Get Mystery Box with random crypto!

ሶፋ ወይስ አልጋ? አስፈላጊው ነገር ላይ የማተኮር ምስጢር! “ወሳኙና ትኩረታችንን ልንጥልበት | የስብዕና ልህቀት

ሶፋ ወይስ አልጋ?

አስፈላጊው ነገር ላይ የማተኮር ምስጢር
!

“ወሳኙና ትኩረታችንን ልንጥልበት የሚገባው ነገር ሰው የሚያይልንና የሚያደንቅልን ነገር ላይ ሳይሆን ለሕልውናችንና ለእድገታችን አስፈላጊ የሆነው ጉዳይ ላይ ሊሆን ይገባዋል”

የትኩረት አስፈላጊነት የገባቸው ሰዎች የሰዎችን አድናቆት ከማግኘት የዘለለ የሕይወት ዘይቤ ያዳበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ሰዎች አይተውላቸው “ደስ ይላል” ብለው የሚያደንቁላቸውን ነገራቸውን የማስዋብን አስፈላጊነት ባይክዱም ከዚያ የበለጠ ትኩረት የሚገባው ነገር ግን ለእድገታቸውና ለሕልውናቸው ወሳኝ የሆነው ነገር እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ ትኩረታቸውም በዚያ ላይ ነው፡፡  

አንድ ሰው በሚኖርበት ማሕበረሰብ አካባቢ አንድን ጥናት ማድረግ ፈለገ፡፡ ከጥናቱ ሊያገኝ የፈለገው እውነታ ይህንን ይመስላል፡፡  በአንድ በኩል ትኩረታቸው ከላይ ለሰዎች የሚታየውን ብቻ ቀባ ቀባ ማድረግ የሆነና ለታይታ ብቻ የሚኖሩ ሰዎችን የሕይወት ሁኔታ ማወቅ ፈለገ፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ለታይታ ብቻ ሳይሆን በትክክለኛውና በሕይወት ላይ ለውጥ በሚያመጣው ነገር ላይ የሚያተኩሩ ሰዎችን ሁኔታ መገንዘብ ተመኘ፡፡ ይህንን ሁኔታ በቀላሉ ለማወቅ የሚችልበትን ዘይቤ ሲፈልግ አንድ ነገር ብልጭ አለለት፡፡

በየሰፈሩ እየተዘዋወረ ፈቃድን ባገኘበት ቤት ሁሉ እየገባ አንድን ጥያቄ መጠየቅ ጀመረ፡፡ ጥያቄው አጭርና ግልጽ ነበር፡- “በቤትዎት ካለው ሶፋ እና አልጋ በዋጋ የትኛው ይበልጣል? እነዚህንስ እቃዎች ሲገዙ ብዙ ትኩረት የሰጡበት የትኛውን ነው? ብዙ ዋጋ ላወጡበት እቃስ ያንን ያህል ዋጋ እንዲያወጡ ያነሳሳዎት ምንድን ነው?” የሚል ነበር፡፡ እነዚህን ሶስት ጥያቄዎች ከጠየቀ በኋላ የሰዎቹን የአኗኗር ሁኔታ በቀስታ ያጤን ነበር፡፡ በመቶ የሚቆጠሩ ቤቶችን በመጎብኘት ይህንን መጠይቅ ለማቅረብና መረጃ ለመሰብሰብ ወደ አንድ አመት ፈጅቶበታል፡፡ በመጨረሻ ያገኘው መልስ ሲጨመቅ አስገራሚ ስእል አመላከተው፡፡

በዚህ ጥናታዊ መጠይቅ ላይ ከተሳተፉት ሰዎች አብዛኛዎቹ ለገዙት አልጋ ካወጡት ዋጋ ይልቅ በብዙ እጥፍ የከፈሉት ለሶፋቸው ነበር፡፡ ከዚህ በላይ ግዢውን ሲፈጽሙ ብዙ አማራጭ ለማግኘት ጊዜን የወሰዱትና ብዙ ሰው ያማከሩበት እቃ ሶፎውነበር፡፡ አልጋ ለመግዛት ካወጡት ገንዘብና ለምርጫ ካሳለፉት ጊዜ ይልቅ በሶፋ ላይ የበለጠ ገንዘብና ጊዜ የማውጣታቸውን ምክንያት ሲጠየቁ የሰጡት መልስ ሲጨመቅ፣ “ሰዎች ሲገቡ የሚያዩት ሶፋውን ስለሆነ ነው፣ አልጋውንማ ማን ያየዋል?” የሚል ነበር፡፡

ግኝቱ ይህ ነው፡- አንድ ሰው በቀን ውስጥ በአማካኝ ሰባት ወይም ስምንት ሰዓታትን በአልጋው ላይ ያሳልፋል፡፡ በቀን በሶፋው ላይ ተቀምጦ የሚያሳልፈው ጊዜ ግን በአማካኝ ከሶስትና ከአራት ሰዓት በላይ አይሆንም፡፡ ስምንት ሰዓታት ሰውነቱን ጥሎበት የሚያሳልፈው ይህ አልጋ የተሰኘው ነገር በአካላዊ ጤንነቱ ላይ ይህ ነው የማይባል ስፍራ አለው፡፡ በተጨማሪም ከማይመች አልጋ የሚመጣ የእንቅልፍ ማጣት ችግር ለቀን ተግባር ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑም እሙን ነው፡፡

አስፈላጊ ከሆኑት  በሕልውናችንና በስኬታማነታችን ላይ ዘላቂ ተጽእኖ ከሚያመጡት የሕይወታችን ጉዳዮች ላይ ትኩረታችንን ማንሳት ብዙ አሉታዊ ተጽእኖዎች አሉት፡፡ እንዲህ አይነቱ አካሄድ ከታይታ ወደማያልፉ ነገሮች እንድንዞርና ብዙ ውድ ነገሮቻችንን እንድናባክን አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ ለምሳሌ ጊዜአችንን፣ ገንዘባችንንና ሃሳባችን በተለያዩ ጊዜአዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የመበታተን የሕይወት ዘይቤ ውስጥ እንገባለን፡፡ ትኩረቱን ከጊዜአዊውና ለታይታ ከሆነው ነገር ላይ በማንሳት ወደ አስፈላጊውና ወደ ዘላቂው ነገር ያዞረ ሰው ለጊዜው ሰዎች አይተው የሚያደንቁለት ነገር ባይኖረውም እንኳ ለነገ እንደሚሰራ ያውቀዋል፡፡

የሚታየውንና ጥቅሙ ውስን የሆነውን የኑሮአችንን ሁኔታ ከማይታየውና ጥቅሙ እጅግ የላቀ እንዲሁም ደግሞ ዘላቂ ከሆነው ሁኔታ ለመለየት ልናስታውሳቸው የምንችላቸው እውነታዎች አሉን፡፡ ምናልባት ለረጅም አመታት ከለመድነው የኑሮ ዘይቤ ለመላቀቅ ከባድ ቢሆንም እንኳ የማይቻል አይደለምና ዛሬውኑ ጉዞውን መጀመር እንችላለን፡፡

1.  ከስውር የዝቅተኝነት ስሜት ተላቀቅ:- ለታይታ ለመኖር የመጣጣር አንዱ ምንጭ የዝቅተኝነት ስሜት ነው፡፡ ከሌሎች በታች የሆንን ሲመስለንና በዚህ ስሜት በስውር ስንጠቃ አውቀነውም ሆነ ሳናውቀው ራሳችንን ከሌላው ለማስተካከል ወይም የበለጥን እንደሆንን ለማሳየት ስንጣጣር እንታያለን፡፡

2.  የትርጉም ማስተካከያ አድርግ:- ትክክለኛ ኑሮ ማለት እኛ ሲመቸን እንጂ በእኛ ሁኔታ ሌላው ሲገረም ማለት አይደለም፡፡ ዘላቂ ስኬት ማለት እኛ ተመችቶን ለሌላው ስንተርፍ እንጂ ኑሮአችን ወድቆ በውጫዊው “ውበታችን” ሌላው ሲገረም ማለት አይደለም፡፡

3.  የእቅድ ሰው ሁን:- ከሰው ጋር መወዳደርን አቁምና ለራስህና ለቤተሰብህ መሻሻል ካወጣኸው እቅድ አንጻር መሮጥ ጀምር፡፡ ትክክለኛ ስኬት ማለት የት መድረስ እንደሚፈልጉ ማወቅና በዚያ አቅጣጫ በመገስገስ፣ በሂደቱም መርካት ማለት ነው፡፡

ዶ/ር እዮብ ማሞ