Get Mystery Box with random crypto!

[ማነቂያ] የሰኔ ጢንፍ የሚያበሰብሰው፣ አቋምና ማገሩ መጋለጥ የጀመረ የጭቃ ግድግዳቸውን ተደግፎ | ወግ ብቻ

[ማነቂያ]

የሰኔ ጢንፍ የሚያበሰብሰው፣ አቋምና ማገሩ መጋለጥ የጀመረ የጭቃ ግድግዳቸውን ተደግፎ ከካፊያው ጋር የሚመጣውን ቅዝቃዜ ሽሽት ከእድሜ ብዛት መነሾ የሳሳ ኮሌታው የተበዘበዘ ሸሚዙን ከአንገቱ አጣብቆ ኩርምት ብሏል። እናቱን ጥበቃ!

እሷ እንደሁልጊዜው ሁሉ "የትልቅ ሰው ወሬ ልናወራ ስለሆነ ውጭ ቆይ! ጎሽ የ'ኔ ልጅ!" በማለት ነበር በሩን ከውስጥ የቀረቀረችበት።

እናቱ በየዕለቱ ከተለያዩ ወንዶች ጋር ምን እንደምታወራ አያውቅም። ቢያውቅም አይገባውም። ብቻ ወሬአቸው ቶሎ እንዲያልቅ ከደጃፍ ተቀምጦ እላዩ ላይ የሚፈረፈረውን ወደ መፍረሱ የተጠጋውን የግድግዳ አፈር እያራገፈ በተቻለው ሁሉ በእንቅልፍ ላለመውደቅ እየታገለ ይጠብቃታል።

በርግጥ የሆነ ቀን ግን ብርዱ በጣም ሲብስበት የፒያሳ ጎዳና ተዳዳሪ ውሾች ዛቻ ሲፀናበት "እማ ጨለማውን ፈራሁት ወሬአችሁን አልሰማባችሁም አስገቢኝ” ብሏት ያውቃል።

ለዚህ እሮሮው ከእናቱ ያገኘው መልስ ግን "ወንድ ልጅ አይደለህ ለምን ትፈራለህ…" የሚል ነበር። አንዳንዴ ሳስበው ወንድ መሆን መረገም ይመስለኛል!! ወንድ መሆን በራሱ ጫንቃ የሚያደነድን የሚመስላቸው ብዙ አውቃለሁ። ወንድነት ፍዳን ከመቀበል ጋር ያለውን አወንታዊ ቁርኝት የሚያሳስበው ማግኘት እምብዛም ነው!

በርግጥ በእሷም ፍርድ የለ! ምን ታድርገው! ገላዋን ለጎረምሳ የስካር ማብረጃ መስዋዕት ካላቀረበች እሷንም ልጇንም አድፍጦ የሚጠብቃቸው ከርሳም ርሃብ ይበላቸዋል።

እዚህ መሸት ሲል አዳኝና ታዳኝ፣ ገጸባህርይ እና ድርሰት፣ ንጋትና ምሽት፣ ገሃነምና ገነት፣ ገዥና ሻጭ የሚገዙበትን ገንዘብ የሚሸጡትን እቃ ይዘው በድንግዝግዙ ይገናኛሉ።

የገዢው መድረሻ ከደቂቃዎች ሀሴት የሻጭም ዋጋ ወስፋትን ገሎ ከማደር አልፎ አያውቅም። እዚህ ህይወት ዛሬን ተንፈስ ስለማለት ጠግቦ ስለማደር እንጂ ነገን ስለመድረስ አይደለችም።

እዚህ እናትነት በአደባባይ ለሽያጭ ይቀርባል፣ እህትነት ይሸቀጣል። አባትነት ይረክሳል፣ ወንድምነትም እንዲሁ። ሁሉም ለስሜቱና ለሆዱ ብቻ፤ ትግሉ፣ መፍጨርጨሩ፣ ሳንጃ መሞሻለቁ፣ ቡጢ መሰናዘሩ፣ ይሉኝታን መጣሉ… ዛሬን ይተርፉ ዘንድ ብቻ ነው። እዚህ ሁሉም የሚሰዋለት የየግል ጥም አለው። ይህ ዶሮ ማነቂያ ነው!

በረድፍ ተደጋግፈው የተሰደሩት ጠባብ ገላ መሸቀጫ ቤቶች የእነሱን ቤት ጨምሮ መጋረጃቸውን ከውጭ አድርገው በውሽንፍር እያውለበለቡ ከውስጥ ተቀርቅረዋል። የአልጋዎች መንሰጣሰጥና በወሲብ የሚቃትቱ ድምፆች ሰፈዋል።

እንግዲህ
የመጋረጃቸው ከውጭ ሆኖ በሩ ከውስጥ መቀርቀር ቤቱ በወሲብ ፈረስ እየተጋለበ ስለመሆኑ ምልክት መሆኑ ነው። ማንም አንቀጽና ገጽ ጠቅሶ ያላወጀው ግና ሁሉም የሚያወቀው ምልክት። ገዥና ሻጭ፣ ኢላማና ፍላፃ የሚግባቡበት እጅግ የረቀቀ ምልክት።

ቀስ እያለ
ካፊያን ውሽንፍር አመሻሽን ወድቅት ተስፋን ሀዘን ተካቸው። አልፎ አልፎ እየተሯሯጡ ከሚያልፉ የውሻ መንጋ በቀር በሰፈሩ ብቅ የሚል አይታይም። የሰፈሩን ሰርጣሰርጥ ቅያሱንም ሁሉ እንደ መቃብር ቤት ያለ ጭርታ ከበበው። ከላይ ጎርፉ እያንከባለለ የሚያመጣቸው የለስላሳ ጠርሙሶች እየተንገጫገጩ አረፋ እየደፈቁ ከቤታቸው ፊት በሚገኝ ቦይ ስር ያልፉ ጀመር። የህይወቱ ማለዳ ልጅነቱ እየተንገጫገጨ ያለፈ መሰለው…

“አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣አራት…”

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Tamiru temesgen