Get Mystery Box with random crypto!

«ብዙ ጠበቅኩሽኮ ሜል! አንድም ሶሻል ሚዲያ አካውንትሽ አክቲቭ አይደለም!! ካንቺ ሳልሰማ ብዙ የቆ | ወግ ብቻ

«ብዙ ጠበቅኩሽኮ ሜል! አንድም ሶሻል ሚዲያ አካውንትሽ አክቲቭ አይደለም!! ካንቺ ሳልሰማ ብዙ የቆየሁበት ቀን 12 ቀን ነው መጀመሪያ የታሰርሽ ጊዜ!! ቢያንስ እንዳላስብ በሰው ትልኪብኝ ነበርኮ!! ቢቸግረኝ መልዕክት ላኩልሽኮ (ትዝ አለኝ! ቁጥሩ ከማይታይ ላኪ ላመስግን ወይስ ልፀልይ? የሚል መልዕክት ስልኬ ነበረው! ስላልገባኝ እንጂ!! ምንም ቢፈጠር የምደውልለት እኔ ነኝ እንጂ እሱ እንዳይደውል ህግ አለን!! ስልኩን በቃሌ ነው የማውቀው እንጂ ሴቭ አላደርገውም!!)

…… በእኔ አስችሎሽ በጤናሽ ሁለት ወር እንደማትቆዪ አውቃለሁ። እኔስ አንቺን ባጣ ሰው እንደማልሆን አታውቂም? ከዛ በላይ መጠበቅ አልችልም ነበር ትኬቴን ቆርጬ መጣሁ!! የያዝኩትን ሻንጣ የያዝኩት ሆቴል ክፍል ወርውሬ ልብሴን እንኳን ሳልቀይር ማንን መጠየቅ እንደነበረብኝ እርግጠኛ ስላልነበርኩ እቤት መሄዱ አደገኛ ሊሆን ስለሚችል ብዬ ክለቡጋ ሄድኩ!! መምጣቴንም እዛ መሆኔንም ማን እንደነገራቸው አላውቅም!! ከዛ ወጥቼ ታክሲ ልይዝ ስጠብቅ መጥተው በመኪናቸው ከበቡኝ!!»

«ቆይ ቆይ ቆይ (ከእቅፉ ወጣሁ!) ክለብ ማንን አገኘህ? ማንን አናገርክ? ስንት ሰዓት ነው የሄድከውስ?»

«አመሻሽ ነገር 11 ወይ 12 ሰዓት ገደማ!! ብዙ ሰው ነበርኮ እኔእንጃ!» አለኝ ግራ እየገባው።

«ከበር ጀምሮ ያናገርከውን ሰው አንድ በአንድ ንገረኝ!! ለማስታወስ ሞክር!» እያልኩት መኪናውን አስነስቼ መንዳት ጀመርኩ።

«ጋርዶቹን? መግባት አይቻልም ሰዓት ገና ነው ብለው እንቢ አሉኝ መጀመሪያ እ ….. ከዛ አንቺን ፈልጌ እንደሆነ ከካናዳ የተላከ ዕቃ ላደርስ እንደሆነ ነገርኳቸው እና ከውስጥ የሆነ ሰው ጠርተው አገናኙኝ። ከዛ ለእነርሱ የነገርኳቸውን ስነግረው ሄደሽ እንደማታውቂ …. አንድ ቀን ብቅ ብለሽ እንደነበር ነገረኝ። የግድ ማድረስ ያለብኝ እቃ አለ ስለው እሱም ገብቶ ዳዊት የሚባል ሰው ጠራልኝ። ፍቅረኛሽ መሆኑን ነገረኝ (እዚህጋ የአይመስለኝም ሽርደዳ ያለበት ፈገግታ ፈገግ ብሎ በቁም ነገር የሚያወራውን እየተከታተልኩ እንደሆነ ሲያውቅ ወደ ቁምነገሩ ተመለሰ።) እሱ ወደ ውስጥ እንድገባ ጋበዘኝ እና ከዛ በቃ ያልታወቀ ሰው በሽጉጥ መትቶሽ እንደነበር ከዛም ድጋሚ ከሰዎች ጋር ተጣልተሽ እስከሆስፒታል የሚያደርስ ጉዳት ደርሶብሽ እንደነበር እና እቤት እንደማገኝሽ ነገረኝ።»

« ከኤርፖርት ሆቴልህ? ከሆቴልህ ክለብ? በመሃል የሄድክበት ቦታ አለ? አስታውስ? ያናገርከው ሰው? ሁለቴ የገጠመህ ሰው?»

«ሜል? እኔን ታውቂኝ የለ? ጀርባዬን እያየሁ የምሄድ ሰውኮ አይደለሁም!! ግን ማንንም አላገኘሁም!! ከዛ ውጪ የትም አልሄድኩም! ያናገረኝም ያናገርኩትም ሰው የለም ከሪሴፕሽኖቹ ውጪ!!» አለኝ ተጨንቆ

«ክለብ ውስጥ ሌላ ማን ነበር?»
«የሚሰሩ ሰዎች ነበሩ!! ቤቱን እያስተካከሉ ምናምን የነበሩ እኔ እንጃ በደንብ አላስተዋልኩም ግን ሴቶችም ነበሩ!!»

«ስምህን የነገርከው ወይም የእኔ ወንድም መሆንህን የነገርከው ሰው አለ?»
«ለዳዊት! ስሜን ነግሬዋለሁ ግን ያንቺ ወንድም መሆኔን አልነገርኩትም!! ዳዊት እባላለሁ ሲለኝ ኪዳን! ብዬዋለሁ!!»

«ምን ያህል ይሆናል ውስጥ የቆየኸው?»
«እኔ እንጃ አንድ ሰዓት!! የሚጠጣ ጋብዞኝ አንድ አንድ ብርጭቆ ይዘን ነው የሆነውን የነገረኝ!! ይኸው ጀመረሽ ነገር ስትቀምሪ መሃል ቤት እኔን የምታጦዥኝ ነገርሽ!»

«ጥርጣሬ እንጂ ያረጋገጥኩት ነገር ስለሌለ ልነግርህ አልችልምኮ ኪዳንዬ! መጠጡን የጋበዘህ እሱ ነው? አልጠጣም ብለኸው ነበር? እንድትጠጣ ወተዋተህ?»

«አይ እውነትም ፍቅረኛሽ ነበር በሚገባ ነው የምታውቂው!! አዎ አልጠጣም እቸኩላለሁ ስለው። <እዚህ ድረስ መጥተህ ሳላስተናግድህ መሄድህን ሜሉ ብትሰማ ትቀየመኛለች፤ አንድ ብርጭቆ ይዘን የሆነውን ላውራህ አለኝ!!»

«ይሄ የውሻ ልጅ!! እውነት ባይሆን ነው የሚሻለው እንጂ አልለቀውም! (ይሄ ጤነኛ ንዴት ይሆን አልገባኝም! ጭንቅላቴ ከውስጥ የተወጠረ አይነት ስሜት ነው የሚሰማኝ የሆነ ሊፈነዳ የቀረበ ነገር። ደረቴ ላይ እልህ እና ቁጣ ከትንፋሼ ጋር እኔ ልውጣ እኔ ልቅደም ግብ ግብ የገጠሙ አይነት ስሜት) ይሄ ሙት እሱም ሰው ሆኖ መሆኑ ነው?» ኪዳን እየሆነ ያለው ግራ ገብቶት

«ሜል? እሱ ደውሎላቸው ነው የመጡት ብለሽ ነው የምታስቢው? ከአጠገቤኮ ለአፍታም ዞር አላለም ነበር። ኸረ በፍፁም እንዲህ የሚያደርግ ሰው አይመስልም! ግማሹን ሰዓትኮ እንዴት እንደሚወድሽ ነው ሲነግረኝ የነበረው። ደግሞ ፍቅሩ አይኑ ላይ ያስታውቃል። ምንም ከማድረግሽ በፊት አጣሪ እህትዬ በእኔ ሞት? እ?»

«ሌባ አይኑ እና ቅቤ ምላሱ አይሸውድህ!! በእርግብ ላባ ያጌጠ እባብ ነው!! ታውቀኛለህ ደግሞ ባልተረጋገጠ ነገር ምንም አላደርግም!!» እያልኩት ስልኬን አውጥቼ ደወልኩ!!

«ሻለቃ! ሜላት ነኝ!!»
«ሜላት ሜላት?»
«አውቀኸኛል ባክህ! እንዴት አስታውሳ ደወለች ብለህ ከሆነ ግራ የተጋባኸው አዎ አስታውሼ ነው!! አደጋ የደረሰብኝ ቀን ለኤግዝቢትነት በሚል የወሰዳችሁትን ስልኬን መረጃውን ከውስጡ አፅድታችሁ እንደመለሳችሁልኝም ጭምር ነው ያስታወስኩት! ለሶስተኛ ወገን አሳልፋችሁ ሰጥታችሁ ማለቴ ሸጣችሁ የግሌን መረጃ እንደነገዳችሁበትም ጭምር!! ልቀጥል?»

«ምን እንደምታወሪ ታውቂዋለሽ? ወይስ ጥይቱ ሚሞሪሽን ብቻ ሳይሆን ማሰቢያሽንም ነው የወሰደው?»

«ምን እንደማወራ አሳምረህ ታውቃለህ!! ፌስቡኬ የእኔ መሆኑን ሰይጣን እንኳን አይደርስበትም። ድንገት እኔ በተመታሁ በነጋታው 10 ዓመት ሙሉ ማን መሆኔ ሳይታወቅ የተጠቀምኩበት አካውንት በአስማት ታወቀና ዘጉት ነው የምትለኝ ያለኸው? ኦው ለምን ስልኬን እንደሚፈልጉት አልነገሩህም ማለት ነው?» ዝም አለ ለአፍታ

«የውልህ! በጣም በተቻለኝ አቅም ጥሩ ሴት ልሆን እየሞከርኩ ያለሁበት ሰዓት ላይ በመሆኑ ፈጣሪህን አመስግን!! ከናንተ ጋር አውጫጭኝ የምጫወትበት ጊዜ የለኝም!! አንድ መረጃ ብቻ ነው የምፈልገው!! የመታኝን ሰው ማወቅ ነው የምፈልገው!! መሃል ከተማ ነው! አመለጠ ምናምን በሚል ተረት ተረት እኔን አትሸውደኝም!! ግማሽ መንገድ ላግዝህ?  ጥቁር ጃጓር መኪና የጎማው ቸርኬ ወርቅማ ፣ ከኋላው መስታወት በቀኝ በኩል ጠርዝ ላይ ትንሽዬ ቀይ ስቲከር ያለበት፣ ታርጋ ቁጥሩ የመጨረሻ ሁለት ቁጥር 52 ነው!! እኔ ሁለት ጥይት መትቶኝ ይሄን ሁሉ መረጃ ስቶር ማድረግ ከቻልኩ ምርመራውን የያዘው ወይም ይዞ የለቀቀው ባልደረባህ በአንድ ሰዓት ውስጥ ሙሉ መረጃውን ጠረጴዛህ ላይ ማኖር አይቸግረውም!! ሌላው ደግሞ ሴት ናት!! ወንድ ለመምሰል የሞከረች ሴት ናት!! መኪናው በማን ስም እንደተመዘገበ እና ሴትየዋ ማን እንደሆነች ብቻ ነው ማወቅ የምፈልገው። ከአንድ ሰዓት በኋላ እደውልልሃለሁ! ከዛ ቀድመህ አሁንም ቢሆን የምትነግረኝ ነገር ካለህ ግን ዝግጁ ነኝ!!» ዝም አለኝ። ስልኩን ዘጋሁት!! እና ወደኪዳን ዞሬ

«ያረፍክበት ሆቴል ደውል እና ሻንጣህን መውሰድ እንደምትችል አረጋግጥ!! የምታርፍበት ሌላ ቦታ እንፈልጋለን። ለጊዜው እኔም ወደቤት መሄድ ያለብኝ አይመስለኝም!!»


«በእንዲህ ዓይነት ሰዓትኮ ሌላ የማላውቃት ሴት ነው የምትሆኝብኝ!! ውስጥሽ ሁለት ሴት ያለች ነው የሚመስለኝ! የእኔ ሜል እና የሌላ ሰው ሜላት! የእኔዋ እናት፣ እህት፣ ስስ ፣ የምታለቅስ ፣ የምታቅፍ ፣ የምታባብል ፣ ቀድማኝ የምትሞትልኝ …….. ያችኛዋ አያድርስ ነው!! » አለ ኪዳን በመገረም ሲያየኝ ቆይቶ!!