Get Mystery Box with random crypto!

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ ሶስት) (ሜሪ ፈለቀ) | ወግ ብቻ

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ ሶስት)
(ሜሪ ፈለቀ)


ኪዳን የመጠጥ ውሃ የሞላው ብርጭቆ ይዞ ወደሳሎን ብቅ ሲል ልቤ ወደቦታዋ ተመለሰች። እዚህ ድረስ ያለውን በድል ተወጥቼዋለሁ!! ብርጭቆውን ተቀብዬው ለደሳለኝ ከወገቤ ጎንበስ ብዬ በሁለት እጄ ሳቀብለው ጭራሽ የሚያወራው ተወነባበደበት። ጋዜጠኛው በሚሆነው ትርምስ ትዕግስቱ ነው ያለቀው። ኪዳን እየሆነ ያለው ነገር ግር ብሎት አይኑን ከወድያ ወዲህ ያንቀዋልላል። ወደጆሮው ጠጋ ብዬ «አምላክን በልመና አታድክም!! » አልኩት እና ጠቀስኩት።  ፈገግ ብሎ ደረቱን እንደመንፋት አድርጎ ጎምለል እያየ ዙሪያውን መቃኘት ጀመረ። አተኩሮ ላየው የሆነ ቁራጭ የፊልም ትወና እየከወነ ነው የሚመስለው። ሁሌም እንዲህ ነው! ከልጅነታችን ጀምሮ ከልጆች ጋር ተደባድቤ እኔ ከሆንኩ ያሸነፍኩት የፀቡ መሃል ሜዳ ይገባና ደረቱን ነፍቶ ይንቀባረራል። «ማን መሰለችህ? የእኔ እህት እኮ ናት!!» ይላል እየተጀነነ።

•  * * * * * * * * * * * * *

ድሮ ልጅ እያለን አባቴ እናቴ ላይ ሙድ የሚይዝበት መላው ነበር አሁን እኔ እና ኪዳን የምንግባባበት ኮድ። እናቴ ብር እጇ ላይ ቢኖርም ባይኖርም አለኝ አትለውም!! ብር ጨርሰሻል ወይ ብሎ ቀጥታ ከጠየቃት መልሷ ሁሌም አዎን ነው። በአቋራጭ ነው የሚያጣራው

«አስካል እንደው ከአባወራዎቹ ልደብለቅበት እስኪ መቀነትሽን ፈትሽልኝ!» ይላታል

«አይ እንግዲህ እንኳን ላንተ አምቡላህን መጋቻ ለልጆቼም የሚቀምሱትን ማሰናዳበት አልሞላልኝ» ትለዋለች

«ውይ በሞትኩት እናቴን! አያ ተካን አበድረኝ ልበለው ይሆን? እንደው ቸሩ መድሃንያለም ለልጆቼ የምሰጠው አታሳጣኝ» ይላል ወደላይ እንደማንጋጠጥ ብሎ በአንድ አይኑ እሷን አጮልቆ እያየ እና እያስተዛዘነ (ልበደራቸው የሚላቸው ሰዎች ስም ይቀያየራል)

«አይ እንግዲህ አምላክን በልመና ማድከም ደግም አይደል!! የምንችለውን እናደራርግና በተረፈው ማመስገን ነው። ያመሰገንነው አምላክ የጎደለውን ይሞላል!» ትለዋለች ልትወጣ ነጠላዋን እላይዋ ላይ እያደረገች። አለኝም እንዳትለው ለእሱ መጠጫ መስጠት አትፈልግም። የለኝም እንዳትለው ባሏ የሰው ፊት ሊያይባት ሲሆን በዘዴ አድበስብሳ! አባቴ እሷ ዞር ስትል ጠብቆ እየሳቀ

«እም! መች አጣኋት እናታችሁን? አላት ማለት ነው! አሁን ዘንቢል ሙሉ ሸምታ ትመጣ የለ? ምንአለ በሉኝ!» ይላል። እንዳለውም ከገበያ መዓት ነገር ሸማምታ ስትመጣ አባቴ ያላትን አንነግራትም ተያይዘን እንስቃለን!!

የእውነትም እጇ ላይ ብር ከሌላት መልሷ ይለያል። የአባዬ ጥያቄ ስሞቹንና አጠያየቁን ቀይሮ ያው ነው። የመጨረሻው <ለልጆቼ የምሰጠው አታሳጣኝ> የሚልበት ጋር ሲደርስ

«እንግዲህ አንድዬ ያውቃል!! እርሱ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድር!!» ካለች አባቴ አሁንም እሷ ዞር ስትል ጠብቆ

«አሁን የእውነቷን ነው የላትም ማለት ነው!!» ብሎ ከኛ ፊቱን አዙሮ ብር ይቆጥር እና « ገበያ ውረጅበት ብሎሻል! ብላችሁ ስጧት» ብሎ ለአንዳችን ያቀብለናል። ለምን እራሱ እንደማይሰጣት አሁንም ድረስ አይገባኝም!! ምናልባት ለእኛ ማስተማር የፈለገው ነገር ይኖር ይሆን ነበር። ሁሌም መልሷ እንዲሁ ነው። ሁሌም የእርሱ አጠያየቅ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ነው። ገና እሱ ሲጠይቃት በተለይ እኔ ሳቄ ይመጣል። ለእማዬ <እየፈተነሽ ነው!> አልላትም!! ለትንሿ ልቤ የእነርሱ የፍቅር ቋንቋቸው መሆኑ ገብቷት ነው መሰለኝ በተለይ የሌላት ጊዜ እሱ ሲያዝንላት ልቤ በሙቀት ቅልጥ ትላለች።

ከኪዳን ጋር ልጆች ሆነን እናታችንን የምናስታውስበት አንዱ ጨዋታችን ነበር። አድገን የህይወት ውጥንቅጥ ውስጥ የተነከርን ጊዜ ደግሞ ምልክት መሰጣጫችን ሆነ። ያለንበት ሁኔታ ተስፋ ያለው፣ መውጫ ያለው ፣ ደህንነታችን ጥሩ ሁኔታ ላይ ከሆነ። «አምላክን በልመና አታድክሚ….. » የምትለዋ! ለምሳሌ ባለፈው ኪዳን እንዳለኝ « ደህና ነኝ አታስቢ! አልጎዱኝም!! ተረጋግተሽ መላውን ፈልጊ!»  እንደማለት ነው!! ወይም ደግሞ « አንድዬ ያውቃል» ብዬ መልዕክት ካደረስኩት «እንዳትደውልልኝ፣ በምንም መንገድ ልታገኘን አትሞክር! ያለሁበት ሁኔታ ሲሪየስ ነው!!» እንደማለት ነው። እንደገባንበት ማጥ መልእክቱ ይለያያል። እኔ እና እሱ እንግባባበታለን!! በደፈናው ያለንበትን ሁኔታ አስከፊነት የምንለዋወጥበት ነው።

•                   
•  * * * * * * * * *

ጋዜጠኛው ከዚህ በኋላ ላይቭ እንዳለ ሊቆይ የሚችለው ከ2 ደቂቃ አይበልጥም!! እንደየትም ብሎ ቢያራዝምልኝ ሊጨምርልኝ የሚችለው 1 ደቂቃ ነው። በዛ 2 ደቂቃ ደግሞ መኪናችን ጋር መድረስ አለብን። ለጋዜጠኛው ተጨማሪ ደቂቃ ማስረዘም ከቻለ ምልክት ሰጠሁት። ትከሻውን ሰበቀ። እሞክራለሁ እንደማለት ነገር።

«አንቺ እስከበሩ ትሸኝናለሽ እኮ!!» አልኳት ሚስትየውን። ባሏ አፉ እዛ ይለፍልፍ እንጂ አይኑም ቀልቡም እኛጋ ነው። ባይገባትም እየመራችን ወጣች። በፍጥነት ወደአጥሩ በር እየተጓዝኩ

«ልትከተሉኝ ብታስቡ! መንገዴ ላይ የሆነ ነገር ልትፈጥሩ ብትሞክሩ ውርድ ከራሴ!! ወጥተሽ ጋዜጠኞቹ መኪና ውስጥ ገብተሽ ማረጋገጥ ትችያለሽ!! አሁን ላይቭ እየተላለፈ ያለው የባልሽ ቃለመጠይቅ ብቻ ነው። አንዲት ዝንፍ ያለች ነገር አደርጋለሁ ብላችሁ ብትሞክሩ እዛ መኪና ውስጥ ያሉት ባለሞያዎች አንድ በተን ብቻ ነው መጫን የሚጠበቅባቸው። ቤትሽ እያንዳንዱ ክፍል ካሜራ አስቀምጫለሁ!! እየሆነ ያለው ነገር አሁን እኔና አንቺ የምናወራውም ምስል ሳይቀር ሪከርድድ ነው። መኪናዬ በስህተት ጎማዋ ቢቀንስ አልኩሽ ሁሉንም ምስል ገጣጥሞ ዜና ማዋቀር አይከብድምኣ? ቻው! መልካም እድል በይልኝ ባልሽን!! እም ጷ» በእጄ የመሳም ምልክት አሳይቻት ራሷ ለዘበኞቹ እንዲያሳልፉኝ ምልክት ሰጠቻቸው እና እኛ ስንወጣ

«ቱ » ብላ በንዴት እና በጥላቻ ምራቋን ስትተፋ እሰማታለሁ። እኔና ኪዳን በሩጫ መኪናችን ውስጥ ስንገባ ጋዜጠኛው የላይቭ ስርጭቱን ጨርሷል። ከአካባቢው እስክርቅ ድረስ በማይነዳ ፍጥነት እየነዳሁ ምንም ቃል ሳልተነፍስ ሸመጠጥኩት። ብዙ እርቀን እንኳን እንዳልተረጋጋሁ ያወቅኩት ኪዳን

«ሜል በፍፁም እዚህ ድረስ ሊከተሉሽ አይችሉምኮ!» ሲለኝ ነው።

«አይችሉም ብሎ ተዘናግቶ ወጥመዳቸው ውስጥ ከመውደቅ ሊሞክሩ ይችላሉ ብሎ መጠንቀቅ ነው የሚያዋጣው!! አታውቃቸውም እስከምን ጥግ መሄድ የሚያስችል ጭካኔ እንዳላቸው።» እጁን ሰዶ ትከሻዬን ዳሰስ ዳሰስ ሲያደርገኝ ዞሬ አየሁት። የናፍቆቴ መጠን እየሆኑ በነበሩት ክስተቶች ተከድኖ እንጂ ገደቡን የጣሰ እንደነበር የገባኝ ዓይኖቹን ሳያቸው ነው። መኪናዬን ጥጉን አስያዝኩት እና አቀፍኩት!!

«ለምን መጣህ? በዝህች ዓለም ያለኝ ብቸኛ ነገሬ አንተ መሆንህን አታውቅም? የሆነ ነገር ሆነህብኝስ ቢሆን? ሰው እንደማልሆን አታውቅም?» ቁጣም ፍቅርም እንባም ሳግም ያንቀረቅቡኝ ጀመር። ያውቀዋል ስስቴን!! ሁሌም እየተቆጣሁት ወይ እየጮህኩበት ሳለቅስ አይመልስልኝም። ስረጋጋ ነው ምክንያቱን የሚነግረኝ!!

«ይቅርታ ሜል! ይቅርታ እሺ!» አለኝ ከእኔ በላይ አጥብቆ አቅፎኝ እያባበለኝ!! መረጋጋቴን ሲያይ!!