Get Mystery Box with random crypto!

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ አራት) (ሜሪ ፈለቀ) « | ወግ ብቻ

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ አራት)
(ሜሪ ፈለቀ)

«ጓደኛዬ ነው!! ትናንት አንተን ትተን ስንወጣ ተከትለውን ነበር።» ብዬ ሆስፒታል የመተኛቱን ሚስጥር አብራራሁ ጎንጥን ምኔ ነው ብዬ ማስተዋወቅ እንዳለብኝ ግራ ሲገባኝ ማቅረቤ ይሁን ማራቄ ልኬቱን እንጃ!!  ወዲያው ግን ስም ሲለዋወጡ በስሙ ያውቀዋል እና ኪዳን ዞሮ አየኝ! <ጎንጥ ይሄ እኔ የማውቀው ጎንጤ?> ዓይነት አስተያየት! ምንም እንዳይጠይቀኝ በልምምጥ ሳየው እኔን ተወኝ! ከዛ ግን ወንበር ስቦ ጎንጥ ፊት ተቀምጦ አንዱን ጥያቄ ከሌላው እያስከተለ ይደራርብ ጀመር።

«ቤተሰብ አለህ? ማለቴ የራስህ ሚስትና ልጆች? አዲስአበባ ከመጣህ ቆየህ? ሜልጋ ሳትሰራ በፊት ምንድነበር የምትሰራው? ሴት ጓደኞችህን ሁሉ <ዓለሜ> ብለህ አትጠራም መቼም አይደል? ስራህ ስለሆነ ነው ወይስ ሜል ስለሆነች ነው (በአገጩ የተመታውን ጠቆመው) ከዳንክ በኋላ ….. »

«ኪዳን?» አልኩኝ በልመና መጠየቁን እንዲያቆም ….. በአንድ በኩል ግን መልሳቸውን ልሰማቸው የምፈልጋቸው ጥያቄዎች መሆናቸው ለጎንጥ መልስ እንድጓጓ አደረገኝ። የእውነት ከዳነ በኋላስ?

«ሴት ልጅ አለችኝ!» የሚለውን ብቻ ነው ከዚህ ሁሉ ጥያቄ ፈገግ እያለ መርጦ የመለሰው። ኪዳን ሌላውን ጥያቄ እንዲመልስለት አንገቱን አስግጎ ጠብቆ ዝም ሲለው

«come on!» አለ

«መሽቶም የለ? ሂዱና ጎናችሁን አሳርፉ!! » ሲል ነው ጎኔ አልጋ ከነካ 48 ሰዓት እንዳለፈው ትዝ ያለኝ።

«እርግጠኛ ነህ ብቻህን ምንም አትሆንም?»

«ምንም አልሆን አልኩሽ እኮ!!» ያለበት ድምፅ <ዓለሜ> እንደሚለው ያለ ማባበል አለው ነገር? ወይም መስሎኝ ነው 48 ሰዓት ያልተኛ ሰው ብዙ ያልተባለ ነገር የመስማት እድሉ ከፍተኛ ነው።

ይሄን ካለ በኋላ ለሆነ ደቂቃ የሆነ ያልተለመደ ዓይነት ዝምታ ተፈጠረ። ቻው ብዬው መውጣት እፈልጋለሁ ግን የአልጋው ግርጌጋ እንደተገተርኩ ነው። ልቤና እግሬ ተጣሉብኝ!!  እንድሄድ እየጠበቀ ነው ግን በዓይኖቹ እንድቆይለት እያባበለኝ ነው ወይም መሰለኝ። በእንደዛ ዓይነት ፖዝ ፎቶ አንሺ ያስቆመኝ ነው የምመስለው።

«እኔ የምለው? እኔኮ ብቻዬን ማደር እችላለሁ! አንቺ ለምን እዚህ አትቆዪም?» የሚለው የኪዳን ንግግር ነው እኩል ሁለታችንንም እንደመባነን ያደረገን

«አይሆንም!» አልን ሁለታችንም በአንድ ድምፅ ግንኮ አሁንም ኪዳንን ያየው የለም እኔና እሱ ዓይናችን አልተፋታም! ከዛ ደግሞ ራሴው አይሆንም ያልኩትን እሱም አይሆንም ማለቱ ለምን ከፋኝ?

«እህእ? ወይ ሶስታችንም እዚሁ እንደር?» አለ ኪዳን ሳቅ እያፈነው። አሁን ሁለታችንም አየነው። ስንወጣ ሲያበሽቀኝ እንደሚያድር አውቃለሁ።

«ደግ! በሉ ቸር እደሩ!! ትከሻሽን መገላመጥ አትዘንጊ!» አለ በቃ ተሰናብቼሻለሁ ሂጂ እንደማለት ነገር ከነበረበት በቀስታ ዘወር እያለ።

«የምትባባሉትን ተባባሉ በሩጋ ነኝ!» ብሎ ኪዳን ወጣ!! ምን እንደሚባል የማውቀው የለኝም!! ማለት የምፈልገው መኖሩንም እንጃ! ካለሁበት ተንቀሳቅሼ ልቀርበው ፈልጌ ማፈር ነው ግራ መጋባት የማላውቀው ስሜት ጨመደደኝ። ጭንቅላቴም ልቤም ሰውነቴም ተባብረውብኝ ማድረግ የምሻው ብቸኛ ነገርኮ እሱን መንካት ነው። እንዲህ ሆኖ የሚያውቅ ሰው ኖሮ ያውቅ ይሆን አላውቅም! ገብቶት ነው መሰለኝ ወይም እሱም እንደእኔ አካላቶቹ አምፀውበት ሊነካኝ ፈልጎ እጁን እንድይዘው ዘረጋልኝ። ከረሜላ አይቶ ሲቁለጨለጭ ምራቁ አፉ ውስጥ ሞልቶ ወደ ጎሮሮው ሲደፍቅበት ቆይቶ ከረሜላውን እንደሰጡት ህፃን በአንድ እርምጃ ዘልዬ እጁን ያዝኩት። እጁን እጄ ላይ ከማጫወቱ ውጪ በቃላት አላወራኝም። በዓይኖቹ የሚያወራው ደግሞ ትርጉሙ እኔ እንደምፈታው ይሆን ሌላ እየገባኝ አይደለም። <የዓይን ቋንቋ እንደፈቺው ነው!>

«ከዳንክ በኋላስ?» አልኩት ለሚመልስልኝ መልስ ሳልዘጋጅ

«አላውቅም!» አለኝ ከአይኔ ውስጥ ቆፍሮ የሚያወጣው ስሜት ያለ ይመስል በአይኑ አይኔ ውስጥ እየቆፈረ። መልሱ ምን ሊሆን እንደሚችል የጠበቅኩት ነገር ስላልነበረ አልከፋኝም! እሙ እንዳለችው ከመጃጃልም በላይ እየሆንኩ እንደሆነ የገባኝ ከ<አላውቅም> አስከትሎ <ዓለሜ> አለማለቱ ከፋኝ! አንዴ አለሜ በለኝ ብለው ሆዱን ይዞ አይስቅብኝም? ይባላልስ?

«አንቺ ምንድነው የምትፈልጊው?» አለኝ

«አላውቅም! ምን እንደምፈልግ አላውቅም!» አለ አፌ! የምፈልግ የነበረው  ግን ዓለሜ እንዲለኝ ፣ የምፈልግ የነበረው እንደቀኑ የእጄን መዳፍ መሃሉን እንዲስምልኝ፣ እምፈልግ የነበረውማ  ለአንዴ በህይወቴ ጀግና ጀግና የማልጫወትበት ሰው እንዲሆነኝ …….  ለአንዴ ብቻ ፍርሃቴን ፣ ድክመቴን ፣ ማፈሬን ፣ ሽንፈቴን ፣  ….  ከእንባዬ ጋር ለውሼ ደረቱ ላይ እንድተነፍሰው በክንዱ ደግፎ ደረቱ ላይ እንዲያቅፈኝ ….. እፈልግ የነበረውማ ይሄ ያልኩት ሁሉ ሲሆን ዘመናት ቢቆጠሩ ነበር። ቀጥዬ ያልኩት ግን

«ኪዳን አባት ሊሆን ነው!» የሚለውን ነው! ሳልፈልግ ድምፄ ውስጥ መከፋቴ ተሰማብኝ። የያዘውን እጄን ስቦ ወደደረቱ አስጠግቶ ደረቱ ላይ አጥብቆ ያዘው። ይሄ ሰውዬማ ከእጄጋር የሆነ ነገር አለው! ነውስ እጄና ልቤ የሚያገናኛቸው ነገር አለ እጄን የሆነ ነገር ሲያደርገኝ ልቤ አብሮ የሚያሸበሽበው?

«ዳር የተተውሽ መሰለሽ?» ሲለኝ እንባዬ ታገለኝ!! ነግሬዋለሁ? አልነገርኩትም! የተሰማኝን በልከኛው ቃል እንዴት ማስቀመጥ ቻለበት? አንዲት ፊደል ከአፌ ቢወጣ እንባዬ እንደሚያጅበው ስለገባኝ ዓይኖቹን ሸሽቼ ዝም አልኩ። ደረቱ ላይ የያዘውን እጄን እዛው ትቶት በእጁ አገጬን ደግፎ ዓይኖቹን እንዳያቸው አደረገኝ።

«መቼም ቢሆን በምንም የማይተካሽ እህቱ ነሽ!! ሚሽትና ልጁ ያንቺን ቦታ አይጋፉም!! ኪዳንን በዚህ ሁሉ መዓት ፍቅር ስትወጂ ልብሽ ጠቦሽ አባትሽን አስወጥተሻል? ወይሳ እናትሽን? እኔን ወደልብሽ ስታስገቢስ ልብሽ አልበቃ ብሎ ከኪዳን ፍቅር አጎደልሽ? የእርሱን ቦታ ቀነስሽ?»

«አይ!!» ብዬ ጭንቅላቴን በአሉታ ከነቀነቅኩ በኋላ ነውኮ መጨረሻ ላይ ያለውን ለራሴ ደግሜ ስሰማው ዓይኔን የማሳርፍበት የጠፋኝ። ጥሩ እየሰማሁት ነበርኮ ከመጨረሻው እሱን ልቤ ካስገባበት ዓረፍተ ነገር በፊት! <አይ> ያልኩት ምንድነው ቆይ? የኪዳንን ፍቅር ሳታጎድል ነው ልቤ የገባኸው ነው አይደል ያልኩት? የጥያቄው መልስ እንደተመለሰለት ፈገግ ብሎ አገጬ ላይ አውራ ጣቱን አሸት አሸት ነገር አድርጎ እጁን ደረቱ ላይ ወደተወው እጄ መልሶ እንደቅድሙ አጥብቆ ደረቱ ላይ ያዘው።

«ያልኩት ሀቅ አለው?» ብሎ አወነባበደብኝ። ምናለ ዝም ቢለኝ ገብቶት የለ?
«ምኑ?»
«ከልብሽ ገብቻለሁ?»
«አዎ! መሰለኝ! እኔ እንጃ አላውቅም! በምን አውቃለሁ?» በዚህ ነፋሻማ አየር እንዲህ ሊሞቀኝ ይገባ ነበር? ስፈራ ጉልበቴን እንደቁርጥማት እንደሚያደርገኝ ነገር አሁን ሊሰማኝ ይገባ ነበር? ሳቅ እንደማለት ነገር ብሎ

«በይ ተነሽ ሂጅ አሁን እየጠበቀሽ ነው!!» ብሎ እጄን አንስቶ አገላብጦ ይስመው ጀመር!! አንዴ ሁለቴ ሶስቴ ….. ሁለቴ አይበሉባውን አንዴ ወይም ሶስቴ መሃል እጄን…..  እኔ እንጃ አንድ አራቴ ጎኑን …..