2023-03-20 19:40:24
ክፍል ፩] ታቦተ ሰንበት
━━━━✦✿✦━━━━
በዓለ ደብረ ዘይት እኩለ ጾም ነው፤ የጌታችን ምጽኣቱ ዓለም በተፈጠረበት ዕለት በዕለተ ሰንበት መሆኑን ቅድስት ቤተክርስቲያን ታምናለች ታስተምራለችም! ቸሩ ጌታችን "በሰንበት ኢይኩን ጉያክሙ ⇨ ስደታችሁ በሰንበት አይሁን" ብሎ የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያቱን ሰብስቦ በዕለተ ሰንበት አሕማላት (የለመለሙ ዕፀዋት) ካሉበት ቦታ ከ"ዐጸደ ሐምል" ተራራ ዐጸደ ዘይትም ወደበዛበት ሥፍራ አስጠግቶ ነገረ ምጽአቱን ያስተማረበት መታሰቢያ በዓለ ደብረ ዘይት ይባላል። ቀኑ ለኹዳዴ እኩለ ፆም ነው!
ባለቅኔው
"ተዝካሮ ግበሩ ባሕታውያን ደቂቁ፤
ለምውት ጾም እስመ ደብረ ዘይት መንፈቁ።" እንዳለ።
ገባሬ ሕይወት እግዚአ ለሰንበት ራሱ ጌታችን የቀደሳትና ከፍ ከፍ ያደረጋት ዕለት በመሆኗ "ቀደሳ ወአልዓላ" እያልን በእርሷ ደስ ብሎን ስናከብራትና ስናገናት እንውላለን።
በእርግጥ ጊዜው የእግዚአብሔርን በዓላት ከምድር ላይ እንሻር የሚሉ የበዙበት ዘመን መሆኑን ስናይ የዳዊት ትንቢት እያነሳን የትንቢቱ መፈጸሚያ በሆኑት እንደነቃለን።
“አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው። ኑ፥ የእግዚአብሔርን በዓሎች ከምድር እንሻር አሉ።” ☞ 【መዝ ፸፬፥፰ 】
በዓለም ታሪክ እ.አ.አ. ከ1536 በፊት «በካቶሊካዊት» ቤተ እምነት በዐመት ውስጥ 95 የሚሆኑ የ«ቤተክርስቲያኗ» በዓላትና 52 ሰንበታት ይከሩ እንደነበር፤ ነገር ግን ከ1536 አንስቶ በተሃድሷውያኑ ጫና በዓላቱን ወደ 27 አውርደዋቸዋል።
ኋላ ላይ የተነሱት ከካተሊካዊ ባህል ፕሮቴስታንቱን እናነፃለን የሚሉ ወገኖች (The Puritans) በዓላቶችን በሙሉ (ገናና ፋሲካን ሳይቀር) በመሻር ዝክረ ዕለታትን ከሁለት ወገን ይከፍላሉ፦
① ችግር ጉዳትና አደጋ ከላይ የወረደ ቁጣ ተብለው የሚዘከሩባቸው ቀናት «ዕለታተ ፆም» ( Days of Fasting) ሲባሉ
② ልዩ በረከት ከአምላክ የሚሰጡባቸው ቀናት ዕለታተ ባርኮ/የምስጋና ቀናት (Days of Thanksgiving) ብለዋቸዋል።
【James W. Baker የተጻፈው "Thanksgiving: The Biography of an American Holiday" 】
ዛሬም የእኛዋን ቤተክርስቲያን አውቀው ይሁን ሳያውቁ በዚህ ወጀብ የሚንጧትን አበልጻጊዎች አስታግሶ ፣ ከመፍቀሬ ሁከት ሰይጣን ሰውሮ ፣ በመፍቀርያነ ምሕረት መላእክቱ ከልሎ ፈተናውን ሁሉ ያሻግርልን።
ወደዛሬው የመጀመሪያ ቀን ጉዳያችን እንለፍ፤ ትናንት በተሠጠው ጥቆማ መሠረት [https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=6005958766119252&id=100001155652281&mibextid=Nif5oz]
ታቦተ ሰንበትን የሚመለከቱ ጥቂት ሐሳቦች እናሳለን። መነሻ ጥያቄው እንዲህ የሚል ነው
☞ ለሰንበት ታቦት ይቀረጻል? በሳማ ሰንበት፣ በመናገሻ ጋራው መድኃኔዓለም ፣ በምሑር ኢየሱስ ፣ በአጤ ዋሻ… «ታቦተ እግዚኣ ለሰንበት» ፣ «ታቦተ ደብረ ዘይት» … መባሉ ስለምን ነው?
ቀድመን የሚከተለውን ጥያቄ እናንሳ
ጽላት/ታቦት ለማን ይቀረጻል (በማን ይሰየማል) ?
በአጭር መልስ በስማቸው ጽላት የሚቀረጽላቸው ፣ መቅደስ የሚታነጽላቸው ፣ ጠበል የሚፈልቅና የሚሰየምላቸው ፣ ድርሳን ገድል መልክእ የሚጻፍ የሚደረስላቸው ቅዱሳን ናቸው።
ቅዱሳንስ የምንለው ማንን ነው?
የኔታ ሐረገወይን አገዘ (ሊቀ ጠበብት) ነገረ ቅዱሳንን ሲያስረዱ ቅድስና የባህሪ ገንዘቡ የሆነ አምላክነትና ፈጣሪነትን ከማንም ያልተቀበለ ልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነው።
ይሁንና ግን ከባህሪ ቅድስና በታች ያሉ በሥጦታ ቅድስናን ገንዘብ ያደረጉ ቅዱሳንም አሉ ፤ እነዚህም ቅዱሳን/ቅዱሳት ዘበጸጋ ይባላሉ።
ለዚህ የጸጋ ቅድስና ምክንያቶች (ምንጮች) ደግሞ በጥቅሉ ሦስት ናቸው።
★ በመጽናት ቅዱሳን የምንላቸው አሉ ፦ ቅዱሳን መላእክት
★ በመመረጥ ቅዱሳን የምንላቸው ፦ እመቤታችን፣ ንዋያት [ታቦት፣ መስቀል፣ መካናት/መቅደስ፣ ሥዕላት ፣ ንዋያተ ቅድሳት … ] ፣ ዕለታት ፣ መጻሕፍት፣ በጸሎት የከበሩ ቅብዓት [ቅብዓ ሜሮን ፣ ቅብዕ ቅዱስ፣ ቅብዓ ቀንዲል… ]
★ በተጋድሎ ቅዱሳን የምንላቸው ፦ በቅድስናው ማዕረግ ከፍ ያሉ መስተጋድላን ጻድቃን ጽኑዓን …
መጽሐፍ ‘ሰብእ ይቄድሶ ለመካን ፤ ወመካን ይቄድሶ ለሰብእ’ ይላል፤ ደግሞም ቅዱሳን የረገጡትን ቦታ ብቻ ሳይሆን ገቢረ ተዓምራት የፈጸሙባቸውን ዕለታት ጭምር ቅዱስ ያሰኛሉ።
" ኀበ ቅዱሳን ይከውን ቅዱሰ ⇨ ከቅዱሳን ጋር የሚውል ቅዱስ ይኾናልና" 【ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ ፻፳፮】
ሰንበት ቅድስት ዕለት ናት። በእርግጥ በገዳማትና በአንድአንድ "ሊቃውንት" አንደበት የሰንበት ታቦት የሚባል የለም "እግዚኣ ለሰንበት" እንጂ ሲሉ ይደመጣል።
በአገባቡ «እግዚኣ ሰንበትና እግዚአ ለሰንበት» የሚሉት መልእክታት ፍቺና ምሥጢራቸው ለየቅል ነው።
እስኪ ደግመን አንድ ጥያቄ እናንሳ
ለዕለታትና ለንዋያት ታቦት ይቀረጻል ወይ?
መልሱ፦ አዎ።
አስረጅ ፦ በእመቤታችን ስም ጽላት/ታቦት እንደሚቀረጽ ሁላችን እናውቃለን ፤ የዕረፍቷን መታሰቢያ መነሻ አድርጎ በ፳፩ ክብረ በዓሉ የሚታሰብ ሲሆን ሌሎቹን ታቦተ ልደታ ፣ ታቦተ በዓታ … እያሉ ለቀናቱ መታሰቢያ በመስጠት ዕለታት ይዘከሩባቸዋል። ከዚሁ ጋር በተገናኘ በቅዱስ መስቀሉ ስም ጽላት/ታቦት ተቀርጾ መቅደስ ታንጾ ድርሳን ተደርሶ መልክእ ተጽፎ ሲከብር እናያለን።
ሰንበትም እንዲሁ ድርሳነ ሰንበት ፣ መልክአ ሰንበት ፣ ታቦተ ሰንበት ያለው እንዲያውም የበዓላት ኹሉ በኲር የሆነ በዓል ነው።
ከመልኩ ክፍል ይህን የሚያስረዳ መልእክት እንዲህ ሠፍሮ እናገኛለን
ሶበ አእመርኩ በስምኪ ከመ ታቦተ ይቄድሱ፡
ወድሶተኪ ወጠንኩ ለአእምሮትየ መጠነ ናእሱ፡
ሰንበተ ክርስቲያን ቅድስት ንግሥተ መሳፍንት ስሱ፡
እለሰ ኪያኪ አርኰሱ፡
ፈቀዱ ሞተ ወኵነኔ ኃሠሡ፡፡
[በስምሽ እንደታቦት የሚቀደስ መሆኑን ባወቅኹ ጊዜ በትንሿ እውቀቴ ምስጋናሽን ጀመርኩ
ለስድስቱ መሳፍንት ንግሥት የምትሆኚ ቅድስቲቱ የክርስቲያኖች ሰንበት ሆይ አንቺንስ ያረከሱ ሰዎች ሞትን ወደው መኮነንን የፈለጉ ናቸው።]
አንዳንዶች እግዚኣ ለሰንበት በሚል መጠሪያ የሰንበት ጌታ ስለሚል « ጌታ እንጂ ሰንበትን የሚወክል ታቦት የለም» ይላሉ። ይሁን እንጂ ሰንበት ራሱ ዕረፍት ነው ታቦተ ማርያም ተዝካረ ዕረፍቷ እንደሚታሰብበት ታቦታ ሰንበትም በሁለቱ ሰንበታት (ቅዳሜና እሑድ) ጌታችን ማረፉን የምንዘክርበት ጽላት/ታቦት ነው።
⇝ ቀዳሚት ሰንበት ፍጥረትን ፈጥሮ ያረፈበት በዓል ሲሆን ⇝ እሑድ (ሰንበተ ክርስቲያን) ደግሞ በሐዲስ ኪዳን ሁሉን ‘አዲስ’ ሊያደርግ ከልደቱ ጀምሮ ሲፈጽም የነበረውን የማዳን ሥራ በምድር ዕለተ ዓርብ ፈጽሞ እስከ እሑድ ነፍሳትን ከሲኦል አግዞ በትንሳኤው በሐዲስ ተፈጥሮ የመፍጠሩን ሥራ የፈጸመበት / ያረፈበት ዕለት ነው።
“ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።” 【 ፪ኛ ቆሮ ፭፥፲፯
150 viewsተεพ๑δr๑ร (አግናጥዮስ)𝕿𝖊𝖜𝖔𝖉𝖗𝖔𝖘 𝕭𝖊𝖑𝖊𝖙𝖊 𝕸𝖊𝖓𝖌𝖎𝖘𝖙𝖚 Ignatius Theophoros (Ἰγνάτιος Θεοφόρος), 16:40