Get Mystery Box with random crypto!

መሰውር - ኘሌቶ ምንጭ ፦ ፍልስፍና (ከዘርዐ ያዕቆብ እስከ ሶቅራጠስ) ፀሀፊ ፦ ፍሉይ አለም በ | የስብዕና ልህቀት

መሰውር - ኘሌቶ

ምንጭ ፦ ፍልስፍና (ከዘርዐ ያዕቆብ እስከ ሶቅራጠስ)
ፀሀፊ ፦ ፍሉይ አለም

በመንገድህ ላይ አንዲት አሮጊት አጋጠመችህ፤ እናም ይህቺ ሴት ትንሽ፣ ግን እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነን ስጦታ ሰጠችህ - አስማተኛ ቀለበት!

ይህም ቀለበት አንተን ለሌሎች እንዳትታይ አድርጎ ይሰውርሃል፤ ወደፈለግከው ስፍራ መጓዝ ትችላለህ፤ ማንም ሰው አንተን ማየት አይችልም፡፡

ጥያቄውም ይህ ነው በዚህ ቀለበት ምን ታደርጋለህ? ይህን አስማታዊ ኃይል እንዴት ትጠቀመዋለህ?

“የጋይጂ ቀለበት” ሪፐብሊክ በተሰኘው የፕሌቶ ዘመን አይሽሬ ስራ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ መጽሐፉ የፕሌቶ ታላቅ ወንድም ስለሆነውና ግላውኮን ጋይጂ ስለተባለ አንድ ተራ በግ ጠባቂ ታሪክ ይነግረናል።

ይህ እረኛ ከክርስቶስ መወለድ ሰባት መቶ አመታት በፊት የሊድያ ግዛት ተብላ በምትጠራው ስፍራ ይኖር ነበር፡፡ (ይህን ግዛት አሁን ላይ በቱርክ ውስጥ እናገኘዋለን።)

ፕሌቶ ታሪኩን እንዲህ ይተርከዋል፡-

ከእለታት በአንዱ ቀን በእጅጉ ሃይለኛ
የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ በሊድያ ግዛት ውስጥ ተከሰተ፡፡ በምድር ገጽ ላይም ትልቅ መሰንጠቅ ተፈጠረ፡፡ በስንጥቁ መሃልም እረኛው ጋይጂ አንድ የተደበቀ ዋሻ ተመለከተ፡፡ በዋሻው ውስጥም ጋይጂ ከነሐስ የተሰራ የፈረስ ሐውልት አገኘ፡፡ በዚህ ሐውልት ውስጥ በከፊል የበሰበሰ የአንድ ግዙፍ ሰው ሙት አካል ይገኝበት ነበር፡፡ በአስክሬኑ የቀኝ እጅ አንደኛው ጣት ላይም ወርቃማ ቀለበት ያብረቀርቅ ነበር፡፡ እናም ጋይጂ ይህንን ቀለበት ለራሱ ወሰደው፡፡

እረኛው ይህ ቀለበት ተራ ቀለበት እንዳልነበረ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ በቀለበቱ አናት ላይ ያለችውን ጌጥ ሲያሽከረክራት፣ ጋይጂ ሰው እንዳያየው ሆኖ ተሰወረ፡፡ ቀለበቱ ለጋይጂ የመሰወርን ኃይል ሰጠው።

አስደናቂ የመሰወር ኃይልን እንዳገኘም፣ ይህ ተራ የበጎች እረኛ ወደ ቤተ መንግስት ቅጥር ዘለቀ፡፡ በዚያን ዕለት ምሽትም ከንግስቲቷ ጋር ተኛ፡፡ ንጉሱንም ገደለው፡፡ ንግስናንም ተቀበለ፡፡ እናም ራሱን የሊድያ ግዛት ገዢ አድርጎ ሾመ።

ፕሌቶ በዚህ ታሪክ ውስጥ ለማስተላለፍ የሞከረው ዋነኛ ሃሳብ ቢኖር ይህ ነው ሰዎች መጥፎ ድርጊቶችን የማያደርጉት ብያዝስ በሚል ፍራቻ ነው።

ሙሉ ለሙሉ የማንታይበት እና የምንሰወርበት ኃይል ቢኖረን - ከውርደት፣ ከመያዝ አልያም ከመታየት ፍራቻ እንላቀቃለን፡፡ ፕሌቶም - የመሰውርን ኃይል ያገኘ እና የሌላን ሰው ንብረት ላለመዝረፍ ያሰበ አልያም መጥፎ ተግባርን መፈጸም ያልፈለገ ቢኖር፣ እርሱ የአለማችን ሞኝ ሰው ነው' ይለናል፡፡

አንተስ የመሰወር ኃይል ቢኖርህ ምን ታደርጋለህ?

በአጠገብህ ያለ ጓደኛህን ጠይቀው፤ ራስህንም ጠይቅ፡፡

የሚያስገርም፣ የሚያስቅ አልያም የሚያሳቅቅ ምላሽን ታገኛለህ ። እናስ የመሰውር ኃይል ቢሰጥህ ባንክ ቤት አትዘርፍም? ልክ እንደ ጋይጂ ወደ ቤተመንግስት ለመግባት አትሞክርም? ከዚህም ሲከፋ ለመናገር የሚከብዱ ወንጀሎችንስ አትፈጽምም?

እናም... እኛን ወንጀልን ከመፈጸም የከለከለን ነገር ቢኖር “ሰው ምን ይለኛል' የሚለው ሃሳብ ብቻ ነው።

የፕሌቶ 'ሰዎች መልካም የሚሆኑት በምርጫቸው ሳይሆን ተገደው ነው' የሚለው ሃሳብ ለዘመናት ብዙ ፈላስፋዎችን አጨቃጭቋል። ሆኖም ይህ የጋይጂ ቀለበት ከሁለት ሺ አመታት በላይ ያስቆጠረ አፈ-ታሪክ ቢሆንም፣ ከምንግዜም በላይ አሁን ላይ ላለነው ሰዎችም የሚሰራ ምሳሌ ነው።

ለምሳሌ፤ ትክክለኛ ማንነታቸውን የማይገልጽ የፌስቡክ አካውንት ያላቸው ግለሰቦች፣ ማን እንደሆኑ አይታወቁምና እጅግ በዘቀጠ ሁናቴ ጸያፍ ስድቦችን ሲወራወሩ አልያም ጠብ አጫሪ እና በህግ ሊያስጠይቋቸው የሚችሉ የጥላቻ ንግግሮችን ሲዘሩ ይውላሉ፡፡

ሌላ ምሳሌ የሚሆነን እና የዘመናዊው ዓለም የመሰውር ቀለበት የሆነው ገንዘብ ነው፡፡ አስተውለህ ከሆነ የናጠጡ ሃብታሞች ምን ያህልም ጥፋት ቢያጠፉ ከህግ አይን የሚሰውራቸው ኃይል አላቸው፡፡ በገንዘባቸው ከምንም አይነት የወንጀል ውንጀላ ነጻ ይሆናሉ፡፡ ይህ ደግሞ በእጅጉ ጨካኝ የሆኑ እና ስለ ሌላው ግድ የሌላቸውን ህሊና አልባ ሰዎችን ፈጥሯል።

@Zephilosophy
@Zephilosophy