናቴ ቆማ እኔን በአንክሮ ስትሰልል .....

ልጅነት እንደ ጧት ጤዛ አላፊ ነው ረጋፊ ወጣትነትም እጢ ነው ክው ያሉ ለታ ጠፊ ... እሱን በጠበኩባቸው ዘመናት መኻል የታዘብኩት ፍቅርን ከኖሩት በላይ የናፈቁት ናቸው የሚያውቁት።ጊዜ አቃጣሪ ነውና ጉርምስናዬን አስጥሎ ምን ለእርጅና ቢድረኝም እንደ አዲስ "ቀን አንድ" ብዬ ዳግም ብጠብቀው ቅር አይለኝም።

የስልኬ ሰሌዳ ላይ ሚሴንጀሬን ከፍቼ መፃፍ ጀመርኩ ።
"አለሜ በሰላም ግባ ... የሆነ ቀን ግን ናልኝ ለእኔ ብቻ ብለህ እኔ ጋር ብቻ ናልኝ"

Note :- ናፍቆት ከፍቅር ይበልጣል።

@getem
@getem
@paappii

By Elsa mulgeta
1.9K viewsPapi, 07:29
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-07-03 12:32:23 ወግ ብቻ pinned a photo
09:32
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-07-03 12:31:53
ሥዕል ለማሳል በ+251984740577
ወይም @gebriel_19 ላይ  ፎቶ  በመላክ በ ተመጣጣኝ ዋጋ  ማዘዝ ይችላሉ!


@seiloch
@seiloch
2.2K viewsLeul M., 09:31
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-07-02 08:34:41 ስራ ፈት አንቺ ነሽ። እንጂ በስርሽ የማይሰራ የለም። ብቸኛው ሰነፍ አንቺ ነሽ ... እንጂ በስርሽ ያልበረታ የለም።... ተነሺ... ልብስሽን አስተካክይ... ልብሽን አስተካክይ...
ከሱ አስቀያሚ ጥግ... ውጪ...
ከትጉሕ ሰራተኞችሽ ብለጪ...

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Rediet aseffa
2.9K viewsPapi, 05:34
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-07-02 08:34:38 «ጉድ ሆንኩኝ ዛሬ...!» ይላል ጭንቅላቱን በሁለት እጆቹ ጭብጥ... ልቅቅ... ውርጭት እያደረገ... የእልህና የሀዘን ዲቃላ እንባውን ..ከዐይኑ እየጠረገ... አስፓልቱ ያቆራቸውን የውሀ ኩሬዎች በቆዳ ጫማው ጠርዝ በእልህ እየረጫጨ... በላዩ ላይ የሚወርደውን ካፊያ ከምንም ሳይቆጥር በቀስታ ይጓዛል። መሀል ላይ «ወይኔ ተዋረድኩ ዛሬ!» ይላል።

በዚህ ወር ብቻ ሰባተኛ ሥራ ከእጁ ወጥቷል። ከዚያ በፊት በነበሩት ስድስት ወራት የቀድሞ ደንበኞቹ በተለያየ ምክንያት ትተውት... አዳዲስ ደንበኞች ማጥመድ ተስኖት... ሥራ በጨረታም... በልመናም... በልምምጥም እየሞከረ አልተሳካለትም። መጨረሻ የተገኘችው ስራ ሁለት ወይ ሶስት ወር ያልፋታል... የዛሬዋ ግን ከሁሉም አንገብግባዋለች። ተስፋውን ሁሉ ጥሎባት ነበርና ማጣቱ ወፈፍ ሊያደርገው ደረሰ። «ወይኔ ተዋረድኩ... በተከበርኩበት ሀገር!» ይላል እየተንተባተበ።

አስራ ሶስት ሰራተኞች ቀጥሮ ያሰራል። የሰራተኞች ደሞዝ፡ የቢሮ ኪራይ አለበት። የመጋዘን ኪራይ... የመኪና ኪራይ የጥሬ እቃ... የመብራት ፡ የውሃ ...የስልክ... የኢንተርኔት... የነዳጅ....የግብር የፍቃድ ማደሻ... ስም ያለው ስም የሌለው መዓት ወጪ አለበት። በዚያ ላይ ስራ ባጣባቸው ወራት ወጪዎቹን ለማስታገስ ብሎ ከስንት ተቋም...ከስንት ሰው ብር ተበድሯል። በዚያ ላይ የሱ ኑሮ ደሞ አለ። የመኖሪያ ቤት ኪራይ...ልጆቹ ትምህርት ቤት... የቤት አስቤዛ ወጪ... የእናቱ ሕክምና እና ሌላ የወጪ ክምር ደግሞ በገዛ ኑሮው በኩል ይጠብቀዋል።

እሱ ግን መንቀሳቀሻ ሳንቲም እንኳ ከኪሱ ከጠፋ ከራርሟል... ኮትና ሱሪውን ለብሶ ለትራንስፖርትና ለምሳ መክፈል እያቃተው ባዶ ሆዱን በእግሩ ስንት ቦታ እንደተንከራተተ የሚያውቀው የሰማዩ ጌታ ብቻ ነው። ግን ከሁሉም የዛሬዋ ቁስሉ ባሰች። ተስፋውን ሁሉ አሟጥጦ አሸክሟት ነበርና... ስትወድቅ አብሮ ሁሉ ነገሩ ወደቀበት... ተስፋ ቆረጠ።

የገዛ መስሪያቤቱ የሰራተኞቹን ዐይን ላለማየት ብሎ ከሄደ ሰነባብቷል። ስልክ ማንሳት እንደጦር ይፈራል። መንገድ ላይ ከአበዳሪዎቹ አንዱ እንዳያዩት ኮፍያና መነፅር ማድረግና ውስጥ ለውስጥ መንገድ ማቋረጥ ልማዱ ሆኗል። ዛሬ ግን እየተንተባተበ... ዝናብ እያረጠበው በተከበረበት በዋናው ጎዳና ላይ... ያለኮፍያና መነፅር ጭንብል... እንደእብድ ጮክ ብሎ እያወራ እንደልጅነቱ ውሃ እያንቦራጨቀ... ወደገዛ መስሪያ ቤቱ ደመነፍሱን እየሄደ ነው።

ሰዓቱ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት ጥቂት አልፏል። የሰራተኞች መውጫ ሰዓት ማለፉን እንኳ ሳያገናዝብ እየተወራጨ መስሪያ ቤቱ ደረሰ። ምን ሊያደርግ እንዳሰበ አላወቀም። ግን ምንም ብርሃን አይታየውም። ጨለማ ነው። ከዚህ አይነት ውርደት ሞት የተሻለ እንደሆነ አንዳች መንፈስ ሹክ ይለዋል። የእልህ እንባ እና ሳግ እያደናቀፈው አሁንም አሁንም... «ኧረ መቅለል...! » እያለ የመስሪያቤቱን ደረጃ በፍጥነት ወጥቶ መግቢያው መጋዝን ጋ ሲደርስ ቆመ።

ለቢሮነት የተከራያቸው ክፍሎችና የስፌቱ መጋዝን በሕንፃው አንደኛ ፎቅ ላይ የሚገኙ ናቸው። ሕንፃው ላይ የሚሰሩት ሁሉም ሰራተኞች ባለመኖራቸው ከውጭ ምንም የሰው እንቅስቃሴ አይታይም። የሱ ቢሮዎችና መጋዘኑ ያለበት አንደኛው ፎቅ ግን በብርሃን ደምቆ ነበርና ገና እንዳየው ተናደደ። «እኔ ለራሴ የእዳ ማእበል ሊወስደኝ አሰፍስፏል...ጭራሽ መብራት አብርተው እየሄዱ ውዝፍ እዳ ሊከምሩብኝ ነው? a bunch of stupid people» ብሎ ሰራተኞቹን ተራግሞ ሰዓቱን ጎንበስ ብሎ አየ... ለአንድ ሰዓት አስር ጉዳይ። « ወይኔ የማንም መሀይም መቀለጃ ሆንኩ!» ብሎ መጋዝኑን ለመክፈት ቁልፍ ከኪሱ አውጥቶ ሊያስገባ ሲል የመጋዝኑ በር አልተዘጋም ነበርና... ወለል ብሎ ተከፈተ።

በንዴት ጦፎ ወደ ውስጥ ሲገባ ... ሁሉም ሰራተኞች በፍጥነትና በትጋት ስራቸውን እየሰሩ አየና በድንጋጤ ፀጥ አለ። መምጣቱን ስላላዩ ወደርሱ አልዞሩም ያለአንዳች መናጠብና ግዜ ማባከን በጥራትና በብቃት ስራቸውን እየሰሩ ነው። ቀስ ብሎ አንገቱን እያሽከረከረ ሁሉንም ሰራተኞቹን ቃኘ... የሚያወራ እና ስራ የፈታ አንድም የለም። ቀስ ብሎ የኋሊት ተራምዶ ወደሌሎቹም ቢሮዎች ሄደ። ሁሉም ሰራተኞች በትጋት እየሰሩ ነው። የቀረ .... ያልመጣ ... የእረፍት ጊዜዬ ደርሷል ብሎ አቋርጦ የወጣ የለም። ሁሉም አለቃቸው ሳይሰልላቸውና ሳይቆጣጠራቸው... እስከዚህ ሰዓት አምሽተው ሊያውም በእረፍት ቀን እየሰሩ ነው።

ቀሰስ ብሎ ወደገዛ ቢሮው ሄደና ወንበሩ ላይ ተቀመጠ። ተስፋ የመቁረጡ ስሜት ለራሱ አናደደው። «እንዴት ያለእረፍት ... ሳልቆጣጠራቸው... ሀያአራት ሰዓት... ሰባት ቀናት... ወሩን አመቱን ሙሉ የሚለፉልኝ የሚተጉልኝ ባለሞያ ሰራተኞች ይዤ ተስፋ እቆርጣለሁ? ተሳካለት? ወይስ አልተሳካለት ሳይሉ... ቢሮ ገባ አልገባም ሳይሉ... ደሞዝ ዘገየብን ቆየብን ሳይሉ... ሰራተኞቼ እየለፉ እኔ ምን ነክቶኝ... ምን ገጥሞኝ.. ምን ከብዶኝ... ተስፋ እቆርጣለሁ? አለ። ብቸኛው... ስራ ፈት እኔ ነኝ። እንጂ በስሬ የማይሰራ የለም። ብቸኛው ሰነፍ እኔ ነኝ ... እንጂ በስሬ ያልበረታ የለም አለ... አለና ልብሱን አስተካክሎ በግለት እየሮጠ ወጣ ...

እሱ ሲወጣ አንተ የት ጋ ነህ ወንድሜ?
ሰራተኞችህን እያቸው እስኪ አይንህን ጨፍንና። ልብህን እያት አንተን ጌታዋን ታምና ...ብታያትም ባታያትም ከማሕፀን ከመመስረትህ ጀምሮ ያለማቋረጥ እየተንደቀደቀች እየሰራች ነው። ኩላሊትህ ፈሳሽ ከማጣራት አልቦዘነም። ሳንባዎችህ ንፁህ አየር ከማስገባት የተበከለውን ከማስወጣት ተዘናግተው አያውቁም። ጉበትህ አንጀትህ ጨጓራህ... እግሮችህ... እጆችህ... ጆሮዎችህ አይኖችህ ምላስና ከንፈርህ... የደም ስሮችህ ...የነርቭ ጅማቶችህ... እጢዎችህ... የምታውቃቸውም የማታውቃቸውም እልፍ ሰራተኞችህ አንተ እንደአንተ እንድትቆም እንድትራመድ እንድታስብ እንድትኖር... የእድሜ ዘመንህን ያክል ያለእረፍት እየተጉ እየለፉ ነው። አለቃቸውን አንተን ሕያው ለማድረግ ስትቆጣጠራቸውም ሳትቆጣጠራቸውም የሞያቸውን ያክል የባህሪያቸውን ያክል ይለፋሉ። እንዴት ብትጨክንባቸው? እንዴት ብትንቃቸው? እንዴት ብታቃልላቸው? እንዴት ከመጤፍ ባትቆጥራቸው ነው ተስፋ የቆረጥከው ወንድሜ?

ምን ችግር ምን መከራ ቢገጥምህ... ምን ብትዝል ምን ብትንገሸገሽ... ቅን ሰራተኞችህስ? ልፋታቸውስ? እነሱ ቆመው እያደሩ ወድቀህ ልትቀር? እነሱ እየተራወጡ እየዋሉ አንተ ፈዝዘህ ልትመክን? ትጉህ ሰራተኞች የነበሩት ወዳቂ... ባለሞያዎች የሚለፉለት ብኩን ልትሆን? ይሄን ሁሉ በብርሃን በጨለማ ቢታሰስ ቢፈለግ የማይገኝ የኤክስፐርት መዓት ሰብስበህ መስሪያቤቱን ልትዘጋው? ልትተወው? ልትዘነጋው? ልትጥለው? ተስፋ ልትቆርጥ?

እህቴ...እንዴት ያለእረፍት ... ሳትቆጣጠሪያቸው... ሀያአራት ሰዓት... ሰባት ቀናት... ወሩን አመቱን ሙሉ የሚለፉልሽን የሚተጉልሽን ባለሞያ ሰራተኞችሽን ይዘሽ ተስፋ ትቆርጫለሽ? ተሳካላት? ወይስ አልተሳካላት ሳይሉ... ተኛች አልተኛችም ሳይሉ... ምግብ ...ዘገየብን መድሃኒት ቆየብን ሳይሉ... ወደውስጥሽ የምትዶያቸው የመርዝና የኬሚካል መአት ሳይበግራቸው... ሰራተኞችሽ...እየለፉ አንቺ ምን ነክቶሽ... ምን ገጥሞሽ.. ምን ከብዶሽ.. ለውጫዊ ሰው... ለውጫዊ ነገር... ለውጫዊ ሁኔታ ብለሽ...ተስፋ ትቆርጫለሽ? ። ብቸኛው...
2.8K viewsPapi, 05:34
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-07-01 20:29:44 በአንድ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ሲሰሩ ነበር የተዋወቁት ፡ እና ተቀራረቡና ፡ አንድ ቀን እራት ልጋብዝሽ አላት ።

ጥሩ ቦታ ወሰዳት ፡ አሪፍ እራት በሉ ፡ እና ወደቤት ሊሄዱ ተነሱ ፡ ዴንዝል ዋሽንግተን የተጠቀሙበትን ሂሳብ ከፈለና ፡ ኪሱ ውስጥ የቀረውን ገንዘብ ሲያይ ደነገጠ ። በወቅቱ ሁለቱም መኪና የላቸውም ። ኪሱ ውስጥ የቀረው ገንዘብ ለታክሲ ላይበቃ ይችላል ። እና በባቡር እንሂድ ልበላት ? ወይስ ፡ ለምን ወክ አናደርግም ብዬ እስከቤት ልሸኛት ? የሚለውን እያሰበ እያለ ፡ ከሆቴሉ ወጥተው በሩ ላይ የተደረደሩት የሜትር ታክሲዎች ጋር ደረሱ ።

ፓውሌታ የአንዱን ታክሲ በር ከፍታ ገባች ። ዴንዝል ተከተላትና ፡ ወደቤቷ አቅጣጫ መጓዝ ጀመሩ ፡ እና እያወራት ፡ በመሀል ስንት እንደቆጠረ የታክሲውን ሜትር ያያል ።
ኬሎሜትሩ በጨመረ ቁጥር ፡ ብሩም እያደገ ሄደ ። ዴንዝል ዋሽንግተን ፡ ሀሳብ ገባው ፡ በመጀመሪያ ቀን ዴቲንግ ፡ የታክሲ መክፈል ያልቻለ ሰው ሆኗል ።
በመጨረሻም ቤቷ ደረሰች ። ዴንዝል ነገራት ።
ብር ጨርሻለሁ
ታዲያ ምን ችግር አለ ብላ የመጣችበትን እና እሱን ቤቱ ሊያደርሰው የሚችለውን ጨምራ ከፍላ ወረደች ።
......
ግንኙነታቸው እያደገ ሄዶ ፡ አንድ ቀን ቀለበት ገዝቶ ተንበረከከ
ፓውሌታ ፡ አብረን እንድንኖር እፈልጋለሁ ። ታገቢኛለሽ ? ሲል ጠየቃት
አላገባህም አለችው
ቀለበቱን ኪሱ ከቶ ተለያዩ ።
.....
ትንሽ ቆይቶ አንድ ቀን ይህንኑ ጥያቄ ደገመው ።
እኔና አንቺ ባልና ሚስት መሆን ያለብን ሰወች ነን ፡ አብረን እንድንኖር እፈልጋለሁ ፡ አለና ያንኑ ቀለበት አውጥቶ ለጋብቻ ጠየቃት ።
አዝናለሁ ዴንዝል አላገባህም ብላው ሄደች ።
እሱም ሄደ ።
....

ከወራት በኋላ አንድ ቀን ያችኑ የፈረደባት ቀለበት አውጥቶ ፡ ለሶስተኛ ጊዜ አግቢኝ ሲል ጠየቃት ።
ፓውሌታ ይህን ተስፋ የማይቆርጥ ሰው ፡ አትኩራ አየችው እና የቀለበት ጣቷን ዘረጋችለት ።
እሽ አገባሀለሁ ።
..........
ቆየት ብለው ሰርግ ደገሱ ፡ ትንሽ ሰርግ ነበር ። እና የሚበላ ነገር በጠሯቸው ሰወች ልክ ተዘጋጀ ።

እንግዶች እየተመገቡ እያለም ፡ ሙሽሮቹ ዴንዝል ዋሽንግተንና ፡ ፓውሌታ ፒርሰን ፡ በሰርጋቸው ላይ የተገኙትን እንግዶች ፡ እየዞሩ ሰላም ሲሉና አብረው ፎቶ ሲነሱ ቆይተው. . ምግብ ሊያነሱ ወደ ጠረጴዛው ሲሄዱ ፡ ባዶ ነው ።
ምግቡ አልቋል ።
......
እንግዶቻቸውን ሸኝተው በሰርጋቸው ቀን ሬስቶራንት ሄደው ተመገቡ ።

ይህ ከሆነ አሁን አርባ አመታት አለፈ ። በዚህ መልኩ የተገናኙት ጥንዶች አራት ልጆች ወልደው ፡ ሶስት መቶ ሚሊየን ዶላር በባንክ አጭቀው ፡ ሆሊውድን የሚያምሰው የመፋታት አባዜ ሳያገኛቸው ፡ እስካሁን አሉ ።
....
በዩቲዩብ ቻናላችን የሚቀርቡ ስቶሪዎችን መስማት ለፈለገ ፡ ከስር ያለው ሊንክ መገኛችን ነው ።

@wegoch
@wegoch
@paappii

By wasyihun
2.7K viewsPapi, 17:29
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-06-29 14:36:51 ውድ አልማዞች!
•••••••
የግመል ነጋዴው በገበያው ለሽያጭ ከቀረቡት ግመሎች መካከል በአንዱ እጅግ ስለተሳበ ከሻጩ ጋር ድርድር ጀመረ። በገዢና በሻጭ መካከል ብዙ ደቂቃዎችን የፈጀ የቀንስልኝ፣ አልቀንስም ክርክር ከተደረገ በኋላ ገዢው በዋጋ ተስማምቶ ግመሉን ገዝቶ ወደ ቤቱ ሄደ።

የግመል ነጋዴው ቤቱ እንደደረሰ አገልጋዩን ጠርቶ የግመሉን ኮርቻ እንዲያወርድ ይነግረዋል። አገልጋዩ የግመሉን ኮርቻ ሲፈታ ከኮርቻው ስር አነስተኛ መጠን ያላት የተቋጠረች ከረጢት ያገኛል። ከረጢቷን ሲፈታ በውድ የአልማዝ ማእድን ተሞልታለች።

አገልጋዩም "አለቃ የገዟት ግመል በነጻ ጭና ያመጣችውን በረከት ይመልከቱ!" ሲል በደስታ ተሞልቶ ጮኸ። ነጋዴውም በአገልጋዩ መዳፍ ላይ በጸሐይ ብርሀን የሚንቦጎቦጉ የአልማዝ እንክብሎች ሲመለከት እጅግ ተደነቀ።

ይሁንና "ግመሏን እንጂ አልማዞቹን አልገዛኋቸውም። አሁኑኑ ለባለቤቱ መመለስ አለብኝ" አለ - ነጋዴው።

አገልጋዩም "ምን የማይረባ አለቃ ነው ያለኝ?!" ሲል በሆዱ ካወራ በኋላ "ማንም ሰው የአልማዞቹን ትክክለኛ ባለቤት ሊያውቅ አይችልም! ሲል ተናገረ።

ይሁንና ነጋዴው ምክሩን ችላ ብሎ ጊዜ ሳይወስድ ባለቤቱን ፍለጋ ወደ ገበያው ተመለሰ። ብዙም ሳይለፋ የተቀሩ ግመሎችን ለመሸጥ ገዢ ሲጠብቅ የነበረውን የግመል ሻጭ አግኝቶ ትንሿን ከረጢት መለሰለት።

የግመል ሻጩም እጅግ ተደስቶ " እጅግ የከበሩ ማእድናቴን በኮርቻው ስር መደበቄን ዘንግቼ ነበር። አሁን ሽልማት እንዲሆንህ በከረጢቱ ውስጥ ካሉት አልማዞች ውስጥ ለዐይንህ ደስ ያሰኘህን ውሰድ!' አለ።

"ለከፈልኩት ገንዘብ ጥሩ ግመል ሽጠህልኛል። ተጨማሪ ሽልማትም ስጦታም አልቀበልም።" አለ - ነጋዴው። ነጋዴው ስጦታውን አልቀበልም ቢልም ግመል ሻጩ እንዲቀበለው ይወተውተው ጀመር።

በመጨረሻም ነጋዴው በፈገግታ ተሞልቶ "ከረጢቱን ልመልስልህ ስወስን ሁለት እጅግ የከበሩ አልማዞችን እራሴ ዘንድ አስቀርቻለሁ! ከእነርሱ የሚልቅ ሽልማት የለም!" አለው።

የግመል ሻጩ የነጋዴው የእምነት ቃል ሲሰማ እጅግ ተበሳጭቶ በከረጢቱ ውስጥ ያሉትን ውድ አልማዞች የጨርቅ እራፊ ላይ ደፍቶ ይቆጥራቸው ጀመረ። ይሁንና ቆጠራውን እንደጨረሰ በእፎይታ ተሞልቶ "በከረጢቱ ውስጥ ከነበሩት አልማዞቼ መካከል አንድም አልጎደለም። የትኞቹን ውድ አልማዞች ነው ለራሴ አስቀርቻለሁ ያልከኝ?"

ነጋዴውም በኩራት ተሞልቶ "እኔ ዘንድ ያስቀረኋቸው ውድ አልማዞች ታማኝነቴና ለእራሴ ያለኝ ክብር ናቸው!" ሲል መለሰለት።

ሻጩ የሰማውን ነገር ባለማመን ዐይኖቹን አፍጥጦ ነጋዴውን ከመመልከት ውጪ መልስ ሊሰጠው አልቻለም።

**
ሁላችንም ወደ እራሳችን መመልከትና እነዚያ ውድ አልማዞች እንዳሉን እንፈትሽ። ሁለቱ ውድ አልማዞች ያለው ማንኛውም ሰው የዓለማችን ባለጸጋው ሰው ነው።

@wegoch
@wegoch
@paappii
3.4K viewsPapi, 11:36
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-06-26 10:50:45 ሀገር ሰላም ብዬ የተቀመጥኩበት ታክሲ ውስጥ ጎኔ ያለችው ልጅ በሹክሹክታ ድምጽ ምን አለችኝ አባቱ ትወርድልኛለህ? ደሞ የአይኖቿ መስለምለምስ ትውልዱ አይን አውጥቷል ስትሉኝ አለማመኔ my dirty mind

ባለፈው አዳነች አቤቤ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሀይል ለመናድ ከአንድ ክልል ብቻ የሚደረግ ከፍተኛ ፍልሰት አለ ስትል ዲቻ ምንም እንዳልመሰለው ሳስብ ብቻዬን ሳቄ ያመልጠኛል ጦሶ

ትናንት ምሳ የበላሁበት ስጋ ቤት ቆራጩ" የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ" እያለ እየዘፈነ ነፍ ስጋ የሰጠኝ በደህና ነው ትላላችሁ አሁን በጠዋት ችክክም ችክክም ችከክም በል በል እያለኝ እኮ ነው

አርባ አመት ሙሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ለመሆን የታገለው ቀጨላ መርዳሳ የኦነግን የምስረታ በአል አብሮ ያከብራል ማለት ነው

በየ ለቅሶ ቤቱ ግን ከቀብር በኋላ የሚዘጋጅ የምሳ ግብአት ቀይ ምስር እና አልጫ አተር እንዲሆን ያወጁት ቀደምት እናቶች በማ ዘመነ መንግስት እንደነበሩ ዶክተር ሮዳስ ሲያብራራ ሰምቼው አላውቅም ወይስ አምልጦኝ ነው

ከአባታቸው ባገኙት አስር ሚሊየን ብር እና አምስት ተሽርካሪ ደሞ የሆነ የሆነ ሱቅ ተነስተው የሀብት ማማ ላይ የተቀመጡ ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ብለው ንግግር የሚጀምሩ  ቱጃሮች በወንጀል እንዲከሰሱልን ስል በትህትና አመለክታለሁ

በቀደም እለት ዶፍ ዝናብ እየዘነበ ጣራችንን እንደ አታሞ ሲደልቅ ከዛ የዝናብ ኳኳታ ጋር በሚታገል ጮክ ባለ ድምጽ እናቴ
"እስቲ አንድ ልጅ ወልደህ አምጣልኝ" ብላ ያሳቀቺኝ ሳቅ አመቱን ሙሉ ከሳቅኩት ይበልጣል እኔ እኮ እድሜዬን መቁጠር የረሳች መስሎኛል ለካ እስከዛሬ እየቆጠረች ነው Shame on you Mom እኔ ላንቺ ጊዜ ምን ብዬሽ አውቃለሁ

ያቺ በጣም ቆንጆ ሂጃቢ ያስሚን ወንድ አትጨብጥም 2 አመት እኮ አንድ መስሪያ ቤት አብረን ሰርተናል ሁሌም ስንገናኝ በርቀት እንደታቦት ብቻ ጎንበስ ቀና ብዬ ተሳልሜ ነበር ሰላም የምላት ምናል አንድ ቀን ከሀር የሚለዝብ የሚመስለኝ ለስላሷ እጇን ብታስነካኝ መዳፌ ላይ ያረፈ ጠረኗን ከሷ ተደብቄ አንድ ቀን ባሸተው ምነበረ

በቀደም መንገድ ላይ እየሄድኩ በሀሳብ ጭልጥ ከማለቴ የተነሳ የማስበው ጠፍቶኝ ወደራሴ ስመለስ 801, 802, 803, 804 እያልኩ አገኘሁት ራሴን ምን ለምን እየቆጠርኩ እንደነበረ ግን ስካሁን ትዝ አላለኝም። እየጨለልኩ ነው እንዴ

ከላይ ያልኩት ሁሉ አይረባም አውቃለሁ
አንዳንዴ እንዲ ነኝ
ወፈፍ ያደርገኛል እዘባርቃለሁ

By Binyam behaylu

@wegoch
@wegoch
@paappii
4.2K viewsPapi, 07:50
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-06-21 10:24:55 ኩርፊያህን ለምን እንደምናፍቀው ይገባህ ይሁን…… የምልህ አለአይደል ስትነጫነጭ ጊዜ …… ወይ ስትቆጣ ንዴትህን ግልፅ ስታደርግልኝ…… ትኩረቴን ፈልገህ ልክ እንደህፃን ሲያደርግህ በሆነው ባልሆነው ስታኮርፍ ኩርፊያህ ታስፈልጊኛለሽ የሚል መልዕክት ያለው ይመስለኛል እንክብካቤ ፈልገህ ትኩረቴን ሽተህ ይመስለኛል …… ሰዎች ፊት የነበረህን ኩራት አሽቀንጥረህ እኔ ዘንድ ብሶትህን ስትነፋረቅ…… ከጉያዬ ሽሽግ ስትል ፀጉርህን በጣቶቼ ዳበሳ ስበታትናቸው ጭንቀትህም አብሮ ቢበተን ……ትኩስ እንባህን በፈገግታዬ ባብስልህ…… እኚህን ሁሉ ሁነቶች እወዳቸዋለሁና ኩራትህን አሽቀንጥረህ መሸሸግን ፈልገህ ናልኝ…… በዚህች በጠበበችህ አለም ሳይታክትህ ትሸጎጥበት ዘንዳ እቅፌ ላንተ ሰፊ ነውና መሰልቸትን እኔ ጋር አታስበው…… የነፍስህ ጭንቀት ሲራገፍ የስስት አይኖችህ በፈገግታ ሲያበሩ እኔነቴን አንተው ውስጥ አየዋለሁ እናም አለም ሁሉ ብትጠብህ እቅፌ ላንተ ሰፊ ነው

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Fereha nuraddis
5.6K viewsPapi, 07:24
ክፈት / አስተያየት ይስጡ