2023-06-09 09:10:26
በዋናው ነገር ላይ ማተኮር!
(“ትኩረት” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ)
አንድን እጅግ በጥበብ የላቀን ሰው አገኘሁትና ባለችኝ የጋዜጠኝነት ሙያ ተጠቅሜ መጠየቅ የምችለውን ያህል ለመጠየቅ ሞከርኩ፡፡
ጠቢቡ - “ና ጠጋ በል … ጥያቄ ልትጠይቀኝ እንደፈለግህ ታስታውቃለህ” አለኝ፣ የልቤን ፍላጎት ገምቶ፡፡
እኔ - “ጊዜ ካለህ” አልኩት፡፡
ጠቢቡ (ልብን በሚሰርቅ ፈገግታ) - “ለማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ጊዜ አለኝ” ብሎ መለሰልኝ፡፡
ይህ ጥበበኛ እንዴት ለሰው ሁሉ ጊዜ ሊኖረው ቻለ? እያልኩ ሳወጣና ሳወርድ በፈገግታና በትእግስት ይጠብቀኝ ነበር፡፡
እኔ፡- “ስለ ሰው ፍጥረት ከሚያስገርሙህ ነገሮች መካከል ጥቂቱን ንገረኝ” አልኩት፡፡
ጠቢቡ - • “ልጆች ሳሉ መሰልቸታቸውና ትልቅ ለመሆን መሮጣቸው … ካደጉ በኋላ ደግሞ ልጅ መስሎ ለመታየት መሯሯጣቸው ያስገርመኛል …
• ገንዘብ ለማካበት ጤንነታቸውን ማጣታቸው … ጤናቸውን ለመመለስ ደግሞ እንደገና ያንኑ ገንዘብ ማፍሰሳቸው ያስደንቀኛል …
• ስለ ነገ በመጨነቅ ዛሬን ለመኖር አለመቻላቸውና ከዛሬም ሆነ ከነገ ሳይሆኑ መንከራተታቸው ያስገርመኛል …
• ልክ እንደማይሞት ሰው መኖራቸውና ልክ እንዳልኖረ ሰው ተጽእኖ ቢስ ሆነው መሞታቸው ያስገርመኛል፡፡
ይህን ጠቢብ ዝም ብለው ሌሎች ሃሳቦች እንደሚጨምር እየተሰማኝ በማቋረጥ፣ “ሌላ ጥያቄ ልጠይቅህ?” አልኩት፡፡
ጠቢቡ፡- ደስ በሚያሰኝ ፈገግታ ፈቃደኝነቱን ገለጠልኝ፡፡
እኔ፡- “የሰው ልጅ ሁሉ አባት ብትሆን ለሰው ልጆች እንዲያደርጉ ከምትመክራቸው ነገሮች መካከል ጥቂቶቹን ንገረኝ” አልኩት፡፡
ጠቢቡ (ረዥም ጺሙን ዳበስ ዳበስ በማድረግ ካሰበ በኋላ)፡-
• ማንም ሰው እንዲወዳቸው ማስገደድ እንደማይችሉ፣ ነገር ግን ማድረግ የሚችሉት የሚወደድ ማንነትን ማሳደግ ብቻ እንደሆነ እንዲያወቁ እመክራቸው ነበር፡፡
• መልካም ማንነትንና የተመሰከረለት ማህበራዊ ሕይወት ለመገንባት አመታት እንደሚፈጅ፣ ለማፍረስ ግን አንድ ደቂቃ እንደሚፈጅ እንዲያውቁ አስተምራቸው ነበር፡፡
• የሕይወታችቸውን አቅጣጫ የሚወስነው ያላቸው ንብረትና ሃብት ሳይሆን በሕይወታቸው ያስጠጓቸው የወዳጆች አይነት እንደሆነ እንዲገነዘቡ አሳስባቸው ነበር፡፡
• ታላላቅ ሕልሞችን ለማለምና ከግባቸው ለማድረስ የሚያስፈልገው ታላቅ ሰው መሆን ሳይሆን ከግብ ለመድረስ የቆረጠ ማንነት እንደሆነ እንዲያውቁ የተቻለኝን አደርግ ነበር፡፡
• ሃብታም ሰው ብዙ ገንዘብና ቁሳቁስ ያለው ሰው ሳይሆን የሚያስፈልገውን ነገር ያወቀ ሰው እንደሆነ እንዲያውቁልኝ እጥር ነበር፡፡
• ራሳቸውን ከሌላው ጋር ማነጻጸርና ማወዳደር እንደማይገባቸውና ከእነርሱ የሚያንስ ሰው እንዳለ ሁሉ የሚበልጥም ሰው የመኖሩን እውነታ እንዲቀበሉት አስረዳቸው ነበር፡፡
• አመለካከታቸውን መቆጣጠር እንዳለባቸው አለዚያ አመለካከታቸው እነሱን እንደሚቆጣጠራቸው እንዲማሩ እሞክር ነበር፡፡
• እጅግ በጣም የሚወዷቸውና የሚያከብሯቸው ነገር ግን ያንን በቅጡ ለመግለጽ የማይሆንላቸው ብዙ ወዳጆች እንዳሏቸው አስረዳቸው ነበር፡፡
• እውነተኛ ጓደኛ ማግኘት እጅግ ከባድ እንደሆነ፣ ያንን ያገኘ ግን የሕይወቱን አብዛኛውን ችግሩን እንዳቃለለ እንዲያውቁ እመክራቸው ነበር፡፡
• የቅርብ ወዳጆቻቸውን ለማቁሰል ሰከንድ እንደሚበቃ ለመፈወስ ግን አመታት እንደሚፈጅ እንዲገባቸው እጣጣር ነበር፡፡
• ሰዎችን ለመቆጣጠር በመሞከር እንደሚያጧቸው፣ ምርጫቸውን በማክበር ነጻነታቸውን በመስጠት ግን ለዘለቄታው ወዳጆች እንደሚያደርጓቸው እንዲገነዘቡ ለማድረግ እሞክር ነበር፡፡
• የውስጥ ሰላም ለማግኘት ከሰዎች ይቅርታን ማግኘት ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም ይቅር ማለት እንደሚገባቸው እንዲያስታውሱ አሳስባቸው ነበር፡፡
• ከመናገር በሚቆጠቡበት ነገር ላይ ጌታ፣ በልቅነት ለሚናገሩት ንግግር ደግሞ ባሪያ ሆነው እንደሚኖሩ አሳውቃቸው ነበር፡፡
• እውነተኛ ደስታ የውሳኔ ጉዳይ እንደሆነ፣ በማንነታቸውና ባላቸው ነገር ደስተኛ መሆን፣ አለዚያ በቅንአትና በፉክክር ወጥመድ ውስጥ እንደሚገቡ አስገነዝባቸው ነበር፡፡
• በአጭሩ በዋናው የሕይወት ነገር ላይ ያተኮረ ዝንባሌ ቢኖራቸው እመክራቸዋለሁ፡፡
@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
4.2K views06:10