2023-04-08 20:38:54
#ዘንባባ_እና_ሆሣዕና
✠. ✠ ✠ .✠
ሙሽራይቱ የሆነችውን ቅድስት ቤተክርስቲያኑን መሠረት ሆኖ ያጸናት ፣ ራስ ሆኖ የሚገዛት ፣ በደሙም የዋጃትና አካሉ ሆና ያከበራት ክርስቶስ እንኳን ለዘንባባው በዓል አደረሳችሁ። ሆሣዕና በአርያም
የቅዱስ ቀሌምንጦስ ዘሮምን ምስክርነት መነሻ እናድርግ "ቤተክርስቲያን እንቲአነ ፍሬሃ ከመ በቀልት እንዘ አሐቲ ለሊሃ ወብዙኃት ሕንባባቲሃ … የእኛ የሆነች ቤተክርስቲያን ፍሬዋ እንደዘንባባ ፍሬ ነው ለራሷ አንዲት ስትሆን ቅርንጫፎቿ ብዙዎች ናቸው" 【ቀሌ. ፰፥፷፯】
ዘንባባ የሚለው ቃል ሰሌን፣ ጸበርት/ፀመርት ፣ ተምር፣ በቀልት … የሚሉትን ሁሉ ተክቶ የተነገረ ነው። ይሆንና ግን በቀልት የሚለው ግንዱን ፀመርት ደግሞ ቅጠሉ ሲሆን ተምር ፍሬው እንደሆነ መተርጉማን ያስረዳሉ።
በዚህ መንገድ ዘንባባ የሚለው ፍሬው ተዘርቶ የሚበቅል ቁመታም ሰሌን የቴምር ዛፍ ግእዙ በቀልት እያለ የሚጠራው ነው።
በእብራይስጡ ደግሞ ተምር (תָּמָר) ወይም ቶሜር (תֹּמֶר) የሚለው የቴምር ዛፍ ዘንባባን ወክሎ የሚነገር ሲሆን በግሪኩም ፎይኒክስ (φοῖνιξ) የሚለው የዘንባባ ዛፍን ወክሎ ተነግሯል።
በምሥጢር ግን ዘንባባ ራሱ ሆሳዕና ተብሎም ተጠርቷል!
ለምሳሌ ለቅዱስ ማቴዎስ ክርስቶስ በአምሳለ ወሬዛ(ወጣት) ተገልጾለት ካህናተ ጣዖት ወዳሉበት ሀገር ሲገባ ምን ማድረግ እንዳለበት ሲነገረው ሆሣዕና በእጅህ ያዝ እንዳለው ስንክሳራችን ይነግረናል ይህንንም ዘንባባ ነው ሲል መልሶታል።
“አንተሰ ኢትክል ከመ ትባእ ውስተ ዛቲ ሀገር ዘእንበለ ትላፂ ርእሰከ ወጽሕመከ ወዘእንበለ ትእኅዝ ሆሳዕና በእዴከ … አንተ ግን ጽሕምህን (ፂምህን) ካልተላጨህ በእጅህም ሆሣዕና/ ዘንባባ ካልያዝክ መግባት አትችልም”【ስንክሳር ጥቅምት ፲፪ ቁጥር ፲፫ 】
ይህንንም ሊቁ አባ ጊዮርጊስ እየደጋገመ ለእመቤታችን ምሳሌ አድርጎ አስታውሶታል።
☆ በኆኅተ ብርሃን "ወደ ካህናቱ በገባ ጊዜ ለማስተማር የያዛት የማቴዎስ የሰሌን ዘንባባ አንቺ ነሽ… "
☆ በመዓዛ ቅዳሴም "የእንድርያስ የሕይወቱ መርከብ፣ ለያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ የስብከቱ መጽኛ፣ ብፁዕ ለሚሆን ለማቴዎስም የምልክቱ ዘንባባ የምትሆኚ ማርያም ሆይ ነዪ"
#ሆሣዕና ለሚለው ቃል የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ ሆሳና (ὡσαννά) የሚለውን የጽርእ ቃል ቀጥታ ይጠቀመው እንጂ መነሻው የእብራይስጡ «ሆሺዓህናእ» የሚለው ጥምር ቃል ነው። ይህም ሆሺዓህ (יָשַׁע) ናእ (נָא) ከሚሉት ሁለት ቃላት የተገኘ ነው።
ትርጉሙም ሆሺዓህ= አድን፣
ናእ ደግሞ አሁን/እባክህ/አቤቱ በሚለው ይገለጻል።
☞ አሁን አድን ፣ እባክህ አድን፣ አቤቱ አድን ማለት ነው።
ዘንባባ በሕይወታችን ስላለው ትርጉም ውዳሴ አምላክ የቀዳሚት ምንባብ ይህን ይላል "መልካም ፍሬን እንደምታፈራ እንደ ሰሌን ሥር ጽናት በልቡና ጽናትና በነፍስ ዝምታ በቦታዬ ትከለኝ" ከዚህ ጸሎት በመንፈሳዊው ሕይወት የዘንባባን ሃይማኖታዊ መገለጫ በሥሩ ጽናት ከቦታ አለመናወጽ ለነፍስ አለመታወክ ምሳሌ ሆኖ መጠቀሱን እንረዳለን። ውኃ በሌለበት በረሐ እየበቀለ ባለ ፍሬ መሆኑ መከራ በበዛበት ዓለም እየኖሩ ፣ በተኩላዎች መኃል እንደበግ ተልከው ስለእውነት እየመሰከሩ ፣ በመልካም ምግባር ጸንተው ፍሬ ላፈሩ… ጽኑዓን መስተጋድላን ሁሉ ምሳሌ ሆኖ ይነገራል።
በቅዱስ መጽሐፍ ዘንባባ ያለውን ቦታ መረዳት እንድንችል ተከታዮቹን ተጨማሪ ታሪኮች እንመልከት ፦
✧ ታላቋ ባለቅኔ ሴት ዲቦራ በእስራኤል ላይ ስትፈርድ ትቀመጥ የነበረው ከዘንባባ በታች ነው። ዛፉም በስሟ ይጠራ እንደነበር መጽሐፍ እንዲህ ሲል ዘግቦልናል “እርስዋም በተራራማው በኤፍሬም አገር በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዛፍ ከሚባለው ከዘንባባው በታች ተቀምጣ ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እርስዋ ለፍርድ ይወጡ ነበር።” 【መሳ ፬፥፭】
✧ በኦሪቱ መቅደስ ጠቢቡ ሰሎሞን እንዲቀርጽ (እንዲሥል) ከታዘዙት ሦስት ሥዕላት ውስጥ ሥዕለ ኪሩብ የፈነዳ አበባ እና የዘንባባ ዛፍን ነው። 【፩ኛ ነገ. ፮፥፳፱–፴፯】
✧ ታላቁ የዜና አይሁድ ታሪክ ጸሐፊ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን (Flavius Josephus / Yoseph Ben Mattithyahu) በዜና አይሁድ በሦስተኛው ክፍል በ፳፱ኛው ምዕራፍ ስለ ልማደ አይሁድ ሲዘግብ «በቂጣ በዓል ላይ የደስታና የክብር መገለጫ አድርገው በዘንባባ ዝንጣፊ የመማታት ጨዋታን እንደ ሕግና ልማድ ይፈጽሙት ነበር» ይላል።
✧ ሌላው በአይሁድም በሮማውያንም ዘንድ ዘንባባ ያለው ተምሳሌታዊ ሥፍራ ትልቅ ነው። ለድል አድራጊዎች በእምነታቸው ለጸኑትና ለሰላም አብሳሪዎች እንደ መገለጫ ሆኖ ያገለግላል። በተለይ ነቢያቱ የሰላም ዘመን እንዲመጣ ለሕዝቡ ለማብሰር በአሕያ ላይ ተቀምተው የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ወደ ከተማ ሲገቡ ይታዩ ነበር ፤
ቅዱስ መጽሐፋችንም ድል ነሺዎች የክብራቸው መገለጫ አድርገው በሰማዩ መቅደስ ዘንባባ ይዘው መገለጣቸውን እንዲህ ሲል ይመሰክርልናል።
“ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤” 【ራእ ፯፥፱】
በምሳሌነቱም ዘንባባ (በቀልት) የኢየሱስ ክርስቶስ ፣ የድንግል ማርያምና የሌሎቹም ቅዱሳን ጻድቃን ወኪል ሆኖ በየአገባቡ ሲመሰገኑበትና ክብራቸው ሲገለጥበት እንመለከታለን።
. . ዘንባባ = ክርስቶስ
『 ስነ ቆምከ በቀልት ወመልክእከ ሕይወት ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አምደ ሃይማኖት፣ ሥርግው ስነ ስብሐት በሰጊድ ስብሐት 』 ⇨ የቁመትህ ውበት ዘንባባ መልክህም ሕይወት የሆነ የሃይማኖት አምድ ክርስቶስ ሆይ ባማረ ምስጋና የተሸለምክ በመስገድ ላንተ ምስጋና እናቀርብልሃለን።
. . ዘንባባ = ድንግል ማርያም
『 ለሕሊናኪ ንጽሕት እምነ ኵሉ ትውዝፍት፡ ለንጽሐ ሥጋኪ ዘአልቦ ርስሐት፡ ለቆምኪ ስነ በቀልት በሰጊድ ሰላም』 ⇨
. . ዘንባባ = አቡነ ተክለሃይማኖት
『ተክለ ሃይማኖት በቀልት ወጽጌ ገነት ፡ ዘናቄርብ ለከ መዓዛ ስብሐት 』 ⇨
. . ዘንባባ = አቡየ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
『 ጻድቅሰ ከመ በቀልት ይፈሪ ወይበዝኅ ከመ ዘግባ ዘሊባኖስ አባ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፡፡ ኖመ ኖመ ኢየሩሳሌም በፍሥሓ ወበሐሴት፡፡ 』 ⇨
በይበልጥ ደግሞ "ጻድቅ እንደዘንባባ ያፈራል" በሚለው የነቢዩ ንጉሥ ዳዊት ቃል መነሻ በማድረግ 【መዝ ፺፪፥፲፪】በጽድቅ የኖሩ አያሌ ሰማዕታት መስተጋድላን መገለጫቸው ሆኖ ሲወሱበትና ሲወደሱበት ይታያል።
በኋላኛውም ዘመን ገዳማውያኑ መናንያን ሕይወታቸው ከዘንባባ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሆኖ ታይቷል። ሥራቸው ሰሌን መታታት (ሠርቶ ሰፍቶ ለምንጣፍ ለቅርጫት፣ ለቆብና ለቀሚስ ማዘጋጀት) ፣ ለራሳቸውም የሚለብሱት ቆባቸውና ልብሳቸው ጭምር ከሰሌን የሚሠራ ነበር። ኋላም ዐረፍተ ዘመን ሲገታቸው የከበረ ሥጋቸው በሰሌን ተከፍኖ ግብኣተ መሬት ይፈጸምላቸዋል።
ከሰይጣን ውጊያ ለማረፍ እና ከስንፍና ለመለየት ከጸሎት ጋር መነኮሳት ሊተገብሩት ከሚገባ ተግባረ እድ ዋናው ሰሌን መታታት ሊሆን እንደሚገባ ቅዱስ መልአክ ለርእሰ መነኮሳት አባ እንጦንስ አስተምሮታል (ስንክሳር ዘጥር ፳፪) የባህታዊው አባ ጳውሊ ቀሚስ የአባ እንጦንስም ቆብ ከሰሌን የተሠራ ነበር መጽሐፈ መነኮሳቱና ዜና ገድላቸው ይነግረናል።
1.4K viewsተεพ๑δr๑ร (አግናጥዮስ)𝕿𝖊𝖜𝖔𝖉𝖗𝖔𝖘 𝕭𝖊𝖑𝖊𝖙𝖊 𝕸𝖊𝖓𝖌𝖎𝖘𝖙𝖚 Ignatius Theophoros (Ἰγνάτιος Θεοφόρος), 17:38