2023-02-19 22:25:52
ታሪክ ጌታ ከቅድስት ሰኞ ጀምሮ እስከ ዓርብ ኒቆዲሞስ ከቆመ ሳያርፍ ከዘረጋ ሳያጥፍ ዓርባ ቀን በትህርምት ጾሟል ሐዋርያት እሑድ እሑድን አውጥተው ቢቄጥሩ ጎደለባቸው አስቀድመው አምስት ቀን ጹመው ለስብከተ ወንጌል ይፋጠኑ ነበርና …
የኋላውንም ሁለት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ታሪኮች ደግሞ እንዲህ ያብራራልናል።
① በኢየሩሳሌም ፎቃ በሮም ህርቃል ነገሠ ፎቃ በኢየሩሳሌም ባሉ ምእመናን መከራ አጸናባቸው ምንም አንድ አካል ሁለት ባሕርይ በማለት ብንለያይ ወረደ ተወለደ በማለት አንድ ነንና መጥተህ አጥፋልን እኛ ላንተ እንገዛለን ብለው ወደ ሕርቃል ላኩበት እሱም ከአይሁድ ጋራ ጨዋታ መሐላ ነበረውና ቸል ብሎ ተዋቸው ኋላ ግን "ግዙራን ይነሥእዋ ለመንግሥትከ" የሚል ራእይ አየ።
መንግሥቱን የሚወስድበት ኡመር ወልደ አድ እንደሆነ ባያውቅ "ግዙራን የተባሉ ሌላን እለ? አይሁድ አይደሉምን" ብሎ "ያን የላካችሁብኝ ነገር አልረሳሁትም ነገር ግን ሐዋርያት ነፍስ የገደለ መላ ዘመኑን ይጹም ብለዋል ጾሙን ብፈራ ነው እንጅ" አላቸው ያንድ ሰው ዕድሜ ቢኖር ሰባ ሰማንያ ዘመን ነው ይህንንስ እኛ እንጾምልሃለን አሉት መጥቶ አጥፍቶላቸዋል በኢየሩሳሌም ያሉ ምእመናን አምስት አምስት ቀን ተካፍለው ጹመውለታል ያላወቁት አንድ ጊዜ ጹመው ትተውታል ያወቁትን ግን ቀድሞም ሐዋርያት ጹመውታል ብለው ሥራት አድርገው በዓመት በዓመት የሚጾሙት ሁነዋል!
② የሮም ሊቃነ ጳጳሳት ቀሳውስት ዲያቆናት ምእመናን ጹመውታል የሮሙን ንጉሥ ከፋርሱ ንጉሥ ተጋብቶ ሲኖር ሚስቱን በድሎ ሰደዳት ሒዳ ለአባቷ አንተን ያህል አባት እያለኝ በድሎ ሰደደኝ አለችው። እሱም ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብሎ ሒዶ እኔ ከሀገሩ ጠብ የለኝም ጠቤ ካንድ ሰው ነው ጠላቴን ስጡኝ ባትሰጡኝ ግን ጠቤ ከናንተ ጋራ ነው አላቸው ቢትወደዱ «ፎቃ» ይባላል ባንድ ሰው ምክንያት ብዙ ሰው እናስጠፋለን። አውጥተን እንስጥ እንጂ አላቸው። ማን ይነግሣል አሉት እኔ እነግሣለሁ አላቸው አወጥተው ሰጡት ፎቃ ነገሠ።
የጥጦስን የአስባስያኖስን ዘመን ለመመለስ በሮም ባሉ ምእመናን አገዛዝ አጸናባቸው ኋላ ባሪያውን ለማይገባ ገረፈው ህርቃልን ቢትወደድነት ሹሞት ነበረና ሔዶ በማይገባ ገረፈኝ ብሎ ነገረው አትገድለውም አለው ማን ይነግሣል አለው እኔ እነሣለሁ አለው ጊዜ አይቶ ገደለው ህርቃል ነገሠ። ከዚህ በኋላ የሮም ምእመናን መጥተው እኛም ከወገኖቻችን ካነገሥክልን ብድራችንን እንድንመልስ አይሁድን አጥፋልን ብለው አማሉት እሱም ከአይሁድ ጋራ ጨዋታ መሐላ ነበረውና ቸል ብሎ ተዋቸው ኋላ ግን ግዙራን ይነሥእዋ ለመግሥትከ የሚል ራእይ አየ ግዙራን የተባሉ ሌላ እለን አይሁድ አይደሉምን ብሎ ያን ያላችሁኝን ነገር አልረሳሁትም ነገር ግን ሐዋርያት ነፍስ የገደለ መላ ዘመኑን ይጹም ብለዋል ጾሙን ብፈራ ነው እንጂ አላቸው ያንድ ሰው ዕድሜ ቢኖር ስባ ሰማንያ ዘመን ነው። ይህነንስ #እኛ_እንጾምልሃለን አሉት መጥቶ አጥፍቶላቸዋል በሮም ያሉ ምእመናን አምስት አምስት ቀን ተካፍለው ጹመውለታል ያላወቁት አንድ ጊዜ ጹመው ትተውታል ያወቅቱ ግን ቀድሞውም ሐዋርያት ጹመውታል ብለው ሥርዓት አድርገው ባመት ባመት የሚጾሙት ሁነዋል።
ወደ እኛ የደረሰው እንዴት እንደሆነ ለማሳየትም ለመሰናዶው ሳምንት የሕርቃልነቱን ስያሜ ተቀብለው ከዐቢይ ጾም ቀድሞ ባለው ሳምንት እንዲዘከር በድንጋጌ ያጸኑ በዘመነ ሕርቃል በእስክንድርያ የነበሩ ፴፯ኛው ፓትርያርክ አቡነ አንደራኒቆስ መሆናቸውን ዜና ጳጳሳቱ ይነግረናል።
"Pope Adronicus, the 37th Patriarch of Alexandria, acknowledged this request. From that time, “Heraclius Week” began to be observed."
በአጋዥ የታሪክ ማነጻጸሪያ ደግሞ በስንክሳራችን ዕረፍቱ ጥር ፰ የሚዘከረው በቅዱስ ማርቆስ መንበር ፴፯ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቅዱስ አንደራኒቆስ በዘመኑ የፋርስ ንጉሥ ክስራ [Kessra the king of Persia] ከሮሙ ንጉሥ ህርቃል ጋር ስላደረገው ጦርነትና እስክንድርያ ባሉ ምእመናንም ላይ ይደርስ ስለነበረው መከራ ተከታዩን ታሪክ ይነግረናል።
«በሹመቱም ወራት ፀሐይን የሚያመልክ የፋርስ ንጉሥ ክስራ ተነሣና የሶርያንና የፍልስጤምን ከተሞች ወርሮ ዘረፋቸው፡፡ ወደ ግብጽም መጥቶ እስክንድድርያ ከተማ ደረሰ፡፡ በዙሪዋ በመነኮሳት የተሞሉ ሰባት መቶ ገዳማት ነበሩ፡፡ እነርሱም ገንዘብ ያላቸው በተድላ የሚኖሩ ነበሩ፡፡ ስለዚህም በእነርሱ ላይ እግዚአብሔር ሥልጣንን ሰጥቶት ገዳማቱን አፈረሰ፡፡ እነርሱንም ሸሽተው ካመለጡት በቀር ሁሉንም ገደላቸው፡፡ ገንዘባቸውንም ሁሉ ማረከ፡፡
የእስክንድርያ ሰዎችም ንጉሥ ክስራ ያደረገውን ባዩ ጊዜ የከተማውን በር ከፈቱለት፡፡ እርሱም ‹ይህችን አገር በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ አታፍርሳት፣ በውስጧ ያሉትን ብርቱዎች ግደላቸው-ዐመፀኞች ናቸውና› እንደሚለው በሕልሙ አየ፡፡ በዚህም ጊዜ የሀገሩን ንጉሥ ይዞ ካሠረው በኋላ ለሀገሩ ሰዎች ‹‹በጦር ሠራዊት አደራጃቸዋለሁና ከ18 ዓመት ጀምሮ ያሉትን ብርታት ያላቸውንም ሁሉ ሰበስቡልኝ፣ ለእያንዳንዳቸው ደመወዛቸውን 20 የወርቅ ዲናር እከፍላለሁ›› አላቸው፡፡ ሕዝቡም ሁሉ እውነት ወርቅ የሚቀበሉ መስሏቸው 8 ሺህ ብርቱዎችን ቆጥረውና መዝግበው በሰጡት ጊዜ ንጉሡ ክስራ ሁሉንም በሰይፍ ገደላቸው፡፡ ወደላይኛው ግብጽ በመሄድም ኒቅዮስ ደርሶ ሰባት መቶ በሥራቸው ክፉ የሆኑ መነኮሳትን በሰይፍ ገደላቸው፡፡ የሮም ንጉሥ ሕርቃልም የፋርሱ ንጉሥ ክስራ ያደረገውን በሰማ ጊዜ ሠራዊቱን ሰብስቦ መጥቶ ንጉሥ ክስራን ከነሠራዊቱ ሀገሩንም ጭምር አጠፋቸው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የአባ እንድራኒቆስ ገድሉ እጅግ ያማረ ነበር፡፡ … »
ሕርቃል ከአርመናውያን ቤተሰቦች በ575 ዓ.ም. በቀጰዶቅያ ተወልዶ በ641 ዓ.ም. በቁስጠንጥንያ ያረፈ በእምነቱም የመለካውያኑ (Chalcedonian Christianity) ተከታይ የነበረ የሮማውያን ንጉሥ ቢሆንም ካቶሊካውያኑ የእኛውን ንጉሥ አፄ ካሌብን [Saint Elesbaan] በቅድስና እንደሚዘክሩት «ምንም አንድ አካል ሁለት ባሕርይ በማለት ብንለያይ ወረደ ተወለደ በማለት አንድ ነንና መጥተህ አጥፋልን» ብለው ደጅ ለጠኑት በእስክንድርያ እና በኢየሩሳሌም ለነበሩ ምእመናን ባለውለታ በመሆኑ ኦርቶዶክሳውያኑ የልዩነት ድንበሩን ጠብቀው ሲያከብሩት ኖረዋል።
የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ሰላም ፣ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ወላዲተ አምላክ ማርያም ፍቅርና የኢየሱስ ክርስቶስ የረድኤቱ ሀብት የቅዱስ መስቀሉም ሞገስ ሁል ጊዜ ለዘለዓለሙ ከሁላችን አይራቅ!
ከሰሙነ ሕርቃል በረከት ያሳትፈን!
reposted from ቴዎድሮስ በለጠ መጋቢት ልደታ ፳፻፲፫ ዓ.ም. ተጻፈ
581 viewsተεพ๑δr๑ร (አግናጥዮስ)𝕿𝖊𝖜𝖔𝖉𝖗𝖔𝖘 𝕭𝖊𝖑𝖊𝖙𝖊 𝕸𝖊𝖓𝖌𝖎𝖘𝖙𝖚 Ignatius Theophoros (Ἰγνάτιος Θεοφόρος), 19:25