Get Mystery Box with random crypto!

ጊዜ እንዳለኝ እያሰብኩ ነበር — እንደምኖር። በመጻሕፍት መደርደሪያዬ እኔን መጠበቅ ያደከማቸው | የስብዕና ልህቀት

ጊዜ እንዳለኝ እያሰብኩ ነበር — እንደምኖር።

በመጻሕፍት መደርደሪያዬ እኔን መጠበቅ ያደከማቸው ያልተነበቡ መጻሕፍት ተገጥግጠዋል።

አንድ ቀን እንደማነባቸው ተስፋ ሳደርግ ምጽዓት ደረሰ —ሀገሬ። በሲዖል ውስጥ መጽሐፍ ማንበብ አይቻልም። አንደኛ ሀገሩ የእሳት ነው። በእሳት ሀገር ወረቀት ቀለም ይዞ አይቆይም። ይነዳል፥ አመድ ይሆናል። ብዙ ጩኸት አለ —ሰቆቃ። እና አይመችም። ዙሪያው ገደል ነው። ልብ ዝቅ ያደርጋል።

ቀን በቀን መጻሕፍቴን እየተሰናበትኩ ነበር። ምን ትርጉም አለው? ሳልፈልግ አእምሮዬ እንደተረበሸ ከተማ ሐሳብ ይጎሎጉላል።  በሥነ ሥርዓት ላጠነጥን እሞክራለሁ —መሥመር ላስይዝ። ግን አልችልም ይሳከርብኛል። አንጎሌ፥ ሰውነቴ ይሰንፋል። 

የምናደርገው ነገር ትርጉም መስጠት ያቆመበት በሚመስልበት ጊዜ ላይ ነን። እዚህ ሀገር ልጅ እንወልዳለን። የምናወርሰው ሀገር ግን ሲዖል ነው። ምሽቶች ባሎቻቸው ድንገት በወጡበት ይቀራሉ። ይታፈናሉ፥ ይታገታሉ። ልጆች ያልጠገቡትን፥ በውል ያለዩትን አባቶቻቸውን ባልጠበቁት ቅጽበት ይሰናበታሉ። ለሀገራቸው ውለታ የዋሉ ዋርካ ሰዎች በልጅ እግሮች ይገደላሉ። ደም ይፈሳል —በየመንገዱ፥ በየጫካው።  አድባራት አንድ ባንድ ይፈርሳሉ። ማንም ምንም ማምጣት የሚችል አይመስልም። ድንገት ኢምንትነት እንዲሰማህ ትሆናለህ።

ሞት እየጠራህ ትማራለህ? ሞት እያነፈነፈህ ታከማቻለህ? በደጅህ ሞት እያደባ ታገባለህ? ሀገር እየተቃጠለ ትሰርጋለህ? ቆንጆ ቆንጆ ልጆች የጥይት እራት እንዲሆኑ ትወልዳለህ? መሣሪያ የታጠቀ ወንበዴ ቤትህን እየሠረሠረ ታንቀላፋለህ? ዳሩ ብትነቃስ ምን ታደርጋለህ? የዓለም ምጽዓት አንተ ጋር እስከሚደርስ ብትተኛ አይከፋም፥ ብትማር፥ ብትቆጥብ፥ ብታገባ፥ ብትወልድ።

ሀገሩ የባለጌ ነው። ማን ጌታ እንደሆነ አይታወቅም። በመንገድ ስታልፍ ረግጦህ የገላመጥከው ሰው ዘመደ ብዙ ነው። የጦር መሣሪያ አለው። ባታውቀውም የጎበዝ አለቃ ነው። ትንሽ መንግሥት ነው። ሕይወትህን ከአፈር ይደባልቀዋል። ያየህ እስከማይገኝ ድረስ ድራሽህ ይጠፋል። ወዝህ ያስቀናው ሰው ዳር ሊያስይዝህ ይችላል።

ሀገርህ ከየት እስከየት እንደሆነ አታውቅም። እግርህ ከቤት ወጣ እንዳለ የጠላት ሀገር ነህ። በካርታ ባይከለልም የተበጀ ድምበር አለ። ድንገት  ትጨመደዳለህ፥ እጅ ትሰጣለህ። ብትማረክም ትገደላለህ። ከቀን ውሎህ ተርፈህ፥ በሰላም ወጥተህ ከገባህ እድለኛ ነህ።  ከሄድክበት ስትመለስ ቤትህን በገነባህበት ስፍራ ላታገኘው ትችላለህ። ማንንም መርዳት አትችልም። ግፍና መከራ ተንከባሎ በሁሉም ቤት ይደርሳል። እስከዚያው ግን ተራው ያንተ ከሆነ ያንተ ነው። ትከሻህን ማስፋት፥ መቻል፥ መቀበል ይጠበቅብሃል። እውነት አይመስልም አይደል? ትላንት በእቅፍህ የነበረ ሰው እንደወጣ ሲቀር? ደብዛው ሲጠፋ?? ግን ይህ የብቻህ እውነት ነው። ይህ የብቻህ ሕመም ነው —ጽና።


እ. . .


ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን በሌላ አውድ የጻፈው አንድ ግጥም አለ። ያለ ዐውዱ እዚህ ጋር እንድጠቀመው ይፈቀድልኝ፦

“...ተገልለህ ርቀህ
እውነት ይተዉኛል ብለህ
እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?! . . . .
ተስፋ አድርገህስ ምን ልትሆን ፡ ወይስ ተስፋው ምን ሊሆንህ ?
እንቅልፍ እንጂ እሚያስወስድህ።”


እሱባለው አበራ

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence