Get Mystery Box with random crypto!

ጣቶቼን …… ከመጀመሪያው በኋላ እንኳን ቁጥሩን ላውቀው እንደባለፈው ራሴንም አለመዘንጋቴ በቸርነቱ | ወግ ብቻ

ጣቶቼን …… ከመጀመሪያው በኋላ እንኳን ቁጥሩን ላውቀው እንደባለፈው ራሴንም አለመዘንጋቴ በቸርነቱ ነው። ከዛ ነገና ዛሬዬን ከደባለቀብኝ በኋላማ ምንም እንዳልሆነ ነገር እጄን መለሰልኝ። ማድረግ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበር። ግን ለመሄድ ተነሳሁ እና ወደበሩ መንገድ ጀመርኩ። ልቤማ ደረቴ ውስጥ የለችም! እንጂ ሰውነቴ እንዲህ ወደኋላ ባልጎተተኝ። በሩጋ ደርሼ ዘወር አልኩና

«ነገ እኮ እማዬጋ ልሄድ እችል ይሆናል።» አልኩት ለምን እንዳልኩት ሁሉ እኔ እንጃ! ምናልባት አንድ ደቂቃ እሱጋ መቆያ ምክንያት እየፈለግኩ መሰለኝ።

«ደግ!!» ብቻ ነው ያለው!! እንዴ? ምንድነው ሰው ማግዶ እሪሪሪ እስኪሉ መጠበቅ? ኮስተር እንዳልኩ ለራሴ እየታወቀኝ በሩን ይዤ ቆምኩ!

«ምነው ዓለሜ? የምትነግሪኝ አለሽ እንዴ?» ሲል ከንፈሬ ሳላዘው ሸሽቶ ያለኝ ጥርስ ሁሉ ንፋስ ዳበሰው

«ምንም የለም! ደህና እደር በቃ!» ብዬው ወጣሁ። መኪናው ጋር እስክንደርስ ከኪዳን ጋር ምንም ቃል አልተለዋወጥንም! መጣሁ መጣሁ እያለ እየተናነቀው እንደሆነ ያስታውቅበታል።

«ትከሻሽን መገላመጡን አትርሽ ዓለሜ!» አለ መጨረሻ ላይ ከት ብሎ እየሳቀ

«አፍህን ዝጋ እሺ!! አንድ ነገር እንዳትለኝ!» አልኩት ሳቅም ማፈርም በደባለቀው ቁጣ

«ጀግና ነው ግን ሜል ሙች!! ይፈርምልኝ! ጠባቂ ሆኖ ገብቶ ጠብ ያድርግልኝ? ሜል ገና ስታይው ፍስስ እኮ ነው ያልሽው!»

«ኪዳን ተወኝ አልኩ እኮ!»

«አንዴማ ጨብጬው ልምጣ ሜል ሙች» ብሎ ወደኋላው እንደመመለስ አለ

«ባክህ አርፈህ መኪና ውስጥ ግባ አትጨማለቅ!!»

የማውቀው ገስትሀውስ ደውዬ አልጋ ያዝኩ። መንገዱን ሁሉ ሲያበሽቀኝ እና ሲገረም ዘለቅነው «ምን አባቱ አድርጎሽ ነው ግን ስንቱን ወንድ ያሸና ልብሽን ዘጭ ያደረገው? ፣ እኔንኮ እዛ እንደሌለሁ ረሳችሁኝ ሆ! ፣ እድሜ ደጉ ሜል ስትሽኮረመም ያሳየኝ? ፣ ፍቅር በሀገርኛ ግን ጆሮ ላይ ደስ ይላል አንቺ? ነፍሴን አወክሻትኮ ዓለሜ! ነው ያለው? > አያቆምም ይለፈልፋል። በመሃል

«ሜል ሻምበሉጋ ከአንድ ሰዓት በኋላ እደውላለሁ ካልሽው ሁለት ሰዓት አለፈ!» ሲለኝ ሰዓቴን አየሁት። መርሳቴ እኔንም ኪዳንንም ገረመን!! አንድ ሰው እንዲህ የሰውን ሀሳብ መቆጣጠር ይችላል?

«እኩለለሊት ሊሆን ነው!! ጠዋት ብደውል ይሻላል!!» ስለው ኪዳን አይኑን ጎልጎሎ አውጥቶ አፈጠጠብኝ

«you know am happy for you!! ሜል ነገር አሳደረች? ያውም ሊገድላት የሚከረ ሰው ? ፍቅር ግን ደስ ሲል!!»

«ለምንድነው ግን አፍህን የማትዘጋው?»

ለሁለት ደቂቃ ዝም ይልና ደግሞ ይጀምረኛል። ማረፊያችን ደርሰን የምናወራው ቁምነገር መኖሩን ተኮሳትሬ እስክነግረው ማብሸቁን አላቆመም!!

«አሁን የምር አስጨነቅሽኝ! ምንድነው ንገሪኝ!!» አለኝ አጠገቤ አልጋው ላይ እየተቀመጠ አንድ እጁን እንደማቀፍ ትከሻዬ ላይ ጣል እያደረገ

«እማዬ አልሞተችም! በህይወት አለች!! እና ልታይህ ትፈልጋለች!»

«ማለት?» ብሎ እጁን ከትከሻዬ ላይ አነሳው

«በሰዓቱ ላንተ እውነቱን መንገር ከምትሸከመው በላይ ስለሚሆንብህ ነው ከአጎቴ ጋር ተነጋግረን እንደሞተች የነገርንህ! ታዲያ የታለች ብትለን ኖሮ መልስ አልነበረንም!»

«እና የት ነበረች?» ብሎ ስፈራው እና ስሸሸው የኖርኩትን ጥያቄ ጠየቀኝ። እንዴት ብዬ እንደምነግረው ስጨነቅ

«ሜል ያኔ ህፃን ስለነበርኩ ነው የዋሸሽኝ አሁን ግን ትልቅ ሰው ነኝ ንገሪኝ!!» ብሎ ሲሆን አይቼ እንደማላውቀው ተኮሳተረ። የዛን ቀን ያየሁትን ነገር በሙሉ ነገርኩት። እየጠበቅኩ የነበረው የሚናደድ ወይ ሌላ ጥያቄ የሚያስከትል ነበር። እሱ ግን መጥቶ እያቀፈኝ

«አንቺምኮ ይሄን ሁሉ ብቻሽን የምትሸከሚበት እድሜ ላይ አልነበርሽም!!» አለኝ። ቀጥሎ ግን «አንቺ ትታን ስለሄደች አላዘንሽባትምኣ?» ብሎ ያላሰብኩትን ጥያቄ ጠየቀኝ።

«አላውቅም የኔ ኪዳን! ልጅ እያለን ብዙ ጊዜ ተናድጄባት አውቃለሁ። የምናደደው ግን ትታኝ ከመሄዷ በላይ ካየሁት ነገር በላይ እናትነቷን እንደማይላት እንዴት አልተረዳችልኝም ብዬ ነው! ከውርደቷ በላይ ፍቅሯ እንደሚገዝፍብኝ እንዴት ማሰብ አትችልም ብዬ ነው። ከዛ ግን የዛን ቀን ዓይኗ ውስጥ ያየሁት ህመሟ ከምናደድበት ይበልጥብኝና አንድ ቀን አጊንቻት ባቅፋት ነበር የምመኝ የነበረው»

«እሺ አገኛታለሁ!! ላገኛት ፈልጋለሁ!!» አለኝ።

«ታማለች ኪዳንዬ" አልኩት!እናቱን የማግኘት ተስፋ እንደሰጠሁት ትዝ ሲለኝ ብዙ ከማለሙ በፊት እየተሽቀዳደምኩ ይመስል ተቅለብልቤ

«ታማለች ማለት? የከፋ?»

«አዎን!! ታውቃለህ ለበደሌ እየቀጣኝ ሁሉ መስሎ ተሰምቶኝ ያውቃል! ዓይኗን ደግሜ ባየው ብዬ ዘመኔን የተመኘሁላት እናቴን በመጨረሻ ሳገኛት ለሞቷ ቀናት እየቆጠረች ሆነ።» ከዚህ በኋላ ለረዥም ሰዓት ዝም ተባባልን!! በቃ ዝም! የዛለው ሰውነቴ የተቀመጥኩበት ወደቀ። እግሬን ወደላይ ሰብስቤ ተጋደምኩ።

የነቃሁት የቧንቧ ውሃ ሲወርድ ሰምቼ ነው። ኪዳን ቀድሞኝ ነቅቷል ወይም አልተኛም! አልጋው ጫፍ ላይ እንቅልፍ እንደወሰደኝ ልብስ ደርቦልኛል። ምናልባት እንቅልፍ አልወስድ ብሎት የነበረ ይሆን ብዬ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ። በደቂቃዎች ውስጥ እናትህ አለችም ልትሞትም ነው የሚል መርዶ አርድቼው እኔ እንቅልፌን ስለጥጥ አደርኩ። እናቴን አግኝቻት ልትሞት መሆኑን ሳውቅ ለወራት መቀበል አቅቶኝ የሆንኩትን መሆን አስቤ ያጠፋሁ መሰለኝ። ብቅ ሲል

«ይቅርታ ቀሰቀስኩሽ እንዴ?» አለኝ

«ነግቶ የለ! ምነው እንቅልፍ አልወሰደህም እንዴ?»

«አይ ተኝቻለሁ!» ይበለኝ እንጄ የእኔን ኪዳን መች አጣሁት እንቅልፍ በአይኑ ሳይዞር ነው ያደረው። አስር ጊዜ <ደህና ነህ> እለዋለሁ። <ደህና ነኝ> ይለኛል።

«ማውራት ትፈልጋለህ ኪዳንዬ?»

«አልፈልግም! ዝም ብለን እንሂድ!» አለኝ።

ከመሄዴ በፊት ብዙ ማድረግ የምፈልጋቸው ነገሮች ነበሩኝ። ሆስፒታል ሄጄ ጎንጥን ማየት። ሻለቃው ጋር መደወል፣ ሴትየዋ ማን መሆኗን አውቄ ማግኘት….. ብዙ!! ከኪዳን የሚበልጥ ነገር የለኝም አይደል? እሱ እንዲህ በዝምታ ተለጉሞ የሚሰማውን እንኳን ሳላውቅ ራሴን ማስቀደም አልሆንልሽ አለኝ!! ክፍላችን የመጣውን ቁርስ እንደነገሩ እየለኳኮፍን መኪና ስፈልግ የሚያዘጋጅልኝ ሰው ጋር ደውዬ መኪና እንዲያመጣልኝ ካደረግኩ በኋላ የዳዊትን መኪና ሌላ ቦታ ወስዶ እንዲያቆምልኝ አደረግኩ። ለዳዊት ደውዬ መኪናውን ከቆመበት እንዲወስድ ስነግረው ምንም እንዳልጠረጠርኩ ለመምሰል ከራሴ ታገልኩ። መንገድ ከጀመርን በኋላ ሻንበሉ ደወለ። የመኪናው ባለቤት እና ልትገድለኝ የሞከረችው ሴት የተለያዩ ናቸው። ግን ሁለቱም በስማቸው የማውቃቸው አይደሉም!!

«ቢሮ ብቅ ካልሽ የሁለቱንም ፎቶ ላሳይሽ እችላለሁ!!» ብሎ ስልኩን ዘጋው!! መልዕክቱ አንድም ለመላክ አላምንሽም ነው ሁለትም ፎቶውን ለማየት ተጨማሪ ዋጋ አለው ነው። ስልኩን ዘግቼ ዝም አልኩ! ኪዳንም ምንም አልጠየቀኝም!! ዝምታው አስጨነቀኝ!! ልቤ ድንጋይ የተጫነበት እስኪመስለን ድረስ እንደከበደኝ ተጉዘን ከሰዓታት በኋላ እነእማዬጋ ደረስን!! አጎቴ ከበር እንደተቀበለን ኪዳንን እያገላበጠ ስሞ አልጠግብ አለው!!