Get Mystery Box with random crypto!

እግዚአብሔርን የሚያምንና የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ በዚህ አንፀባራቂና የደስታ በዓል ደስ ይበለው፡፡ ብ | ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴

እግዚአብሔርን የሚያምንና የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ በዚህ አንፀባራቂና የደስታ በዓል ደስ ይበለው፡፡ ብልህ አገልጋይ ቢኖር፥ እርሱ ወደ ጌታው ሐሴት ገብቶ ዕልል ይበል፡፡

በጾም የደከመ ቢኖር፥ አሁን ደመወዙን ይቀበል፡፡ በመጀመሪያው ሰዓት ወደ አምላኩ የቀረበ ቢኖር፥ ዛሬ ሽልማቱን ይውሰድ፡፡
በሦስተኛው ሰዓት የመጣ ቢኖር፥ እርሱ በዓሉን በምስጋና ያክብር፡፡  በስድስተኛው ሰዓት የደረሰ ቢኖር፥ አይጎድልበትምና አይጠራጠር፡፡ እስከ ዘጠነኛ ሰዓት የዘገየ ቢኖር፥ ሳይጠራጠር ይቅረብ፡፡ እስከ ዐሥራ አንደኛዋ ሰዓት የዘገየ ቢኖር፥ ስለ መዘግየቱ አይደንግጥ፡፡ ጌታ ቸር ነውና፤ በመጨረሻ የመጣውንም እንደ መጀመሪያው አድርጐ ይቀበሏልና፡፡ በዐሥራ አንደኛው ሰዓት ለመጣው ከመጀመሪያው ሰዓት አንሥቶ ሲደክም ከነበረው ጋራ እኩል ይሰጧልና፡፡
መጨረሻ ለመጣው ጌታ ምሕረቱን ይለግሰዋል፤ መጀመሪያ ለመጣውም ያስብለታል፡፡ ለአንደኛው ይሰጠዋል፤ ለሌላኛውም ጸጋውን ያድለዋል፡፡ ለአንደኛው መልካም ምግባሩን ይቀበልለታል፡፡ ለሌላኛውም መልካም ፍቃዱን ይቀበልለታል፡፡ ለአንዱ ምግባሩን ያከብርለታል፤ ለሌላኛውም በቅን ልቡና የሚያደርገውን ጥረት ያደንቅለታል፡፡ ስለዚህ ኹላችሁም ወደ ጌታችሁ ደስታ ግቡ፡፡

ፊተኞች ኋለኞችም ሆይ! እኩል ደመወዛችሁን ተቀበሉ፡፡ ባለጸጐች ድኾችም ሆይ! በአንድነት ዘምሩ፡፡ እናንተ ብርቱዎች ደካሞችም ሆይ! በዓሉን አክብሩት፡፡ እናንተ የጾማችሁ መጾም ያልቻላችሁም ሆይ! ዛሬ ላይ ደስ ይበላችሁ፡፡
መሠዊያው ሙሉ ነውና ኹሉም በማዕዱ ደስ ይበለው፡፡ ፍሪዳው የሰባ ነውና አንድ ሰው ስንኳ እንደ ተራበ እንዳይሔድ፡፡ ኹላችንም የእምነት በዓሉን እንካፈል፤ ከቸርነቱና ከፍቅሩ ሀብትም እንቋደስ፡፡

ማንም ስለ ድኽነቱ አይዘን፥ ኵላዊቷ መንግሥት ተገልጣለችና፡፡ ማንም በኃጢአቱ አያንባ፥ ከመቃብሩ የይቅርታ ብርሃን ተንቦግቧልና፡፡ ማንም ሞትን አይፍራ፥ የመድኃኒታችን ሞት ከዚህ ነጻ አውጥቶናልና፡፡ ለእርስዋ  በመታዘዝም ጌታ አጥፍቷታልና፡፡
በሞቱ ሞትን ገደለው፡፡ ወደ ሲዖል በመውረድ ሲዖልን በዘበዘው፡፡

ኢሳይያስም አሰምቶ እንደ ተናገረ ሲዖል ከጌታችን ጋር ፊት ለፊት ተገናኘች፤ መረራትም! ከንቱ አድርጓታልና መረራት! ሸንግሏታልና መረራት! ሽሯታልና መረራት!
ነፍሳትን ይዛ እንዳታስቀር አስሯታልና መረራት!
[መቃብር የዕሩቅ ብእሲ] ሥጋ አገኘሁ ብላ ዋጠችው፤  ስትውጠው ግን እግዚአብሔር ኾኖ አገኘችው - መረራትም!

ሞት ሆይ! መውጊያህ ወዴት አለ? ሲዖል፥ መቃብርም ሆይ! ድል መንሣትህ ይዞም ማስቀረትህ ወዴት አለ?
ክርስቶስ ተነሣ፤ ሞት ሆይ፥ አንተም ጠፋህ!
ክርስቶስ ተነሣ፣ አጋንንትም አዘኑ!
ክርስቶስ ተነሣ፤ መላእክትም ሐሴት አደረጉ!
ክርስቶስ ተነሣ፤ የሰው ሕይወትም ነጻ ወጣች!
ክርስቶስ ተነሣ፤ መቃብርም ባዶ ኾነች!
ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶ ለአንቀላፉት ኹሉ በኵር ኾኖላቸዋልና፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ


╭══•:|★✧♡ ♡✧★|: ══╮
  @orthodox1 @orthodox1
  @orthodox1 @orthodox1
  @orthodox1 @orthodox1
╰══•:|★✧♡ ♡✧★|:  ══╯