2023-02-05 08:43:28
. በደወል የተጠሩ ደወሎቻችን
᳀᯼͟͞ ͟͞ ͟͞ ̸͟͞ ͟͞ ͟͞ ͟͞ ̸͞͝ ͟͞᳀͟͞ ͟͞ ̸͟͞ ͟͞ ͟͞ ͞ ͟͞ ̸ ͟͞ ͟͞᯼᳀
"ወይደምጽ ድምጸ መጥቅዕ ወኲሉ ዘሰምዓ ይደነግፅ ⇨ ደወል [ረቂቅ ነጋሪት] ይሰማል : የሰማውም ሁሉ ይደነግጣል" 【ዕዝራ ሱቱኤል ፬፥፳፫】
በትናንቱ የቅዱስ ሲኖዶስ አዋጅ ውሥጥ እንዲህ የሚል "ሲኖዲቆን" ተቀምጧል
"በሰባቱ የጸሎት ሰዓታት እየተጠበቀ በተመሳሳይ ሰዓታት ለአምስት ደቂቃ ያህል በማያቋርጥ ደወል በመደወል የማስተጋባት ሥራ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤"
መደወሉ ከሰይጣን ማሳት እንድናመልጥ ፣ ከጠላት ወጥመድ እንድንወጣ ፣ ከገቢረ ኃጢኣት እንድንለይ ፣ ከድካም ሀኬት እንድንበረታ… እንደ ጴጥሮስ ዶሮ ልብን ለመመለስ የሚደወል ነው። እንደ ቃጭል ወይም መረዋ አነስተኛው ደወል ቃለ ዓዋዲ ተብሎ የመጠራቱ ምክንያት ይህ ነው።
በምሕላና በእግዚኦታ ጊዜ ደወል እንዲደወል ቤተክርስቲያን የምታውጀው በምሳሌነቱ ⇨ ከመስቀሉ አጠገብ ያልተለዩ የክርስቶስን መከራ አይተው ያለቀሱ የእመቤታችንና የቅዱሱን ሐዋርያ ዮሐንስ ወንጌላዊ የልቅሶ ድምፅ በማሰብ ነው። ዛሬም የጌታቸውን መንገድ ለሚከተሉ በእውነተኛ ምስክርነት ሕይወታቸው በግፍ ለሚያልፍ እንደቅጠል ለሚረግፍ ሰማዕታት መታሰቢያ እንዲሆን ይደወላል።
ደወል የራቁትን ያቀርባል የተበተኑትን ይሰበስባል ለዚህም ነው በዓላትና አጽዋማትን ሰብስቦ የሚነግረን የባሕረ ሐሳቡ ማውጫ ጥንተ መጥቅዕ የሚባለው!
የአጽዋማትና በዓላት በየዓመቱ መመላለስ መሪ የሆነ መባጃ ሐመሩንም የዓመቱን መጥቅዕ እና የመጥቅዕን ዕለተ ተውሳክ በመደመር እናገኘዋለን።
ለሐመሩ (ለመርከቡ) እና ለመጥቅዑ (ለደወሉ) መነሻ በኩፋ ፮፥፳፯ የተነገረው የኖኅ መርከብና ደወል ነው።
ኖኅ መርከቡን ከጥፋት ማምለጫ እንዲሆነው ሲያሰናዳ ቁመቱ ሦስት ክንድ፣ ስፋቱ አንድ ክንድ አድርጎ ደወል እንደሠራና በየዕለቱ በነግህ ለጸሎት፣ በቀትር ለምግብ፣ በሰርክ ለማሰናበት ሦስት ጊዜ እየደወለ ይጠቀምበት እንደነበር በመጽሐፈ ቀሌምንጦስ ምዕራፍ ፫ ከቁጥር ፷፪ ጀምሮ ተዘግቦልናል።
"ኖኅም… ሦስት ክንድ ርዝማኔና አንድ ክንድ ጉድን ያለው ደወል ከሊባኖስ ዕንጨት ሠራ። መርከቡን በሚሠራበት ጊዜ ሁልጊዜ ጧት ጧት ለሥራ እንዲሠበሰቡ ደወል ይደውላል። ቀትር ሲሆን ምሳ ለመብላት እንዲሰበሰቡ ይደውላል ቀኑ አልፎ ምሽት ሲሆን ወደየቤታቸው እንዲገቡ ይደውላል። መርከቡን ለምን እንደሚሠራው ጠያቂ ቢነሳበት እግዚአብሔር የጥፋት ውሃን ይህቺን የረከሰች ምድር ለማጠብ እንደሚያዘንምና። በዚሁም ምክንያት ራሱን ሚስቱን ልጆቹንና ሚስቶቻቸውን ለማዳን መርከብን እንዲሠራ መታዘዙን ይገልፅለታል።"
የደውሉም አገልግሎት እንዲህ እያለ ከኖኅ እስከ ሙሴ ደርሷል። ሙሴም ማኅበሩን መሰብሰቢያ የብር መለከቶችን አዘጋጅቶ እንደነበር መጽሐፍ ይነግረናል
“ሁለት የብር መለከቶች አጠፍጥፈህ ለአንተ አድርግ ማኅበሩን ለመጥራት ከሰፈራቸውም ለማስጓዝ ይሁኑልህ።” 【ዘኁ ፲፥፪】
እኛም ይህን ምሳሌ ይዘን በቤተክርስቲያናችን ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንጠቀምበታለን። በተለይ እንደኖኅ ዘመን የሥራ ደወል ከጥፋት ለማምለጥ የምንሠራውን ይህን መርከብ የሆነ ሰውነታችንን ሕንፃ ሥላሴ አካላችንን በንሰሐና በቁርባን እንድናበጃጀው ደወሉ ያለማቋረጥ ሲመታ እንሰማለን።
አገልግሎቱም ሌሊት የተኙትን በመቀስቀስ ለሰዓታትና ለማኅሌት እንዲተጉ ፲፭ ጊዜ ይደወላል፤ በነግህ በ፫ ሠዓት ለዋዜማ ቁመት ፲፪ ጊዜ ይደወላል፤ በሰርክ ለቅዳሴ መግቢያ ፫ ጊዜ ይደወላል፤ በጻዑ ንዑሰ ክርስቲያን ጊዜ ፫ ጊዜ ይደወላል፤ በእግዚኦታ ጊዜ ፯ ጊዜ ይደወላል፤ በድርገት ጊዜ ፭ ጊዜ ይደወላል።
ምሳሌውም የቀርነ መለከት ሲሆን ፲፭ ጊዜ መደወሉ የ፲፭ቱ ነቢያት ምሳሌ ነው፤ ፲፪ ጊዜ መደወሉ የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው፤ ሌሊት መደወሉ ነቢያት በዘመነ ጽልመት መኖራቸው ምሳሌ ነው፤ በሰርክ መደወሉ ብርሃን የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመገለጹ ምሳሌ ነው።
በሥርዓተ ቅዳሴው ላይ ብቻ ለ፭ ምክንያቶች ሲደወል እንሰማለን፤ ምሳሌውን ከነምክንያቱ እንመልከት
፩】. የተጋብኦ ደወል
✦━━━━━━━
ካህናትና ምእመናን ለልዩ ልዩ አገልግሎት ወደ ቤተክርስቲያን እንዲሰበሰቡ የሚጠራ የቤተ ክርስቲያን በሮች ከመከፈታቸው በፊት የሚደወል ነው።
ምሳሌነቱ፦
የትንቢተ ነቢያት ነው:: ደውሉ ካህናትና ምእመናንን ቀስቅሶ ለአገልግሎት /ለጸሎት/ እንደሚዘጋጅ፤ ነቢያትም የሕዝቡን ልብ እየቀሰቀሱ፤ ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር እየመለሱ፤ ለአዲስ ኪዳን አገልግሎት እንዲዘጋጁ ያደርጉ እንደነበር ያሳያል።
፪】.የቅዳሴ መግቢያ ደወል
✦━━━━━━━━━━
ይህ ደወል ካህናት መሥዋዕቱን አክብረው ከቤተልሔም ወደ መቅደስ ሲጓዙ የሚደወል ነው፡፡
ምሳሌነቱ፦
የብሥራተ ገብርኤል ነው፤ አንድም ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ (ዮሐ ፩፥፪፱፡፡) በማለት የጮኸው /የተናገረው/ ድምፅ ነው።
፫】. የወንጌል ደወል
✦━━━━━━━
ይህ ደወል “ፃኡ” በሚባልበት የቅዳሴ ክፍል መካከል የሚደወል ነው።
ምሳሌነቱ፦
የስብከተ ዮሐንስ፣ የሐዋርያትና የሰብአ አርድዕት ልቅሶ ነው። (ሉቃ፫፥፫‐፯፡፡) ይህ ደወል ከተደወለ በኋላ ያለው የቅዳሴ ክፍል ፍሬ ቅዳሴ ይባላል:: ይህም መሥዋዕተ ወንጌል የሆነው የክርስቶስ ሥጋውና ደሙ የሚቀርብበት ነው:: ደወሉ ሐዋርያትና አርድእት ቅዱሳት አንስትም ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ያዘኑትን ሐዘን፥ ያለቅሱትንም ለቅሶ፣ ያፈሰሱትንም ዕንባ የሚያስታውስ ነው።
፬】.የእግዚኦታ ደወል
✦━━━━━━━
በቅዳሴ ጊዜ መጨረሻ አካባቢ ካህናትና ምእመናን በቅብብሎሽ /በማስተዘዘል /፵፩፥ ፵፩/ ጊዜ እግዚኦታ ያደርሳሉ:: በዚህን ጊዜ ከላይ የገለጽነው ደወል ይደወላል::
ምሳሌነቱ፦
ከመስቀሉ አጠገብ ያልተለዩ የክርስቶስን መከራ አይተው ያለቀሱ የእመቤታችንና የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ የልቅሶ ድምፅ ነው:: /ዮሐ ፲፱፥፳፭‐፳፰፡፡/
፭】.የድርገት ደወል
✦━━━━━━━
ሥጋ ወደሙ ለቆራብያን ሊሰጥ (ሊታደል) ልዑካኑ ከመቅደስ ወደ ቅድስት ሲወጡ የሚደወል ነው።
ምሳሌነቱ፦
ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በገነዙት ጊዜ ያለቀሱት ልቅሶ ነው:: አንድም የሐዋርያትና የሰብአ አርድእት ትምህርት ነው:: ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የጌታችንን ሥጋ በገነዙበት ጊዜ እያለቅሱ ነፍስ የተለየውን፣ መለኮት የተዋሐደውን የጌታችንን ሥጋ ገንዘው ባዲስ መቃብር “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር…” ብለው እንዳኖሩት፤ ካህናትም በቅዳሴ ጊዜ ነፍስ የተለየውን መለኮት ያልተለየውን (የተዋሐደውን) የክርስቶስን ሥጋና ደም እንዲያቀብሉ ደወል ይደወላል:: ሐዋርያትና ሰብአ አርድእት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ወንጌልን በመላው ዓለም አስተምረዋል፤ ሰብከዋል። ዞረው ማስተማራቸውንና በስብከታቸው የሰው ልጆች ሁሉ ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገራቸውን ለማሰብና ምእምናንም ዛሬ በደወሉ ድምፅ የዘለዓለም ሕይወት ወደሚያገኙበት፥ የክርስቶስ ሥጋና ደም እንደሚቀርቡ ለማመልከት ነው::
ደወሉ ትናንት ሁከት በነገሡባቸው ቦታዎች ምእመናንን ለክብር ወደ ምድራዊቷ ቤተመቅደስ ብቻ ሳይሆን ወደሰማይ ማደርያ ወደ ዘልዓለማዊው መኖርያ ጠርቷል። ጉባኤ ጳጳሳቱም "ተገቢውን ሲኖዶሳዊ እና ሃይማኖታዊ ጸሎት በማድረግ በሁሉም አጥቢያ ሥርዓተ ፍትሐት እንዲፈጸምላቸው" ትዕዛዝ አስተላልፏል።
3.9K viewsተεพ๑δr๑ร (አግናጥዮስ)𝕿𝖊𝖜𝖔𝖉𝖗𝖔𝖘 𝕭𝖊𝖑𝖊𝖙𝖊 𝕸𝖊𝖓𝖌𝖎𝖘𝖙𝖚 Ignatius Theophoros (Ἰγνάτιος Θεοφόρος), 05:43