በዋናው ነገር ላይ ማተኮር! (“ትኩረት” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ) አንድን እጅግ በጥበብ የላቀን ሰው አገኘሁትና ባለችኝ የጋዜጠኝነት ሙያ ተጠቅሜ መጠየቅ የምችለውን ያህል ለመጠየቅ ሞከርኩ፡፡ ጠቢቡ - “ና ጠጋ በል … ጥያቄ ልትጠይቀኝ እንደፈለግህ ታስታውቃለህ” አለኝ፣ የልቤን ፍላጎት ገምቶ፡፡ እኔ - “ጊዜ ካለህ” አልኩት፡፡ ጠቢቡ (ልብን በሚሰርቅ ፈገግታ) - “ለማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ጊዜ አለኝ” ብሎ መለሰልኝ፡፡ ይህ ጥበበኛ እንዴት ለሰው ሁሉ ጊዜ ሊኖረው ቻለ? እያልኩ ሳወጣና ሳወርድ በፈገግታና በትእግስት ይጠብቀኝ ነበር፡፡ እኔ፡- “ስለ ሰው ፍጥረት ከሚያስገርሙህ ነገሮች መካከል ጥቂቱን ንገረኝ” አልኩት፡፡ ጠቢቡ - • “ልጆች ሳሉ መሰልቸታቸውና ትልቅ ለመሆን መሮጣቸው … ካደጉ በኋላ ደግሞ ልጅ መስሎ ለመታየት መሯሯጣቸው ያስገርመኛል … • ገንዘብ ለማካበት ጤንነታቸውን ማጣታቸው … ጤናቸውን ለመመለስ ደግሞ እንደገና ያንኑ ገንዘብ ማፍሰሳቸው ያስደንቀኛል … • ስለ ነገ በመጨነቅ ዛሬን ለመኖር አለመቻላቸውና ከዛሬም ሆነ ከነገ ሳይሆኑ መንከራተታቸው ያስገርመኛል … • ልክ እንደማይሞት ሰው መኖራቸውና ልክ እንዳልኖረ ሰው ተጽእኖ ቢስ ሆነው መሞታቸው ያስገርመኛል፡፡ ይህን ጠቢብ ዝም ብለው ሌሎች ሃሳቦች እንደሚጨምር እየተሰማኝ በማቋረጥ፣ “ሌላ ጥያቄ ልጠይቅህ?” አልኩት፡፡ ጠቢቡ፡- ደስ በሚያሰኝ ፈገግታ ፈቃደኝነቱን ገለጠልኝ፡፡ እኔ፡- “የሰው ልጅ ሁሉ አባት ብትሆን ለሰው ልጆች እንዲያደርጉ ከምትመክራቸው ነገሮች መካከል ጥቂቶቹን ንገረኝ” አልኩት፡፡ ጠቢቡ (ረዥም ጺሙን ዳበስ ዳበስ በማድረግ ካሰበ በኋላ)፡- • ማንም ሰው እንዲወዳቸው ማስገደድ እንደማይችሉ፣ ነገር ግን ማድረግ የሚችሉት የሚወደድ ማንነትን ማሳደግ ብቻ እንደሆነ እንዲያወቁ እመክራቸው ነበር፡፡ • መልካም ማንነትንና የተመሰከረለት ማህበራዊ ሕይወት ለመገንባት አመታት እንደሚፈጅ፣ ለማፍረስ ግን አንድ ደቂቃ እንደሚፈጅ እንዲያውቁ አስተምራቸው ነበር፡፡ • የሕይወታችቸውን አቅጣጫ የሚወስነው ያላቸው ንብረትና ሃብት ሳይሆን በሕይወታቸው ያስጠጓቸው የወዳጆች አይነት እንደሆነ እንዲገነዘቡ አሳስባቸው ነበር፡፡ • ታላላቅ ሕልሞችን ለማለምና ከግባቸው ለማድረስ የሚያስፈልገው ታላቅ ሰው መሆን ሳይሆን ከግብ ለመድረስ የቆረጠ ማንነት እንደሆነ እንዲያውቁ የተቻለኝን አደርግ ነበር፡፡ • ሃብታም ሰው ብዙ ገንዘብና ቁሳቁስ ያለው ሰው ሳይሆን የሚያስፈልገውን ነገር ያወቀ ሰው እንደሆነ እንዲያውቁልኝ እጥር ነበር፡፡ • ራሳቸውን ከሌላው ጋር ማነጻጸርና ማወዳደር እንደማይገባቸውና ከእነርሱ የሚያንስ ሰው እንዳለ ሁሉ የሚበልጥም ሰው የመኖሩን እውነታ እንዲቀበሉት አስረዳቸው ነበር፡፡ • አመለካከታቸውን መቆጣጠር እንዳለባቸው አለዚያ አመለካከታቸው እነሱን እንደሚቆጣጠራቸው እንዲማሩ እሞክር ነበር፡፡ • እጅግ በጣም የሚወዷቸውና የሚያከብሯቸው ነገር ግን ያንን በቅጡ ለመግለጽ የማይሆንላቸው ብዙ ወዳጆች እንዳሏቸው አስረዳቸው ነበር፡፡ • እውነተኛ ጓደኛ ማግኘት እጅግ ከባድ እንደሆነ፣ ያንን ያገኘ ግን የሕይወቱን አብዛኛውን ችግሩን እንዳቃለለ እንዲያውቁ እመክራቸው ነበር፡፡ • የቅርብ ወዳጆቻቸውን ለማቁሰል ሰከንድ እንደሚበቃ ለመፈወስ ግን አመታት እንደሚፈጅ እንዲገባቸው እጣጣር ነበር፡፡ • ሰዎችን ለመቆጣጠር በመሞከር እንደሚያጧቸው፣ ምርጫቸውን በማክበር ነጻነታቸውን በመስጠት ግን ለዘለቄታው ወዳጆች እንደሚያደርጓቸው እንዲገነዘቡ ለማድረግ እሞክር ነበር፡፡ • የውስጥ ሰላም ለማግኘት ከሰዎች ይቅርታን ማግኘት ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም ይቅር ማለት እንደሚገባቸው እንዲያስታውሱ አሳስባቸው ነበር፡፡ • ከመናገር በሚቆጠቡበት ነገር ላይ ጌታ፣ በልቅነት ለሚናገሩት ንግግር ደግሞ ባሪያ ሆነው እንደሚኖሩ አሳውቃቸው ነበር፡፡ • እውነተኛ ደስታ የውሳኔ ጉዳይ እንደሆነ፣ በማንነታቸውና ባላቸው ነገር ደስተኛ መሆን፣ አለዚያ በቅንአትና በፉክክር ወጥመድ ውስጥ እንደሚገቡ አስገነዝባቸው ነበር፡፡ • በአጭሩ በዋናው የሕይወት ነገር ላይ ያተኮረ ዝንባሌ ቢኖራቸው እመክራቸዋለሁ፡፡ @Human_Intelligence @Human_Intelligence 4.2K views06:10