Get Mystery Box with random crypto!

ወግ ብቻ

የቴሌግራም ቻናል አርማ wegoch — ወግ ብቻ
የቴሌግራም ቻናል አርማ wegoch — ወግ ብቻ
የሰርጥ አድራሻ: @wegoch
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 21.12K
የሰርጥ መግለጫ

✔በየቀኑ ምርጥ ምርጥ የጥበብ ስራዎችን ለማግኘት የቻነላችን ተከታይ ስለሆኑ እናመሰግናለን።
✔ @getem @serenity13
✔ @wegoch @Words19
✔ @seiloch
✔ @zefenbicha
Creator @lula_al_greeko

Ratings & Reviews

4.33

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

2

4 stars

0

3 stars

1

2 stars

0

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 8

2022-11-18 17:54:52 #የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ ስድስት)
(ሜሪ ፈለቀ)

የእማዬ ቀብር ላይ የአባቴ ገዳዮች ዘመድ አዝማድ እና ልጆች ሁሉ ሊቀብሯት ሲያጅቧት ፤ አንዳንዱም ሲያለቅሱላት እያየሁ የተሳከረ ስሜት ወረረኝ። የዛን እለት ከአቶ አያልነህ ጋር የነበሩት ሰውም አረፋፍደው ተቀላቀሉ። የኛም ወገን የእነሱም ወገን የተፈጠረውን እልቂት ይቅር ተባብለው ተሻግረውት እኔ ብቻ ነበርኩ በጥላቻ የሰከርኩት? አይደለም! እዚህ ያሉት ናቸው በይቅርታ የተሻገሩት!! ጥላቻ እና ቂማችንን ይዘን ከተማ የገባን እኔና መሰሎቼ በየሶሻል ሚዲያው በቃላት ተዋግተናል፣ ካለመንደራችን በተገናኘንበት ተጠማምደን ተጠላልፈናል፣ የደማችንን ምንጭ ተጠያይቀን ለአባቶቻችንን ፀብ እኛ ተሰነካክለናለን ተጫርሰናል፣ እኛ እንደአባቶቻችን በጥይት ተጫርሰን ባናሳያቸውም ለወለድናቸው ልጆቻችንን እና ታናናሾቻችን ጥላቻችንን አጋብተናል። እነርሱ ግን እረስተውትም እንኳን ባይሆን አልፈውት የአንዳቸውን ለቅሶ ይላቀሳሉ። እኔ ግን ከወራት በፊት እንኳን የእነእርሱን የልጅ ልጅ እንኳን ባገኝ በማያውቀው የአያቱ በደል  ጥላቻዬ ውስጤ ይፈላ ነበር።

ከቀብር መልስ ሰው እየተሰናበተን ሲወጣ አቶ አያልነህ ከሚስታቸው ጋር ተሰናብተው ሊወጡ ሲሉ እጄን ያዝ አድርገው።

«እግዜሃር ያፅናሽ!» ሲሉኝ እጃቸውን በደንብ ጨብጬ ይዤ

«ዛሬ ነው የፈቱኝ!! እስከዛሬ የእርሶ እስረኛ ነበርኩ።» ስላቸው ቁጥብ ያለ ፈገግታ ፈገግ ብለው

«እኔ ይቅር ብያለሁ እርሱ ጨርሶ ይቅር ይበልሽ!! በርቱ!!» ብለውኝ ወጡ!!

በኋላ ላይም ወዳጃቸው የተቀመጡበት ሄጄ እጃቸውን ያዝ አድርጌ (በአካል ስላላገኘኋቸው ሁሌ ይከነክነኝ ነበር) «የማይገባኝን ይቅርታ ስለሰጡኝ አመሰግናለሁ!!» አልኳቸው። እሳቸው ከአቶ አያልነህ በላይ በተፈታ መንፈስ

«እግዜር ያፅናሽ ልጄ!! እቤቴ በተውሽው መልዕክት የልጆቼን ህይወት ነው የቀየርሽው!! ልብሽ ቀና ነው የእኔ ልጅ ቂምና ጥላቻ ለማንም አይበጅ! ለአባትሽም ለእኛም አልሆነን!! ልብሽን ከክፉ ጠብቂው!» ብለው ጭራሽ እኔኑ አበረቱኝ።

የቀብር ቀን ማታ ፍራሽ ላይ ተቀምጠን ሊያማሽ የመጣውን ለቀስተኛ እየተቀበልን ስንሸኝ በሚገባ እና በሚወጣው ሰው መሃል ጎንጥ በሞላ ሞገሱ ጎንበስ ብሎ ድንኳኑን ሲዘልቅ ሳየው የእማዬን መሞት አሁን የተረዳሁ ይመስል ድንኳኑን በለቅሶ ደበላለቅኩት። እስከአሁን ሲገባ ሲወጣ ከነበረው ሰው የበለጠ ፣ እስከአሁን ሊያፅናናኝ ከሞከረው ህዝብ በበለጠ ፣ እንደነፍሴ ከምወደው ኪዳኔ እንኳን የበለጠ ፣ ከአጎቴም የበለጠ ……. እሱ ብቻ የበለጠ ህመሜ የሚገባው ዓይነት ነው የመሰለኝ። ድንኳኑ እንደአዲስ በለቅሶ ተናጠ። ሌላ ሰው መኖሩን ረሳሁ!! ዘልዬ እቅፉ ውስጥ ገባሁ!! አላባበለኝም አብሮኝ አለቀሰ። ሽማግሌዎች <ከመሸ እንዲህ አይለቀስም> ብለው ሊያረጋጉ ሲሞክሩ አጎቴ ከውጭ ብቅ ሲል ጎንጥን ሲያየው ከእኔ ብሶ አረፈው። ልክ የሆነ ታናሽ ወንድሙን ያገኘ ወይ ታላቅ ልጁን አልያም የብዙ ጊዜ ወዳጁን ያገኘ ይመስል

«አመለጠችኝኮ! አትከብጅኝም ትንሽ ቆይ እያልኳት አሻፈረኝ ብላ ሄደች! እንብኝ አለች! ናፍቆቴ አልወጣልኝም እያልኳት ተሸነፍኩ አለች!» እያለ ሲያለቅስ ድንኳኑ ተተራመሰ። ጭራሽ ሁለቱ ተቃቅፈው ሲላቀሱ የተወሰኑ ቀናት አብረው ያሳለፉ ሳይሆን ሳይነጋገሩ የሚግባቡ ቤተሰቦች ነው የሚመስሉት። እኔስ ስለወደድኩት ወይ ይወደኛል ብዬ ስላሰብኩ ለልቤ አቅርቤው መሰለኝ ሳየው ሀዘኔ የፈነቀለኝ። አጎቴስ? ምናልባት እኔ ያልሰማኋቸውን ቅፅበት የልብ የልባቸውን አውግተውበት ተናበው ይሆን? ወይስ ለልብ ለመቅረብ የተለየ ነፍስ ያለው ሰው አለ?

ለቅሶው ሲበርድ አጠገቤ መጥቶ ፍራሽ ላይ ተቀመጠ። ለቀስተኛው ማን ስለመሆኑ ግራ እየተጋባ ሲጠያየቅ አጎቴ «ቤተሰብ ነው!» እያለ ይመልሳል። አንድ ዘመዳችን

«የአባትሽ ቤተሰብ ነው? የእነርሱ ደም ይመስላል!» ስትለኝ በደንብ አስተዋልኩት። በጭንቅላቴ ውስጥ ሊጠፋ የደበዘዘ የአባቴን መልክ ለማነፃፀር እየታገልኩ ….. ቁመቱ ፣ ትከሻው ፣ ግርማ ሞገሱ ፣ ጥይምናው ፣ ጅንንነቱ …… ከአባቴ ጋር ይመሳሰላል። ለአፍታ <የተሸነፍኩት ሳላውቀው አባቴን እሱ ውስጥ ስላገኘሁ ይሆን?> ብዬ አሰብኩ። ሳይታወቀኝ አፍጥጬ እያየሁት ስለነበር

«ምን አስፈልጎሽ ነው?» አለኝ

«ምንም! ስለመጣህ ደስ ብሎኛል።» አልኩት

«እንዴት ይቀራል ብለሽ አሰብሽ?» ብሎ ወደትከሻው አጥብቆ ከያዘኝ በኋላ የህመም ትንፋሽ ተነፈሰ። ከሆስፒታል የሚወጣበት ቀን ቀናት እንደሚቀሩት እያወቅኩ እሱን አለማሰቤ አሳፈረኝ። እሱ አጠገቤ መሆኑን እንጂ የእርሱን ቁስል አላሰብኩለትም።

«ውይ! ይቅርታ!» ብዬ ከትከሻው ቀና ስል መልሶ ከቅድሙ በላላ ሁኔታ ትከሻው ላይ አስደግፎኝ
«ደህና ነኝ!!» አለኝ

«ሆስፒታል መቆየት ነበረብሃ?»

«አንድ ሁለት ተጨማሪ ቀን ነበረብኝ! የእኔ ሀሳብ አይግባሽ!! ደህና ነኝ አልኩሽ እኮ ዓለሜ? አንች መድሃኒቴ አይደለሽ? ሆስፒታል ምናባቱ?» ብሎ ከደቂቃዎች በፊት ስንሰቀሰቅ የነበርኩትን ሴት ያሽኮረምመኛል? እያየኝ ያለ ሰው መኖሩን ለማረጋገጥ አይኔን የተቀመጠው ለቀስተኛ ላይ አንቀዋለልኩ።

እናቴ የሞተችብኝ እኔ ከዛ ደግሞ የተሽኮረመምኩትም እኔ …… ለሰው የሀዘኔን ጥልቀት አሳይቼ መሽኮርመሜን መደበቅ ያለብኝም እኔው!! ምክንያቱም ምንም እንኳን ሊያፅናኑ ቢመጡም ስፅናና እንደሚዳኙኝ አውቃለሁ። <የእናቷ ለቅሶ ላይ ተሽኮረመመች፣ የእናቷ ለቅሶ ላይ ስታስካካ ነበር ፣ ምን እሷ ምንም አልመሰላት ኸረ አላያችኋትም እንዴ እናቷን መቅበሯን ረስታ ከወንድ ጋር ስትለፋደድ?> እንደሚሉኝ አውቃለሁ። ግራ የሚገባኝ ሊያፅናኑኝ የሚሞክሩት የውሸት ነው ማለት ነው? ሀዘን ማብዛት ጥሩ አይደለም የሚሉት ስለሚባል ነው ማለት ነው? ስፅናና ወይ ስስቅ ታዲያ ለምን ይከፋቸዋል? <በደንብ አላለቀሰችም!> ሁሉ እንደሚባል አውቃለሁ!!

ስለዚህ ተሰብስቤ ተቀመጥኩ። እኔ ትቼው የምሄደው ህዝብ እና መንደር ቢሆንም ለአጎቴ ወሬ ትቼለት መሄድ አልፈለግኩም!! በሁለተኛው ቀን ጎንጥ የምጨራርሰው ጉዳይ አለኝ ብሎ ወደከተማ ተመለሰ።

ከእማዬ ቀብር በኋላ ቤቱ ውስጥ የሚተራመሰው ዘመድ አዝማድ እና ጎረቤት እየተመናመነ ሄዶ ድንኳኑ ከተነሳ በኋላም ኪዳን መሄድ የፈለገ አይመስልም። «ትንሽ ቀን እንቆይ!» ሲል ብዙ ቆየን። ሁሉም ወደቤቱ ገብቶ ሶስታችን ብቻ የቀረን ቀን ማታ ሀዘናችን በረታ እና እንደአዲስ መላቀስ ያዝን። ኪዳን ከሁለታችን ብሶ «ምናለ ትንሽ ቀን ብትሰጣት? ፣ ምናለ ትንሽ ቀን ብጠግባት? ፣» እያለ ከአምላኩ ጋር ሲሟገት አንጀቴ ልውስ ብሎብኝ ተንሰፈሰፍኩ። አጎቴ እንደልማዱ «እህቴ ፤ ክፋዬ ፣ አንድ ደሜ …. » እያለ እንዳልተነፋረቀ እንባውን በፎጣው አደራርቆ

«ተው ደግም አይደል። የፈጣሪን አይን አትውጉ! ሳናያት ሳናውቅ አልፋስ ቢሆን? የልጆቿን ዓይን ዓይታ ፤ ጠረናችሁን ስባ በትውልድ ቀዬዋ ሀገሬው ቤቱን ነቅሎ ወጥቶ በፍቅር የሸኛት እሰቡት አምላክ እንዴት ቸር እንደሆነ? ደግም አይደል?» ብሎ ተቆጥቶ አረጋጋን!! እንባችንን አቆምን እንጂ ለሚቀጥሉት ቀናት እንደተኳረፈ ሰው በመሃከላችን ብዙም የቃላት ልውውጥ አልነበረም። የሆነ ቀን ውጪ ሳሩ ላይ ተቀምጠን

«የኔ ኪዳን? አሁንም ከዚህ በላይ መቆየት ትፈልጋለህ?» አልኩት

«እኔ እንጃ ሜል! ወደ አዲስአበባ መመለስ ከፈለግሽ እንመለስ! እኔ አሁን ምን እንደምፈልግ ራሱ አላውቅም!!» አለኝ።
1.1K viewsDAVE / PAPI, 14:54
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-17 12:23:23 አዲስ አበባ ከገባሁ ከአመታት በኋላ ባለገንዘብ የሆንኩ ጊዜ ወደእሳቸው መንደር ላገኛቸው ተመልሼ ነበር። አፈላልጌ በጥቆማ እቤታቸውን ፈልጌ ሳገኝ እኔ አወቅኳቸው። ከዘራ ይዘው እያነከሱ ከበራቸው ወደቤት እየገቡ። እሳቸው ግን አላወቁኝም ነበር። ከአመታት በፊት ካየኋቸው አርጅተው። ተጎሳቁለው ነበር። ሰላም ካልኳቸው በኋላ ከከተማ መምጣቴን ስነግራቸው ወደቤታቸው ጋበዙኝ።

«ያስታውሱኝ ይሆን?» አልኳቸው

«ዓይኔ እያስቸገረኝ ነው ልጄ አላስታወስኩሽም! የማን ልጅ ነሽ?»

«ማን እንደሆንኩ እነግሮታለሁ! መጀመሪያ ግን ማንነቴን ስነግርዎት የምለውን ሰምተው እንደሚያስጨርሱኝ ቃል ይግቡልኝ!!»

«ልጄ እያስጨነቅሽኝኮ ነው!!»

«ቃል ይግቡልኝ!! የምለውን ሁሉ ይሰሙኛል?»

«እሽ ቃሌ ነው!!»

«ከብዙ ዓመት በፊት ከገበያ ሲመለሱ አንዲት ሴት እንደዘረፈችዎት አይጠፋዎትም መቼስ!»

«እንዴት ይጠፋኛል! ቤቴን እኮ ነው ያፈረሰችው! » ብለው በደንብ አዩኝና « አምሳል ነኝ እንዳትይኝና እዚህ ደም እንዳንፋሰስ!!»

«እስከመጨረሻው እሰማሻለሁ ብለው ቃል ገብተውልኝ የለ?»

«በይ ልስማዋ!!»

እግራቸው ላይ ወደቅኩ!! «ከዛን ቀን በኋላ ሳላስቦት የዋልኩ ያደርኩበት ቀን የለም! አንዲት ቀን እንኳን ፀፀት ሳይፈጀኝ አልፎ አያውቅም!! ይቅር አይበሉኝ! ግን ከዚህ በላይ አይቅጡኝ!! የምሰጦትን ገንዘብ ይቀበሉኝ!» አልኳቸው

ተነስተው በፍፁም አሉ!! ሚስታቸው ከጓዳ ትሰማ ነበር እና

«ደግም አይደል አያል! ይህች ልጅ ተጠጥታ መጣችም አይደል? እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል አቤቱ በደላችንን ይቅር በል ብለንም አይደል የምንጠልይ? ተነሽ ይበሏት በቃ!» አሉ። ከስንት ልምምጥ በኋላ እንዳኩረፉ ያመጣሁላቸውን ገንዘብ ተቀበሉኝ። አብረዋቸው ከነበሩት ሰዎች አንደኛው ማረፋቸውን ነገሩኝ! ሌላኛውን እቤታቸው ሄጄ ስላላገኘኋቸው መልዕክቴን ከገንዘቡ ጋር አስቀምጬ ተመልሼ ለአቶ አያልነህ ይቅርታዬን እንዲነግሩልኝ ለምኜ ልወጣ ስል እንዲህ አሉኝ

«ጨርሶ ይቅር ያልኩሽ እንዳይመስልሽ!! ድህነት አይኑ ይጥፋ ዛሬም ለልጆቼ ፍራንካው ስለሚያስፈልግ እንጂ ለራሴ ቢሆን እመቤቴ ምስክሬ ናት ፍንክች አላደርገውም!!» ብለውኝ ነበር። ከዓመታት በኋላ ለቅሶዬን ሊደርሱኝ የመጡት በልባቸው ይቅር የሚሉበት ፍቅር አጊንተው ቢሆን አይደል? ይቅር መባል እንዲህ ደስ እንደሚል ባውቅ ስንት ይቅርታ የምጠይቀው ነበረኝ!!


                            ........ አልጨረስንም ......,

@wegoch
@wegoch
@paappii
1.3K viewsDAVE / PAPI, 09:23
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-17 12:23:23 #የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ አምስት)
(ሜሪ ፈለቀ)

ብዙ ነገር አጥቼ እንደነበር የተሰማኝ አሁን ላይ ነው። የእማዬን አልጋ ከበን ቡና ተፈልቶ ቆሎ እየቆረጠምን አንዱን ወሬ ስናነሳ አንዱን ስንጥል በብዙ ሳቅ እና ደግሞ በደስታ ለቅሶ የታጀበ ቀን እየዋልን ያለፉ አመታቴን አስቤ ብዙ እንደጎደለኝ ገባኝ።

ደግሞ በዚህ ሁሉ የቤተሰብ ፍቅር ታቅፌ ልቤ ክንፍ አውጥታ ጎንጥ ጋር ስትሄድ፣ የያዘኝን አያያዝ ፣ የሳመኝን መሳም ፣ የጠራኝን መጥራት አሰብ አድርጌ ብቻዬን ፈገግ ስል ባለፉት ዓመታቶቼ ብዙ እንዳለፈኝ ገባኝ። ብዙ እንዳልኖርኩ ገባኝ!!

«እትዬ ዛሬ ሌላ ሰው ሆነው በንፁህ ልብ ስለተቀበሉት ነው የሚያጎብጥ ሸክም የሆነብዎት። ቂም ባቄመና በጠለሸ ልብ ሆነው ሲቀበሉት እንዲህ አልተሰማዎት ይሆናል።» ነበር ያለው ጎንጥ እንዴት ይሄን ሁሉ ጥላቻ ተሸክሜ ኖርኩ ስለው?
በንፁህ ልብ አይደለም። በፍቅር ልብ ሳየው ነው ዓለምን እና ዙሪያዬን የማይበት መነፅር የተቀየረው። በፍቅር ዓይን!!  ሁሉ እንዳለኝ የተሰማኝ፣ መኖር ደስ የሚል ነገር መሆኑን ማሰብ የጀመርኩት በፍቅር ልቤ ማየት ስጀምር ነው።

እናቴን አቀፍኳት፣ ኪዳንዬ አለኝ፣ አጎቴን አለኝ፣ ጎንጥ ይኑረኝ አይኑረኝ ባላውቅም አዎ በልቤ ውስጥ ግን ከነጥጋቡ አለኝ!! ምን እጠይቃለሁ ሌላ? አጎቴ እናታችን ስለደከመች ካጠገቧ ባንርቅ መልካም መሆኑን ስለነገረን በአካሌ ላለመሄድ ወሰንኩ። ግን ልትሞት ቀናት የቀራት እናቴን አቅፌ ልቤ አዲስአበባ መሸምጠጡ ራስወዳድነት ነው? እንደዛ እየተሰማኝኮ ራሴን እገስፃለሁ። ልቤ አልሰማኝ አለኝ እንጂ!!


የገባን ቀን ማታ ምናልባት ለጥንቃቄ በሚል። በኪዳን ስልክ ዋትሳፕ መልዕክት ላኩለት። ሁለት መስመር ለመፃፍ ከ20 ደቂቃ በላይ ፈጀብኝ። ለኪዳን ካልሆነ በቀር ፅፌ የማውቀው ማስፈራሪያ ወይ ቢዝነስ ነክ ነገር አልያም የሆነ መልእክት እንጂ ፍቅር ነክ ነገር እንዴት እንደሚፃፍ አላውቅም። ምን ተብሎ ነው የሚጀመረውስ? ሀይ ጎንጥ? ስሙ ደግሞ ሲጠራ ምንም የፍቅር ቅላፄ የለውም!! እንዴት ዋልክ ዓለሜ? ልበለው? አይሆንም እሱ ሲል ነው እንደሱ የሚያምርበት! ሀኒ ልበለው? ሆ ጎንጥን ሀኒ? ራሴኑ አሳቀኝ!! ያቺ የድሮ ሚስቱ እንደጠራችው ጎኔ ልበለው? ኡፍፍፍ

«ሰላም ዋልክ? እኔ ነኝ!! በጠዋት ላይህ ሳልችል ቀርቼ እማዬጋ መጥቻለሁ!! ደህና አድረህ ዋልክ?» በቃ መፃፍ የቻልኩት ይሄን ብቻ ነው። ምን አይነቷ ነፈዝ ነኝ በፈጣሪ!! ከዛማ ስልኩን አቅፌ የፃፍኩለት መልዕክት ሰማያዊ የራይት ምልክት እስኪያሳየኝ ስልኩ ላይ አፍጥጬ ቀረሁ።

«ዓለሜ ናፈቀሽ እንዴ?» ይለኛል ኪዳን ሲያበሽቀኝ

«ለምን ግን አታርፍም?» እላለሁ

«ጎንጤን ነው?» ይላል አጎቴ

«እንዴ? እኔ ብቻ ነኝ የማላውቀው ማለት ነው? አንደኛውን ሽማግሌ ልኳል አትይኝም እንዴ?»

«እዚህ ከርሞ አይደል እንዴ የሄደው? ዓይነውሃው ያስታውቃልኮ ፍቅር እንዳለበት! መች አይኑን ከርሷ ላይ አንስቶ! <ጎንጤ እርሻ ወረድ ብለን እንምጣ ?> ብለው <አይ ጋሼ ከርሷ ባልርቅ ነው የሚሻል። ደህና መሆኗን ማየት አለብኝ> ይለኛል። <እንደው ታች ሰፈር ደረስ ብለን ብንመጣስ?> ብለው <ይቅርታ ጋሼ ዛሬ ልክም አይደለች ርቄ አልሄድ> ይለኛል። ኋላማ <እኔ የምለው ጎንጤ? ትከጅላታለህ እንዴ?> እለዋለሁ ቆጣ ብሎ <ምን ማለቶት ነው!> አለኛ» እናቴን ጨምሮ ሁሉም ይስቃሉ። እንደኮረዳ እሽኮረመማለሁ።

ስልኩ መልዕክት መቀበሉን የሚገልፅ ድምፅ ሲያሰማ ከመቀመጫዬ እንደመዝለል ሁሉ ሲያደርገኝ ቡና የምታፈላው ትንሽዬ ዘመዳችን ሳትቀር በአንድ ላይ አውካኩብኝ። የትልቅ ሰው ያልሆነ ማፈር አፍሬ መልዕክቱን ለማየት ሁሉ ስግደረደር ቆየሁ።

<እኔ ደግ ነኝ! የሚቻልሽ ከሆነ ድምፅሽን ታሰሚኛለሽ?> ነው የሚለው መልዕክቱ! አሁን ይሄ እሺ ምኑ ነው የሚያስቦርቀው? በፍቅርሽ ሞቻለሁ የተባለች ኮረዳ እንኳን እኔ የምሆነውን መሆን አትሆንምኮ! ትቻቸው ወደበር ወጣሁ እና ደወልኩለት። ቶሎ አውርተሽ መጨረስ አለብሽ የተባልኩ ይመስል የተፈጠረውን ለምን ሳላየው እንደመጣሁ እማዬ ስለደከመች ወደከተማ እንደማልመለስ በጥድፊያ ትንፋሽ እስኪያጥረኝ አውርቼ ሳበቃ ሳቅ ብሎ

«ለመዝጋት ተቻኮልሽ እንዴ?» አለኝ
«አይ!» እያልኩ በቆምኩበት በጫማዬ መሬቱን እየቆፈርኩ መሆኑን አየሁ

«ደግ! ያሻሽን ያህል ጊዜ ቆይ!! » አለኝ

«አንተስ?»

«እኔ ምን እሆናለሁ?» አለኝ እኔ ማወቅ የፈለግኩት ከዛስ የሚለውን….. እኔ ያሻኝን ያህል ጊዜ እዚህ ስቆይ እሱስ? ከሆስፒታል ሲወጣ ቤት ሄዶ ይጠብቀኛል? ወይስ ያለሁበት ይመጣልኛል? ወይስ እኔ ወደማላውቀው ቤቱ ይሄድብኛል?

ያናደደኝን ወይ የተጣላኝን ሰው በጉልበት እንዴት እንደማግተው አውቅ ነበርኮ! የወደድኩትን ሰው እንዴት አባቴ አድርጌ ነው የራሴ የማደርገው? እሱን አልችልበትም!! በጉልበት ባገቱት ሰው ላይ ሙሉ ስልጣን ማራመድ ይቻላል። በፍቅር የወደቁለትን ሰው ራሱ ፈቅዶ ወደእኔ ካልቀረበ ምንድነው የማደርገው? ዝም አልኩ!!

«ዝም አልሽኝ እኮ ዓለሜ?» አለኝ ጠብቆ

«ምን እንደምል አላውቅበትም!! ያለፍከውን አላውቅም! ወደፊት ምን እንደምታስብ አላውቅም! ነገ ምን እንደምንሆን አላውቅም! አሁንም ምን እንደሆንን አላውቅም!! አላውቅህምኮ ጭራሽ! እኔ ግን እዚህ ልትሞት ያለች እናቴን አቅፌ ካንተ ሌላ ሀሳብ የለኝም!! ይሄ እንዴት ያለ መሸነፍ ነው ቆይ?» አልኩት።

«የት እሄድብሻለሁ? አለሁ አደል? ሁሉን ትደርሽበት የለ? አንች ብቻ የተሸነፍሽ አታድርጊው እንጅ!!» ብሎ ግማሽ መልስ ምን ግማሽ እሩብ መልስ ይመልስልኛል።

«እንዲህ እንድትለኝ አይደለም የምፈልገው!» ስለው እየሳቀ

«እንዴት እንድልሽ ነው የምትፈልጊ? ቁጣው የምንድነው ታዲያ?» ሲለኝ ነው እየተቆጣሁ እንደሆነ ያስተዋልኩት

«እንደምትወደኝ ነው ማወቅ የምፈልገው!! እንዳልነሳ ሆኜ በፍቅርህ ከመውደቄ በፊት እየተሰማኝ ያለው ስሜት የእኔ ብቻ እንዳልሆነ ነው ማወቅ የምፈልገው! አይሆኑ አሸናነፍ ከመሸነፌ በፊት እንደማላጣህ እርግጠኛ መሆን ነው የምፈልገው? እ?» ስለው መሳቁን ሳያቆም

«ፍቅርሽም ቁጣ ነው? እንደምወድሽማ ታውቂያለሽ! መስማቱን ከሆነ የፈለግሽ እወድሻለሁኮ ዓለሜ!! ነገ ምን እንደሚሆን ከፈጣሪ ጋር እናበጀዋለን!! ዛሬን ልውደድሽ ዓለሜ ዛሬን ውደጂኝ!!»

እንኳን ፊት ሰጥቶኝ ዘጭ ለማለት እየተንደረደረ የነበረ ልቤ ዝርፍጥ ብሎ በፍቅር ነሆለለ። ከዛን ቀን በኋላ በየቀኑ ተደዋወልን!! በየቀኑ እንደሚወደኝ ነገረኝ። በየቀኑ ደጋግሜ ተሸነፍኩ። በየቀኑ ከእማዬጋ ሳቅን። በየቀኑ ድሮ ያጣነውን እቅፏን ናፍቆት መሬት ላይ አንጥፈን ለሶስት እቅፏ ውስጥ አደርን። በየቀኑ ደስ አላት!! በአስራ ሶስተኛው  ቀን ጠዋት እኔና ኪዳን በቀኝና በግራዋ ሙቀቷን እየሞቅን እማዬ ዝም አለች።

እማዬን ስላጣኋት ከፋኝ። አግኝቻት ስለሞተች ደግሞ አመሰገንኩ። ኪዳንም ተመሳሳይ ስሜት ነበር የተሰማው ግን ከእኔ በላይ የእርሱ ሃዘን በረታ!! ምናልባት እኔ ለእርሱ ለመሆን ስታትር ዘመኔን ስለኖርኩ አጎደልኩበት ብዬ እንዳላስብ ዝም ብሎኝ እንጂ ሁሌም የእናቱ ናፍቆት ያንገበግበው ነበር ይሆናል። በኖረችልኝ ብሎ ሲመኝ ይሆናል የኖረው። እኔና አጎቴ ከእርሱ በርትተን እሱን ማበርታት ጀመርን።

የቀብሯ ቀን ሬሳዋ ከቤት ሲወጣ አይኖቼን ደጋግሜ አሸሁ ያየሁትን ሰው ለማጣራት። አቶ አያልነህ! ፈገግ አልኩ! ይቅር ብለውኛል ማለት ነው።
1.3K viewsDAVE / PAPI, 09:23
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-16 12:24:05 «አቤት አንተ መድሃንያለም ምን ይሳንሃል!! አስካል ልጅሽ መጣልሽ!» እያላት ወደ ውስጥ ገባ!! እማዬ ለመነሳት በዛለ ጉልበቷ ተፍጨረጨረች። ከሁለት ቀን በፊት ካየኋት በላይ ገርጥታለች። ይብሱን የከሳችም መሰለኝ። ዝም እንዳባባሉ ፣ እንደማታው አጠያየቁ  ከኪዳን ጋር ሲተያዩ አሁን የሚሆኑትን የሚሆኑ አይመስልም ነበር። ጉልበቷን አቅፎ ተንሰቀሰቀ። ፀጉሩን እየደባበሰች ተንፈቀፈቀች።  እኔና አጎቴ የሁለቱን መሆን እያየን ስንነፋረቅ ቆይተን! አጎቴ ፊቱ ላይ የተዝረከረከ እንባውን ጠራርጎ ሲያበቃ ደግሞ እንዳላለቀሰ ሰው ኮስተር ብሎ

«አይ ደግም አይደል የምን ለቅሶ ነው?» አላለም?

       .......... አልጨረስንም!! ..............

@wegoch
@wegoch
@paappii
1.9K viewsDAVE / PAPI, 09:24
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-16 12:24:04 ጣቶቼን …… ከመጀመሪያው በኋላ እንኳን ቁጥሩን ላውቀው እንደባለፈው ራሴንም አለመዘንጋቴ በቸርነቱ ነው። ከዛ ነገና ዛሬዬን ከደባለቀብኝ በኋላማ ምንም እንዳልሆነ ነገር እጄን መለሰልኝ። ማድረግ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበር። ግን ለመሄድ ተነሳሁ እና ወደበሩ መንገድ ጀመርኩ። ልቤማ ደረቴ ውስጥ የለችም! እንጂ ሰውነቴ እንዲህ ወደኋላ ባልጎተተኝ። በሩጋ ደርሼ ዘወር አልኩና

«ነገ እኮ እማዬጋ ልሄድ እችል ይሆናል።» አልኩት ለምን እንዳልኩት ሁሉ እኔ እንጃ! ምናልባት አንድ ደቂቃ እሱጋ መቆያ ምክንያት እየፈለግኩ መሰለኝ።

«ደግ!!» ብቻ ነው ያለው!! እንዴ? ምንድነው ሰው ማግዶ እሪሪሪ እስኪሉ መጠበቅ? ኮስተር እንዳልኩ ለራሴ እየታወቀኝ በሩን ይዤ ቆምኩ!

«ምነው ዓለሜ? የምትነግሪኝ አለሽ እንዴ?» ሲል ከንፈሬ ሳላዘው ሸሽቶ ያለኝ ጥርስ ሁሉ ንፋስ ዳበሰው

«ምንም የለም! ደህና እደር በቃ!» ብዬው ወጣሁ። መኪናው ጋር እስክንደርስ ከኪዳን ጋር ምንም ቃል አልተለዋወጥንም! መጣሁ መጣሁ እያለ እየተናነቀው እንደሆነ ያስታውቅበታል።

«ትከሻሽን መገላመጡን አትርሽ ዓለሜ!» አለ መጨረሻ ላይ ከት ብሎ እየሳቀ

«አፍህን ዝጋ እሺ!! አንድ ነገር እንዳትለኝ!» አልኩት ሳቅም ማፈርም በደባለቀው ቁጣ

«ጀግና ነው ግን ሜል ሙች!! ይፈርምልኝ! ጠባቂ ሆኖ ገብቶ ጠብ ያድርግልኝ? ሜል ገና ስታይው ፍስስ እኮ ነው ያልሽው!»

«ኪዳን ተወኝ አልኩ እኮ!»

«አንዴማ ጨብጬው ልምጣ ሜል ሙች» ብሎ ወደኋላው እንደመመለስ አለ

«ባክህ አርፈህ መኪና ውስጥ ግባ አትጨማለቅ!!»

የማውቀው ገስትሀውስ ደውዬ አልጋ ያዝኩ። መንገዱን ሁሉ ሲያበሽቀኝ እና ሲገረም ዘለቅነው «ምን አባቱ አድርጎሽ ነው ግን ስንቱን ወንድ ያሸና ልብሽን ዘጭ ያደረገው? ፣ እኔንኮ እዛ እንደሌለሁ ረሳችሁኝ ሆ! ፣ እድሜ ደጉ ሜል ስትሽኮረመም ያሳየኝ? ፣ ፍቅር በሀገርኛ ግን ጆሮ ላይ ደስ ይላል አንቺ? ነፍሴን አወክሻትኮ ዓለሜ! ነው ያለው? > አያቆምም ይለፈልፋል። በመሃል

«ሜል ሻምበሉጋ ከአንድ ሰዓት በኋላ እደውላለሁ ካልሽው ሁለት ሰዓት አለፈ!» ሲለኝ ሰዓቴን አየሁት። መርሳቴ እኔንም ኪዳንንም ገረመን!! አንድ ሰው እንዲህ የሰውን ሀሳብ መቆጣጠር ይችላል?

«እኩለለሊት ሊሆን ነው!! ጠዋት ብደውል ይሻላል!!» ስለው ኪዳን አይኑን ጎልጎሎ አውጥቶ አፈጠጠብኝ

«you know am happy for you!! ሜል ነገር አሳደረች? ያውም ሊገድላት የሚከረ ሰው ? ፍቅር ግን ደስ ሲል!!»

«ለምንድነው ግን አፍህን የማትዘጋው?»

ለሁለት ደቂቃ ዝም ይልና ደግሞ ይጀምረኛል። ማረፊያችን ደርሰን የምናወራው ቁምነገር መኖሩን ተኮሳትሬ እስክነግረው ማብሸቁን አላቆመም!!

«አሁን የምር አስጨነቅሽኝ! ምንድነው ንገሪኝ!!» አለኝ አጠገቤ አልጋው ላይ እየተቀመጠ አንድ እጁን እንደማቀፍ ትከሻዬ ላይ ጣል እያደረገ

«እማዬ አልሞተችም! በህይወት አለች!! እና ልታይህ ትፈልጋለች!»

«ማለት?» ብሎ እጁን ከትከሻዬ ላይ አነሳው

«በሰዓቱ ላንተ እውነቱን መንገር ከምትሸከመው በላይ ስለሚሆንብህ ነው ከአጎቴ ጋር ተነጋግረን እንደሞተች የነገርንህ! ታዲያ የታለች ብትለን ኖሮ መልስ አልነበረንም!»

«እና የት ነበረች?» ብሎ ስፈራው እና ስሸሸው የኖርኩትን ጥያቄ ጠየቀኝ። እንዴት ብዬ እንደምነግረው ስጨነቅ

«ሜል ያኔ ህፃን ስለነበርኩ ነው የዋሸሽኝ አሁን ግን ትልቅ ሰው ነኝ ንገሪኝ!!» ብሎ ሲሆን አይቼ እንደማላውቀው ተኮሳተረ። የዛን ቀን ያየሁትን ነገር በሙሉ ነገርኩት። እየጠበቅኩ የነበረው የሚናደድ ወይ ሌላ ጥያቄ የሚያስከትል ነበር። እሱ ግን መጥቶ እያቀፈኝ

«አንቺምኮ ይሄን ሁሉ ብቻሽን የምትሸከሚበት እድሜ ላይ አልነበርሽም!!» አለኝ። ቀጥሎ ግን «አንቺ ትታን ስለሄደች አላዘንሽባትምኣ?» ብሎ ያላሰብኩትን ጥያቄ ጠየቀኝ።

«አላውቅም የኔ ኪዳን! ልጅ እያለን ብዙ ጊዜ ተናድጄባት አውቃለሁ። የምናደደው ግን ትታኝ ከመሄዷ በላይ ካየሁት ነገር በላይ እናትነቷን እንደማይላት እንዴት አልተረዳችልኝም ብዬ ነው! ከውርደቷ በላይ ፍቅሯ እንደሚገዝፍብኝ እንዴት ማሰብ አትችልም ብዬ ነው። ከዛ ግን የዛን ቀን ዓይኗ ውስጥ ያየሁት ህመሟ ከምናደድበት ይበልጥብኝና አንድ ቀን አጊንቻት ባቅፋት ነበር የምመኝ የነበረው»

«እሺ አገኛታለሁ!! ላገኛት ፈልጋለሁ!!» አለኝ።

«ታማለች ኪዳንዬ" አልኩት!እናቱን የማግኘት ተስፋ እንደሰጠሁት ትዝ ሲለኝ ብዙ ከማለሙ በፊት እየተሽቀዳደምኩ ይመስል ተቅለብልቤ

«ታማለች ማለት? የከፋ?»

«አዎን!! ታውቃለህ ለበደሌ እየቀጣኝ ሁሉ መስሎ ተሰምቶኝ ያውቃል! ዓይኗን ደግሜ ባየው ብዬ ዘመኔን የተመኘሁላት እናቴን በመጨረሻ ሳገኛት ለሞቷ ቀናት እየቆጠረች ሆነ።» ከዚህ በኋላ ለረዥም ሰዓት ዝም ተባባልን!! በቃ ዝም! የዛለው ሰውነቴ የተቀመጥኩበት ወደቀ። እግሬን ወደላይ ሰብስቤ ተጋደምኩ።

የነቃሁት የቧንቧ ውሃ ሲወርድ ሰምቼ ነው። ኪዳን ቀድሞኝ ነቅቷል ወይም አልተኛም! አልጋው ጫፍ ላይ እንቅልፍ እንደወሰደኝ ልብስ ደርቦልኛል። ምናልባት እንቅልፍ አልወስድ ብሎት የነበረ ይሆን ብዬ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ። በደቂቃዎች ውስጥ እናትህ አለችም ልትሞትም ነው የሚል መርዶ አርድቼው እኔ እንቅልፌን ስለጥጥ አደርኩ። እናቴን አግኝቻት ልትሞት መሆኑን ሳውቅ ለወራት መቀበል አቅቶኝ የሆንኩትን መሆን አስቤ ያጠፋሁ መሰለኝ። ብቅ ሲል

«ይቅርታ ቀሰቀስኩሽ እንዴ?» አለኝ

«ነግቶ የለ! ምነው እንቅልፍ አልወሰደህም እንዴ?»

«አይ ተኝቻለሁ!» ይበለኝ እንጄ የእኔን ኪዳን መች አጣሁት እንቅልፍ በአይኑ ሳይዞር ነው ያደረው። አስር ጊዜ <ደህና ነህ> እለዋለሁ። <ደህና ነኝ> ይለኛል።

«ማውራት ትፈልጋለህ ኪዳንዬ?»

«አልፈልግም! ዝም ብለን እንሂድ!» አለኝ።

ከመሄዴ በፊት ብዙ ማድረግ የምፈልጋቸው ነገሮች ነበሩኝ። ሆስፒታል ሄጄ ጎንጥን ማየት። ሻለቃው ጋር መደወል፣ ሴትየዋ ማን መሆኗን አውቄ ማግኘት….. ብዙ!! ከኪዳን የሚበልጥ ነገር የለኝም አይደል? እሱ እንዲህ በዝምታ ተለጉሞ የሚሰማውን እንኳን ሳላውቅ ራሴን ማስቀደም አልሆንልሽ አለኝ!! ክፍላችን የመጣውን ቁርስ እንደነገሩ እየለኳኮፍን መኪና ስፈልግ የሚያዘጋጅልኝ ሰው ጋር ደውዬ መኪና እንዲያመጣልኝ ካደረግኩ በኋላ የዳዊትን መኪና ሌላ ቦታ ወስዶ እንዲያቆምልኝ አደረግኩ። ለዳዊት ደውዬ መኪናውን ከቆመበት እንዲወስድ ስነግረው ምንም እንዳልጠረጠርኩ ለመምሰል ከራሴ ታገልኩ። መንገድ ከጀመርን በኋላ ሻንበሉ ደወለ። የመኪናው ባለቤት እና ልትገድለኝ የሞከረችው ሴት የተለያዩ ናቸው። ግን ሁለቱም በስማቸው የማውቃቸው አይደሉም!!

«ቢሮ ብቅ ካልሽ የሁለቱንም ፎቶ ላሳይሽ እችላለሁ!!» ብሎ ስልኩን ዘጋው!! መልዕክቱ አንድም ለመላክ አላምንሽም ነው ሁለትም ፎቶውን ለማየት ተጨማሪ ዋጋ አለው ነው። ስልኩን ዘግቼ ዝም አልኩ! ኪዳንም ምንም አልጠየቀኝም!! ዝምታው አስጨነቀኝ!! ልቤ ድንጋይ የተጫነበት እስኪመስለን ድረስ እንደከበደኝ ተጉዘን ከሰዓታት በኋላ እነእማዬጋ ደረስን!! አጎቴ ከበር እንደተቀበለን ኪዳንን እያገላበጠ ስሞ አልጠግብ አለው!!
1.7K viewsDAVE / PAPI, 09:24
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-16 12:24:04 #የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ አራት)
(ሜሪ ፈለቀ)

«ጓደኛዬ ነው!! ትናንት አንተን ትተን ስንወጣ ተከትለውን ነበር።» ብዬ ሆስፒታል የመተኛቱን ሚስጥር አብራራሁ ጎንጥን ምኔ ነው ብዬ ማስተዋወቅ እንዳለብኝ ግራ ሲገባኝ ማቅረቤ ይሁን ማራቄ ልኬቱን እንጃ!!  ወዲያው ግን ስም ሲለዋወጡ በስሙ ያውቀዋል እና ኪዳን ዞሮ አየኝ! <ጎንጥ ይሄ እኔ የማውቀው ጎንጤ?> ዓይነት አስተያየት! ምንም እንዳይጠይቀኝ በልምምጥ ሳየው እኔን ተወኝ! ከዛ ግን ወንበር ስቦ ጎንጥ ፊት ተቀምጦ አንዱን ጥያቄ ከሌላው እያስከተለ ይደራርብ ጀመር።

«ቤተሰብ አለህ? ማለቴ የራስህ ሚስትና ልጆች? አዲስአበባ ከመጣህ ቆየህ? ሜልጋ ሳትሰራ በፊት ምንድነበር የምትሰራው? ሴት ጓደኞችህን ሁሉ <ዓለሜ> ብለህ አትጠራም መቼም አይደል? ስራህ ስለሆነ ነው ወይስ ሜል ስለሆነች ነው (በአገጩ የተመታውን ጠቆመው) ከዳንክ በኋላ ….. »

«ኪዳን?» አልኩኝ በልመና መጠየቁን እንዲያቆም ….. በአንድ በኩል ግን መልሳቸውን ልሰማቸው የምፈልጋቸው ጥያቄዎች መሆናቸው ለጎንጥ መልስ እንድጓጓ አደረገኝ። የእውነት ከዳነ በኋላስ?

«ሴት ልጅ አለችኝ!» የሚለውን ብቻ ነው ከዚህ ሁሉ ጥያቄ ፈገግ እያለ መርጦ የመለሰው። ኪዳን ሌላውን ጥያቄ እንዲመልስለት አንገቱን አስግጎ ጠብቆ ዝም ሲለው

«come on!» አለ

«መሽቶም የለ? ሂዱና ጎናችሁን አሳርፉ!! » ሲል ነው ጎኔ አልጋ ከነካ 48 ሰዓት እንዳለፈው ትዝ ያለኝ።

«እርግጠኛ ነህ ብቻህን ምንም አትሆንም?»

«ምንም አልሆን አልኩሽ እኮ!!» ያለበት ድምፅ <ዓለሜ> እንደሚለው ያለ ማባበል አለው ነገር? ወይም መስሎኝ ነው 48 ሰዓት ያልተኛ ሰው ብዙ ያልተባለ ነገር የመስማት እድሉ ከፍተኛ ነው።

ይሄን ካለ በኋላ ለሆነ ደቂቃ የሆነ ያልተለመደ ዓይነት ዝምታ ተፈጠረ። ቻው ብዬው መውጣት እፈልጋለሁ ግን የአልጋው ግርጌጋ እንደተገተርኩ ነው። ልቤና እግሬ ተጣሉብኝ!!  እንድሄድ እየጠበቀ ነው ግን በዓይኖቹ እንድቆይለት እያባበለኝ ነው ወይም መሰለኝ። በእንደዛ ዓይነት ፖዝ ፎቶ አንሺ ያስቆመኝ ነው የምመስለው።

«እኔ የምለው? እኔኮ ብቻዬን ማደር እችላለሁ! አንቺ ለምን እዚህ አትቆዪም?» የሚለው የኪዳን ንግግር ነው እኩል ሁለታችንንም እንደመባነን ያደረገን

«አይሆንም!» አልን ሁለታችንም በአንድ ድምፅ ግንኮ አሁንም ኪዳንን ያየው የለም እኔና እሱ ዓይናችን አልተፋታም! ከዛ ደግሞ ራሴው አይሆንም ያልኩትን እሱም አይሆንም ማለቱ ለምን ከፋኝ?

«እህእ? ወይ ሶስታችንም እዚሁ እንደር?» አለ ኪዳን ሳቅ እያፈነው። አሁን ሁለታችንም አየነው። ስንወጣ ሲያበሽቀኝ እንደሚያድር አውቃለሁ።

«ደግ! በሉ ቸር እደሩ!! ትከሻሽን መገላመጥ አትዘንጊ!» አለ በቃ ተሰናብቼሻለሁ ሂጂ እንደማለት ነገር ከነበረበት በቀስታ ዘወር እያለ።

«የምትባባሉትን ተባባሉ በሩጋ ነኝ!» ብሎ ኪዳን ወጣ!! ምን እንደሚባል የማውቀው የለኝም!! ማለት የምፈልገው መኖሩንም እንጃ! ካለሁበት ተንቀሳቅሼ ልቀርበው ፈልጌ ማፈር ነው ግራ መጋባት የማላውቀው ስሜት ጨመደደኝ። ጭንቅላቴም ልቤም ሰውነቴም ተባብረውብኝ ማድረግ የምሻው ብቸኛ ነገርኮ እሱን መንካት ነው። እንዲህ ሆኖ የሚያውቅ ሰው ኖሮ ያውቅ ይሆን አላውቅም! ገብቶት ነው መሰለኝ ወይም እሱም እንደእኔ አካላቶቹ አምፀውበት ሊነካኝ ፈልጎ እጁን እንድይዘው ዘረጋልኝ። ከረሜላ አይቶ ሲቁለጨለጭ ምራቁ አፉ ውስጥ ሞልቶ ወደ ጎሮሮው ሲደፍቅበት ቆይቶ ከረሜላውን እንደሰጡት ህፃን በአንድ እርምጃ ዘልዬ እጁን ያዝኩት። እጁን እጄ ላይ ከማጫወቱ ውጪ በቃላት አላወራኝም። በዓይኖቹ የሚያወራው ደግሞ ትርጉሙ እኔ እንደምፈታው ይሆን ሌላ እየገባኝ አይደለም። <የዓይን ቋንቋ እንደፈቺው ነው!>

«ከዳንክ በኋላስ?» አልኩት ለሚመልስልኝ መልስ ሳልዘጋጅ

«አላውቅም!» አለኝ ከአይኔ ውስጥ ቆፍሮ የሚያወጣው ስሜት ያለ ይመስል በአይኑ አይኔ ውስጥ እየቆፈረ። መልሱ ምን ሊሆን እንደሚችል የጠበቅኩት ነገር ስላልነበረ አልከፋኝም! እሙ እንዳለችው ከመጃጃልም በላይ እየሆንኩ እንደሆነ የገባኝ ከ<አላውቅም> አስከትሎ <ዓለሜ> አለማለቱ ከፋኝ! አንዴ አለሜ በለኝ ብለው ሆዱን ይዞ አይስቅብኝም? ይባላልስ?

«አንቺ ምንድነው የምትፈልጊው?» አለኝ

«አላውቅም! ምን እንደምፈልግ አላውቅም!» አለ አፌ! የምፈልግ የነበረው  ግን ዓለሜ እንዲለኝ ፣ የምፈልግ የነበረው እንደቀኑ የእጄን መዳፍ መሃሉን እንዲስምልኝ፣ እምፈልግ የነበረውማ  ለአንዴ በህይወቴ ጀግና ጀግና የማልጫወትበት ሰው እንዲሆነኝ …….  ለአንዴ ብቻ ፍርሃቴን ፣ ድክመቴን ፣ ማፈሬን ፣ ሽንፈቴን ፣  ….  ከእንባዬ ጋር ለውሼ ደረቱ ላይ እንድተነፍሰው በክንዱ ደግፎ ደረቱ ላይ እንዲያቅፈኝ ….. እፈልግ የነበረውማ ይሄ ያልኩት ሁሉ ሲሆን ዘመናት ቢቆጠሩ ነበር። ቀጥዬ ያልኩት ግን

«ኪዳን አባት ሊሆን ነው!» የሚለውን ነው! ሳልፈልግ ድምፄ ውስጥ መከፋቴ ተሰማብኝ። የያዘውን እጄን ስቦ ወደደረቱ አስጠግቶ ደረቱ ላይ አጥብቆ ያዘው። ይሄ ሰውዬማ ከእጄጋር የሆነ ነገር አለው! ነውስ እጄና ልቤ የሚያገናኛቸው ነገር አለ እጄን የሆነ ነገር ሲያደርገኝ ልቤ አብሮ የሚያሸበሽበው?

«ዳር የተተውሽ መሰለሽ?» ሲለኝ እንባዬ ታገለኝ!! ነግሬዋለሁ? አልነገርኩትም! የተሰማኝን በልከኛው ቃል እንዴት ማስቀመጥ ቻለበት? አንዲት ፊደል ከአፌ ቢወጣ እንባዬ እንደሚያጅበው ስለገባኝ ዓይኖቹን ሸሽቼ ዝም አልኩ። ደረቱ ላይ የያዘውን እጄን እዛው ትቶት በእጁ አገጬን ደግፎ ዓይኖቹን እንዳያቸው አደረገኝ።

«መቼም ቢሆን በምንም የማይተካሽ እህቱ ነሽ!! ሚሽትና ልጁ ያንቺን ቦታ አይጋፉም!! ኪዳንን በዚህ ሁሉ መዓት ፍቅር ስትወጂ ልብሽ ጠቦሽ አባትሽን አስወጥተሻል? ወይሳ እናትሽን? እኔን ወደልብሽ ስታስገቢስ ልብሽ አልበቃ ብሎ ከኪዳን ፍቅር አጎደልሽ? የእርሱን ቦታ ቀነስሽ?»

«አይ!!» ብዬ ጭንቅላቴን በአሉታ ከነቀነቅኩ በኋላ ነውኮ መጨረሻ ላይ ያለውን ለራሴ ደግሜ ስሰማው ዓይኔን የማሳርፍበት የጠፋኝ። ጥሩ እየሰማሁት ነበርኮ ከመጨረሻው እሱን ልቤ ካስገባበት ዓረፍተ ነገር በፊት! <አይ> ያልኩት ምንድነው ቆይ? የኪዳንን ፍቅር ሳታጎድል ነው ልቤ የገባኸው ነው አይደል ያልኩት? የጥያቄው መልስ እንደተመለሰለት ፈገግ ብሎ አገጬ ላይ አውራ ጣቱን አሸት አሸት ነገር አድርጎ እጁን ደረቱ ላይ ወደተወው እጄ መልሶ እንደቅድሙ አጥብቆ ደረቱ ላይ ያዘው።

«ያልኩት ሀቅ አለው?» ብሎ አወነባበደብኝ። ምናለ ዝም ቢለኝ ገብቶት የለ?
«ምኑ?»
«ከልብሽ ገብቻለሁ?»
«አዎ! መሰለኝ! እኔ እንጃ አላውቅም! በምን አውቃለሁ?» በዚህ ነፋሻማ አየር እንዲህ ሊሞቀኝ ይገባ ነበር? ስፈራ ጉልበቴን እንደቁርጥማት እንደሚያደርገኝ ነገር አሁን ሊሰማኝ ይገባ ነበር? ሳቅ እንደማለት ነገር ብሎ

«በይ ተነሽ ሂጅ አሁን እየጠበቀሽ ነው!!» ብሎ እጄን አንስቶ አገላብጦ ይስመው ጀመር!! አንዴ ሁለቴ ሶስቴ ….. ሁለቴ አይበሉባውን አንዴ ወይም ሶስቴ መሃል እጄን…..  እኔ እንጃ አንድ አራቴ ጎኑን …..
1.7K viewsDAVE / PAPI, 09:24
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-13 13:38:21 «መሸነፊያዬም መጀገኛዬም አንተ መሆንህን አታውቅም? ባንተ ሲመጡብኝ ነው እጅ የምሰጠውም አውሬ የምሆነውም! ያን ታውቃለህ አይደል?»

«አውቃለሁ ሜል። ግን አሁንኮ ትልቅ ሰውዬ ነኝ!! ሚስትኮ ላገባ እየተሰናዳሁ ያለው ግብዳ ሰውዬ ነኝ! እስከመቼ ነው የምትጠብቂኝ? (ዞር ብዬ ያለፉትን ቀናት እንደማስታወስ ሳየው) ይሄ የተለየ situation ነው። እንዲህ ያለ አጋጣሚ ከተፈጠረማ በድዴም ቀርቼ እንደምትደርሺልኝ አውቃለሁ። ገብቶሻል ምን ማለት እንደፈለግኩ!! መቼ ነው አንቺ የራስሽ የሆነ ህይወት የሚኖርሽ? ለእኔ ብለሽ ፣ ለአባዬ ብለሽ ወይም ለእማዬ ብለሽ የማትኖሪው። ለሜላት ብለሽ የምትኖሪው ቀን መቼ ነው? (ይሄን ሲለኝ ስለእማዬ ለካ መንገር አለብኝ። ምን ብዬ ነው የምነግረው? የሞተችዋ እናታችን ከሞት ተነሳች! ነው የምለው?)  ደግሞ አባት ልሆንልሽ ነው!» ሲለኝ ስለእማዬ ያሰብኩት ጠፋብኝ። መኪናውን አቆምኩ።

«ሊንዳ እርጉዝ ናት? ስንት ወሯ ነው?» እያልኩት እሺ የአሁኑ እንባ ምን የሚሉት ነው? እንደትናንት በሚመስለኝ የቀናት ርዝመት ውስጥ እግሬ ላይ ተጠምጥሞ ትተሽኝ አትሂጂ ብሎ የሚያለቅስ ትንሽዬ ልጅ ነበርኮ!! አባቱ የሞተበት እናቱ ትታው የሄደች ቀንኮ <አባዬ ዳቦ ገዝቶ ሲመጣ ዳቦ በሻይ ነው የምበላው እንጀራ አልበላም!> ብሎ ያለቀሰ የአባቱ ሳጥን ውስጥ መቆለፍ ያልገባው ሚጢጢ ነበረ።

«ስድስት ወር ሆናት! ሴት ናት!» አለኝ እንደመኩራትም እያደረገው። ዝም አልኩ!! ዝምታዬ ውስጥ ግን ብዙ ጩኸት ነበረ። ደስ የሚል ከዛ ደግሞ የሚከፋ ስሜት እንዴት ተብሎ ይብራራል? የእኔ ኪዳን ፣ ልጄ ፣ ታናሼ ፣ ዓለሜ ፣ ብቸኛ የዓይን ማረፊያዬ አደገልኝ!! እሱ አድጎ ልጅ ሊያሳድግ ነው!! እንዲኖረው የተመኘሁለትን እና የተመኘውን ሁሉ አንድም ሳይጎድልበት አግኝቷል። በህይወቴ ትልቁ ድሌ እና ስኬቴ እኮ እሱ ነው!! ከዛ ግን ለምን የመከፋት ስሜት ተሰማኝ? ለእሱ ደስ አለኝ ለእኔ ግን ከፋኝ። የሆነ እዝህች ምድር ላይ ለመኖር የመጣሁበትን ዓላማ የጨረስኩ ፤ የምኖርለት ምክንያት ምንም ያልቀረኝ ፤ ከዚህ በኋላ እኔ የማላስፈልገው ፤ የራቀኝ ዓይነት ስሜት ተሰማኝ። ይሄን ግን ለእርሱ ልነግረው አልፈለግኩም። ደስታው ትንሽ እንኳን እንዲደበዝዝበት አልፈልግም!! አቅፌው እንባዬን እየጠረግኩ ደስ እንዳለኝ ነግሬው መኪናዬን መንዳት ጀመርኩ። ሆቴሉ ደውለን ሪሴፕሽን እቃውን እንዲያስቀምጡልን አድርገን። የሚከፋፈለውን ከፍለን ሻንጣውን ወሰድን። ለአፍታም ቢሆን ከእኔ እይታ ዘወር እንዲል ስላልፈለግኩ ሆቴል ከመያዛችን በፊት ጎንጥን ለማየት ወደሆስፒታል ነዳሁ።

«የእኔ ኪዳን? አውቃለሁ ታጥበህ ልብስ ለመቀየር እንደቸኩልክ!! ለትንሽ ደቂቃ ሆስፒታል የሆነ ሰው ጠይቀን እንመለስ እና ደግሞም የምነግርህ ትልቅ ነገር አለ።» አልኩት በመንገዳችን።

«ምንድነው እሱ? የምነግርህ ትልቅ ነገር ስትዪ ሁሌም የሚከተለው ደስ የማይል ነው!! ምንድነው እሱ? ምን ልታደርጊ ነው? ደህና ነሽ አንቺኣ?»

«ኸረ ጭራሽ እንደሱ አይነት ነገር አይደለም!! እንደውም ደስ የሚል ነው መሰለኝ! ቢያንስ በግማሽ!»

ጎንጥ የተኛበት ክፍል ስንገባ ትንፋሹን ሰብስቦ የሆነ መርዶ እየጠበቀ ያለ ይመስል ነበር። ከሆዱ ድረስ ትንፋሹን ስቦ በረጅሙ የመገላገል ዓይነት ተነፈሰ እና ፈገግ አለ።

«ነፍሴን እኮ አወክሻት ዓለሜ? ከቤቱ ወጣች ካሉኝ ቆየ!! ስትዘገዪ ከመንገድ ምን አገኘሽ ብዬ ነፍሴ ከስጋዬ ልትለይ?» አለ የመጨረሻውን ዓረፍተ ነገር መልስ ባልጠበቀ ጥያቄ ዓይነት አስረዝሞ!! ማለት የፈለግኩት የነበረው <ልቤንኮ በረደኝ! እጄን ያዘኝ! ጦሽ ብዬ ላልቅስና! ኸረ በመድሃንያለም ነፍሴን አታስጨንቂያት! እያልክ አባብለኝ!> ነው። ያልኩት ግን «የኪዳንን ሻንጣ ልናመጣ በዛው ሄድን! ይቅርታ ቢያንስ መልዕክት እንኳን መላክ ነበረብኝ!»

ኪዳን አንዴ እኔን አንዴ እሱን <እየሆነ ያለውን ነገር አንዳችሁ ትነግሩኝ?> በሚል አስተያየት ያየናል።


        .......... አልጨረስንም .......... 

@wegoch
@wegoch
@paappii
1.2K viewsDAVE / PAPI, 10:38
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-13 13:38:20 «ብዙ ጠበቅኩሽኮ ሜል! አንድም ሶሻል ሚዲያ አካውንትሽ አክቲቭ አይደለም!! ካንቺ ሳልሰማ ብዙ የቆየሁበት ቀን 12 ቀን ነው መጀመሪያ የታሰርሽ ጊዜ!! ቢያንስ እንዳላስብ በሰው ትልኪብኝ ነበርኮ!! ቢቸግረኝ መልዕክት ላኩልሽኮ (ትዝ አለኝ! ቁጥሩ ከማይታይ ላኪ ላመስግን ወይስ ልፀልይ? የሚል መልዕክት ስልኬ ነበረው! ስላልገባኝ እንጂ!! ምንም ቢፈጠር የምደውልለት እኔ ነኝ እንጂ እሱ እንዳይደውል ህግ አለን!! ስልኩን በቃሌ ነው የማውቀው እንጂ ሴቭ አላደርገውም!!)

…… በእኔ አስችሎሽ በጤናሽ ሁለት ወር እንደማትቆዪ አውቃለሁ። እኔስ አንቺን ባጣ ሰው እንደማልሆን አታውቂም? ከዛ በላይ መጠበቅ አልችልም ነበር ትኬቴን ቆርጬ መጣሁ!! የያዝኩትን ሻንጣ የያዝኩት ሆቴል ክፍል ወርውሬ ልብሴን እንኳን ሳልቀይር ማንን መጠየቅ እንደነበረብኝ እርግጠኛ ስላልነበርኩ እቤት መሄዱ አደገኛ ሊሆን ስለሚችል ብዬ ክለቡጋ ሄድኩ!! መምጣቴንም እዛ መሆኔንም ማን እንደነገራቸው አላውቅም!! ከዛ ወጥቼ ታክሲ ልይዝ ስጠብቅ መጥተው በመኪናቸው ከበቡኝ!!»

«ቆይ ቆይ ቆይ (ከእቅፉ ወጣሁ!) ክለብ ማንን አገኘህ? ማንን አናገርክ? ስንት ሰዓት ነው የሄድከውስ?»

«አመሻሽ ነገር 11 ወይ 12 ሰዓት ገደማ!! ብዙ ሰው ነበርኮ እኔእንጃ!» አለኝ ግራ እየገባው።

«ከበር ጀምሮ ያናገርከውን ሰው አንድ በአንድ ንገረኝ!! ለማስታወስ ሞክር!» እያልኩት መኪናውን አስነስቼ መንዳት ጀመርኩ።

«ጋርዶቹን? መግባት አይቻልም ሰዓት ገና ነው ብለው እንቢ አሉኝ መጀመሪያ እ ….. ከዛ አንቺን ፈልጌ እንደሆነ ከካናዳ የተላከ ዕቃ ላደርስ እንደሆነ ነገርኳቸው እና ከውስጥ የሆነ ሰው ጠርተው አገናኙኝ። ከዛ ለእነርሱ የነገርኳቸውን ስነግረው ሄደሽ እንደማታውቂ …. አንድ ቀን ብቅ ብለሽ እንደነበር ነገረኝ። የግድ ማድረስ ያለብኝ እቃ አለ ስለው እሱም ገብቶ ዳዊት የሚባል ሰው ጠራልኝ። ፍቅረኛሽ መሆኑን ነገረኝ (እዚህጋ የአይመስለኝም ሽርደዳ ያለበት ፈገግታ ፈገግ ብሎ በቁም ነገር የሚያወራውን እየተከታተልኩ እንደሆነ ሲያውቅ ወደ ቁምነገሩ ተመለሰ።) እሱ ወደ ውስጥ እንድገባ ጋበዘኝ እና ከዛ በቃ ያልታወቀ ሰው በሽጉጥ መትቶሽ እንደነበር ከዛም ድጋሚ ከሰዎች ጋር ተጣልተሽ እስከሆስፒታል የሚያደርስ ጉዳት ደርሶብሽ እንደነበር እና እቤት እንደማገኝሽ ነገረኝ።»

« ከኤርፖርት ሆቴልህ? ከሆቴልህ ክለብ? በመሃል የሄድክበት ቦታ አለ? አስታውስ? ያናገርከው ሰው? ሁለቴ የገጠመህ ሰው?»

«ሜል? እኔን ታውቂኝ የለ? ጀርባዬን እያየሁ የምሄድ ሰውኮ አይደለሁም!! ግን ማንንም አላገኘሁም!! ከዛ ውጪ የትም አልሄድኩም! ያናገረኝም ያናገርኩትም ሰው የለም ከሪሴፕሽኖቹ ውጪ!!» አለኝ ተጨንቆ

«ክለብ ውስጥ ሌላ ማን ነበር?»
«የሚሰሩ ሰዎች ነበሩ!! ቤቱን እያስተካከሉ ምናምን የነበሩ እኔ እንጃ በደንብ አላስተዋልኩም ግን ሴቶችም ነበሩ!!»

«ስምህን የነገርከው ወይም የእኔ ወንድም መሆንህን የነገርከው ሰው አለ?»
«ለዳዊት! ስሜን ነግሬዋለሁ ግን ያንቺ ወንድም መሆኔን አልነገርኩትም!! ዳዊት እባላለሁ ሲለኝ ኪዳን! ብዬዋለሁ!!»

«ምን ያህል ይሆናል ውስጥ የቆየኸው?»
«እኔ እንጃ አንድ ሰዓት!! የሚጠጣ ጋብዞኝ አንድ አንድ ብርጭቆ ይዘን ነው የሆነውን የነገረኝ!! ይኸው ጀመረሽ ነገር ስትቀምሪ መሃል ቤት እኔን የምታጦዥኝ ነገርሽ!»

«ጥርጣሬ እንጂ ያረጋገጥኩት ነገር ስለሌለ ልነግርህ አልችልምኮ ኪዳንዬ! መጠጡን የጋበዘህ እሱ ነው? አልጠጣም ብለኸው ነበር? እንድትጠጣ ወተዋተህ?»

«አይ እውነትም ፍቅረኛሽ ነበር በሚገባ ነው የምታውቂው!! አዎ አልጠጣም እቸኩላለሁ ስለው። <እዚህ ድረስ መጥተህ ሳላስተናግድህ መሄድህን ሜሉ ብትሰማ ትቀየመኛለች፤ አንድ ብርጭቆ ይዘን የሆነውን ላውራህ አለኝ!!»

«ይሄ የውሻ ልጅ!! እውነት ባይሆን ነው የሚሻለው እንጂ አልለቀውም! (ይሄ ጤነኛ ንዴት ይሆን አልገባኝም! ጭንቅላቴ ከውስጥ የተወጠረ አይነት ስሜት ነው የሚሰማኝ የሆነ ሊፈነዳ የቀረበ ነገር። ደረቴ ላይ እልህ እና ቁጣ ከትንፋሼ ጋር እኔ ልውጣ እኔ ልቅደም ግብ ግብ የገጠሙ አይነት ስሜት) ይሄ ሙት እሱም ሰው ሆኖ መሆኑ ነው?» ኪዳን እየሆነ ያለው ግራ ገብቶት

«ሜል? እሱ ደውሎላቸው ነው የመጡት ብለሽ ነው የምታስቢው? ከአጠገቤኮ ለአፍታም ዞር አላለም ነበር። ኸረ በፍፁም እንዲህ የሚያደርግ ሰው አይመስልም! ግማሹን ሰዓትኮ እንዴት እንደሚወድሽ ነው ሲነግረኝ የነበረው። ደግሞ ፍቅሩ አይኑ ላይ ያስታውቃል። ምንም ከማድረግሽ በፊት አጣሪ እህትዬ በእኔ ሞት? እ?»

«ሌባ አይኑ እና ቅቤ ምላሱ አይሸውድህ!! በእርግብ ላባ ያጌጠ እባብ ነው!! ታውቀኛለህ ደግሞ ባልተረጋገጠ ነገር ምንም አላደርግም!!» እያልኩት ስልኬን አውጥቼ ደወልኩ!!

«ሻለቃ! ሜላት ነኝ!!»
«ሜላት ሜላት?»
«አውቀኸኛል ባክህ! እንዴት አስታውሳ ደወለች ብለህ ከሆነ ግራ የተጋባኸው አዎ አስታውሼ ነው!! አደጋ የደረሰብኝ ቀን ለኤግዝቢትነት በሚል የወሰዳችሁትን ስልኬን መረጃውን ከውስጡ አፅድታችሁ እንደመለሳችሁልኝም ጭምር ነው ያስታወስኩት! ለሶስተኛ ወገን አሳልፋችሁ ሰጥታችሁ ማለቴ ሸጣችሁ የግሌን መረጃ እንደነገዳችሁበትም ጭምር!! ልቀጥል?»

«ምን እንደምታወሪ ታውቂዋለሽ? ወይስ ጥይቱ ሚሞሪሽን ብቻ ሳይሆን ማሰቢያሽንም ነው የወሰደው?»

«ምን እንደማወራ አሳምረህ ታውቃለህ!! ፌስቡኬ የእኔ መሆኑን ሰይጣን እንኳን አይደርስበትም። ድንገት እኔ በተመታሁ በነጋታው 10 ዓመት ሙሉ ማን መሆኔ ሳይታወቅ የተጠቀምኩበት አካውንት በአስማት ታወቀና ዘጉት ነው የምትለኝ ያለኸው? ኦው ለምን ስልኬን እንደሚፈልጉት አልነገሩህም ማለት ነው?» ዝም አለ ለአፍታ

«የውልህ! በጣም በተቻለኝ አቅም ጥሩ ሴት ልሆን እየሞከርኩ ያለሁበት ሰዓት ላይ በመሆኑ ፈጣሪህን አመስግን!! ከናንተ ጋር አውጫጭኝ የምጫወትበት ጊዜ የለኝም!! አንድ መረጃ ብቻ ነው የምፈልገው!! የመታኝን ሰው ማወቅ ነው የምፈልገው!! መሃል ከተማ ነው! አመለጠ ምናምን በሚል ተረት ተረት እኔን አትሸውደኝም!! ግማሽ መንገድ ላግዝህ?  ጥቁር ጃጓር መኪና የጎማው ቸርኬ ወርቅማ ፣ ከኋላው መስታወት በቀኝ በኩል ጠርዝ ላይ ትንሽዬ ቀይ ስቲከር ያለበት፣ ታርጋ ቁጥሩ የመጨረሻ ሁለት ቁጥር 52 ነው!! እኔ ሁለት ጥይት መትቶኝ ይሄን ሁሉ መረጃ ስቶር ማድረግ ከቻልኩ ምርመራውን የያዘው ወይም ይዞ የለቀቀው ባልደረባህ በአንድ ሰዓት ውስጥ ሙሉ መረጃውን ጠረጴዛህ ላይ ማኖር አይቸግረውም!! ሌላው ደግሞ ሴት ናት!! ወንድ ለመምሰል የሞከረች ሴት ናት!! መኪናው በማን ስም እንደተመዘገበ እና ሴትየዋ ማን እንደሆነች ብቻ ነው ማወቅ የምፈልገው። ከአንድ ሰዓት በኋላ እደውልልሃለሁ! ከዛ ቀድመህ አሁንም ቢሆን የምትነግረኝ ነገር ካለህ ግን ዝግጁ ነኝ!!» ዝም አለኝ። ስልኩን ዘጋሁት!! እና ወደኪዳን ዞሬ

«ያረፍክበት ሆቴል ደውል እና ሻንጣህን መውሰድ እንደምትችል አረጋግጥ!! የምታርፍበት ሌላ ቦታ እንፈልጋለን። ለጊዜው እኔም ወደቤት መሄድ ያለብኝ አይመስለኝም!!»


«በእንዲህ ዓይነት ሰዓትኮ ሌላ የማላውቃት ሴት ነው የምትሆኝብኝ!! ውስጥሽ ሁለት ሴት ያለች ነው የሚመስለኝ! የእኔ ሜል እና የሌላ ሰው ሜላት! የእኔዋ እናት፣ እህት፣ ስስ ፣ የምታለቅስ ፣ የምታቅፍ ፣ የምታባብል ፣ ቀድማኝ የምትሞትልኝ …….. ያችኛዋ አያድርስ ነው!! » አለ ኪዳን በመገረም ሲያየኝ ቆይቶ!!
977 viewsDAVE / PAPI, 10:38
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-13 13:38:20 #የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ ሶስት)
(ሜሪ ፈለቀ)


ኪዳን የመጠጥ ውሃ የሞላው ብርጭቆ ይዞ ወደሳሎን ብቅ ሲል ልቤ ወደቦታዋ ተመለሰች። እዚህ ድረስ ያለውን በድል ተወጥቼዋለሁ!! ብርጭቆውን ተቀብዬው ለደሳለኝ ከወገቤ ጎንበስ ብዬ በሁለት እጄ ሳቀብለው ጭራሽ የሚያወራው ተወነባበደበት። ጋዜጠኛው በሚሆነው ትርምስ ትዕግስቱ ነው ያለቀው። ኪዳን እየሆነ ያለው ነገር ግር ብሎት አይኑን ከወድያ ወዲህ ያንቀዋልላል። ወደጆሮው ጠጋ ብዬ «አምላክን በልመና አታድክም!! » አልኩት እና ጠቀስኩት።  ፈገግ ብሎ ደረቱን እንደመንፋት አድርጎ ጎምለል እያየ ዙሪያውን መቃኘት ጀመረ። አተኩሮ ላየው የሆነ ቁራጭ የፊልም ትወና እየከወነ ነው የሚመስለው። ሁሌም እንዲህ ነው! ከልጅነታችን ጀምሮ ከልጆች ጋር ተደባድቤ እኔ ከሆንኩ ያሸነፍኩት የፀቡ መሃል ሜዳ ይገባና ደረቱን ነፍቶ ይንቀባረራል። «ማን መሰለችህ? የእኔ እህት እኮ ናት!!» ይላል እየተጀነነ።

•  * * * * * * * * * * * * *

ድሮ ልጅ እያለን አባቴ እናቴ ላይ ሙድ የሚይዝበት መላው ነበር አሁን እኔ እና ኪዳን የምንግባባበት ኮድ። እናቴ ብር እጇ ላይ ቢኖርም ባይኖርም አለኝ አትለውም!! ብር ጨርሰሻል ወይ ብሎ ቀጥታ ከጠየቃት መልሷ ሁሌም አዎን ነው። በአቋራጭ ነው የሚያጣራው

«አስካል እንደው ከአባወራዎቹ ልደብለቅበት እስኪ መቀነትሽን ፈትሽልኝ!» ይላታል

«አይ እንግዲህ እንኳን ላንተ አምቡላህን መጋቻ ለልጆቼም የሚቀምሱትን ማሰናዳበት አልሞላልኝ» ትለዋለች

«ውይ በሞትኩት እናቴን! አያ ተካን አበድረኝ ልበለው ይሆን? እንደው ቸሩ መድሃንያለም ለልጆቼ የምሰጠው አታሳጣኝ» ይላል ወደላይ እንደማንጋጠጥ ብሎ በአንድ አይኑ እሷን አጮልቆ እያየ እና እያስተዛዘነ (ልበደራቸው የሚላቸው ሰዎች ስም ይቀያየራል)

«አይ እንግዲህ አምላክን በልመና ማድከም ደግም አይደል!! የምንችለውን እናደራርግና በተረፈው ማመስገን ነው። ያመሰገንነው አምላክ የጎደለውን ይሞላል!» ትለዋለች ልትወጣ ነጠላዋን እላይዋ ላይ እያደረገች። አለኝም እንዳትለው ለእሱ መጠጫ መስጠት አትፈልግም። የለኝም እንዳትለው ባሏ የሰው ፊት ሊያይባት ሲሆን በዘዴ አድበስብሳ! አባቴ እሷ ዞር ስትል ጠብቆ እየሳቀ

«እም! መች አጣኋት እናታችሁን? አላት ማለት ነው! አሁን ዘንቢል ሙሉ ሸምታ ትመጣ የለ? ምንአለ በሉኝ!» ይላል። እንዳለውም ከገበያ መዓት ነገር ሸማምታ ስትመጣ አባቴ ያላትን አንነግራትም ተያይዘን እንስቃለን!!

የእውነትም እጇ ላይ ብር ከሌላት መልሷ ይለያል። የአባዬ ጥያቄ ስሞቹንና አጠያየቁን ቀይሮ ያው ነው። የመጨረሻው <ለልጆቼ የምሰጠው አታሳጣኝ> የሚልበት ጋር ሲደርስ

«እንግዲህ አንድዬ ያውቃል!! እርሱ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድር!!» ካለች አባቴ አሁንም እሷ ዞር ስትል ጠብቆ

«አሁን የእውነቷን ነው የላትም ማለት ነው!!» ብሎ ከኛ ፊቱን አዙሮ ብር ይቆጥር እና « ገበያ ውረጅበት ብሎሻል! ብላችሁ ስጧት» ብሎ ለአንዳችን ያቀብለናል። ለምን እራሱ እንደማይሰጣት አሁንም ድረስ አይገባኝም!! ምናልባት ለእኛ ማስተማር የፈለገው ነገር ይኖር ይሆን ነበር። ሁሌም መልሷ እንዲሁ ነው። ሁሌም የእርሱ አጠያየቅ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ነው። ገና እሱ ሲጠይቃት በተለይ እኔ ሳቄ ይመጣል። ለእማዬ <እየፈተነሽ ነው!> አልላትም!! ለትንሿ ልቤ የእነርሱ የፍቅር ቋንቋቸው መሆኑ ገብቷት ነው መሰለኝ በተለይ የሌላት ጊዜ እሱ ሲያዝንላት ልቤ በሙቀት ቅልጥ ትላለች።

ከኪዳን ጋር ልጆች ሆነን እናታችንን የምናስታውስበት አንዱ ጨዋታችን ነበር። አድገን የህይወት ውጥንቅጥ ውስጥ የተነከርን ጊዜ ደግሞ ምልክት መሰጣጫችን ሆነ። ያለንበት ሁኔታ ተስፋ ያለው፣ መውጫ ያለው ፣ ደህንነታችን ጥሩ ሁኔታ ላይ ከሆነ። «አምላክን በልመና አታድክሚ….. » የምትለዋ! ለምሳሌ ባለፈው ኪዳን እንዳለኝ « ደህና ነኝ አታስቢ! አልጎዱኝም!! ተረጋግተሽ መላውን ፈልጊ!»  እንደማለት ነው!! ወይም ደግሞ « አንድዬ ያውቃል» ብዬ መልዕክት ካደረስኩት «እንዳትደውልልኝ፣ በምንም መንገድ ልታገኘን አትሞክር! ያለሁበት ሁኔታ ሲሪየስ ነው!!» እንደማለት ነው። እንደገባንበት ማጥ መልእክቱ ይለያያል። እኔ እና እሱ እንግባባበታለን!! በደፈናው ያለንበትን ሁኔታ አስከፊነት የምንለዋወጥበት ነው።

•                   
•  * * * * * * * * *

ጋዜጠኛው ከዚህ በኋላ ላይቭ እንዳለ ሊቆይ የሚችለው ከ2 ደቂቃ አይበልጥም!! እንደየትም ብሎ ቢያራዝምልኝ ሊጨምርልኝ የሚችለው 1 ደቂቃ ነው። በዛ 2 ደቂቃ ደግሞ መኪናችን ጋር መድረስ አለብን። ለጋዜጠኛው ተጨማሪ ደቂቃ ማስረዘም ከቻለ ምልክት ሰጠሁት። ትከሻውን ሰበቀ። እሞክራለሁ እንደማለት ነገር።

«አንቺ እስከበሩ ትሸኝናለሽ እኮ!!» አልኳት ሚስትየውን። ባሏ አፉ እዛ ይለፍልፍ እንጂ አይኑም ቀልቡም እኛጋ ነው። ባይገባትም እየመራችን ወጣች። በፍጥነት ወደአጥሩ በር እየተጓዝኩ

«ልትከተሉኝ ብታስቡ! መንገዴ ላይ የሆነ ነገር ልትፈጥሩ ብትሞክሩ ውርድ ከራሴ!! ወጥተሽ ጋዜጠኞቹ መኪና ውስጥ ገብተሽ ማረጋገጥ ትችያለሽ!! አሁን ላይቭ እየተላለፈ ያለው የባልሽ ቃለመጠይቅ ብቻ ነው። አንዲት ዝንፍ ያለች ነገር አደርጋለሁ ብላችሁ ብትሞክሩ እዛ መኪና ውስጥ ያሉት ባለሞያዎች አንድ በተን ብቻ ነው መጫን የሚጠበቅባቸው። ቤትሽ እያንዳንዱ ክፍል ካሜራ አስቀምጫለሁ!! እየሆነ ያለው ነገር አሁን እኔና አንቺ የምናወራውም ምስል ሳይቀር ሪከርድድ ነው። መኪናዬ በስህተት ጎማዋ ቢቀንስ አልኩሽ ሁሉንም ምስል ገጣጥሞ ዜና ማዋቀር አይከብድምኣ? ቻው! መልካም እድል በይልኝ ባልሽን!! እም ጷ» በእጄ የመሳም ምልክት አሳይቻት ራሷ ለዘበኞቹ እንዲያሳልፉኝ ምልክት ሰጠቻቸው እና እኛ ስንወጣ

«ቱ » ብላ በንዴት እና በጥላቻ ምራቋን ስትተፋ እሰማታለሁ። እኔና ኪዳን በሩጫ መኪናችን ውስጥ ስንገባ ጋዜጠኛው የላይቭ ስርጭቱን ጨርሷል። ከአካባቢው እስክርቅ ድረስ በማይነዳ ፍጥነት እየነዳሁ ምንም ቃል ሳልተነፍስ ሸመጠጥኩት። ብዙ እርቀን እንኳን እንዳልተረጋጋሁ ያወቅኩት ኪዳን

«ሜል በፍፁም እዚህ ድረስ ሊከተሉሽ አይችሉምኮ!» ሲለኝ ነው።

«አይችሉም ብሎ ተዘናግቶ ወጥመዳቸው ውስጥ ከመውደቅ ሊሞክሩ ይችላሉ ብሎ መጠንቀቅ ነው የሚያዋጣው!! አታውቃቸውም እስከምን ጥግ መሄድ የሚያስችል ጭካኔ እንዳላቸው።» እጁን ሰዶ ትከሻዬን ዳሰስ ዳሰስ ሲያደርገኝ ዞሬ አየሁት። የናፍቆቴ መጠን እየሆኑ በነበሩት ክስተቶች ተከድኖ እንጂ ገደቡን የጣሰ እንደነበር የገባኝ ዓይኖቹን ሳያቸው ነው። መኪናዬን ጥጉን አስያዝኩት እና አቀፍኩት!!

«ለምን መጣህ? በዝህች ዓለም ያለኝ ብቸኛ ነገሬ አንተ መሆንህን አታውቅም? የሆነ ነገር ሆነህብኝስ ቢሆን? ሰው እንደማልሆን አታውቅም?» ቁጣም ፍቅርም እንባም ሳግም ያንቀረቅቡኝ ጀመር። ያውቀዋል ስስቴን!! ሁሌም እየተቆጣሁት ወይ እየጮህኩበት ሳለቅስ አይመልስልኝም። ስረጋጋ ነው ምክንያቱን የሚነግረኝ!!

«ይቅርታ ሜል! ይቅርታ እሺ!» አለኝ ከእኔ በላይ አጥብቆ አቅፎኝ እያባበለኝ!! መረጋጋቴን ሲያይ!!
1.0K viewsDAVE / PAPI, 10:38
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-13 00:46:37 አቅራቢያው ስደርስ የጋዜጠኛው ቡድን እኩል ደረሰ። ስልኬ ላይ የማየውን እቤት ያሉት ካሜራዎች እይታ አቀበልኳቸው። እነርሱ በኮምፒውተር ፣ በተለያዩ ገመዶች ፣ ማይክራፎኖች  እና ሌሎች ነገሮች በሞላው የመኪናቸው ጀርባ የሚሰካካውን ሰካክተው ዝግጁ መሆናቸውን ሲነግሩኝ መኪናችንን የአጥር በሩጋ አስጠግተን አቁመን እኔ እና አንድ ማይክራፎን የያዘ ጋዜጠኛ እና ሌሎች ሁለት ካሜራ እና ካሜራ ረዳት ወርደን ስንጠጋ ጠባቂው የያዘውን መሳሪያ ወደፊት አስቀድሞ ወደእኛ ቀረበ።

«ጋዜጠኞች ነን!! ላይቭ ነው! አቶ ደሳለኝ ስለምርጫው ትንሽ እንዲሉልን ነው!» አለው አብሮኝ ያለው ጋዜጠኛ። ጠባቂው ምኑም አልተመቸውም። ለሌላኛው ጠባቂ መልዕክቱን ለአቶ ደሳለኝ እንዲያስተላልፍ ጮክ ብሎ ተናግሮ እኛን እንድንጠብቅ አዘዘን። ሌላኛው ጠባቂ ከደቂቃዎች በኋላ አቶ ደሳለኝን አስከትሎ ብቅ አለ።

«እኔ ከምንም ዓይነት ጋዜጠኛ ጋር ቀጠሮ አልያዝኩም!! ምን አይነት ጣጣ ነው! ሰው ማረፍ አይችልም? ደግሞ ይሄን ቤት ማን አሳያችሁ?» እያለ እየተነጫነጨ ቀና ሲል ከእኔ ጋር ተያየን። ሊቀየር ሲዳዳው አብሮኝ ያለው ጋዜጠኛ ለካሜራ ማኑ እንዲጀምር ምልክት ሰጠው። ቀጥሎም የቴሌቭዥን ጣቢያውን ፈቃድ እያቀበለው

« አቶ ደሳለኝ ላይቭ የኢትዮጵያ ህዝብ እየተከታተሎት ነው። በዚህ ምርጫ ለየት ባለ የምርጫ ቅስቀሳዎ የህዝብን ቀልብ የሳቡ ይመስላል። ወደ ውስጥ ገብተን አንድ ሁለት ነገር ቢሉን? » አለው። ግራ ተጋባ እና እየተወነባበደ ሳቅ አይሉት ስላቅ ያልለየለት ፈገግታ ፈገግ እያለ ወደውስጥ ጋበዘን። ይሄኔ ፅፌ አዘጋጅቼው የነበረውን መልዕክት ኪዳን ያለበትን ክፍል ጨምሮ ካሜራ የተገጠመባቸውን ክፍሎች ምስል ከሚያሳየው ምስልጋ ላኩለት። ስልኩ መልዕክት መቀበሉን ቢሰማም አላየውም።

«አቶ ደሳለኝ መልዕክቱ የሚያስፈልጎ መልዕክት ይመስለኛል።» አልኩት ጠጋ ብዬው። በጥፍሮቹ ቢቦጫጭረኝ ደስ እንደሚለው እያስታወቀበት የግዱን ፈገግ ብሎ ወደሳሎን እየመራን መልዕክቱን አነበበው።

« ቴሌቭዥንህን ክፈተው ካላመንከኝ ላይቭ ነህ!! ኪዳን ያለበት ክፍል ጨምሮ ኮሪደርህ እና ሳሎንህ በድብቅ ካሜራ እይታ ውስጥ ነው። የምስሉ መዳረሻ መቼም ይገባሃል የኢትዮጵያ ህዝብ አይን ነው። አርፈህ በቀጣፊ ምላስህ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለህን ፍቅር እና ብትመረጥ የማታደርገውን የውሸት ቃልህን ላይቭ ዘብዝበህ የምርጫ ቅስቀሳህን ብታደርግ ይሻልሃል ወይስ ዜናውን ከምርጫ ቅስቀሳ ወደአፈና ወንጀል ብንቀይረው? ምርጫው ያንተ ነው!! ከጋዜጠኞቹ ጋር እያወራህ ወንድሜን ሳሎን አስመጣልኝ። ምንም ግርግር ሳንፈጥር ከጋዜጠኞቹ ቀደም ብዬ ውልቅ ብዬ እወጣልሃለሁ!! አይ ካልክ ግን እዚሁ ላይቭ ወንድሜን እንዳገትከው ከነምስሉ ለጋዜጠኛው ሹክ እለዋለሁ። እዛው ላይቭ ጮማ ዜና አይመስልህም? በዛ ላይ ያን የቪዲዮ ቅጂ እመርቅላቸዋለሁ።!!» እያነበበ ጋዜጠኛው ደጋግሞ ስሙን ይጠራዋል። አልሰማውም!! እንደመባነን ብሎ

«እ እ!! የሆነ ትንሽ አስቸኳይ መልዕክት ደርሶኝኮ እ!!» ተንተባተበ።
«አዝናለሁ መጥፎ ዜና ነው?» አለው ጋዜጠኛው።
«አይ እንደው ትንሽ ነገር ነው። እኔ የምልህ እና አሁን ይሄም ላይቭ እየተላለፈ ነው?» ብሎ የቴሌቭዥኑን ሪሞት አንስቶ እየከፈተ  የሆነች ተንኮል ያለበት አስተያየት ወደእኔ አየ። ልቤ በመጠኑም ቢሆን መደለቅ ጀመረ። ደቂቃ እንኳን ዝንፍ ያለ ክፍተት ከተፈጠረ ሰውየው እዛ ያለነውን በሙሉ ጭጭ አድርጎ የቀደመ እቅዱን ለማሳካት የጋዜጠኞቹ ብዛትም ማንነትም የሚያሳስበው ሰው አይደለም። ጋዜጠኛው ነውም አይደለምም ሳይለው (ምክንያቱም እስከዛ ደቂቃ ድረስ ላይቭ አልነበረም) ቀጠለ። በቴሌቭዥኑ ዜና የምታቀርበዋ ሴት ስለአቶ ደሳለኝ አውርታ ስታበቃ ባልደረባዋን ጋበዘችው። ጋዜጠኛው ጥያቄውን ቀጠለ። መልሱም መላ ቅጡ የጠፋበት ወሬ ከመሆኑ በተጨማሪ በተቀመጠበት ላብ ያጠምቀው ጀመር። እየተንተባተበ ጥቂት እንዳወራ ሚስትየው ብቅ እንዳለች እየሆነ ባለው ነገር ግራ ተጋብታ ፍሬን ያዘች። በሚቀባጥረው ወሬ መሃል ወደሚስቱ ዞሮ «እስቲ ኪዳንን የሚጠጣ ውሃ እንዲያመጣ አድርጊልኝ! ቡናም ሻይም ሳልላችሁ በሞቴ ለእናንተስ ምን ይምጣላችሁ?» አለው ጋዜጠኛውን! ጋዜጠኛው ቀጥታ በዜና መሃል እየተላለፈ ያለ ፕሮግራም ላይ መዘለባበዱ እያናደደው ግን በጨዋ ደንብ ቀጠለ።

«በእውነቱ አቶ ደሳለኝ በዚህ አጋጣሚ ሳይዘጋጁ የመጣንቦት ቢሆንም እንግዳ ተቀባይነትዎ እና ልግስናዎ አልተለየንም። ከልብ እናመሰግናለን!! ባልደረባዬ የቀሩትን ዜናዎች ለማቅረብ እየተጠባበቀች ስለሆነ ለህዝቤ ማለት አለብኝ የሚሉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጦት!! »

ጋዜጠኛውን በቅጡ የሰማው አይመስልም። ሚስቱ እንደጅብራ መገተሯ አሳስቦት በግንባሩ መልዕክት ሊያስተላልፍላት እየሞከረ ነው። እያመነታች ከሳሎኑ ስትወጣ ልቤ መደለቋን ቀጠለች። እሱም ለዚህ የፈረደበት የኢትዮጵያ ህዝብ ላቡንና ወሬውን በቲቪ ማስተላለፉን ቀጠለ። ኪዳን የመጠጥ ውሃ የሞላው ብርጭቆ ይዙ ወደሳሎን ብቅ ሲል ልቤ ወደቦታዋ ተመለሰች። እዚህ ድረስ ያለውን በድል ተወጥቼዋለሁ!!


                       ..........  አልጨረስንም!! .........

@wegoch
@wegoch
@paappii
465 viewsDAVE / PAPI, 21:46
ክፈት / አስተያየት ይስጡ