Get Mystery Box with random crypto!

Fifty shades of him ' ' አለሜ የምለው እርሱ 'የኔ ጨረቃ ' ብሎ ያለኝ ለታ ስሸሻት | ወግ ብቻ

Fifty shades of him
'
'
አለሜ የምለው እርሱ "የኔ ጨረቃ " ብሎ ያለኝ ለታ ስሸሻት የኖርኳት የምጠላት ጨረቃ ፊት እስክቆም ድረስ የአምስተኛ ክፍል ሳይንስ መምህራችን "ፀሃይ ትልቋ ኮከብ ናት .... ጨረቃ ደግሞ ከእርሷ ብርሃን ትሰበስባለች "ካሉን ቀን ጀምሮ ብርሃን መስረቋ አናዶኝ ጨረቃን ጠምጄ ያዝኳት።

ስንቴቴ "የዛሬው ብርሃንስ ጤፍ ያስለቅማል" በተባለለት ምሽት ሰማይ ኮርኒስ ላይ የተንጠለጠለች የብርሃን ኳስ ፅልመቱ ላይ የተንሰራፋች ለታ፣ እርሷን ለመሸሽ ስሮጥ አምጪ የተባልኩትን የታናሽ እህቴን ወተት ንጬ ቅቤ ወጣለት።
እናቴም የተቀበለችኝን የወተት እቃ ከፍታ እያየች "ብራ ጨረቃ እየጠበቀማ የሚያበር ጋኔል ሰፍሮብሻል" ስትል የምሮጠው ጨረቃ ወለል ስላለች መሰላት እንጂ ከእርሷ እየሸሸሁ እንደሆነ አታውቅም ነበር።

የኋላ ኋላ የጠመድኳት ጨረቃ መልሳ ጠምዳኝ ነው መሠል የሃምሌ ጭጋግ በጋረደው ምሽት መሃል አግኝቶኝ "ቤት ሄደን ጃኬት ደርቤ ልሸኝሽ " ያለኝን የሰፈሬን ጎረምሳ ተከትዬ ቤቱ ደርሰን ጃኬት ይደርባል ብዬ ስጠብቅ ልብሱን ሁሉ አውልቆ ርቃኑን ወደ ቆምኩበት መጥቶ ወተቴን ተቀብሎኝ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦ ልብሴን ሲያወላልቅ እንደበግ እየተነዳሁለት የሆነው ሁሉ ሆኖ " አይዞሽ" እያለኝ አስሬ እንደምንም ለባብሼ ከቤቱ ስንወጣ ቀና ብዬ ሳይ፣ ቅድም የጋረዳትን ጭጋግ ገፍፋ የወጣች ሙሉ ጨረቃ ቁልቁል ስታየኝ አየኋት። የያዘኝን እጁን መንጭቄ በጉያዬ መኻል ያለውን ህመም ችዬ እየተደነቃቀፍኩ ለመሮጥ ስንቧቸር በብሩህ ጨረቃ ቀናት የማይነሳሳ ሴትነቴን በደመና ተከልላ ያታለለችኝ ሙሉ ጨረቃ ላስታውሰው እንኳ ለማልሻው ደብዛዛ ሰው ድንግሌን እንደሸለመች፣ ከእኔ እንዳስነጠቀችብኝም እያሰብኩ ነበር።

እና "የኔ ጨረቃ " ያለኝ ቀን ዘመናት በመሃላችን በኩርፊያ ያለፉት እኔና እርሷ ማዶ ለማዶ ፊት ለፊት ተፋጠጥን። አልጠላኋትም የዛን ቀን አልሸሸኋትም ያን ማታ ብቻ ግን እርሷን ሆንኩላት፤ እኔንም የሆነች መሰለኝ።

በእኔና በእርሱ መካከል የነበረው የቦታ ርቀት በዘመን ሁሉ የሚሰፈር ይመስለኝ ነበር። በቃ እርሱን የማቀርብበት ከእርሱ የምገናኝበት ምንም መንገድ የለም ብዬ ተስፋ ከቆረጥኩ ብሰነብትም አለሜ አፍ አውጥቶ "አንተያይም ተስፋ ቁረጪ" ሲለኝ ቅስሜ ደቅቆ ተሰበረ።

ገላዬ የናፍቆት ብርድ ያቆራመተው ነው። በእርሱ መታቀፍ በእርሱ መነካት ብቻ ይፈልግ ነበር። ጭኔ ላይ ያቆጠቆጡ ጥቃቅን ፀጉራት ሲቆሙ ይታወቀኛል፣የጡቴ ጫፎች ሲሾሉ ይታወቀኛል ፣ ብሽሽቴን ሲሞቀኝ ይታወቀኛል፣ ገላዬን የኔ ያልሆነ ያህል ልመቆጣጠር ሲያቅተኝ።

እየሩስዓለሜ ነበር። ሰርክ ዕለት ልሳለመው የማልመው ነክቼው ልፈወስ ዳብሼው ካለ እና ከሚመጣው ነገር ሁሉ ልነፃበት የምፈልገው።

ዳስሼው ከቅዱስነቱ ቅንጣት ቆንጥሬ ዘመኔን ሁሉ በደጄ የሚፈስ የቅባ መውደዱን ዘይት ነፍሴን እንዲያረሰርስ፤ ከአላፊ አግዳሚው መሃል ጨርቁን ጨብጬ ልፈወስ ....

"ካለሽበት የምመጣበት መንገድ ጠቧል" ሲለኝ ለመዓከ ገብሬል አባቴ በእለተ ቀኑ ነግሬው፣ "በግራም በቀኝም የለኝ ካላንተ የማስቸግረው" ብዬ ከቅፅሩ ተንበርክኬ የደጁን ጠጠር ዘግኜ ነጠላዬ ጫፍ የቋጠርኩት፣ ቤቴ ስመለስ ጎረቤቴ ለሣምንቱ ሰባት ቀናት ሁለት ጡት ያላቸው ሶስት ጀበናዎች አፈራርቃ የምትካድም፣ የፋጤና ከድጃን ቀናት የምታከብር፣ በአርሲዋ እመቤት ምትምል ባለውቃቢ ደግ ሴት የገብሬል ቡና ካልጠጣሽ ብላ ስትበቅተኝ፣ እንደታቦት ቀን እየቆጠረች ከምታወጣቸው ፍንጀሎቿ በአንዱ ያፈላችውን ቡና አቀብላኝ ...ምን አስተከዘሽ ብትለኝ "የምወደው ሰው የሰው ሃገር ቀረብኝ " ብያት እጆቿን ወደ ላይ ዘርግታ መአት አይነት መለዓክ፣ መአት አይነት መላይካ እየጠራች በአማርኛ በኦሮምኛ ተማፅኖዋን ስታንበለብል
"በየአፍ መፍቻቸው ይሆን የምትፀልይላቸው?" እያልኩ እየሰማዃት.....

የማግሁትን ቡና ሲኒውን ላቀብላት ከተቀመጥኩበት ስነሳ ነጠላዬ ጫፍ ከተቋጠሩ የገብሬል ጊቢ ጠጠሮች መሃል አንዲቷ ጊርጊራዋ ላይ ድንገት ተፈትታ ብትወድቅ ከእጣን ማጨሻዋ ላይ ሃምራዊ ጢስ ሲንቦለቦል አየሁ ...በሰፈሩ ቀድሞ ያልነበረ ጣዕመ አልባስጥሮስ ጠረን ሸተተኝ። ይህም ለመምጣቱ ምልክት ሆኖኝ መላዕክት መላይካዎቹ ጭላንጭል ተስፋ ቢያሳዩኝ ታላቁ ፀገመ እንዳለው ተስፋ መቀነት ሆነኝ።

አመታት እንደቀናት አልፈው "ካለሽበት የምመጣበት መንገዱ ሁሉ ቁልፍ ነው" ያለኝ አለሜ ሃገር ቤት ድረስ መጣ። ግን የሌላ ሰው ሆኖ ከሌላ ሰው በፍቅር ከንፎ ያለሁበት ከተማ ውስጥ ተገኘ።

ይህን ሳውቅ "ምን ከከፍታ ሆነው ወደ ታች ቢወረውሩት እርሱ እንደሁ እንደ ላባ ነው ተችሏቸውም አይሰብሩት" ብዬ የታባልኩለት ልቤ እንክት ብሎ ወደ እልፍ ቅንጣቶች ደቀቀ። እንባዬ በጉንጬ መም ነድሎ እንደ ጤግሮስ ዥረት ሆነ።

ደውሎ "ላግኝሽ" አለኝ
ግን ላገኘው አቅም አነሰኝ .... ናፍቆቴ ዘመን ተሻግሮ መጥቶልኝ ከኔ ከተማ ላገኘው ጉልበቴ ከዳኝ ላገኘው ወኔዬ ጠፋ የሰው መሆኑን ስሰማ።

የሚሰሙኝን ስሜቶች ስም ልሰጥ ስጥር ከረምኩኝ ቅናት ነው? ፍቅር ነው? በእርሷና በእርሱ የሚሰማኝ ይህ ነገር ምቀኝነት ነው? እያልኩኝ.... ሌት ተቀን ስብከነከን እህህ ብዬ ከረምኩኝ።

አንድ ቀን መልክት ደረሰኝ
"በዚህ ፀባይሽ ሳላገኝሽ ልሄድ ነው።"
"መች?" አልኩት መለስኩና "ዛሬ" አለኝ......ይሄኔ አንጀቴ ተላወሰ ጥፋተኝነት ተሰማኝ "ከማንስ ጋር ቢሆን ምን አለ አንዴ እንኳ ባየው ?" እያልኩኝ ፀፀት እንደጦስ ዶሮ አርባ ዘጠኝ ጊዜ ሲዞረኝ ቤት ገባሁ። በረንዳ ወጣሁ። ምጥ እንደያዛት ድርስ እርጉዝ ስንቆራጠጥ ቆይቼ ድንገት ወደ ላይ ቀና ብል ጨረቃ ከአናቴ ቆማ እኔን በአንክሮ ስትሰልል .....

ልጅነት እንደ ጧት ጤዛ አላፊ ነው ረጋፊ ወጣትነትም እጢ ነው ክው ያሉ ለታ ጠፊ ... እሱን በጠበኩባቸው ዘመናት መኻል የታዘብኩት ፍቅርን ከኖሩት በላይ የናፈቁት ናቸው የሚያውቁት።ጊዜ አቃጣሪ ነውና ጉርምስናዬን አስጥሎ ምን ለእርጅና ቢድረኝም እንደ አዲስ "ቀን አንድ" ብዬ ዳግም ብጠብቀው ቅር አይለኝም።

የስልኬ ሰሌዳ ላይ ሚሴንጀሬን ከፍቼ መፃፍ ጀመርኩ ።
"አለሜ በሰላም ግባ ... የሆነ ቀን ግን ናልኝ ለእኔ ብቻ ብለህ እኔ ጋር ብቻ ናልኝ"

Note :- ናፍቆት ከፍቅር ይበልጣል።

@getem
@getem
@paappii

By Elsa mulgeta