Get Mystery Box with random crypto!

«አዲስአበባ ከሄድን እዛ አንድ ቀን እንኳን እንድታድር አልፈልግም!! ሳይውል ሳያድር እንድትወጣልኝ | ወግ ብቻ

«አዲስአበባ ከሄድን እዛ አንድ ቀን እንኳን እንድታድር አልፈልግም!! ሳይውል ሳያድር እንድትወጣልኝ ነው የምፈልገው ምን ያደርጉብኝ ይሆን ብዬ ማሰብ አልፈልም!!»

«አውቃለሁ!! ግን አንቺስ?»

«እኔ ምን? እኔ ራሴን መጠበቅ አያቅተኝም!!»

«ሜል ብዙ ነገር ተቀይሯል። ምን ያህል እንዳስተዋልሽው አላውቅም እንጂ አንቺም ራሱ ፍፁም ተቀይረሻል። ወደኋላ ተመልሰሽ ያለፈ ህይወትሽን መኖር የምትችዪ አይመስለኝም! እሱን ነው የምታስቢው? ምንድነው የምታስቢው?» አጠያየቁ የእኔ ኪዳን አይመስልም በጣም ተኮሳትሮ እንደታላቅ ነው የሚያወራው

«አላውቅም! ራሴ እንደተቀየርኩ አውቃለሁ ነገር ግን ያለፈውን ህይወቴን ሙሉ ለሙሉ ተፋትቼ መኖር እችል እንደሆነ አላውቅም! ምክንያቱም እኔ ብቻ እንጂ የተቀየርኩት በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችም ሁኔታዎችም እንዳሉ ናቸው። የቱን ጥዬ የቱን ይዤ እንደምቀጥል አላውቅም!»

«ለምን ከሀገር መውጣትን አታስቢበትም? ሁሌ ጀርባሽን መጠበቅ ሳይኖርብሽ አዲስ ህይወት አዲስ ማንነት ትገነቢያለሽ!»

«እኔእንጃ የኔ ኪዳን!!»

«በጎንጥ ምክንያት ነው? የነገ አብሮነታችሁ ምን ሊሆን እንደሚችል ተነጋግራችኋል?»

«አይደለም! ስለነገም ያወራነው የለም! ስለምንም ያወራነው የለም!»

«ሜልዬ እስኪ ዛሬ እንደ ትንሹ ወንድምሽ ሳይሆን እንደ 31 ዓመት ትልቅ ሰው አውሪኝ! እንደምትዋደዱ ግልፅ ነው!! እኔ ሳውቅሽ ለማንም ሆነሽ የማታውቂውን ነው ለሱ እየሆንሽ ያለሽው! ማንንም ሰው ባላቀረብሽው ልክ ነው እሱን ያቀረብሽው! ወደፊትሽን ስታስቢ እሱ አለበት? ያወራችሁት አይኑር! አንቺ ምንድነው የምታስቢው?»

«እኔ እንጃ ኪዳንዬ የእውነቴን እኮ ነው እኔንጃ የምልህ!! ታውቃለህ እኔ ፍቅር አላውቅም!! ፀብ ቢሉኝ አውቃለሁ፣ በቀል ቢሉኝ አውቃለሁ ……. ፍቅር ግን አዲሴ ነው!! ስምጥ ብዬ ከዋኘሁ በኋላ ነውኮ እንደወደድኩት እንኳን የነቃሁት! ደግሞ እኔ ብቻ የማስበው ምን ይፈይዳል? እኔ ስላሰብኩህ ና ወደፊቴ ውስጥ ላካትህ ይባላል?»

«ጠይቂዋ!»

«ምን ብዬ?»

«ምንድነው ስለወደፊት የምታስበው? አብሮነታችን ምን ድረስ ነው የሚዘልቀው? ብለሽ ነዋ!»

«እህ እሱ አይደል እንዴ ወንዱ! ይሄን መጠየቅ ያለበት እሱ አይደለም? በግድ እየገፋፋሁት ቢመስልብኝስ?» ስለው ከቀናት በፊት ሲስቅ የሰማሁትን ሳቅ ሳቀ።

«አይመስልም ዓለሜ (ልክ ጎንጥ በሚልበት ለዛ) ዘመኑ ተቀይሯል!! ሴት ተንበርክካ አግባኝ የምትልበት ዘመን ላይ ነን!»

« ምንስ ፍቅር ብርቄ ቢሆን ጥንቅር ይላታል እንጂ ተንበርክኬማ አግባኝ አልለውም! ጭራሽ? ለተሸነፍኩትም መደበቅ ቢቻለኝ በዋጥኩት! እንቢ እያለኝ እያመለጠኝ እንጂ!!» ተሳሳቅን!!

በሚቀጥለው ቀን ኦንላይን ትኬቱን ቆርጦ አጎቴን ተሰናብተን (ስንብቱ በእንባ የታጀበ ነበር።) ወደ አዲስ አበባ መጣን!! የዛኑ ቀን በረራው ነበረ። ስንሰነባበት

«ሜል አስብበታለሁ በይኝ ከሀገር መውጣቱን?»

«አስብበታለሁ ሙት!!»

«ለዓለሜ እንደምትዪው <የእህቴን ልብ ብትሰብር ውርድ ከራሴ!! ጦርነት በራስህ ላይ እንዳወጅክ ቁጠረው አንላቀቅም!!> ብሎሃል በይልኝ። የምሬን ነው ንገሪው!»

«ሂድ አሁን አርፈህ!! እነግርልሃለሁ!!»

እሱን ሸኝቼው ስመለስ ህይወቴን ካቆምኩበት መቀጠል እንደማልችል ገባኝ። ቤቴ እንኳን ያለስጋት መሄድ እንደማልችል ሳውቅ መኪናውን መንገድ ዳር አቁሜ ውስጥ እንደተቀመጥኩ ብዙ ቆየሁ። የእውነት ምንድነው አሁን የማደርገው? እንደድሮው ባር ሄጄ ወገበ ቀጫጭን ሴቶች የቆመ ፖል ላይ ሲውረገረጉ ፣ ለፍዳዳ ሰካራሞች ለሀጫቸውን እያዝረከረኩ ብራቸውን ሲረጩ …. .፣ አቅላቸውን የሳቱ ሱሰኞች ሀሺሺን ከሺሻው እያደባለቁ ሲያጨሱ …… እያየሁ እየተዘዋወርኩ ብሉልኝ ፣ ጠጡልኝ ፣ አጭሱልኝ ፣ ተዝናኑልኝ እያልኩ ብሬን መምታት ይቻለኛል?

ከአንድ ሰዓት በላይ ከቆምኩ በኋላ የሆነኛው ገስት ሀውስ ይዤ ለዛሬ እርፍ ብዬ መተኛት ፈለግኩና ከዛ በፊት የጎንጥን ድምፅ መስማት ፈለግኩ። አንዱ ሱቅ ገብቼ ደወልኩ። ስልኩ ዝግ ነው። ገስትሀውስ ገብቼ ለማረፍ ሞከርኩ እና ተገላበጥኩ። ራሴን አሁንም ወጥቼ የሱቅ ስልክ ላይ ስደውል አገኘሁት። ዝግ ነው!! ተመልሼ ገብቼ ለጥ ብዬ አድራለሁ ያልኩትን ለሊት ስገላበጥ አደርኩ። ይሄኛው ስሜት ደስ አይልም!! ስልኩን ባይከፍተው የት ብዬ ነው የማገኘው? የድሮ ሚስቱ ቤት ሄጄ <እየገደልሽኝ ሳለ እግረመንገድሽን ጎኔ የት እንዳለ ብቻ ንገሪኝ> ነው የምላት? ደግሞ ለራሴ <ማታ አይደል ያዋራሁት? ይሄኔ ባትሪ ዘግቶበት ነው!> እላለሁ። ዛሬ እንደምመጣ እያወቀ ስልኩን የዘጋው ሊያገኘኝ ስላልፈለገ ቢሆንስ? ምን እየሆንኩ ነው ስንት ሀሳብ እያለብኝ ስለእርሱ ብቻ የማስበው?  ……. ስወራጭ ቆይቼ ሊነጋ ሲቃረብ እንቅልፍ ወሰደኝ!!

እንደነቃሁ ተጣጥቤ ስልኩን ሞከርኩ። አሁንም ዝግ ነው። ወደሰፈሬ ነዳሁ እና ተናኜን ቅያሪ ልብሶች ተቀብያት ጎንጥ ብቅ ብሎ እንደው ስጠይቃት አለመምጣቱን ነገረችኝ። ልብሴን እዛው መኪና ውስጥ ቀይሬ ሻለቃው ቢሮ ሄድኩ። የሰዎቹን ፎቶ ከተገበያየሁ በኋላ እንደማላውቃቸው ሳውቅ መረጃ የሚያቀብለኝ ሰው ጋር ደወልኩ።

«ኢሜል የማደርግልህን ፎቶ ተመልከተውና መረጃ አቀብለኝ» ካልኩት በኋላ የሁለቱን ሰዎች ፎቶ እየላኩለት ልክ እንዳልሆነ የማውቀው ሀሳብ ጭንቅላቴን ወጠረኝ። ላለማድረግ ከራሴ ጋር ታገልኩ። ግን አቃተኝ!! ከስልኬ ውስጥ ጎንጥን ስቀጥረው ይዤው የነበረውን ፎቶ አብሬ ላኩለት። መልሶ ደወለልኝ እና

«ይሄን ሰውዬኮ ከዚህ በፊት ጠይቀሽኝ ነበር።»

«አውቃለሁ!! ተጨማሪ መረጃ ፈልግ!! በጓሮ ሂድ!» አልኩት (ሰውየው በግልፅ ከተመዘገበው መረጃ በላይ የተደበቀ መረጃ አለው ለማለት ነው በጓሮ ሂድ የምንባባለው)

ስልኩን ዘግቼው ኮምፒውተር ቤቱ ውስጥ ፍዝዝ ብዬ ቀረሁ!!!

   ………… አልጨረስንም …………..

@wegoch
@wegoch
@paappii