2023-02-06 08:16:15
«እኔን ብትጥሉኝ ሀገሩ ሰላም ይሆናል!»
°°°°°°°━✦•✧༒✧•✦━°°°°°°°
በደወሉ ተቀስቅሰን ነቅተን ይሆን?
ዮናስ ሆይ "ምንት ያነውመከ?"
↳ “ ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደ ሆነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ” እንጂ (ቁ. ፮)
ያ… ከእግዚአብሔር ርቆ እግዚአብሔርም ርቆት ምሕረት እያባረረ መዓት የሚጠራ ዮናስማ እኛ ነን።
ዛሬ ላይ የደረሰብንና የደረስንበትን ጥፋት በማጤን ብናየው ሌሎቹ ስተውና አሳስተው የመጣ ሳይሆን እኛው ባለማዕተቦቹ አጥፍተንና ጠፍተን ያመጣነው ለመሆኑ እንደ ነቢዩ ዮናስ በላያችን የወጣብን ዕጣ ያሳብቃል፤
ከሁሉ በተለየ እግዚአብሔርን አውቃለሁ በእግዚአብሔርም እታወቃለሁ የምንል ግን በሁከቱ መኃል ከጾምና ከጸሎት ርቀን ተኝተንና ነፋስ በሚጠራ ወጀቡን በሚያጠነክር ዘመቻ ተጠምዶ ወደ ውሥጠኛው የጎጥ ⇨ የዘር ⇨ የነገድ ⇨ የዜግነት ክፍል ወርደን ከባድ እንቅልፍ ጥሎናል!
በአንቂ ስብከትና በአነቃቂ ንግግር (motivational speech & Inspirational sermon) ከተኛንበት ነቅተናል የምንል ዮናሶች ሆይ ከእንቅልፋችን ስንላቀቅ ምን ብለን ምን አድርገን ይሆን?
◆ ዮናስን ቀስቅሰው ፭ ጥያቄ ጠይቀውታል “ ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እባክህ ንገረን፤ ሥራህ ምንድር ነው? ከወዴትስ መጣህ? አገርህስ ወዴት ነው? ወይስ ከማን ወገን ነህ? አሉት።” 【 ዮና ፲፥፰】
ከ፭ቱ ለ፬ቱ ምላሽ ሠጠ አንዱን ግን አልፎታል ፦ ሊቃውንቱ “አይቴ ብሔርከ ላሉት ግን አይመልስም” ይላሉ።
ያኛው ዮናስ ዮናስ "ባህርና የብሱን የፈጠረ የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ …" ይላል እንጂ እንደዚህኛው ዮናስ ጠቅላይ ቤተክህነቱን በጎጥ እሳት ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱንም በዘር ምድጃ ላይ ጥዶ «የዚህን ሀገር፣ የዛኛውን ሰፈር የዚህን መንደር እግዚአብሔር ነው የማመልከው» አላለም። (ቁ ፱)
◆ ያኛው ዮናስ ስለችችሩ ምንጭ "አነ አእመርኩ ከመ በእንቲአየ መጽአክሙ ዝንቱ ማዕበል ዐቢይ ⇨ ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁ … " አለ እንጂ እንደዚህኛው ዮናስ «ይህማ የመጣብን በነእንትና ስውር አጀንዳ ፣ በእነ እገሌ ሤራ ፣ በነ እገሊት ሸፍጥ… ነው» አላለም (ቁ ፲፪)
◆ ያኛው ዮናስ ስለመፍትኼው "ንስኡኒ ወወርዉኒ ውስተ ባህር ወየኀድገክሙ ⇨ (እኔኑ) አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፥ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል" አለ እንጂ እንደዚህኛው ዮናስ «በሌሎች ድካምና ስንፍና በእናንተ በደልና ኃጢዓት ይህ ሁሉ በመምጣቱ እነርሱ ቢወገዱ እናንተ ብትጠፉ ችግሩ ተወግዶ መከራው ጠፍቶ መረጋጋት ይሰፍናል» አላለም (ቁ ፲፪)
ብቻ ከዚያኛው ዮናስ ይልቅ ይኼኛው ዮናሶች እጅግ እናሳዝናለን! በጎጥሸ እሳት በዘር ምድጃ ላይ እንደተኛን ነው የምንሰበከው ፣ ዛሬም የሸዋና የጎጃም ሲኖዶስ እያልን ነው የምንጾመው
ሰው ከዚህ አደንዛዥ የዘረኝነት እንቅልፍ ሳይነቃ ፣ ከዚህ ከፋፋይ የጎጥ ቅዠት ሳይባንን ቢጾምና ቢጸልይ ፣ ቢሰበክና ቢማር ፣ ቢሰብክና ቢያስተምር … ጥቅሙ ምንድነው? የተነገረውን አድምጦ እንዴት በልቡ ሊያኖረው ይቻለዋል?
እስኪ መጀመሪያ የተኛ ይንቃ ⇨የነቃ ደግሞ ይማር ⇨ ከዚያ የተማረ ደግሞ ይሰበክ ።
ጠቢቡም ቀዳሚ ሊሆን ስለሚገባው ተግባር እንዲህ ይላል
" አንቅሆ እምዐቢይ ንዋም ለዘይነውም !"
【የተኛ ሰውን ከጽኑ እንቅልፍ ቀስቅሰው】ከዚያ አስተምረህ ከስንፍና ለየው ስንፍናውን በእውቀት ሲረታው ከስሜት ርቆ ይሰበክልሃል። ያለዚያስ?
… ያለዚያማ
"ዘይነግሮ ለአብድ ከመ ዘይነግሮ ለድቁስ ፤ ወሶበ አኅለቀ ነጊሮቶ ይብለከ ምንተ ትቤ ? ⇨ ለሰነፍ ሰው የሚነግር (የሚሰብክ) ሰው ለተኛ ሰው እንደሚነግር ሰው ነው ነግረኸው ከጨረስህ በኋላ ምን ተናገርህ? (ምን ነበር ያልከው?) ይልሃል።" 【ሲራ· ፳፪ ፥፰】
አያሌ «የማኅበረሰብእ አንቂዎች» እየተፈራረቁ በአግባቡ እንዳንተኛ እያባነኑንና በአግባቡ እንዳንነቃ እያቃዡን ከእምነት አጣልተው ወይ ኑሯችንን ሳናልም ወይ ደግሞ ሕልማችንን ሳንኖር እንድንዳክር ጋርደውናል።
አዝማሪው
«የተኛን ቀስቅሶ በማርዳት የለፋ
መች ቀብር ይሄዳል ጡሩምባ ሚነፋ?» ብሏል
"ጥሩምባ ነፊ ቀብር አይሔድም" እያሉ ቀስቃሾቹ ተኝተው፣ አንቂዎቹም ፈዘው ቢገኙ ተያይዞ ማለቅ ነው። ብቻ የነቃ ቀስቃሽ ከደብሩ ፡ ያረዳ አልቃሽ ከቀብሩ ብናይ ሸጋ ነበር።
ከመአቱ እንዲመለስ መቅሰፍቱንም እንዲያስወግድልን የምንችል ነነዌን ከጥፋት መንገድ እናውጣት ካልቻልን ራሳችን ከነነዌ እንውጣ፤ የሆነለት ሌላውን ከጥፋት ለይቶ ለማዳን ይድከም ያልሆነለት ስለራሱ ነፍስ ከመጥፋት ተለይቶ ከነነዌ ይውጣ።
"ነብዩ ዮናስ የተናገረው ነገር ያለውድ በግድ ይደረጋልና ልጄ አሁንም ከነነዌ ውጣ።" 【ጦቢ ፲፬፥፰】
ቴዎድሮስ በለጠ ጥር ፳፱ ነነዌ ፳፻፲፭ ዓ.ም.
6.7K viewsተεพ๑δr๑ร (አግናጥዮስ)𝕿𝖊𝖜𝖔𝖉𝖗𝖔𝖘 𝕭𝖊𝖑𝖊𝖙𝖊 𝕸𝖊𝖓𝖌𝖎𝖘𝖙𝖚 Ignatius Theophoros (Ἰγνάτιος Θεοφόρος), 05:16