Get Mystery Box with random crypto!

እንዳሉ አላውቅም!!!! ብቻ ማናቸውንም ማግኘት ትንሽዬ ማስታወሻዬ ላይ ስማቸውን ፅፎ እንደመያዝ ቀ | ወግ ብቻ

እንዳሉ አላውቅም!!!! ብቻ ማናቸውንም ማግኘት ትንሽዬ ማስታወሻዬ ላይ ስማቸውን ፅፎ እንደመያዝ ቀላል እንዳልሆነ ገብቶኛል። በየቀኑ ግን ወደቤቴ ስገባ ያቺን በመተሻሸት ብዛት ቀለሟን የቀየረች ማስታወሻ ደብተር ገልጬ በኑሮ ደፋ ቀና ጠላቶቼን እንዳልረሳ አስታውስባታለሁ። ቀኑ እንጂ የሚረዝመው እስከእድሜዬ ማለቂያ ድረስም ቢዘገይ እነርሱን ሳላገኝ እንደማልሞት ለራሴ በየቀኑ እነግረዋለሁ።

ህልሜን ለማሳካት (በቀልን ህልም ማለቴ አይግረማችሁ!! ያው ለማሳካት እስከምንም ጥግ የምትደክሙለት ዓላማ መግደልም ቢሆን ህልም አይደል?) አዲስአበባ ላይ ጎበዝ አላሚ ተኳሽ እና እንደንፋስ የፈጠንኩ ካራቲስት መሆን ብቻውን እንደማይበቃኝ አውቄያለሁ። አዲስ አበባ ላይ ከምንም ነገር በላይ እነዚህ ሶስቱ ወይም ከሶስቱ አንዱ ያለው አቅም አለው። ሀብት ፤ ስልጣን እና ዝና!! ከሶስቱ በጥቂቱም ቢሆን ተስፋ ያለኝ ሀብት የሚለው ላይ ቢሆንም እንዴት? የሚለውን ግን እስክደርስበት ድረስ እቅዱ አልነበረኝም። ምንም ዓይነት የቅብጠት ምኞት ስላልነበረኝ የማገኘውን ገንዘብ ለኪዳን ያስፈልገዋል የምለውን ነገር ከማሟላት የተረፈኝን አስቀምጣለሁ። ጎን ለጎን መኪና መንዳት መማር እና ከሰባተኛ ክፍል የተውኩት ትምህርት አማርኛ ከማንበብ እና መሰረታዊ የሂሳብ ስሌት ከመስራት የማያሻግር በመሆኑ ቢያንስ መሰረታዊ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን መጠቀም የሚያስችለኝ እውቀት ለመገብየት ሰውየውን ተከትዬ ሆቴል እና ጭፈራ ቤት ደጅ በምገተርባቸው  ቀናት እየቀረሁም ቢሆን የማታ ትምህርት ቤት ገባሁ። ውሉ ሲጠፋብኝ ኪዳን እቤት እቤት ያስጠናኛል።

ለዓመት ከ6 ወር ደላላው እንዳለው ሰውየው በአጀብ ከመሄድ ልክፍቱ ውጪ ሀገር ውስጥ በነበረበት ጊዜ አንድም አይደለም ሊያጠቃው ጮክ ብሎ የተናገረው ሰው አልሰማሁም። ከዚህ በኋላ የሆነ ቀን ዱባይ ትልቅ ስብሰባ መኖሩን እና እዛ ሲሄድ ሀብትና ጉልበቱን ማሳየት ስለሚፈልግ ሁላችንንም አስከትሎ እንደሚሄድ ተነገረን። ፓስፖርት እንኳን ስላልነበረኝ በሰውየው ጉዳይ አስፈፃሚዎች በኩል ያለቀጠሮ ፓስፖርቴ አልቆ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰውየው የግል አውሮፕላን ተሳፈርኩ። ይሄን ጊዜ የግድ ቀሚስ መልበስ እንዳለብኝ ሲነገረኝ ከሀገር የመውጣት ጉጉቱ ስለበለጠብኝ ተስማማሁ!! ለመጀመሪያ ጊዜ ለረዥም ቀናት ከኪዳን ተለይቼ የቆየሁበት ጊዜ ስለነበር ትቼው መሄዱ ሀሳቤን ለመቀየር እስኪፈታተነኝ ከብዶኝ ነበር። የሚከፈለኝ ብር ብዙ ማድረግ የሚያስችለኝ በመሆኑ ከኪዳን ጋር ተነጋግረን እቤት የምታግዘው ሰራተኛ ቀጥሬለት ሄድኩኝ። እስከዛ ሰዓት ድረስ ሰውየው ምን ይስራ፣ ምን ይኑረው፣ ለምን ኢትዮጵያ ይኖራል? የማወቅ ፍላጎት ኖሮኝም አያውቅም!! የግሉ አውሮፕላን እንዳለው ሳውቅ ግን የገቢ ምንጩን የማወቅ ፍላጎት ኖረኝ። ዱባይ ስንደርስ የአንድ ምግባቸው ዋጋ የእኔን የወር ደመወዝ የሚሆን ሆቴል ብቻውን የያዘው እስኪመስል አንድ ፍሎር ላይ ሰፈርን። አስተናጋጆቹ መሬት በግንባራቸው ሊነኩ እስኪቀራቸው ሰግደው ነው ሰላምታ የሚያቀርቡት።

ሰውየው በሀብቱ የተፈራ እና የተከበረ ልጥጥ ነው። የተለያዩ ሀገራት ላይ ለቁጥር የታከቱ ንብረቶች እና ኢንቨስትመንቶች ባለቤት ነው። በአረብ ሀገራት ውስጥ ታላቅ የተባለ የነዳጅ ካምፓኒ ውስጥ ትልቅ ስቶክ ያለው ባለስልጣኖቹ ሁሉ የሚሽቆጠቆጡለት ሰው መሆኑን ስብሰባው አዳራሽ ሲገባ አስተዋልኩ። አዲስአበባ የሚኖረው ሀገሪቷ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ፈልጎ የኢትዮጵያ መንግስት መንገዱን ስላላቀለለለት እግረመንገዱን በሴቶቻችን እየተዝናና ነው ገባ ወጣ የሚለው።

የዛን ቀን ማታ አንደኛውን አቅም (ሀብት) መገንባት እንደምችል እርግጠኛ ሆንኩ። ስብሰባውም ላይ እኔ ከውጭ ጠባቂ ነበርኩ። የተቀመሱት ናቸው አብረውት አዳራሽ የገቡት። የዛን ቀን የሚዘገንነኝን ሴትነቴን ለማሰብ በትንሹ ገርበብ ያለ ልብ ኖረኝ። ቢሆንም ሀሳቡን ለመፈፀም እሩቅ እንደሆነ እያሰብኩ በሚቀጥለው ማታ እድል ወይ አጋጣሚ ብቻ ክስተት ሆነ። ሰውየው የሁለተኛውን ቀን ስብሰባ ጨርሶ ሆቴሉ ካረፈ በኋላ ወክ ካልወጣው ብሎ ቀበጠ። እኔን ጨምሮ ስምንት ሴት እና ሁለት ጠብደል ወንድ አስከትሎ የተቀሩት ምን እንዲጠብቁ እንደሆነ ባላውቅም ሆቴል ውስጥ ሲጠብቁ እንዲቆዩ አስደርጎ ወጣ!! ከስር ከስሩ ጡል ጡል የሚል ትዕዛዙን የሚቀበል እና የሚያቀብል አንድ ሲያዩት ግዙፍ የሚመስል ሲሽለጠለጥ ቡችላ የሚያክል ሰውዬ ከስር ከስሩ አይለየውም። ከፊት አራት ሁለት ከጎን የተቀረነው ከኋላ ሆነን ከሆቴሉ ወጥተን ትንሽ እንደሄድን (እኔ መጨረሻ ላይ ነኝ) ሰው በበዛበት ጎዳና ሚኒባስ ከሚመስል ዝግ መኪና ውስጥ አንድ እንደእርሱ የለበሰ ባለሀብት የሚመስል ጥቁር ሰውዬ የሰማይ ስባሪ በሚያካክሉ ስድስት በኋላ ላይ ናይጄሪያውያን መሆናቸውን ያወቅኳቸው ወንዶች ታጅቦ ወረደ። የኛውን ሰውዬ ያጀብነው እኔን ጨምሮ ወደሽጉጣችን እጃችንን ላክን ……. ግማሾቻችንም ሰዎቹ ላይ ደቀንን!! የኛው ሰውዬ እንድንረጋጋ ምልክት ሰጥቶን ከሰውየው ጋር በወዳጅነት ሰላም ተባብለው የሰውየውም ጠባቂዎች ከኛ ጋር ተደባልቀው ሁለቱ እያወሩ መጓዝ ያዙ።

ሁላችንም የተቀላቀሉንን እንግዶች ችላ ብለን የተቀረነውን ዙሪያ ገባችንን በንቃት እየቃኘን ትንሽ እንደሄድን ባልታሰበ ቅፅበት ፍጥንጥን ያለ ፊልም የሚመስል ክስተት ሆነ። የሰማይ ስባሪዎቹ አንደኛው የኛን ሰውዬ ሌሎቹ ሁለቱን ወንዶች ጨምሮ ምናልባት ፈጣን ናቸው ያሏቸውን ጠባቂዎች ያዙ። የሚያወሩት አረብኛ ስለሆነ ጥቁሩ ባለሀብት የሚያወራው ባይገባኝም የሆነ የፈለገውን ነገር በጣም በንቀት እያየው ለኛ ሰውዬ እያስረዳው በችኮላ እየነገረው እያለ አውርዳቸው የነበረችው መኪና ዞራ አጠገባችን መጣች እና እንዲገባ ገፈታተሩት። መሳሪያ ያልተደገነብን እና አንገታችን ያልተቆለፈብን ሁላችንምኮ ሽጉጣችንን መዘናል። ግን መተኮስ እንዳንችል አለቃችን ተይዟል። በፍጥነት ለማሰብ ሞከርኩ። ከሰውየው ሁለት እርምጃ የማይሞላ እርቀት ላይ ደርሻለሁ። ግን ከፌቴ በቁመቱ ሙሉ የሚከልለኝ ሰውዬ የፊት ጠባቂዋን አንገት ይዞ ሽጉጡን ጭንቅላቷ ላይ ይዞታል። ምንም ያህል ብፈጥን አደጋ ያለው እርምጃ እንደምወስድ ቢገባኝም ፍርሃት አልተሰማኝም። እንቅስቃሴዬን ትኩረት የሚስብ ዓይነት ሳላደርግ ሽጉጤን የእኛን አለቃ ለያዘው ሰውዬ ግንባር አደረግኩ። ከጀርባ ከተያዘው ወንድ ጠባቂ ጋር ተያየን። እርምጃ ልወስድ እንደሆነ ገብቶታል። አባዬ ፣ አጎቴ ፣ እዚህ ስራ ልቀጠር ስል ደግሞ ቋንቋቸው ሳይገባኝ የተደናቆርኳቸው የሰውየው ሰዎች …… ያስተማሩኝን ኢላማ የምተገብርበት ሰዓት ሆነ። አልፈራሁም!! ምናልባት ብስት ሊፈጠር የሚችለውን ስለማላውቅ ወይም የመጀመሪያዬ ስለሆነ አላውቅም! ምንም ፍርሃት አልተሰማኝም። አለማወቅ አንዳንዴ ጥሩ ድፍረት ነው። ከኋላ የነበረው ልተኩስ እንደሆነ የገባው ጠባቂ ወከባ እና ሁከት ፈጥሮ ትኩረት ሲቀንስልኝ የሰውየውን ግንባር አገኘሁት እና በፍጥነት ከፊቴ የነበረው እግር ስር ዝቅ ብዬ በክንዴ ጉልበቱን ገጨሁት። ከጀርባ የነበረው የእኔን እርምጃ ተከትሎ በተፈጠረው ግርግር አለቃችንን መሬት ላይ ጥሎት እላዩ ላይ ወድቆ ከደነው። ሁለት ከኛ ወገን (እኔን ጨምሮ) ተመትቶ ቆስሎ አንድ ከእነርሱ ወገን ሞቶ ሁለት ቆስሎ አካባቢው በፖሊስ እና በህዝብ ግርግር ተዋክቦ እነሱ ሬሳቸውን ትተው በመጡበት መኪና አመለጡ። የተመታ ክንዴን ታክሜ ወደስራ ስመለስ ከዛን ቀን በኋላ የሰውየው የጎን ጠባቂ ሆንኩ!!