Get Mystery Box with random crypto!

ውድ አልማዞች! ••••••• የግመል ነጋዴው በገበያው ለሽያጭ ከቀረቡት ግመሎች መካከል በአንዱ እጅ | ወግ ብቻ

ውድ አልማዞች!
•••••••
የግመል ነጋዴው በገበያው ለሽያጭ ከቀረቡት ግመሎች መካከል በአንዱ እጅግ ስለተሳበ ከሻጩ ጋር ድርድር ጀመረ። በገዢና በሻጭ መካከል ብዙ ደቂቃዎችን የፈጀ የቀንስልኝ፣ አልቀንስም ክርክር ከተደረገ በኋላ ገዢው በዋጋ ተስማምቶ ግመሉን ገዝቶ ወደ ቤቱ ሄደ።

የግመል ነጋዴው ቤቱ እንደደረሰ አገልጋዩን ጠርቶ የግመሉን ኮርቻ እንዲያወርድ ይነግረዋል። አገልጋዩ የግመሉን ኮርቻ ሲፈታ ከኮርቻው ስር አነስተኛ መጠን ያላት የተቋጠረች ከረጢት ያገኛል። ከረጢቷን ሲፈታ በውድ የአልማዝ ማእድን ተሞልታለች።

አገልጋዩም "አለቃ የገዟት ግመል በነጻ ጭና ያመጣችውን በረከት ይመልከቱ!" ሲል በደስታ ተሞልቶ ጮኸ። ነጋዴውም በአገልጋዩ መዳፍ ላይ በጸሐይ ብርሀን የሚንቦጎቦጉ የአልማዝ እንክብሎች ሲመለከት እጅግ ተደነቀ።

ይሁንና "ግመሏን እንጂ አልማዞቹን አልገዛኋቸውም። አሁኑኑ ለባለቤቱ መመለስ አለብኝ" አለ - ነጋዴው።

አገልጋዩም "ምን የማይረባ አለቃ ነው ያለኝ?!" ሲል በሆዱ ካወራ በኋላ "ማንም ሰው የአልማዞቹን ትክክለኛ ባለቤት ሊያውቅ አይችልም! ሲል ተናገረ።

ይሁንና ነጋዴው ምክሩን ችላ ብሎ ጊዜ ሳይወስድ ባለቤቱን ፍለጋ ወደ ገበያው ተመለሰ። ብዙም ሳይለፋ የተቀሩ ግመሎችን ለመሸጥ ገዢ ሲጠብቅ የነበረውን የግመል ሻጭ አግኝቶ ትንሿን ከረጢት መለሰለት።

የግመል ሻጩም እጅግ ተደስቶ " እጅግ የከበሩ ማእድናቴን በኮርቻው ስር መደበቄን ዘንግቼ ነበር። አሁን ሽልማት እንዲሆንህ በከረጢቱ ውስጥ ካሉት አልማዞች ውስጥ ለዐይንህ ደስ ያሰኘህን ውሰድ!' አለ።

"ለከፈልኩት ገንዘብ ጥሩ ግመል ሽጠህልኛል። ተጨማሪ ሽልማትም ስጦታም አልቀበልም።" አለ - ነጋዴው። ነጋዴው ስጦታውን አልቀበልም ቢልም ግመል ሻጩ እንዲቀበለው ይወተውተው ጀመር።

በመጨረሻም ነጋዴው በፈገግታ ተሞልቶ "ከረጢቱን ልመልስልህ ስወስን ሁለት እጅግ የከበሩ አልማዞችን እራሴ ዘንድ አስቀርቻለሁ! ከእነርሱ የሚልቅ ሽልማት የለም!" አለው።

የግመል ሻጩ የነጋዴው የእምነት ቃል ሲሰማ እጅግ ተበሳጭቶ በከረጢቱ ውስጥ ያሉትን ውድ አልማዞች የጨርቅ እራፊ ላይ ደፍቶ ይቆጥራቸው ጀመረ። ይሁንና ቆጠራውን እንደጨረሰ በእፎይታ ተሞልቶ "በከረጢቱ ውስጥ ከነበሩት አልማዞቼ መካከል አንድም አልጎደለም። የትኞቹን ውድ አልማዞች ነው ለራሴ አስቀርቻለሁ ያልከኝ?"

ነጋዴውም በኩራት ተሞልቶ "እኔ ዘንድ ያስቀረኋቸው ውድ አልማዞች ታማኝነቴና ለእራሴ ያለኝ ክብር ናቸው!" ሲል መለሰለት።

ሻጩ የሰማውን ነገር ባለማመን ዐይኖቹን አፍጥጦ ነጋዴውን ከመመልከት ውጪ መልስ ሊሰጠው አልቻለም።

**
ሁላችንም ወደ እራሳችን መመልከትና እነዚያ ውድ አልማዞች እንዳሉን እንፈትሽ። ሁለቱ ውድ አልማዞች ያለው ማንኛውም ሰው የዓለማችን ባለጸጋው ሰው ነው።

@wegoch
@wegoch
@paappii