Get Mystery Box with random crypto!

ወግ ብቻ

የቴሌግራም ቻናል አርማ wegoch — ወግ ብቻ
የቴሌግራም ቻናል አርማ wegoch — ወግ ብቻ
የሰርጥ አድራሻ: @wegoch
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 21.12K
የሰርጥ መግለጫ

✔በየቀኑ ምርጥ ምርጥ የጥበብ ስራዎችን ለማግኘት የቻነላችን ተከታይ ስለሆኑ እናመሰግናለን።
✔ @getem @serenity13
✔ @wegoch @Words19
✔ @seiloch
✔ @zefenbicha
Creator @lula_al_greeko

Ratings & Reviews

4.33

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

2

4 stars

0

3 stars

1

2 stars

0

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 7

2022-11-21 22:03:30 «ከአባቴ ቀጥሎ እንዳንቺ ያዋረደኝ ፣ ትንሽ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ፣ ራሴን እንድጠላ ያደረገኝ ሰው የለም። ከዛሬ ነገ ትወጂኛለሽ፣ በፍቅርሽ እፈወሳለሁ ብዬ ጠበቅኩሽ። በየቀኑ ናቅሽኝ!! ለፍቅሬ ምላሽሽ ሁሌም እንደበረዶ የቀዘቀዘ ቃላት ነው የምትወረውሪልኝ። <አንተም ወንድ ሆነህ?> ያላልሽኝን ቀን ብቆጥረው ከእጄ ጣት አይበልጥም!! ለአባቴ እንደልጅ እንደሰው ነው የከሸፍኩበት። አንቺ ግን ወንድነቴንም ነው የቀማሽኝ!! አብሬሽ ባሳለፍኩት እያንዳንዱ ቀን ትንሽ በትንሽ በራስ መተማመኔን እየሸረፍሽ ካንቺ ሌላ ሴት እንደወንድ እንኳን የማትቆጥረኝ እየመሰለኝ አብሬሽ ቆየሁ። ምክንያትሽን ሳትነግሪኝ ለወራት ስትዘጊኝ እጠብቃለሁ። ምክንያትሽን ሳትነግሪኝ ስትመለሺ እቀበልሻለሁ። ላንቺ ምንም ነኝ!! በፈለግሽ ሰዓት ሄደሽ ስትመለሺ የምታገኚኝ እቃሽ ነኝ!! እኩል ድርሻ ባለን ቤት ላይ እንኳን ፈላጭ ቆራጯ አንቺ ነሽ!! አንቺ አለቃ እኔ ባሪያሽ ነኝ!! ንገሪኝ ለመጥላት በቂ ምክንያት አይደለም?»

አልመለስኩለትም። ቁጢጥ ካልኩበት ተነሳሁ!!!! ቆሜ ምን እንደማስብ አላውቅም ግን ፈዝዣለሁ። እሱ ከአሁን አሁን ምን ታደርገኛለች ብሎ በሰቀቀን እየጠበቀኝ ነው።

«ይቅርታ!!! ይሄ ሁሉ አይገባህም ነበር። እንዲህ እንዲሰማህ ማድረጌንም አላውቅም ነበር። ስቀህ ማለፍህ ልክ የሆንኩ እንዲመስለኝ አድርጎኛል። ይቅርታ አድርግልኝ!! ከልቤ ነው አንተ ጥሩ ሰው ነህ!! ቢያንስ ለእኔ ጥሩ ሰው ነበርክ!! አይገባህም ያልኩህ የእውነቴን ነው። » አልኩት። ሞቶ መንግስተሰማያት ደርሶ ይሁን በእውኑ እዚህ ምድር ላይ ሆኖ ይሄን ከእኔ አፍ መስማቱ እያወዛገበው አይኑን ጎልጉሎ ያየኛል።

«ሙከራህን ብትደግመው የምምርህ እንዳይመስልህ!! ቤቱን ልሸጠው እፈልጋለሁ!! ህገወጥ ስራውን የምታቆም ከሆነ የእኔን ድርሻ ልሽጥልህና የቤት ኪራይ እየከፈልክ ስራበት። አይ ካልክ ግን ቤቱን ለቀህ ትወጣለህ!! እኔ ጨርሻለሁ!!» ብዬው ወጣሁ።

ከወጣሁ በኋላ ያ ስሜት ተሰማኝ!! ባዶ የሆነ ስሜት!! ጣዕም አልባ ስሜት!! የምሄድበትን ሳላውቅ እየነዳሁ ስዞር ቆይቼ አመሻሽ ላይ አባ መልከፃዲቅ ያሉበት ቤተክርስቲያን ሄድኩ!! እግራቸው ላይ ተደፍቼ ማልቀስ ፈልጌ ነው።ኮቴን ክለብ እረስቼው የለበስኩት እጁ የተጋለጠ ነገር ስለነበረ ሱቅ ገብቼ ነጠላ እና ሹራብ ደርቤ ቀጠልኩ።
በሩን አልፌ ቦታዬጋ ስደርስ አይኔ ከቆቡ ውስጥ ተጎልጉሎ ሊወጣ ደረሰ። አባ የሚቀመጡባት ጉቷቸው ላይ ተቀምጠው ጎንጥ እኔ በምቀመጥበት ቦታ እግራቸው ስር ተቀምጦ ያወራሉ። እግሬ ተወለካከፈብኝና ቆምኩ። አየኝ!! ምንም ቀን እንዳልዘጋኝ!! ልቤ በመከፋት ተኮማትራ ከእጄ ጭብጥ እንዳላሳነሳት፣ መከፋት እና ተስፋ መቁረጥ እንዳላሸከመኝ ሁሉ ፈገግ አለ።

                        ........... አልጨረስንም!! ..........

@wegoch
@wegoch
@paappii
541 viewsDAVE / PAPI, 19:03
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-21 22:03:30 ሙሉሰውም ጭንቅላቱ የተዛባ እስኪመስለኝ ድረስ የሚሰራው ሁሉ የሚበላሽበት ፣ ከቀን ወደቀን የደጋፊዎቹ መወድስ እየቀነሰ  የሚተቸው ሰው ቁጥር እየበዛ ጭራሹኑ አስተካክሎ የሚከውነው ነገር ጠፋው!! እዚህ ነጥብ ላይ እየፈራሁት መጥቼ ነበር። የሆነ ቀን ገድሎኝ ራሱን ሊገድል ይችላል ብዬ ማሰብ ጀምሬ ነበር። ግን ለምንድነው የማልረካው? እሱን በቁሙ ገድዬው ሌሎቹን ጨርሼ አሁንም የተሸነፍኩ ዓይነት ስሜት የሚሰማኝ ለምንድነው? ያ ሁሉ ቁስል እነርሱን ስበቀል የሚድን መስሎኝ አልነበር? ለምን አሁንም እንደድሮ ያመኛል? ያደረግኩት ክፋት እና በቀል ጥያቄዬን እንዳልመለሰ ወይም ህመሜን እንዳልፈወሰ እያወቅኩም በክፋት መቆመሬን ቀጠልኩበት።

ገንዘብ ካለ ሲደመር ስልጣኑ ያለው ሰው ካወቅኩ የማላገኘው ነገር ጥቂት መሆኑን ስረዳ የማይጣሱ ብዙ መስመሮች ጣስኩ። ከአንድ ባልደረባው ጋር በአንድ ውሳኔ ሳይግባቡ ቀርተው እራሱ ስንቴ መጥቶ የባለገበትን ቤት እንደማስፈራሪያ ተጠቅሞ የሙሉ ሰውን እጅ ጠመዘዘው። ሙሉሰው አይደለም የማይፈልገውን ውሳኔ መወሰን ቢሞት ራሱኮ ግድ አይሰጠኝም ግን ሰው መበቀል እና ክፋት ደሜ ውስጥ ያለ ነገር መሰለኝ። ሰውየው ሲባልግ በድብቅ ቀረፅኩት። የተከበረ ባለትዳር እና የልጆች አባት ስለሆነ የቀረፅኩትን ቪዲዮ ሳሳየው ሽንቱን ሱሪው ላይ ሊሸናው ምንም አልቀረውም። የሚገርመው ግን <ከዚህ በላይ ምን ሊመጣ?> ብሎ ይሆን አልገባኝም። እየመጣ መባለጉን አላቆመም!! በድብቅ ካሜራ እንደቀረፅኩት ለአንድ ሰው ትንፍሽ ቢልና አንድ ደንበኛ ባጣ በራሱ እንዲፈርድ አስጠንቅቄዋለሁ። እውነትም ለማንም ትንፍሽ ሳይል ቀርቶ ይሆን ወይም የነገራቸውም ሰዎች እንደእርሱ ሱሳቸው በልጦባቸው አላውቅም የቀረ የለም። ለምናልባቱ የምፈልጋቸውን ሰዎች የፖርን ፊልም ማስቀመጤ አልቀረም። አስፈልጎኝ የምጠቀምበት ቀን እስኪመጣ ድረስ

የሙሉ ሰውን ከቀልቡ አለመሆን ተከትሎ ህዝቡ በሱ ላይ እንዲነሳ አጋጋይ በዛ!! ጨዋ ናቸው የሚባሉት እንኳን እሱን ለመጣል ተወለካከፉ!! ጨዋታው ስላዝናናኝ ብቻ ቆሻሻቸውን እየፈለጉ ሲሸነፉ ማየት የበላይነት ስሜት ስለሚሰጠኝ ወደድኩት። ለእኔ ቀላል ጨዋታ እንደሆነው ለእነሱ አልነበረም እና ከሙሉሰው ጀርባ ነገር የምቀምረው እኔ መሆኔን ሲያውቁ ሁለት ተቃራኒ ጠላቶች አፈራሁ። የተወሰኑት ሊያጠፉኝ የሚያደቡ ሲሆኑ የተቀሩት መዝራት የፈለጉትን ክፋታቸውን እና ወጥመዳቸውን በእኔ ተከልለው መከወን የሚፈልጉ ጥቅመኞች (አጋጣሚውን ካገኙ በራሴው ወጥመድ የሚያጠምዱኝ ሴረኞች ናቸው።) ሁለቱም ወገን በአይነቁረኛ የሚፈራኝ እና የሚጠላኝ ሰውም ሆንኩ። ባሎች ለሚስቶቻቸው ስለእኔ አሙላቸው። ሚስቶች ተሰብስበው ስጋዬን በሉት። በውስጣቸው ግን እነርሱ በባላቸው ላይ የሌላቸው ስልጣን እኔ ስላለኝ ቀኑ!! ተሰብስባ በመንገሽገሽ ስሜን የምትጠራ ለብቻዋ ስትሆን ልታገኘኝ ትፈልጋለች።

እኔም ሲሰለቸኝ እሱም ሲታክተው አንድ ቀን ቤቱ ሄድኩ!! ባልገድልህም ሞተሃል ይበቃሃል ልለው ነበርኮ አካሄዴ! ከልቤ በቅቶኝ በቃህ ካሁን በኋላ የምፈልገውን አግኝቻለሁ እና በቀሌ በቅቶኛል!! ትቼሃለሁ!! ልለው ነበርኮ!!

ሞትን ራሱ በዓይኑ ያየ የሚመስል ህፃን እያባበለ ደረስኩ!! በፊት እቤቱ የነበረው ዘመዱ እኛ መረጃ ከያዝንበት በኋላ አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲያስገባው ያስገደድኩት እኔ ነበርኩ። የህፃኑን መንሰፍሰፍ ሳይ ዘንግቼው የነበረው ያኔ ሱሪውን ዝቅ አድርጎ የመለሰው መጣብኝ። ሲያየኝ ከመደንገጡ፣ መቀበጣጠሩ፣ ውክቢያው፣ ህፃኑ እንዲሄድ ማካለቡ ……. የሆነው ነገር ያልገባኝ መስዬ ተረጋጋሁ!! ህፃኑ የጎረቤት ልጅ መሆኑን አረጋግጬ ልጁን አባብዬ ወደቤቱ መልሼ ምንም እንዳልተፈጠረ ወይም እንዳልገባኝ መሰልኩ። እስኪረጋጋ እና ድንጋጤው እስኪለቀው ጠበቅኩት። ስመጣ አስቤው የመጣሁትን ነገርኩት።

«እውነትሽን ነው? በምን አምንሻለሁ? ቪዲዮዎቹን ካልሰጠሽኝ በምን አምናለሁ? የሆነ ቀን ሀሳብሽን ብትቀይሪስ?» አለኝ

«ከቃሌ ውጪ ምንም ማስተማመኛ የለህም!! ግን ሁሉንም ነገር ወስጄብሃለሁ ከዚህ በኋላ ምን ቀረኝ ብዬ ካንተጋ አኩኩሉ እጫወታለሁ? ግን እኔስ በምን አምንሃለሁ? ማረችኝ ብለህ ልትገድለኝ ብትሞክርስ? ማረችኝ ብለህ አሁንም የሌላ ለጋ ህፃን ህይወት እንደማታበላሽ በምን አውቃለሁ?» ስለው ከተቀመጠበት ዘሎ ተነሳ!! የዚህ ቀን ነው እንደአጓጉል አድርጌ ገድዬው እጄን ለፖሊስ የሰጠሁት!!!
       
                   * * * * * * * * *

ዳዊት በሩን አልፎ ሲገባ ዋናው የጭፈራ ወለል መሃል ቆሜ ቤቱን እየቃኘሁ ነበር። ሌባ አይኖቹ እየተቁለጨለጩ ወደኋላም ወደፊትም ከማለቱ በፊት ፊቴን ማጥናት ያዘ።

«አለቃ የለብኝም ብለህ በፈለግክ ሰዓት ነውኣ የምትገባ የምትወጣው?» አልኩት ሊገድለኝ የድሮ ፍቅረኛውን እንደላከብኝ ምንም ፍንጭ እንደሌለኝ መስዬ

«የኔፍቅር አትደውይልኝም ነበር? መጥቼ እጠብቅሽ ነበርኮ» ብሎ በመገላገል እየተነፈሰ ሊያቅፈኝ ተጠጋኝ!! አንገቱን አንቄ ወደላይ አንጠለጠልኩት እና እግሩ አየር ላይ ሲወራጭ ፣ የግንባሩ ደምስር ሲፈጥ እያፀዱ የነበሩት ሁለት ሴቶች መሄድም መቆምም ተወዛግቦባቸው ሲያዩኝ ቆይተው አንዷ መጥታ እግሬ ስር ወድቃ ትለምነኝ ጀመር።

«ተነሺ ከእግሬ ላይ!!» ብዬ ጮህኩባት

«በእመቤቴ ይዤዎታለሁ!! እንደው በሚወዱት ይሁንብዎ!! እጆት ላይ ይሞታል!! ኸረ እንኳን አንጠልጥለውት በአንድ ጥፍ ባህር የሚሻገር ነፍሰ ቀጭን ሰበብ ይሆንብዎታል።»

«ተነሺ ከእግሬ ላይ አልኩኮ!! እንዲሞት አይደል እንዴ ታዲያ!» ጮህኩኝ ድጋሚ

«እኔንም እንደፈለጉ ያድርጉኝ ከፈለጉ አልነሳም!!» ብላ አንድ እግሬ ላይ ተጠመጠመች። ሌላን ሰው ለመታደግ መሬት መንበርከኳ ገረመኝ። ትንፋሽ አጥሮት ሲልሞሰሞስ እያየሁት አሰብኩ!! ንዴት ላይ ሆኜ በፍፁም የማስብ ሰው አልነበርኩምኮ!! የድሮዋ እኔ ብሆን እጄ ላይ ይህችን ደቂቃ አይቆይም! ገና ሲመጣ ዘግቼው ነበር። ሆኖልኝ ቆይቶ እንኳን ቢሆን እግሬ ስር የተደፋችውን ሴት ታግሼ ተነሺ አትነሺ ግብ ግብ አልገጥምም! ይሄኔ ገንብሬ ጥያት ነበር!! አሁን ተቀይሬያለሁ ወይም ለመቀየር እየሞከርኩ ነው! መሬቱ ላይ ለቀቅኩት!! ሴትየዋ ከእግሬ ላይ ተነሳች። እየተንከባለለ አስሎ ሲያበቃ! መሬቱ ላይ ቁጢጥ ብዬ

«ለምን? ለምን እንዳደረግከው ብቻ እውነቱን ንገረኝ!! ከዋሸኸኝ ኪዳንን ይንሳኝ እጨርስሃለሁ!!» አልኩት! ለገንዘብ ብሎ እንደማያደርገው አውቃለሁ። የገንዘብ ችግር የለበትም!!

« ግልፅ አይደል እንዴ? ስለምጠላሽ!» አለኝ እስከዛሬ አናግሮኝ በማያውቀው ጥላቻ እና ድፍረት። ደነገጥኩ። ወዲያው ከአፌ ቃል አልወጣም!!

«ልትገድለኝ እስከሞከርክ ቀን ድረስ እወድሻለሁ ስትለኝ አልነበር? እየጠላኸኝ ነው አብረኸኝ የነበርከው? ደግሞስ ምን አድርጌህ ነው እስከመግደል የምትጠላኝ?» ስለው ተነስቶ እዛው መሬቱ ላይ ተቀመጠ እና ቆመው ሲያዩን የነበሩትን ሴቶች አያቸው። እየተሯሯጡ ወደ ውስጥ ገቡ።
444 viewsDAVE / PAPI, 19:03
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-21 22:03:30 የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል........ ክፍል ሀያ ዘጠኝ
(ሜሪ ፈለቀ)

ሰውነቴን ያጋራሁት ወንድ ሊያስገድለኝ ከመሞከሩ በላይ የተሸነፍኩለት ሰው ስልኩን ዘጋግቶ መጥፋቱ ልቤን ሊያበድነው ይገባ ነበር? ክህደት ያውም ለመግደል እስከመሞከር የደረሰ ክህደት ይበልጣል ወይስ መተው? ጭፈራ ቤቱ እስክደርስ በዳዊት ከምናደደው እኩል በጎንጥም እየተናደድኩ ነበር የምነዳው! እንደደረስኩ በሩን በረጋግጄ ስገባ ለወትሮው የሚውልበት ቢሮው ዳዊት የለም። እሱ እስኪመጣ እየጠበቅኩ ቤቱን እየተዘዋወርኩ ማየት ጀመርኩ። ገና ረፋድ ስለሆነ ከሚያፀዱት ሰዎች ውጪ ማንም የለም!! ምንድነው የማደርገው አሁን? መቼም እንደድሮው ስራ ብዬ አልቀጥልበትም! ወይም ቢያንስ የአገልግሎቱን ዝርዝር ማስተካከል ይኖርብኛል!! ከዋናው ጭፈራ ቤት ይልቅ ከሀያ እጥፍ በላይ ገቢ የሚያስገኙት ባለሀብቱ እና ባለስልጣናቱ የሚያዘወትሯቸው በድብቅ የሚከወኑት የሴቶቹ ገላ እና የሚሸጡት አደንዛዥ እፆች ናቸው!! እነዚህ አገልግሎቶች ከተቀነሱ እንደማንኛውም የከተማዋ ጭፈራ ቤቶች ሰካራም የሚራገጥበት ወለል ብቻ ነው የሚቀረው!

እዚህ ቤት ስንቷ ወጣት የሀብታም እና የባለሀብት መዝናኛ ሆናለች!! (ስንቷ ክብሯን ሸጣ ሆዷን ሞልታለች! ወይም እናቷን አሳክማለች።)  እዚህ ቤት ስንቱ ወጣት የማይወጣበት ሱስ ውስጥ ተዘፍቋል! (VIP ደንበኛ የሚባሉት ኮኬይን የሚገዙት ናቸው!! ሺሻ እንዲሰራላቸው ያዛሉ ኮኬይን ተደባልቆ ያጨሱታል። ኪሳቸውም ጤናቸውም አብሮ ይጨሳል።) እዚህ ቤት ስንቱ ባለጌ በሚስቱ ላይ ማግጧል (ስንቷ ምስኪን ሚስት እቤቷ ልጆቿን አቅፋ አልቅሳለች) ፣ እዚሁ ቤት ስንቱን ብልግና ማየት ተለማምጄ እንደ ጤንነት ቆጥሬዋለሁ!

ከሙሉሰው ጋር ተጋብተን ትንሽ እንደቆየን ፣ እንግዳ ወይ ጓደኞቹ እቤቱ ሲመጡ እቤቱ ሄጄ እንደሚስት ስብር ቅንጥስ ብሉልኝ ጠጡልኝ ማለት የለመድኩ ጊዜ ፣ እኔ ጠባቂ መሆኔ ቀርቶ በጠባቂ መታጀብ የጀመርኩኝ ጊዜ (አስፈላጊ ሆኖ አልነበረም! ለምን ጠባቂ እንደሚያጅበውም አይገባኝም!! ታይታ ካልሆነ በቀር) ፣ በቴሌቭዥን እንኳን ለማየት ወራት ከምንጠብቃቸው ባለስልጣናት ጋር የተለያዩ ክስተት እና ድግሶች ላይ የባሌን እጅ ቆልፌ መታየት የለመድኩ ጊዜ ፣ አንቱ የምለው ባለስልጣን ሚስት ባሏን ስታማልኝ የለመድኩ ጊዜ ፣ ራሴን ከእነርሱ እንደአንዳቸው ስቆጥር ያልታየ ድግስ ደግሼ እቤት እንዲታደሙልኝ ማድረግ የጀመርኩ ጊዜ፣ ………. ያኔ ጭፈራ ቤቱን በእኔ ስም እንዲያዞርልኝ አስደረግኩት። (እንደ ዓረፍተነገሩ እጥረት ሂደቱ ቀላል አልነበረም!! ትልቁ የገቢ ምንጩ ነው!! ባለስልጣናቱ የሚመጡት እሱን ስለሚያምኑት ነው!! )

ሌላው ጭንቅላቱን የምዘውርበት ጉድፉ ጭፈራ ቤቱ ነው! <ሌላውን ነውርህን ተወውና በወጣት ሴቶች ገላ እንደምትነግድ ፣ እፅ እንደምትነግድ ቢያውቅ እንደቅዱስ መልዓክ የሚያይህ ህዝብ ይቅር የሚልህ ይመስልሃል? > ራስምታት የሚቀሰቅስበት ርዕስ ነው።) ስራውን ለመልመድ ትንሽ ወራት ፈጀብኝ ግን ስለምደው ከእርሱ በተሻለ ያዝኩት ምክንያቱም እኔ ሙሉ ሀይሌን ተጠቅሜ እንጂ እንደእሱ ድብብቆሽ እየተጫወትኩ እና በትርፍ ጊዜዬ አልነበረም የምሰራው። ወደአካውንቴ ከሚያስገባልኝ ጠርቀም ያለ ገንዘብ በተጨማሪ ቁጭ ብዬ ራሴን የምሰማበት ጊዜ ስለማይሰጠኝ ወደድኩት።

እቅዴ በምፈልገው መንገድ እየሄደ ያልሞላልኝ ያን እናቴ ስትሞት መሳሪያ ዘቅዝቆ ይዞባት ተራ ሲጠብቅ የነበረ ደመኛዬን መድፋት ነበር። የሚኖረው አዲስአበባ ቢሆንም እዚህ ግባ የሚባል ማዕረግም ሀብትም ያለው ሰው አልነበረም!! ከሙሉሰው ጋር ግን በየእለቱ የሚገናኙ ሰዎች ባይሆኑም ቢያንስ የአንዳቸውን ፌስቡክ ፖስት አንዳቸው ሼር የሚደራረጉ ወዳጃሞች ናቸው!! እቅዴ ግልፅ ነበር ለሁለታችንም!! አንድ ቅዳሜ <ኸረ ተጠፋፋን ለምን ምሳ አንበላም?> ብሎ ሙሉሰው እንዲቀጥረው፣ ከዛ ሲገናኙ እኔ ባለሁበት ምሳ ልንበላ! (የመጨረሻዋን ምሳ) ስንጨርስ መኪናውን እኔ ልሾፍር ፣ ከዛማ ከከተማ አርቄ ወስጃቸው ትክክለኛ ማንነቴን ነግሬው ሬሳውን ለጅብ ጥዬ መምጣት ነበር እቅዴ!! ይሄን ከ10 ጊዜ በላይ ለሙሉሰው ነግሬዋለሁ!!

የዚህን ወቅት ከእኔ የሚያመልጥበት መንገድ መሞከሩን ተስፋ አልቆረጠበትም ነበር። በእቅዱ መሰረት መጥተን ከምሳ ወጥተን ወደመኪናችን ስንሄድ ሙሉሰው ለሰውየው  እኔ ያልሰማሁትን ግን ሲመስለኝ እራሱን እንዲከላከል ወይ ልገድለው እንደሆነ አልያም ማን እንደሆንኩ ብቻ አላውቅም የነገረው መልዕክት አደባባይ ላይ ሽጉጥ አስመዝዞታል!! (ሙሉሰው አስቦበት ያደረገው ነገር መሆኑ በሚያቃጥርበት መልኩ ሰውየው መሳሪያ ስላልታጠቀ የሱን ሽጉጥ መውሰድ የሚችልበት አቋቋም ላይ ኮቱን ገልጦለት ነበር የቆመው) ሀሳቡ እሱ ማድረግ ያልቻለውን ሰውየው እኔን እንዲገድልለት ነበር። ተቀደመ እና ሰውየው እዛው ሞተ። በሰውየው ሞት ከማዘን በእኔ አለመሞት ሲበሳጭ ላየው ግራ ያጋባ ነበር። አደባባይ ላይ ስለነበር የሆነው ሁሉ የሆነው ታሰርኩ!! የዚህን ጊዜ ነው እስር ቤት ከእሙጋ የተዋወቅነው። ነገር የማትፋታ ጋዜጠኛ ነበረች። ያልሆነ ነገር እያነፈነፈች አላፈናፍን ስትላቸው ነው እረፍት እንድታደርግ ያስገቧት!! እሷ እስር ቤቱን ለምዳዋለች። ሲፈቷት ደግሞ ሲያስሯት፣ ደግሞ የሆነ ነገር ትቆፍራለች ደግሞ ይከቷታል። ለመጀመሪያ ጊዜ በህይወቴ ሳይከብደኝ ያወራኋት ፣ ሳልደብቅ ያጫወትኳት ፣ ሳትፈርድብኝ የሰማችኝ ፣ ውርደት እና ክፋቴን እንኳን የተረዳችኝ የመጀመሪያ ጓደኛዬ ሆነች። ከሶስት ወር በኋላ ምርጫ ስላልነበረው ሙሉሰው በሚኬደው ሄዶ እራሱ አስፈታኝ። እሙም ከወራት በኋላ ተፈትታ ከእስር ቤት ውጪ ጓደኝነታችን ቀጥሎ ነበር።

ወጥቼ ብዙም ሳይቆይ አንድ ባንክ ውስጥ በራሱ ፣ በእህቱ ፣ በአንድ የሩቅ ዘመዱ …… ደማምሮ የያዘውን 48% አክሲዮን ተቀበልኩት። እኔም በራሴ ፣ በኪዳን እና በእሙ ስም አደረግኩት!! የዚህን ጊዜ <እንደውም መልቀቂያ አስገብቼ ስልጣኔን እለቃለሁ!! ከዛ ምን ይመጣል?> ብሎ ፎክሮ ነበር። እንደባለስልጣን ሳይሆን እንደተራ መናኛ ሰው ራሱ የሚጠብቀው ነገር ቅሌት መሆኑን እየደጋገምኩ ማስታወስ ነበረብኝ። ይፎክራል እንጂ እንደማያደርገው አውቃለሁ። የስልጣን ፍቅሩ ነፍሱን እስከመገበር የሚያደርሰው ነው። ቀስ በቀስ ሀብቱን ስቀበለው። <አይኔ እያየ አትበያትም! ገድዬሽ ከሀገር እጠፋለሁ!> የሚልበት ቀን ብዙ ነበር!!

ከዚህ በኋላ ግን ሁሉም ሲኖረኝ ፣ ከህፃንነቴ ጀምሮ የኖርኩለትን ጠላቶቼን የመግደል ህልም ሳሳካ ፣ ካሰብኩት በላይ ገንዘብ እና አቅም ሲኖረኝ ………. ሁሉም ቀስ በቀስ ጣዕሙን እያጣብኝ መጣ!!! የምኖርበት ህልም አጣሁ!! ለራሴ ስል የምለው ምንም ነገር ጠፋኝ!! ለካንስ በበቀል ስካሬ ውስጥ ወጣትነቴን ሰውቼዋለሁ፣ ሴትነቴን ሰውቼዋለሁ፣ እናት የመሆን እድሌን ቀርጥፌዋለሁ ፣ ሚስት የመሆን መንገዴን ዘግቼዋለሁ ፣ ከሁሉ በላይ ግን ሰው መሆንን ገብሬ ከሰውነት ወርጃለሁ!! ………… ከዛማ በህይወቴ ከኪዳን እና በጥቂቱ ከእሙ ውጪ ምንም ነገር ፈገግ የማያስብለኝ ፣ ልኩን ከስህተቱ ያደበላለቅኩ ፣ ባህልን ከዘመናዊነት ያቀላቀልኩ ፣ ብልግናን ከጨዋነት ያጣረስኩ ፣ ምን ለምን እንደማደርግ የተወናበደብኝ ሆንኩ!! ሲረጥቡ መበስበስ ለምጄ የለ? ተበሳበስኩት!!
534 viewsDAVE / PAPI, 19:03
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-20 19:25:49 ብቻ የማስታውሰው ሰውዬ ከልጅነት ቀዬዬ እልፍ ብሎ ያለች ሰፋ ያለች ከተማ ውስጥ ሹም ሆኖ ነበር የሚሰራው!! እሱን ፀጥ ለማድረግ ግርግር አላስፈለገም ነበር።

እናቴ ስትደፈር መሳሪያ ይዞ ቆሞ ሲያያት የነበረውን ሰውዬ ለራሴ ቆጥቤ አስቀመጥኩት!!
እየቆየ ቀን ቀንን ሲተካ ኮሽ ባለ ቁጥር የሚደነግጥ፣ ወኔው የተሰለበ ድንዙዝ እየሆነ መጣ። ያልሞተም ህያው ያልሆነም ድንዙዝ ሆነ። ባልደረቦቹ <ደህና ነው?> ብለው እኔን ይጠይቁኛል። <ኸረ ደህና ነው!> እላለሁ!!

ከአረቡ አለቃዬጋ እዚህጋ ተፋታን!! አንዳንዴ የሆነ ነገር ስፈልግ እደውልለታለሁ። የሚፈልገው ነገር ሲኖር ይደውልልኛል። ሊያስፈልጉኝ የሚችሉ ቁልፍ ሰዎችን መቆለፊያ ተንኮል የጠቆመኝ እሱ ነው!! ወሳኝ ስልጣን ላይ ያሉትን ሰዎች ቆሻሻ መያዝ!!  እዚህ ነጥብ ላይ ከእርሱ የተሻለ ለመረጃ ቅርብ የነበርኩት እኔ ነበርኩ። ምክንያቱም የከፍተኛ ባለስልጣን ሚስት ነኛ!! የታዘዘውን ያቀርባል!! የደሳለንኝ ከውጪ ሀገር ባለሃብት ጋር ተሻርኮ የወርቅ ማዕድን የተገኘበትን መሬት ለአበባ ልማት አንድ ሀገር ሄክታር የተፈራረመበትን ከሰዎቹ ጋር የነበረውን ኮንፍራንስ የሚያሳይ ቪዲዮ ጭምር ያቀበለኝ እራሱ ነው!!!

በዚህን ወቅት ነው ብዙ ክፋቶችን ፣ ብዙ ተንኮሎችን ከዛም ዛሬ መረጃ እንዲያቀብለኝ የምጠብቀውን ሰዌን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ያወቅኩት።

                                              ******
ከጎንጥ በፊ
ት ህይወት ያልነበረኝ ይመስል የምሄድበት ወይ የምሰራው ጠፋኝ!! ቀኑ አልገፋ ብሎኝ እሙጋ ሄጄ የተፈጠረውን አንድ በአንድ ነግሪያት ራሱ ጊዜው አልሄደም። ወደከተማ ተመልሼ ደጋግሜ ብደውልለት ስልኩ አይሰራም!! እንዲህ በአንድ ቀን ሳቄንም ተስፋዬንም ይዞብኝ እብስ የሚለው ምን ቀን ነው እንዲህ ልቤን ለራሴ ሳላስቀር የሰጠሁት? ምን ቀን ላይ ዓለሜ በእርሱ ውስጥ የታጠረው? ማልቀስ አማረኝ ከዛ ደግሞ ሽንፈት መሰለኝና ዋጥኩት። ሲመሻሽ ቤተክርስቲያን ገባሁ ግን ግራ ተጋባሁ!! ለእግዚአብሄር ስለወንድ ይፀለያል? ምን አድርግልኝ ተብሎ ነው የሚፀለየው? ተውኩት!! ዝምብዬ ለረዥም ሰዓት ተቀምጬ ወጣሁ!!

ውሸቱን ነበር! ቢወደኝ ኖሮ ሁለት ቀን ሙሉ እንደምጨነቅ እያወቀ ስልኩን አጠፋፍቶ አይጠፋም!! የእኔ መጨነቅ ይቅር እሱስ አልናፍቀውም? አሁንም እየሰለለኝ ይሆን? አዳር ያልሆነ አዳር አድሬ ጠዋት መረጃውን ላከልኝ!! መጀመሪያ ያየሁት የጎንጥን ነው!! ምንም የተለየ ነገር የለውም!! ተጨማሪ መረጃ ብሎ የጨመረው እኔ የማውቀው ነው!! ስልኩን ደወልኩ

«እንዴት ምንም ተጨማሪ ማስረጃ አታገኝም!?»

«አንቺኮ የፈረንጅ ፊልም ላይ እንደምታዪው ካልሆነ የምትይው ነገር አለሽ!! ሜላት ኢትዮጵያ ውስጥ ነን መረጃዎች በሙሉ አይመዘገቡም!! ከዛ ደግሞ ሰውዪሽ ሌላ ምንም ድብቅ ነገር የሌለው ከሆነስ?»

«ይኖረዋል!! ስለማታውቀው ነው ይኖረዋል!»

«የተቀሩትን መረጃዎች ግን አይተሻቸዋል?» አለኝ አይተሻቸው ቢሆን ኖሮ ስለሰውዬሽ አትጨቃጨቂኝም ነበር በሚል ለዛ። ስልኩን ዘግቼ የተቀረውን ፎልደር ከፈትኩ!!

«ይሄ የውሻ ልጅ አውቄዋለሁ!! እገለዋለሁ!!» አልኩ ለራሴ ጮክ ብዬ!! ኮቴን እንደነገሩ ደርቤ መኪና ውስጥ ገብቼ ወደክለቡ ነዳሁት!!

                        ........ አልጨረስንም!! ............

@wegoch
@wegoch
@paappii
933 viewsDAVE / PAPI, 16:25
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-20 19:25:49 ከዛን ቀን በኋላ በአፉ ምንም ባይናገርም አስተያየቱ ተቀየረ። ዓይኖቹን ሳይነቅል ሲያፈጥብኝ ቆዳዬን ያሳክከኛል። ተስተካክዬ መቆም ያቅተኛል። ከቀናት በኋላ ሆነ ብሎ እዛ ቤት እንድንሄድ አደረገ እና በሴቶቹ ፋንታ ሙሉሰው እንዲመጣ ጠየቀ። ሙሉሰው ከአንድ ጠባቂው ጋር መጥቶ በወዳጅ ሰላምታ ማሽቃበጥ ያበዛበት ዓይነት ሰላም ብሎት ተቀመጠ። ዘለሽ እነቂው እነቂው የሚለኝን ስሜቴን ተቆጣጥሬ ቆምኩ። ሆነ ብሎ እሱ ፈላጭ ቆራጭ መሆኑን ሊያሳያኝ ያደረገው ነገር እንደሆነ ያስታውቅበታል። ቢገጣጠም የማይቀና አማርኛ እያወራ በአይኑ እኔን ያጠናል። ሙሉሰው ወጥቶ ሲሄድ «የዚን ያህል ቀላል ነበር።» ብቻ ብሎ ዝም አለ።

ለሳምንታት በራሴ መንገድ መረጃ ላገኝ ዳከርኩ። ሌላው ቀርቶ ጭፈራ ቤቱ እንኳን ድንገት የሆነ ሰዓት ነው እንጂ የሚመጣው ማንም ሰው የሚመጣበትን ሰዓት አያውቅም። ድንገት እድለኛ ሆኜ እንኳን ባገኘው ጠባቂ አለው!! ከዛ ግን ያ ሰይጣን ሰውዬ ያቀበለኝ ሀሳብ ውስጤ ቀስ በቀስ ማደጉን ያወቅኩት። ባገኘሁት አጋጣሚ ልገድለው አለመፈለጌ ገባኝ!! ቁጭ ብዬ አስቤ አስቤ ማሰሪያዬ  <ከነነፍሱ እፈልገዋለሁ! የዛን ቀን አብረውት የነበሩትን ስማቸውን የማላውቃቸውን ጨምሮ መረጃ ይሰጠኛል። እንደውም እሱ መጨረሻ ላይ ነው መሞት ያለበት!> የሚል ሆነ። ሊሆን የማይችል ቅዠት ይመስለኛል ግን ማሰብ ማቆም አቃተኝ። ግን እንዴት? አላውቅም!!!

«እሺ!» አልኩኝ ጠብ የሚል ነገር ከሌለው ብዙ ልፋት በኋላ!! «ነገር ግን በቅድሚያ የማገኘውን ነገር በዝርዝር ማወቅ እፈልጋለሁ!»

ክብሬን ሸጬ በቀል ሸመትኩበት!!! ካሰብኩት በላይ ነገሮች ቀለሉልኝና የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ኖረኝ። እኔ ግን ጎደልኩ!! ለቀናት እራሴው እሺ ብዬ ተስማምቼ የተኛሁ ሳይሆን እንደእናቴ የተደፈርኩ አይነት ስሜት ተሰማኝ። በእንባ የማላጥበው ዓይነት መቆሸሽ ሆነብኝ!! <ጥላቻ ከፍቅር ያይላል> ያለው ይሄን መሰለኝ። የገዛ ሰውነቴ የሆነ ቦታ አስቀምጬው መንቀሳቀስ ብችል አሰኘኝ። ይሄን የውስጤን ጩኸት ላለመስማት በነጋ በጠባ ሴራ መጎንጎን ሆነ ስራዬ!! ከረጠቡ አይቀር መበስበስ ነው በክፋት ተጠመቅኩ። ተንኮል አስራለሁ እፈታለሁ!! ደጋግሜ ረከስኩ!! ደጋግሜ ራሴን ረሳሁ።

ሙሉሰውን እንዲወደኝ አድርጌው አይደለም ያገባሁት!! እጁ ባይያዝበት የመጀመሪያ መግደል የሚፈልገው ሰው እኔ ነኝ!! እንዲያገባኝ አስገድጄው እንጂ!! አብዛኛው ባለስልጣን አንድ የሆነ ድክመት ወይ አንድ የሆነ ቆሻሻ ይኖረዋል። ወይ በሚስቱ ላይ ሲማግጥ ወይ በሃገር ላይ ሲማግጥ ብቻ የሆነ መረጃ ይገኝበታል። ሙሉሰው አስለፋን!! ጭራሽ ምንም ማግኘት ከበደ። በዘመድ አዝማዱ ስም ጭምር የያዛቸው ንብረቶች እና ከሀገር የዘረፋቸው ሀብቶች ማስፈራሪያ ሊሆን ቢችልም በቀላሉ በገንዘብ ሃይል መረጃዎቹን ድራሻቸውን ማስጠፋት ይችላል። የራቁት ጭፈራ ቤቱ ውስጥ በጓሮ ተሹለኩልከው የሚገቡትን ባለስልጣናት በቀላሉ በሴቶቹ ማጥመድ ይቻላል። እሱ ግን ከሴት ጋርም በፍፁም ምንም አይነት ንኪኪ የሌለው ሆኖ ተገኘ። ምናልባት ቤቱ የሱ ስለሆነ ሰራተኞቹ ባሉበት መልከስከስ ስለማይፈልግ ነው ብለን አስበን። (በሃሳቡ ተስማማሁ እንጂ ሀሳቡን የሚያመነጨው አለቃዬ ነው) እቤቱ የምትሰራዋን ሰራተኛ ያዝናት። ጭራሽ እንደውም በበጎ አድራጎት የሚታወቅ ከላዩ ላይ ዝንቡን እሽ ብል ግር ብሎ የሚወጣለት ህዝብ ያሰለፈ ሰው ነው። እጅ ወደመስጠቱ ስንቃረብ ከስንት መላምትና ልፋት በኋላ ማንም ሰውጋ የማይሰማ ማንም ሰው የማይገምተው ብልግና እቤቱ ሸሽጎ እንደሚኖር ደረስንበት። ሊያሳድገው ከገጠር ያመጣው እቤት አብሮት የሚኖር ዘመድ አለው። ደፍሮት አሁንም እያስገደደው ያባልገዋል። ከዚህ ሰውዬጋ መዋል ከጀመርኩ በኋላ ብዙ ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ብልግናዎች ሰምቻለሁኮ ይሄ ግን ወደር የማይገኝለት ነበር። ከብዙ ሙከራ በኋላ ብልግናውን ቀረፅነው!! ይሄ ነው እጄ ላይ የጣለው!!

ለዘመናት የናፈቅኩት ቀን ተከሰተ እና ፊት ለፊት ተገናኘን። ውርደቱ እጄ ላይ እንዳለ ስነግረው ፊቱን ማየት ለቀናት ሲያቅበጠብጠኝ ነበር። እዛው የራቁት ጭፈራ ቤቱ ከአለቃዬ ጋር ሄደን እሱ ሲመጣ እንዲጎበኘው መልዕክት አስቀመጠ። እዚህ ጋር የማይገባኝ አለቃዬ በእኔ በቀል የሚሰክረው ጉዱ ነበር። ልክ መጥቶ እንደተቀመጠ።

«ሜላት እባላለሁ! ወይም ደግሞ አባቴ ባወጣልኝ ስም አምሳል!» አልኩት እና የአባቴን ማንነት ቀዬዬን እና የዛን ቀን ተፈጥሮ የነበረውን ሳላዛንፍ ነገርኩት። ምንም ታክል የፀፀት ስሜት ሽው ባላለው አነጋገር

«ጦርነት ነው የገጠምነው!! ልንስማችሁ አልነበረም የመጣነው!! እንኳን አንቺ ማን እንደሆንሽ አባትሽንም አላስታውሰውም!» ሲለኝ እሱን ለመበቀል የሄድኩት መንገድ ልክ ነው ብዬ አመንኩ። ቪዲዮውን ላኩለት እና ምንም ከማሰቡ በፊት አንድ ቅጂ አለቃዬ ጋር ፣ ሌላ ቅጂ ተቀባብሎ ሌላ ሰው ጋር  መኖሩን ነገርኩት!! አንድ ነገር ሊያደርገኝ ቢያስብ መረጃውን ከመውጣት እንደማያግደው ሲያውቅ ተሰበሰበ።

«እሺ ምንድነው የምትፈልጊው? ምን ያህል?» ብሎ ራሴን የሸጥኩበትን በቀሌን በገንዘብ ተመነብኝ

«ገንዘብ አይደለም የምፈልገው!! እንድታገባኝ ነው የምፈልገው!!» ስለው በቁሙ ቃዠ።

«ቀልድ ነው የያዝሽው? ጤነኛ ነሽ?» ሲል አለቃዬ በወልካፋ አማርኛ ቅልብ አድርጎ
«ውነቷን ነው! ቀልድ የለም!» አለው።
«ምን አስበሽ ነው?»

«አታስብ ጠዋት ከእንቅልፋችን አንድ ላይ ተነስተን ፣ ደህና አደርሽ ፣ ደህና አደርክ የምንባባል፣ ቁርስ አንድ ላይ የምንበላ ሰዎች አንሆንም!! አንድ ቤትም አንኖርም! ሚዲያዎች የሚዘግቡት ሰርግ ደግሰህ እንጋባለን!! አብረን አንኖርም እንጂ የትም ቦታ ስትሄድ እጄን እጅህ ውስጥ ሻጥ አድርገህ ትሄዳለህ!! ከዛ የቀረውን እያኖርን እንመካከራለን!! ውሳኔህን እንድታሳውኝ 2 ቀን እሰጥሃለሁ። ያው አማራጭ የምትለውን በሙሉ አይተህ እንደማያዋጣ ትደርስበታለህ!!» ተወራጭቶ ወጣ!! እንደምገምተው አማራጭ ሊሆን ይችላል ብሎ የሚያስበውን ሁሉ አስቧል። ጉዱን ለማንም እንደማያዋየው ግልፅ ነው!!

ቪዲዮው ቢወጣ በመድፈር ወንጀል ብቻ አይደለም የሚከሰሰው በፍቅር ከፍ አድርጎ የሰቀለው ራሱ ህዝብ በድንጋይ ወግሮ እንደሚገድለው ያውቃል። ሰው ገደለ፣ ሀገር ከዳ ፣ ሰረቀ …… ምንም ቢባል ኸረ ምንም ጥፋት ቢሆን ይታለፍለታል። ይሄን ግን አያልፉለትም።

በሁለተኛው ቀን መስማማቱን ላከብኝ!! በአደባባይ ሀገር ጉድ ያሰኘ ሰርግ ደግሶ አገባኝ!! ኪዳን ዩንቨርስቲ ገብቶ ነበር። ማንን እንደማገባ ሲያውቅ ለብዙ ሳምንታት አኩርፎኝ ነበር።

ተጋባን እንጂ አብረን አንኖርም ነበር። በአደባባይ እሱ የሚገኝባቸው ቦታዎች ግን እገኛለሁ። በዚህ አጋጣሚ ከባለስልጣኑ ማህበረሰብ ጋር የመቀላቀል እድል ኖረኝም አይደል? ሳይወድ በግዱ እየገለፈጠ <ሚስቴን ተዋወቁልኝ> ይላል። ሰዎቹን ማጥናት ተጨማሪ ስራዬ ሆነ። የመጀመሪያ ስራዬ የነበረው ሌሎቹን የአባቴን ገዳዮች ራሱ እንዲነግረኝ ማድረግ ነው። የድሮ አብሮአደጎቹጋ ሁሉ ደውሎ የዛን ቀን አብረውት የነበሩትን አጣራ!! የምፈልገው አንድ እሱን ሁለት እናቴ ስትደፈር መሳሪያ ይዞ ቆሞ የነበረውን ሶስት የአባቴን ሬሳ ተሻግሮት ያለፈውን አራት እኔ በመልክም በስምም የማላውቀው አባቴ ላይ የተኮሰው ሰውዬ!! አባቴ ላይ የተኮሰውን ሰውዬ እራሱ ሙሉሰው እንዲገድለው አደረግኩ! ተጨማሪ ወንጀልም እንደማስረጃ ለመያዝ!! ሰውየው <ባልታወቀ ሰው ተገድለው ተገኙ> ተብሎ ተቀበረ። የአባቴን ረሳ ተሻግሮት ያለፈው ኮቴውን
750 viewsDAVE / PAPI, 16:25
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-20 19:25:49 #የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል.......( ክፍል ሀያ ስምንት)
(ሜሪ ፈለቀ)

«ታውቂዋለሽ እንዴ? ምነው?» ሲለኝ
<አዎ አውቀዋለሁ! በአንዲት ሰዓት ውስጥ በፍቅር እና በደስታ ከታቀፍኩበት የቤተሰቤ እቅፍ ውስጥ አስወጥቶ ህይወቴን ያመሳቀለው ሰው ነው!> ማለት ብፈልግም …. እንኳን ከዚህም ከዛም ቃርሜ እና በ6 ወር ከስልጠናው ጋር ተምሬ የምኮላተፍበት አረብኛ ቀርቶ የራሴው አማርኛ እንኳን የህመሜን ያህል ገላጭ ቃል የለውም።

«ክፉ ሰው ነው!» ብዬ ብቻ አለፍኩት። ከዛን በኋላ ግን ለሰዓታት መረጋጋት እስኪያቅተኝ ሰውነቴ ምሬት ተፋ። ፊቴ እስኪያስታውቅበት ድረስ ያለፈው ሁሉ መጠቃት፣ እልህ ፣ ቁጣ ……. እንደአዲስ በደምስሬ ከደሜ ጋር ተዘዋወረ። እቤት ደርሰን መውጫ ሰዓቴ ደርሶ ልወጣ ስል ሌሎቹን ጠባቂዎች አስወጥቶ ብቻዬን ሊያወራኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ። ከትዕዛዝ ውጪ ምንም አይነት ነገር አውርተን ስለማናውቅ ግር እያለኝ ተቀመጥኩ።

«ምን አድርጎሽ ነው? የሞት መልዓክ ያየሽኮ ነው የመሰልሽው!» አለኝ

«በልጅነቴ ወላጆቼን ያሳጣኝ ሰው ነው!» አልኩት በደፈናው።

«ጥላቻ ከፍቅር ያይላል። በቀልም ከወሲብ እርካታ በላይ ፍሰሀን ያጎናፅፋል!» አለ ለእኔ ይሁን ለራሱ የተናገረው መለየት በሚቸግር አነጋገር። ቀጠል አድርጎ «ድፍረትሽ ያስታውቃል። ሞትን እስካለመፍራት የሚደፍረው ውስጡ የሚገፋው ጥላቻ እና ያረገዘው በቀል ያለው ሰው ነው። ፍቅር እና ተስፋ ልቡን የሞላው ሰው ፈሪ ነው። ነገን ይፈራል፣ ማጣትን ይፈራል ፣ ሞትን ይፈራል!! በልምድ ብቻ ያገኘሽው ድፍረት እንዳልሆነ ያስታውቃል።»  ያለው በትክክል የገባኝ ከብዙ ጊዜ በኋላ በቀልም ጥላቻም ገፍትረው ልቆም ያላቀድኩበት ውሳኔ ላይ ሲያቆሙኝ ነው!! ይሄን አጀንዳ አንስቼ አይደለም ከሱ ጋር ከኪዳን ጋር እንኳን የምጋራው ባላመሆኑ ዝም አልኩ።

«ብዙ ሰው ባያውቅም ሰውየው የቤቱ ባለቤት ነው! ከዚህ በኋላም ተደጋጋሚ ጊዜ ልትገጣጠሚ ስለምትችዪ እንደፕሮፌሽናል ጠባቂ የግል ስሜትሽን ውጠሽ ስርዓት ባለው መልኩ ለመታየት ሞክሪ!!» አለኝ እንደትዕዛዝ ነገር! ከዛ ሁሉ ትኩረት የሰጠሁት <የቤቱ ባለቤት> የሚለውን ነው። ያውቀዋል ማለት ነው!!?? « ምን ልታደርጊው ነው የምታስቢው?» ሲለኝ ለምን ወይም እንዴት ይሄን ጥያቄ እንደጠየቀኝ አላሰብኩትም። «እገድለዋለሁ!» ያልኩት ጮክ ብዬ መሆኑን ከእርሱ እኩል ነው የሰማሁት። የሆነ የፌዝ ነገር (ቀሽም! የሚል ዓይነት ነገር) ሳቅ ብሎ 

«አትቸኩዪ! በቀል የሚጣፍጠው ሰውየው ሲሰቃይ የማየት እድል ሲኖርሽ ነው!! ከገደልሽውማ ገላገልሽው! ስንት ዓመታት ተሰቃይተሻል? ስንት ዓመታት ባሰብሽው ቁጥር ህመም ተሰምቶሻል? ለዓመታት የተሰቃየሽው ስቃይ በሱ ቅፅበታዊ ሞት ይካካሳል? ይድናል? ገደልሽው! ከዛስ? እድሜ ልክሽን እስር ቤት ትማቅቂያለሽ!! በህይወት እያለም ደስታሽን ቀምቶሽ በሞቱም ደስታሽን ቀምቶሽ! ይሄ ፍትህ ነው ብለሽ ታስቢያለሽ?» ቃላቶቹን ረጋ ብሎ የሚያወራበት ለዛ ልቡ ቀዝቃዛ እና ክፉ መሆኑን ያሳብቅበታል። ያልገባኝ ለምን እኔን እንደሚያቀሳስረኝ ነው!! ሲያወራው ግን እውነትም በቀል እሱ አፍ ላይ ትጣፍጣለች። በቀልን ሳስብ የማስብ የነበረው መግደልን እንጂ በቀል እንዲህ ተሽሞንሙና እና ረቅቃ አስቤያት አላውቅም!!! ሲያዩትኮ ሰውየው ፍፁም ትሁት እና ሳቂታ፣ ካገኘው ሁሉ ጋር ጨዋታ ወዳድ ነው የሚመስለው። ከሴት ጋር ተያይዞ ካለው ስድነቱ ውጪ እቤቱ እንግዳ ጠፍቶ የማያውቅ ቸር ነው ብዬ ነበርኮ የማስበው!

«ለድፍረቴ ይቅርታ ይደረግልኝና አንተ ብትሆን ምን ታደርጋለህ? ቤተሰብህን ፣ ህይወትህን ፣ ቤትህን ፣ ልጅነትህን የቀማህን ሰው ምን ታደርገዋለህ? በድጋሚ ስለድፍረቴ ይቅርታ!»

« ድክመቱን ማግኘት ነው!! በዛ ድክመቱ ገብተሽ የሚወደውን ነገር አንድ በአንድ መንጠቅ! ልክ በቁሙ እያለ መጀመሪያ ተራ በተራ ጣቶቹን፣ ቁስሉ ደርቆ ተሻለኝ ሲል ክንዱን ፣ ቆየት ብለሽ ሙሉ እጁን ፣ ከዛ የሌላኛው እጁን ጣቶች ፣ ክንድ ፣ ሙሉ እጅ …..  እያደረግሽ አካሉን እንደመክተፍ!! ግደዪኝ ብሎ እስኪለምንሽ ወይም ራሱን ለመግደል እስኪወስን ያለውን ማሳጣት!» ሲል የተናገረውን እያንዳንዷን ድርጊት ተግብሮት እንደሚያውቅ ነው። በትክክል እንዲገባኝ የፈለገ ይመስል ወሬውን በምልክት አጅቦ ነው አስረግጦ ያስረዳኝ። አወራሩ የጭካኔ ጥግ የሆነ ወሬ እያወራ ሳይሆን የልደት ኬክ ስለመቁረስ ዓይነት ያለ ጨዋታ እንደሚያወራ ቃላቶቹን በፍቅር ነው ምላሱ ላይ የሚያሽሞነሙናቸው። ለሆነ ቅፅበት አጠገቡ መሆኔን ሁሉ ፈራሁት!!! መልሼ ፍርሃቴ ራሴኑ አሳቀኝ እንጂ! እኔ ከእርሱ በምን ተሽዬ ነው? በተናገረው ነገር ተስቤ በቀልን እሱ በገለፀው መንገድ ጭንቅላቴ ውስጥ ላጣጥመው እኮ ሞክሬያለሁ።

«እርዳታዬን ከፈለግሽ መጠየቅ ብቻ ነው የሚጠበቅብሽ!! ስለሰውዬው ማወቅ የምትፈልጊው ነገር ካለ የሀገሩ ዜጋ አለመሆኔን አትዪ ሁሉም ቦታ አይን አለኝ፣ የሚያስፈልግሽ ገንዘብ ወይም ፋሲሊቲ ምንም ቢሆን !!» አለኝ።

«እውነትህን ነው? ለምን ልትረዳኝ ፈለግክ?» ጥርጣሬም መገረምም ጨረፍ አድርጎኝ የጠየቅኩት ጥያቄ ነበር።

«ፍትህ ሲዛባ ደስ አይለኝም!! የተፃፉ ህጎች ለሁሉም ሰው እኩል ፍትህ አይሰጡም!! ጉልበተኞችን ያሾልካሉ።» ሲለኝ የከተማው ብልጣብልጥነት ብዙም ያልዘለቀው ልቤ አመነው። ወይም ድክመቴን አግኝቶብኛል። አመስግኜው ስለሰውየው ሊጠቅመኝ የሚችል መረጃ ምንም ቢሆን እርዳታውን እንደምፈልግ ነግሬው አቋራጭ መንገድ በማግኘቴ ተደስቼ ሳልጨርስ በምትኩ ከእኔ የሚፈልገው ነገር መኖሩን ነገረኝ። በጅልነቴ ብግን ያልኩት ሰውየው እውነተኛ ማነነቱን በግልፅ አሳይቶኝ እንኳን የሚቀጥለው ጥያቄ ከደግ ልብ የመነጨ እንደሚሆን መጠበቄ!!

ልክ ልከኛ ነገር ያወራ ይመስል፣ ልክ ከእዛጋ ያን ወረቀት አቀብዪኝ እንደማለት ነገር ቀለል አድርጎ …… አንድ ከየትኛው አረብ ሀገር እንደሆነ የማላውቀው አዘውትሮ እሱጋ የሚመጣ ሰውዬ ስለሚቋምጥልኝ ከእርሱ ጋር በመተኛት ውለታውን እንድከፍለው ነገረኝ። በተጨማሪ ሰውየው የምፈልገውን የሚያደርግልኝ ሀብታም መሆኑን አከለበት። ለሆነ ደቂቃ ምንም የምለው ቃል ራሱ ቸግሮኝ ዝም ብዬ እንደሆነ መዓት ሳየው ቆየሁ። ትንሽ ቆይቼ ግን ከአፌ ከወጣ በኋላ የፀፀተኝን ወሬ አወራሁ!!

«አላደርገውም!! ወንድ አልወድም ከወንድ ጋር መተኛትም አልወድም!! ሴት መሆኔን እርሳው!! ህፃን ሆኜ ነው እናቴን አይኔ ስር ሲደፍሯት ያየሁት!! እንደማንኛዋም ወጣት ሴት ያለ ስሜት አይደለም ያለኝ!! ሳስበው ራሱ ትዝ የምትለኝ እናቴ ናት!! ይዘገንነኛል። ምንም ነገር ይቀራል እንጂ አላደርገውም!!» ያልኩት እንዲያዝንልኝ ነው? ፣ እንዲረዳኝ ነው? ፣ ልዋጭ ሳይፈልግ ሙሉሰውን የማጠምድበት መላ እንዲዘይድልኝ ነው? ምን አስቤ እንደሆነ አላውቅም!! ከዚህ ሁሉ ውስጥ እሱ በድፍኑ የተሰማው ሌላ ነው።

«ጭራሽ ወንድ አላውቅም እያልሽ ነው?» ከማለቱ ዓይኖቹ ሰውነቴ ላይ በመቀላወጥ ተርመሰመሱ። በጣም እየቀፈፈኝ ተነስቼ እየቆምኩ

«አዎን ምነው?» ስለው ምንም ድንቅፍ ሳይለው ከዛኛው ሰውዬ ጋር የመተኛቱን ሀሳብ እንደቀየረ (ልክ እኔ የተስማማሁ ይመስል) እና በምትኩ ከእርሱ ጋር እንድተኛና ከፈለግኩ የሙሉሰውን ጭንቅላት ከሰውነቱ ቆርጦ እንደሚያመጣልኝ ነገረኝ። ማለት በቃ በምንም የማንግባባ የተለያየ ቋንቋ የምናወራ ሰዎች መሆናችን ሲገባኝ ተነስቼ ወደቤቴ ሄድኩ። ያወራሁትን አልሰማም?
865 viewsDAVE / PAPI, 16:25
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-19 21:38:28 በሰውየው ዙሪያ ከገንዘብ ነክ ነገሮች በተጨማሪ ብዙ ብልግናዎች እንደሚከወኑ ያወቅኩትም በጎን መቆም ስጀምር ነው። አዲስአበባ ሲመጣ ሳሎኑ መጂልሱ ላይ ተቀምጦ የከተማው እምቡጥ እምቡጥ የመሳሰሉ ሴቶች እየመጡ እንደሚታረድ በግ ሽንጥና ዳሌያቸውን እያገላበጠ ፈትሾ ይመርጥ እና የወደዳትን ለራሱ የተቀሩትን እቤቱ መጥተው አብረውት ሲቅሙ እና ሲያጨሱ ለሚቆዩት እንግዶቹ ልክ <ምን ይምጣላችሁ?> ብሎ እንደሚያቀርበው ምግቡ ያቀርባቸዋል። መጀመሪያ ቀን ነውርነቱ አሳፈረኝ። የሴቶቹ ምንም የማፈር ስሜት ፊታቸው ያለመኖር እኔን መሬት ተሰንጥቃ እንድትውጠኝ እስከመመኘት አሳፈረኝ። ሲቆይ ልምድ ነው አላልኳችሁም? ለመድኩት። ሴቶቹ አንዱ ባለሃብት ላይ አይኔ እያየ ለሁለት የማይኮን ሲሆኑ አይኔን ሳላርገበግብ መቆም ለመድኩበት። ከዛ በኋላ እይዘዋለሁ ብዬ የማላስበውን ያህል ገንዘብ እየኖረኝ መጣ። ከሰውየው ጋር በየሀገሩ መዞርም ለመድኩ። በዞርንበት በተለይ እግሊዝኛ የሚነገርበት ሀገር ስሄድ ያለመማሬ የምር አስቆጨኝ እና እንግሊዝኛ ለመማር እቤቴ አስተማሪ ቀጠርኩ። ከዓመት በኋላ እየተመላለሰ ሰውየው ካስተማረኝ እንግሊዝኛ በላይ በልምድ በዙሪያዬ እነርሱ የሚያወሩት አረብኛ ይገባኝ እና መናገር መሞከር ጀመርኩ።

የጎን ክንፍ አጃቢ ከሆንኩ ከዓመት በኋላ የሰውየው የቅርብ ጠባቂዎች በሙሉ ሰልጥነውት እኔ ያልሰለጠንኩት ስልጠና መኖሩ ተነግሮኝ የመን ለስልጠና ሄድኩ። በየጊዜው ለቀናት ከኪዳን መራቁን እየተላመድነው መጥተናል። እስከአሁንም ቦታው የግለሰብ ይሁን የመንግስት በማይገባኝ ካምፕ በመሰለ ቦታ ስልጠና ለ6 ወር ወሰድኩ። አብዛኛው ስልጠና የወታደር ስልጠና ምን እንደሚመስል ባላውቅም እንደዛ ዓይነት ይመስለኛል። በየቀኑ ፈሴ ጢጥ እስኪል ከብዙ ወንዶች እና በጣት ቁጥር ከማይሞሉ ሴቶች ጋር የሚሰጡኝን የቴክኒክ እና የጉልበት ስልጠናዎች መውሰድ ነበር። አንዳንዴ ደግሞ ለስለላ የሚያሰለጭኑኝ እስኪመስለኝ በሰዓቱ በስርዓቱ የማይገቡኝን የጭንቅላት ስልጠናዎች እና ፈተናዎች ወሰድኩ።

ከስድስት ወር በኋላ ስመለስ የሰውየው ቀኝ እጅ ከመሆኔ በተጨማሪ የሚከፈለኝ ደሞዝ በህልሜ እንኳን አስቤው የማላውቀው ነበር። በዛ ላይ ጭኔን የሚያሳዩትን ብጣቂ ሚኒዎች ያለመልበስ መብት ተሰጠኝ እና በምትኩ ሙሉ ሱፍ በሱሪ መልበስ ጀመርኩ። በገንዘቤ ሳይሆን በሰውየው ገንዘብ መኪና ተገዛልኝ እና የመኪና ባለቤት ሆንኩ። አንድ ቀን እስከዛ ቀን ድረስ ሲሄድ ያልገጠመኝ ቤት አጅቤው ሄድኩ (አሁን የእኔ የሆነው የራቁት ጭፈራ ቤት) ከፊት የሚታየውን የአዘቦት ጭፈራ ቤት የሚመስል በሙዚቃ አንድ ገበያ ህዝብ የሚውረገረግበትን አዳራሽ የሚያክል ሳሎን አልፈን ወደውስጥ በሚስጥር በር ዘለቅን። ኮሪደሩ ላይ የተቀበለን አስተናጋጅ ወደተዘጋ ክፍል ወሰደን። አራት የምንሆን ሴት ጠባቂዎቹ አጅበነው ስንቆም ክፍሉ ከእርሱ ውጪ ማንም አልነበረበትም። ተራ በተራ ሴቶቹ እየገቡ የቆመው ፖል ላይ ሲጥመለመሉ ሲያስቀይር ሌላ ስትመጣ ሲያስቀይር ሌላ ስትመጣ ቆይቶ ሁለቱን መረጠ እና ፓንት ለማለት የሚያስቸግር ክር ነገር ነገራቸው ላይ ጣል አድርገው፣ የጡታቸውን ጫፍ ብቻ የሚሸፍን ጨርቅ ጩታቸው ላይ አገልድመው ይቀነጣጠሱ ገቡ። ለምጄው የለ? እየቆየ የለበሱትን እንዲያወልቁለት አዘዘ እና ረብጣ ብር አስቀመጠ። እኛን ዞር ብለው ሳያዩ እርቃናቸውን ሆኑለት። ……

ከፖላቸው ወርደው አጓጉል ቦታ እየነካኩት ሰውየው ላይ መደነስ ጀመሩ!! እኔ ብቻ ስቀር ሌሎቹን ጠባቂዎቹን እንዲወጡ አድርጎ እንኳን በእውኔ በፊልም ባየው የሚያስመልሰኝ የሚመስለኝን ብልግና ሴቶቹን አስደረጋቸው። የዛን ቀን እየወጣሁ በሴቶቹ ፍርድ አይደለም የፈረድኩባቸው <እንዴት ያለ የማይታለፍ አበሳ ቢገጥማቸው ነው እንዲህ ራሳቸውን ለማዋረድ ግድ ያልሰጣቸው?> እያልኩ አሰብኩ። የሰውየውን ምናምን ባደረጉበት አፋቸው ምግብ ይበሉበታል? እላለሁ።

እዛ ቤት መመላለስ ያዘወትር ጀመር። አንድ ቀን ታዲያ ይገጥመኛል ብዬ በምንም አጋጣሚ ያላሰብኩት ሰው ገጠመኝ። አለቃዬን አጅቤ ከክፍሉ ስወጣ ሙሉሰው በጋርድ ታጅቦ ወደሌላ ክፍል ሲገባ አየሁት። ደንዝዤ ቆምኩ። ሰውየው እንኳን እስኪያስተውለኝ ተደነባበርኩ። እሱ አላየኝም። ምናልባት ቢያየኝም አያውቀኝም። እኔ ግን ደንግጬ እግሬ ከቆመበት አልንቀሳቀስ አለኝ!!

        ..........  አልጨረስንም  ........

@wegoch
@wegoch
@paappii
807 viewsDAVE / PAPI, 18:38
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-19 21:38:28 እንዳሉ አላውቅም!!!! ብቻ ማናቸውንም ማግኘት ትንሽዬ ማስታወሻዬ ላይ ስማቸውን ፅፎ እንደመያዝ ቀላል እንዳልሆነ ገብቶኛል። በየቀኑ ግን ወደቤቴ ስገባ ያቺን በመተሻሸት ብዛት ቀለሟን የቀየረች ማስታወሻ ደብተር ገልጬ በኑሮ ደፋ ቀና ጠላቶቼን እንዳልረሳ አስታውስባታለሁ። ቀኑ እንጂ የሚረዝመው እስከእድሜዬ ማለቂያ ድረስም ቢዘገይ እነርሱን ሳላገኝ እንደማልሞት ለራሴ በየቀኑ እነግረዋለሁ።

ህልሜን ለማሳካት (በቀልን ህልም ማለቴ አይግረማችሁ!! ያው ለማሳካት እስከምንም ጥግ የምትደክሙለት ዓላማ መግደልም ቢሆን ህልም አይደል?) አዲስአበባ ላይ ጎበዝ አላሚ ተኳሽ እና እንደንፋስ የፈጠንኩ ካራቲስት መሆን ብቻውን እንደማይበቃኝ አውቄያለሁ። አዲስ አበባ ላይ ከምንም ነገር በላይ እነዚህ ሶስቱ ወይም ከሶስቱ አንዱ ያለው አቅም አለው። ሀብት ፤ ስልጣን እና ዝና!! ከሶስቱ በጥቂቱም ቢሆን ተስፋ ያለኝ ሀብት የሚለው ላይ ቢሆንም እንዴት? የሚለውን ግን እስክደርስበት ድረስ እቅዱ አልነበረኝም። ምንም ዓይነት የቅብጠት ምኞት ስላልነበረኝ የማገኘውን ገንዘብ ለኪዳን ያስፈልገዋል የምለውን ነገር ከማሟላት የተረፈኝን አስቀምጣለሁ። ጎን ለጎን መኪና መንዳት መማር እና ከሰባተኛ ክፍል የተውኩት ትምህርት አማርኛ ከማንበብ እና መሰረታዊ የሂሳብ ስሌት ከመስራት የማያሻግር በመሆኑ ቢያንስ መሰረታዊ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን መጠቀም የሚያስችለኝ እውቀት ለመገብየት ሰውየውን ተከትዬ ሆቴል እና ጭፈራ ቤት ደጅ በምገተርባቸው  ቀናት እየቀረሁም ቢሆን የማታ ትምህርት ቤት ገባሁ። ውሉ ሲጠፋብኝ ኪዳን እቤት እቤት ያስጠናኛል።

ለዓመት ከ6 ወር ደላላው እንዳለው ሰውየው በአጀብ ከመሄድ ልክፍቱ ውጪ ሀገር ውስጥ በነበረበት ጊዜ አንድም አይደለም ሊያጠቃው ጮክ ብሎ የተናገረው ሰው አልሰማሁም። ከዚህ በኋላ የሆነ ቀን ዱባይ ትልቅ ስብሰባ መኖሩን እና እዛ ሲሄድ ሀብትና ጉልበቱን ማሳየት ስለሚፈልግ ሁላችንንም አስከትሎ እንደሚሄድ ተነገረን። ፓስፖርት እንኳን ስላልነበረኝ በሰውየው ጉዳይ አስፈፃሚዎች በኩል ያለቀጠሮ ፓስፖርቴ አልቆ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰውየው የግል አውሮፕላን ተሳፈርኩ። ይሄን ጊዜ የግድ ቀሚስ መልበስ እንዳለብኝ ሲነገረኝ ከሀገር የመውጣት ጉጉቱ ስለበለጠብኝ ተስማማሁ!! ለመጀመሪያ ጊዜ ለረዥም ቀናት ከኪዳን ተለይቼ የቆየሁበት ጊዜ ስለነበር ትቼው መሄዱ ሀሳቤን ለመቀየር እስኪፈታተነኝ ከብዶኝ ነበር። የሚከፈለኝ ብር ብዙ ማድረግ የሚያስችለኝ በመሆኑ ከኪዳን ጋር ተነጋግረን እቤት የምታግዘው ሰራተኛ ቀጥሬለት ሄድኩኝ። እስከዛ ሰዓት ድረስ ሰውየው ምን ይስራ፣ ምን ይኑረው፣ ለምን ኢትዮጵያ ይኖራል? የማወቅ ፍላጎት ኖሮኝም አያውቅም!! የግሉ አውሮፕላን እንዳለው ሳውቅ ግን የገቢ ምንጩን የማወቅ ፍላጎት ኖረኝ። ዱባይ ስንደርስ የአንድ ምግባቸው ዋጋ የእኔን የወር ደመወዝ የሚሆን ሆቴል ብቻውን የያዘው እስኪመስል አንድ ፍሎር ላይ ሰፈርን። አስተናጋጆቹ መሬት በግንባራቸው ሊነኩ እስኪቀራቸው ሰግደው ነው ሰላምታ የሚያቀርቡት።

ሰውየው በሀብቱ የተፈራ እና የተከበረ ልጥጥ ነው። የተለያዩ ሀገራት ላይ ለቁጥር የታከቱ ንብረቶች እና ኢንቨስትመንቶች ባለቤት ነው። በአረብ ሀገራት ውስጥ ታላቅ የተባለ የነዳጅ ካምፓኒ ውስጥ ትልቅ ስቶክ ያለው ባለስልጣኖቹ ሁሉ የሚሽቆጠቆጡለት ሰው መሆኑን ስብሰባው አዳራሽ ሲገባ አስተዋልኩ። አዲስአበባ የሚኖረው ሀገሪቷ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ፈልጎ የኢትዮጵያ መንግስት መንገዱን ስላላቀለለለት እግረመንገዱን በሴቶቻችን እየተዝናና ነው ገባ ወጣ የሚለው።

የዛን ቀን ማታ አንደኛውን አቅም (ሀብት) መገንባት እንደምችል እርግጠኛ ሆንኩ። ስብሰባውም ላይ እኔ ከውጭ ጠባቂ ነበርኩ። የተቀመሱት ናቸው አብረውት አዳራሽ የገቡት። የዛን ቀን የሚዘገንነኝን ሴትነቴን ለማሰብ በትንሹ ገርበብ ያለ ልብ ኖረኝ። ቢሆንም ሀሳቡን ለመፈፀም እሩቅ እንደሆነ እያሰብኩ በሚቀጥለው ማታ እድል ወይ አጋጣሚ ብቻ ክስተት ሆነ። ሰውየው የሁለተኛውን ቀን ስብሰባ ጨርሶ ሆቴሉ ካረፈ በኋላ ወክ ካልወጣው ብሎ ቀበጠ። እኔን ጨምሮ ስምንት ሴት እና ሁለት ጠብደል ወንድ አስከትሎ የተቀሩት ምን እንዲጠብቁ እንደሆነ ባላውቅም ሆቴል ውስጥ ሲጠብቁ እንዲቆዩ አስደርጎ ወጣ!! ከስር ከስሩ ጡል ጡል የሚል ትዕዛዙን የሚቀበል እና የሚያቀብል አንድ ሲያዩት ግዙፍ የሚመስል ሲሽለጠለጥ ቡችላ የሚያክል ሰውዬ ከስር ከስሩ አይለየውም። ከፊት አራት ሁለት ከጎን የተቀረነው ከኋላ ሆነን ከሆቴሉ ወጥተን ትንሽ እንደሄድን (እኔ መጨረሻ ላይ ነኝ) ሰው በበዛበት ጎዳና ሚኒባስ ከሚመስል ዝግ መኪና ውስጥ አንድ እንደእርሱ የለበሰ ባለሀብት የሚመስል ጥቁር ሰውዬ የሰማይ ስባሪ በሚያካክሉ ስድስት በኋላ ላይ ናይጄሪያውያን መሆናቸውን ያወቅኳቸው ወንዶች ታጅቦ ወረደ። የኛውን ሰውዬ ያጀብነው እኔን ጨምሮ ወደሽጉጣችን እጃችንን ላክን ……. ግማሾቻችንም ሰዎቹ ላይ ደቀንን!! የኛው ሰውዬ እንድንረጋጋ ምልክት ሰጥቶን ከሰውየው ጋር በወዳጅነት ሰላም ተባብለው የሰውየውም ጠባቂዎች ከኛ ጋር ተደባልቀው ሁለቱ እያወሩ መጓዝ ያዙ።

ሁላችንም የተቀላቀሉንን እንግዶች ችላ ብለን የተቀረነውን ዙሪያ ገባችንን በንቃት እየቃኘን ትንሽ እንደሄድን ባልታሰበ ቅፅበት ፍጥንጥን ያለ ፊልም የሚመስል ክስተት ሆነ። የሰማይ ስባሪዎቹ አንደኛው የኛን ሰውዬ ሌሎቹ ሁለቱን ወንዶች ጨምሮ ምናልባት ፈጣን ናቸው ያሏቸውን ጠባቂዎች ያዙ። የሚያወሩት አረብኛ ስለሆነ ጥቁሩ ባለሀብት የሚያወራው ባይገባኝም የሆነ የፈለገውን ነገር በጣም በንቀት እያየው ለኛ ሰውዬ እያስረዳው በችኮላ እየነገረው እያለ አውርዳቸው የነበረችው መኪና ዞራ አጠገባችን መጣች እና እንዲገባ ገፈታተሩት። መሳሪያ ያልተደገነብን እና አንገታችን ያልተቆለፈብን ሁላችንምኮ ሽጉጣችንን መዘናል። ግን መተኮስ እንዳንችል አለቃችን ተይዟል። በፍጥነት ለማሰብ ሞከርኩ። ከሰውየው ሁለት እርምጃ የማይሞላ እርቀት ላይ ደርሻለሁ። ግን ከፌቴ በቁመቱ ሙሉ የሚከልለኝ ሰውዬ የፊት ጠባቂዋን አንገት ይዞ ሽጉጡን ጭንቅላቷ ላይ ይዞታል። ምንም ያህል ብፈጥን አደጋ ያለው እርምጃ እንደምወስድ ቢገባኝም ፍርሃት አልተሰማኝም። እንቅስቃሴዬን ትኩረት የሚስብ ዓይነት ሳላደርግ ሽጉጤን የእኛን አለቃ ለያዘው ሰውዬ ግንባር አደረግኩ። ከጀርባ ከተያዘው ወንድ ጠባቂ ጋር ተያየን። እርምጃ ልወስድ እንደሆነ ገብቶታል። አባዬ ፣ አጎቴ ፣ እዚህ ስራ ልቀጠር ስል ደግሞ ቋንቋቸው ሳይገባኝ የተደናቆርኳቸው የሰውየው ሰዎች …… ያስተማሩኝን ኢላማ የምተገብርበት ሰዓት ሆነ። አልፈራሁም!! ምናልባት ብስት ሊፈጠር የሚችለውን ስለማላውቅ ወይም የመጀመሪያዬ ስለሆነ አላውቅም! ምንም ፍርሃት አልተሰማኝም። አለማወቅ አንዳንዴ ጥሩ ድፍረት ነው። ከኋላ የነበረው ልተኩስ እንደሆነ የገባው ጠባቂ ወከባ እና ሁከት ፈጥሮ ትኩረት ሲቀንስልኝ የሰውየውን ግንባር አገኘሁት እና በፍጥነት ከፊቴ የነበረው እግር ስር ዝቅ ብዬ በክንዴ ጉልበቱን ገጨሁት። ከጀርባ የነበረው የእኔን እርምጃ ተከትሎ በተፈጠረው ግርግር አለቃችንን መሬት ላይ ጥሎት እላዩ ላይ ወድቆ ከደነው። ሁለት ከኛ ወገን (እኔን ጨምሮ) ተመትቶ ቆስሎ አንድ ከእነርሱ ወገን ሞቶ ሁለት ቆስሎ አካባቢው በፖሊስ እና በህዝብ ግርግር ተዋክቦ እነሱ ሬሳቸውን ትተው በመጡበት መኪና አመለጡ። የተመታ ክንዴን ታክሜ ወደስራ ስመለስ ከዛን ቀን በኋላ የሰውየው የጎን ጠባቂ ሆንኩ!!
664 viewsDAVE / PAPI, 18:38
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-19 21:38:28 የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል........ ክፍል ሀያ ሰባት
(ሜሪ ፈለቀ)

የሰው ልጅ ለውጥ የአንድ ጀምበር ክስተት አይሆንም። ወይ ተሸርፎ ተሸርፎ የተጋተው ልምድ እየቆየ ይለውጠዋል አልያም በህይወቱ ከባድ ክስተት እንደሚወዱትን ማጣት ያለ ንዝረት 360 ዲግሪ ይቀይረዋል። የአባቴን ገዳዮች ለመጥላት የአባቴ ሞት እና የእናቴ አይኔ ስር መደፈር በቂ ነበር። የበቀል ጥንስሴን ከዜሮ መቶ ለማድረስ ለቁጥር የሚታክት ጊዜ አባቴ የሞተበት ደጃችን ላይ ተመላልሼ ክስተቱን በጭንቅላቴ ስያለሁ!! አንድ ቀን ባልሳቅኩ ቁጥር፣ ልጅነቴን ሁሉ እኔና ወንድሜ እናትና አባት እንደሌለን ባሰብ ቁጥር ሁሉ አምርሬ ጠልቼ አምርሬ ላጠፋቸው ሰውነቴ ጥላቻ ረጭቷል።

ሴት ልጅ እርቃኗን የወንድ መዝናኛ ሆና የምታስገኘውን ገንዘብ እንደገቢ ከመቁጠሬ ከዓመታት በፊት የሴት ልጅ ገላ ሲቀል አይቼ ዘግንኖኝ ነበር። <እንዴት አይነት አስተዳደግ ብታድግ ነው?>ም ብዬ ፈርጄባታለሁ። ቀን በቀን በትንሽ በትንሹ ስጋተው ቀጭን ወገብ ሳይ ፖሉ ላይ ስትጥመለመል የሚስል ጭንቅላት ኖረኝ እና አረፈው።

ያኔ ታክሲ በር ላይ ተለጥፌ ፒያሳ ሜክሲኮ የምል ጊዜ ……. በጉልበቴ ተከበርኩ። ተራ አስከባሪውም ሹፌሩም ከዛን ቀን በፊት አይቶኝ በማያውቀው የክብር ዓይን አየኝ። ፀሃይ ሲያነደኝ ውዬ የማገኘው ገንዘብ ግን ኪዳንዬን እንደምፈልገው የሚያኖርልኝ አልነበረም። ያ ሰውዬ የሰጠኝን ቢዝነስ ካርድ ለማይቆጠር ያህል ጊዜ ካሸሁት በኋላ ደወልኩለት። ሰውየው ደላላ ነው። ሊያስቀጥረኝ ያጨልኝ ቦታ እንኳን ለእንደእኔ ዓይነቷ ከትንሽ ክፍለሀገር ለመጣች ሴት ቀርቶ የፈረንጅ ፊልም ስታይ ላደገች ከተሜም ቀላል አይመስለኝም። ከተማዋ ውስጥ እኔ ነኝ ያለ የመናዊ ሰውዬ ጠባቂ መሆን ነው። መጠበቁ ደግ ነበር። ሰውየው የጋዳፊ(ስለጋዳፊ ሳውቅ ነው የገባኝ ጉዳዩ) ታናሽ የሚሰራራው ወፈፌ ነው። ጠባቂዎቹ ሴቶች እንዲሆኑ ከመፈለጉ አንድ ደርዘን ሴት እንዲጠብቀው መፈለጉ ግራ ያጋባል። ብስራተ ገብርኤል ካለው ቤቱ ቦሌ ለመድረስ በአራት መኪና እና በ10 ሴት ጠባቂ በሁለት ወንድ አጃቢ መከበብ ጤንነት ነው?

የተገናኘን ቀን ዝርዝሩን ብዙም ሳይነግረኝ ሰውየው ቤት ይዞኝ ሄደ። የቤቱ ስፋትና ውበት ቤተመንግስት ራሱ እንደዚህ ይመስላል የሚል ምስል ጭንቅላቴ ውስጥ የለም። የአጥሩ በርጋ ብቻ ወንድ ሁለት ጠባቂዎች ሲኖሩ በተረፈው ሱፍ ኮት እና ሚኒ ጉርድ የለበሱ  በለበስኩት የመነቸከ ሸሚዝና ጅንስ ሱሪ የሚያሸማቅቁኝ የሚያማምሩ ሴቶች ሲቀባበሉ ብዙ ኮሪደር እና ክፍሎች አልፈን አንደኛው ቢሮ የሚመስል ክፍል አደረሱኝ። ሴቶቹ ምናልባት ከሁለቱ ውጪ ሀበሻ አይደሉም!! ሰውየው ፊቱ ከመንጣቱ የተነሳ የሰው ቆዳ ሳይሆን ነጭ ሸማ የመሰለ ፊት ያለው አረብ ነው። ጭንቅላቱ ላይ በቄንጥ የታሰረ ሻርፕ ነገር አድርጎ እንደወተት የነጣ ቀሚስ ለብሷል። ከደላላው ጋር በአረብኛ ሲነጋገሩ እንዳልወደደኝ ያስታውቅበታል። ከእግሬ እስከራሴ በማጣጣል እያየኝ ቁጣ የመሰለ ነገር ይንጣጣል። ደላላው ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል። ሳይገባኝ አይኔን ከሰውየው ወደ ደላላው እያቁለጨለጭኩ ሳይ ከየት መጣ ያላልኩት የሆነ ጠባቂ መሰለኝ ከጀርባዬ ሳላስበ በእጁ ቆልፎ አንቆኝ ወደላይ አነሳኝ። እነርሱ ጭቅጭቃቸውን ቀጠሉ። ደመነፍሴን እየሆነ ያለው ሳይገባኝ በቀኝ እጄ ያነቀኝን እጁን ጠምዝዤ በግራ እጄ ፍሬውን አጎንኩት። እጁን ጠምዥዤ ወደፊት ስደፋው ነው ሆነ ብለው የፈጠሩት ድራማ መሆኑን ያወቅኩት። ሰውየው <ምንም አትል> አይነት ንቅናቄ ጭንቅላቱን ነቀነቀ።

እዚህ ድረስ ሰላም ነበር። እንድለካው ያመጡልኝን ልብስ ስለብሰው የለበስኩት ፓንት ሊታይ ትንሽ የቀረው ከመሆኑ ለፋሲካ የሚገዙትን በግ አዟዙረው እንደሚያዩት እየዞረኝ ሲገረምመኝ
«ምንድነው እሱ? ስራው ጥበቃ ነው አላልክም? ደግሞ ይሄን ብጣሽ ነገር አገልድሜ አንድ እርምጃ አልሄድም!! አልፈልግም ስራውን!» ብዬ ልብሱን እንድቀይር የወሰዱኝ ክፍል ሄጄ የራሴን ልብስ ስቀይር አሁንም እነርሱ እንደጭቅጭቅ ያለ ወሬ ሲያወሩ ይሰማኛል። ደላላው በኋላ ሲገባኝ ለሚከፈለው ጠርቀም ያለ ገንዘብ ነው ሽንጡን ገትሮ እንድቀጠር ሲከራከር የነበረው። ሰውየው ስራውን አልፈልግም በማለቴ ተናዶ መሆኑን በኋላ ሰማሁ። <ማን እንደሆንኩ አውቃለች? > ብሎ ነበር የደነፋው። ስንወጣ ደላላው ደሞዙን ሲነግረኝ ጠጅ እንደጠጣ ሰው ጉልበቴን ያዘኝ። ግን እንዲያውቅብኝ ስላልፈለግኩ መግደርደሬ እንዲታወቅልኝ

«የምሰራ ከሆነም ያን ቀሚስ አልለብስም። ሱሪ ከተደረገልኝ እሰራለሁ!! ደግሞ ቆይ ሴቶቹስ እግራቸውን ማንሳት ቢኖርባቸው በዛ ቀሚስ እንዴት ነው የሚሆኑት?»

«ሰውየው በሴት የመከበብ ልክፍት ስላለበት እንጂ አሁን ማን ይሙት አዲስአበባ ውስጥ እንዲህ ተከቦ የሚያስኬድ ስጋት ኖሮበት ነው? የሀብታም ነገር ብሩን የሚጥልበት ሲጨንቀው ነው።» አለኝ። ከቀናት በኋላ ሱሪ መልበስ እንደተፈቀደልኝ ነገረኝ እና ስራውን ጀመርኩ። ጀመርኩ እንደዋዛ አይደለም። ከሰውየው ጠባቂዎች ጋር ኢላማ ተፈትኜ…… መጀመሪያ ሰሞን በየሄደበት በር ጠባቂ ካደረገኝ በኋላ ….. ከሀገር ውጪ ሲወጣ ባዶ ቤት ክፍሎች ጠባቂ ከሆንኩ በኋላ ….. ከኪዳን ጋር የተሻለ ቤት ተከራይተን መኖር ከጀመርን በኋላ ……. የግል ትምህርት ቤት ካስገባሁት በኋላ …… የሆነ ጊዜ ደላላው ሲመጣ በር ጠባቂ መሆኔን ሲያይ

«አንቺ ከእነዚህ እሳት ሴቶች ጋር እየዋልሽ ዛሬም በር ላይ ነሽ? አትማሪም? ምንድነው እንዲህ ማካበድ? ይሄኔ ብታቀምሺው ስንት ሀገር አይተሽ ነበር! ያንቺ የተለየ ነው እንዴ ይሄን ያህል?» ሲለኝ እስከዛን ቀን ዙሪያዬ እየሆነ ያለውን አለማጤኔ ገባኝ። አትማሪም ወይ? አለኝ እንጂ ሴቶቹ ከእኔጋ ጊዜ ኖሯቸውም አያወሩ ቢኖራቸውም የእነርሱ ዓይነት አራዳ ስላልነበርኩ ትዝም አልላቸውም። በዛ ላይ ከሁለቱ ሀበሾች ውጪ በቋንቋም አልግባባም!! ደላላው ከሄደ በኋላ ነው ከእኔ ውጪ ሁሉም ሴቶች ባለመኪና የመሆናቸው ሚስጥር እኔ ቅርብ ስራ ጀማሪ መሆኔ ሳይሆን እነርሱ መቀመሳቸው መሆኑ የተገለጠልኝ። እስከዛን ቀን ድረስ ሴትነትን ወይም ድንግልናን አስቤው የማውቅ ባልሆንም ነገሩን አስቤው ዘገነነኝ። ሴትነትን ሳስብ ትዝ የሚለኝ መሬት ላይ ቀሚሷ ተገልቦ የተኛች እናቴ ናት!! ሴቶቹም ዘገነኑኝ!! ሴትነቴም ዘገነነኝ!! ለውጥ የልምድ ውጤት ነው አላልኳችሁም? ለዛን ሰዓት ከመኪናው እና ሴቶቹ ሲይዙ ከማያቸው ውድ ስልኮች እና ሲያደርጉ ከማያቸው ዘናጭ ቦርሳና ጫማዎች በላይ የከዳሁት ሴትነቴን ክብር ማስጠበቅ መረጥኩ!! በየሄደበት በር ላይ መቆሙን ቀጠልኩበት!!

አዲስ አበባ እንደአደግኩበት ክፍለሀገር በጉልበቴ ብቻ የምከበርበት ሀገር አለመሆኑን ከረፈደም ቢሆን አውቄያለሁ። ከኛ ሰፈር የአባቴ ገዳዮች ሰፈር እኩዮቼን አጅቤ ሄጄ ጠላቴን አደባይቼ ልምጣ ብዬ እንደማቅደው የስልጣን ሽልማታቸውን የሚያጣጥሙ ያባቴን ገዳዮች በር አንኳኩቼ እንደማልገድላቸው አውቄያለሁ። ሁሉም ነገር ከባድ እንደሆነ ያወቅኩት እንኳን እኔ ቀርቶ ገጠር ሲመጣ <ሚንስትር ሙሉሰው ዘመዴ ነው! እኛ ቤት ይመጣል> እያለ የሚበጠረቀው የካራቴ አሰልጣኛችን እንኳን የሚንስትሩ ቤት ሰማይ ይሁን ምድር ካለማወቁ ቤተሰቦቹ እንኳን ያለምክንያት የማያገኙት ሩቅ ሰው መሆኑን ስረዳ ነው። ከሀገሬ ስወጣ እገድላቸዋለሁ ብዬ ስም ዝርዝራቸውን የፃፍኳቸው እና ስማቸውን ማወቅ ሳልችል በምልክት ጭንቅላቴ ውስጥ የመዘገብኳቸው ሰዎች ዋና ዋናዎቹ እዚሁ አዲስአበባ ተሿሹመው ሲኖሩ የተቀሩት የት
788 viewsDAVE / PAPI, 18:38
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-18 17:54:52 «አዲስአበባ ከሄድን እዛ አንድ ቀን እንኳን እንድታድር አልፈልግም!! ሳይውል ሳያድር እንድትወጣልኝ ነው የምፈልገው ምን ያደርጉብኝ ይሆን ብዬ ማሰብ አልፈልም!!»

«አውቃለሁ!! ግን አንቺስ?»

«እኔ ምን? እኔ ራሴን መጠበቅ አያቅተኝም!!»

«ሜል ብዙ ነገር ተቀይሯል። ምን ያህል እንዳስተዋልሽው አላውቅም እንጂ አንቺም ራሱ ፍፁም ተቀይረሻል። ወደኋላ ተመልሰሽ ያለፈ ህይወትሽን መኖር የምትችዪ አይመስለኝም! እሱን ነው የምታስቢው? ምንድነው የምታስቢው?» አጠያየቁ የእኔ ኪዳን አይመስልም በጣም ተኮሳትሮ እንደታላቅ ነው የሚያወራው

«አላውቅም! ራሴ እንደተቀየርኩ አውቃለሁ ነገር ግን ያለፈውን ህይወቴን ሙሉ ለሙሉ ተፋትቼ መኖር እችል እንደሆነ አላውቅም! ምክንያቱም እኔ ብቻ እንጂ የተቀየርኩት በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችም ሁኔታዎችም እንዳሉ ናቸው። የቱን ጥዬ የቱን ይዤ እንደምቀጥል አላውቅም!»

«ለምን ከሀገር መውጣትን አታስቢበትም? ሁሌ ጀርባሽን መጠበቅ ሳይኖርብሽ አዲስ ህይወት አዲስ ማንነት ትገነቢያለሽ!»

«እኔእንጃ የኔ ኪዳን!!»

«በጎንጥ ምክንያት ነው? የነገ አብሮነታችሁ ምን ሊሆን እንደሚችል ተነጋግራችኋል?»

«አይደለም! ስለነገም ያወራነው የለም! ስለምንም ያወራነው የለም!»

«ሜልዬ እስኪ ዛሬ እንደ ትንሹ ወንድምሽ ሳይሆን እንደ 31 ዓመት ትልቅ ሰው አውሪኝ! እንደምትዋደዱ ግልፅ ነው!! እኔ ሳውቅሽ ለማንም ሆነሽ የማታውቂውን ነው ለሱ እየሆንሽ ያለሽው! ማንንም ሰው ባላቀረብሽው ልክ ነው እሱን ያቀረብሽው! ወደፊትሽን ስታስቢ እሱ አለበት? ያወራችሁት አይኑር! አንቺ ምንድነው የምታስቢው?»

«እኔ እንጃ ኪዳንዬ የእውነቴን እኮ ነው እኔንጃ የምልህ!! ታውቃለህ እኔ ፍቅር አላውቅም!! ፀብ ቢሉኝ አውቃለሁ፣ በቀል ቢሉኝ አውቃለሁ ……. ፍቅር ግን አዲሴ ነው!! ስምጥ ብዬ ከዋኘሁ በኋላ ነውኮ እንደወደድኩት እንኳን የነቃሁት! ደግሞ እኔ ብቻ የማስበው ምን ይፈይዳል? እኔ ስላሰብኩህ ና ወደፊቴ ውስጥ ላካትህ ይባላል?»

«ጠይቂዋ!»

«ምን ብዬ?»

«ምንድነው ስለወደፊት የምታስበው? አብሮነታችን ምን ድረስ ነው የሚዘልቀው? ብለሽ ነዋ!»

«እህ እሱ አይደል እንዴ ወንዱ! ይሄን መጠየቅ ያለበት እሱ አይደለም? በግድ እየገፋፋሁት ቢመስልብኝስ?» ስለው ከቀናት በፊት ሲስቅ የሰማሁትን ሳቅ ሳቀ።

«አይመስልም ዓለሜ (ልክ ጎንጥ በሚልበት ለዛ) ዘመኑ ተቀይሯል!! ሴት ተንበርክካ አግባኝ የምትልበት ዘመን ላይ ነን!»

« ምንስ ፍቅር ብርቄ ቢሆን ጥንቅር ይላታል እንጂ ተንበርክኬማ አግባኝ አልለውም! ጭራሽ? ለተሸነፍኩትም መደበቅ ቢቻለኝ በዋጥኩት! እንቢ እያለኝ እያመለጠኝ እንጂ!!» ተሳሳቅን!!

በሚቀጥለው ቀን ኦንላይን ትኬቱን ቆርጦ አጎቴን ተሰናብተን (ስንብቱ በእንባ የታጀበ ነበር።) ወደ አዲስ አበባ መጣን!! የዛኑ ቀን በረራው ነበረ። ስንሰነባበት

«ሜል አስብበታለሁ በይኝ ከሀገር መውጣቱን?»

«አስብበታለሁ ሙት!!»

«ለዓለሜ እንደምትዪው <የእህቴን ልብ ብትሰብር ውርድ ከራሴ!! ጦርነት በራስህ ላይ እንዳወጅክ ቁጠረው አንላቀቅም!!> ብሎሃል በይልኝ። የምሬን ነው ንገሪው!»

«ሂድ አሁን አርፈህ!! እነግርልሃለሁ!!»

እሱን ሸኝቼው ስመለስ ህይወቴን ካቆምኩበት መቀጠል እንደማልችል ገባኝ። ቤቴ እንኳን ያለስጋት መሄድ እንደማልችል ሳውቅ መኪናውን መንገድ ዳር አቁሜ ውስጥ እንደተቀመጥኩ ብዙ ቆየሁ። የእውነት ምንድነው አሁን የማደርገው? እንደድሮው ባር ሄጄ ወገበ ቀጫጭን ሴቶች የቆመ ፖል ላይ ሲውረገረጉ ፣ ለፍዳዳ ሰካራሞች ለሀጫቸውን እያዝረከረኩ ብራቸውን ሲረጩ …. .፣ አቅላቸውን የሳቱ ሱሰኞች ሀሺሺን ከሺሻው እያደባለቁ ሲያጨሱ …… እያየሁ እየተዘዋወርኩ ብሉልኝ ፣ ጠጡልኝ ፣ አጭሱልኝ ፣ ተዝናኑልኝ እያልኩ ብሬን መምታት ይቻለኛል?

ከአንድ ሰዓት በላይ ከቆምኩ በኋላ የሆነኛው ገስት ሀውስ ይዤ ለዛሬ እርፍ ብዬ መተኛት ፈለግኩና ከዛ በፊት የጎንጥን ድምፅ መስማት ፈለግኩ። አንዱ ሱቅ ገብቼ ደወልኩ። ስልኩ ዝግ ነው። ገስትሀውስ ገብቼ ለማረፍ ሞከርኩ እና ተገላበጥኩ። ራሴን አሁንም ወጥቼ የሱቅ ስልክ ላይ ስደውል አገኘሁት። ዝግ ነው!! ተመልሼ ገብቼ ለጥ ብዬ አድራለሁ ያልኩትን ለሊት ስገላበጥ አደርኩ። ይሄኛው ስሜት ደስ አይልም!! ስልኩን ባይከፍተው የት ብዬ ነው የማገኘው? የድሮ ሚስቱ ቤት ሄጄ <እየገደልሽኝ ሳለ እግረመንገድሽን ጎኔ የት እንዳለ ብቻ ንገሪኝ> ነው የምላት? ደግሞ ለራሴ <ማታ አይደል ያዋራሁት? ይሄኔ ባትሪ ዘግቶበት ነው!> እላለሁ። ዛሬ እንደምመጣ እያወቀ ስልኩን የዘጋው ሊያገኘኝ ስላልፈለገ ቢሆንስ? ምን እየሆንኩ ነው ስንት ሀሳብ እያለብኝ ስለእርሱ ብቻ የማስበው?  ……. ስወራጭ ቆይቼ ሊነጋ ሲቃረብ እንቅልፍ ወሰደኝ!!

እንደነቃሁ ተጣጥቤ ስልኩን ሞከርኩ። አሁንም ዝግ ነው። ወደሰፈሬ ነዳሁ እና ተናኜን ቅያሪ ልብሶች ተቀብያት ጎንጥ ብቅ ብሎ እንደው ስጠይቃት አለመምጣቱን ነገረችኝ። ልብሴን እዛው መኪና ውስጥ ቀይሬ ሻለቃው ቢሮ ሄድኩ። የሰዎቹን ፎቶ ከተገበያየሁ በኋላ እንደማላውቃቸው ሳውቅ መረጃ የሚያቀብለኝ ሰው ጋር ደወልኩ።

«ኢሜል የማደርግልህን ፎቶ ተመልከተውና መረጃ አቀብለኝ» ካልኩት በኋላ የሁለቱን ሰዎች ፎቶ እየላኩለት ልክ እንዳልሆነ የማውቀው ሀሳብ ጭንቅላቴን ወጠረኝ። ላለማድረግ ከራሴ ጋር ታገልኩ። ግን አቃተኝ!! ከስልኬ ውስጥ ጎንጥን ስቀጥረው ይዤው የነበረውን ፎቶ አብሬ ላኩለት። መልሶ ደወለልኝ እና

«ይሄን ሰውዬኮ ከዚህ በፊት ጠይቀሽኝ ነበር።»

«አውቃለሁ!! ተጨማሪ መረጃ ፈልግ!! በጓሮ ሂድ!» አልኩት (ሰውየው በግልፅ ከተመዘገበው መረጃ በላይ የተደበቀ መረጃ አለው ለማለት ነው በጓሮ ሂድ የምንባባለው)

ስልኩን ዘግቼው ኮምፒውተር ቤቱ ውስጥ ፍዝዝ ብዬ ቀረሁ!!!

   ………… አልጨረስንም …………..

@wegoch
@wegoch
@paappii
1.1K viewsDAVE / PAPI, 14:54
ክፈት / አስተያየት ይስጡ