2024-03-31 14:44:07
ጥቂት ወሳኝ ነጥቦች በለይለተል ቀድር ዙሪያ
~
ለይለቱል ቀድር ማለት ትልቅ ደረጃ ያላት ሌሊት ማለት ነው። ከፊል ዓሊሞች ዘንድ ደግሞ ፍጡራንን የሚመለከቱ የአመቱ ውሳኔዎች የሚተላለፍባት ሌሊት ማለት ነው።
1. የለይለተል ቀድር ደረጃዎች፦
* ቁርኣን የወረደባት ሌሊት ነች። ጌታችን “እኛ (ቁርኣኑን) በለይለተል ቀድር አወረድነው”ብሏል። [አልቀድር፡ 1]
* በሷ ውስጥ የተፈፀመ ዒባዳ ከሌሎች ሌሊቶች ምንዳው የበለጠ ነው። አላህ “የመወሰኛዋ ሌሊት ከሺህ ወር በላጭ ናት” ይላል። [አልቀድር፡ 3]
* በሷ ውስጥ መላእክት ኸይርን ይዘው ወደ ምድር ይወርዳሉ። ጌታችን “በርሷ ውስጥ መላእክትና መንፈሱ (ጂብሪል) በጌታቸው ፈቃድ በነገሩ ሁሉ ይወርዳሉ” ብሏል። [አልቀድር፡ 4]
* ሌሊቷ ዒባዳ የሚበዛባት፣ ሰላም የሚሰፍንባት ለሊት ናት። ጌታችን “እርሷ እስከ ጎህ መውጣት ድረስ ሰላም ብቻ ናት” ብሏል። [አልቀድር፡ 5]
* የተባረከች ሌሊት ናት። ጌታችን “እኛ (ቁርኣኑን) በተባረከች ሌሊት ውስጥ አወረድነው” ብሏል። [ዱኻን፡ 3]
* በዚች ሌሊት አላህ በአመቱ ውስጥ ያሉ የፍጡራኑን የእድሜና የሲሳይ ልኬታዎችን ይፅፋል። “በውስጧ የተወሰነው ነገር ሁሉ ይልለያል” ብሏል አላህ። [ዱኻን፡ 4]
* በዚያች ሌሊት ምድር ላይ የሚኖሩት የመላእክት ብዛት ከጠጠሮች ብዛት የበዛ ነው። [አልባኒይ ሐሰን ብለውታል]
* ለተጠቀመባትና አጅሩን ከአላህ ላሰበ ሰው ከወንጀል መማርያ ሌሊት ነች። ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- “ለይለተል ቀድርን አምኖና አስቦ የቆመ ሰው ያለፈ ወንጀሉ ይታበስለታል።” [ቡኻሪና ሙስሊም]
ስለዚህ ይህቺን ወሳኝና እጅግ የላቀ ዋጋ ያላት ሌሊት ለማገኘት የምንችለውን ሁሉ ልንጣጣር ሌሎችንም ልናበረታታ ይገባል። ኢብኑል ቀይም ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “ለይለተል ቀድር በአመት ውስጥ የምትገኝ አንዲት ቀን ብትሆን እሷን ለማገኘት ስል አመቱን ሁሉ እቆም ነበር። በ(ረመዳን) አስር ሌሊቶች ውስጥ ከሆነችማ ምን ነካህ? (እንዴት እዘናጋለሁ?!)” [በዳኢዑል ፈዋኢድ፡ 1/55]
2. ለይለቱል ቀድር የምትገኘው በየትኛው ጊዜ ነው?
የምትገኘው በረመዷን ብቻ ነው። ከረመዷንም በመጨረሻዎቹ አስሮች ውስጥ። ነብዩ ﷺ “ይቺን ሌሊት እየፈለግኩ የመጀመሪያውን አስር ኢዕቲካፍ አደረግኩኝ። ከዚያም መካከለኛውን አስር ኢዕቲካፍ አደረግኩኝ። ከዚያም (የሆነ አካል) መጥቶኝ ‘እሷ በርግጥም የመጨረሻው አስር ላይ ናት’ አለኝ” ማለታቸው ይህን ያስረግጣል።
ይቺ ታላቅ ሌሊት እንዳታልፈን የምንችለውን ሁሉ ልንጣጣር ይገባል። ነብዩ ﷺ በሐዲሣቸው እንዲህ ብለዋል፡- “በሱ ውስጥ ከአንድ ሺ ወር የምትበልጥ ሌሊት አለች። የሷን ኸይር የተነፈገ በእርግጥም (ትልቅ ነገር) ተነፍጓል።” [ሶሒሑል ጃሚዕ፡ 2247]
3. መቼ እንፈልጋት?
ይበልጥ የሚገመተው 27ኛዋ ሌሊት ናት። ይሁን እንጂ “ለይለተል ቀድርን በ23ኛዋ ሌሊት ፈልጓት” ማለታቸው እንዲሁም “ለይለተል ቀድርን በመጨረሻዎቹ አስሩ (ሌሊቶች) ፈልጓት። ከተረታችሁ በመጨረሻዎቹ 7 ላይ አትረቱ” ማለታቸው ለይለተል ቀድር ሁሌ በአንድ ሌሊት ላይ እንደማትገደብ ያስረዳል። በተለይ ደግሞ በዊትሮቹ (21፣ 23፣ 25፣ 27፣ 29) የመሆን እድሏ ሰፊ ነው። ይህን አስመልክተው ነብዩ ﷺ “ለይለተል ቀድርን ከረመዷን በመጨረሻዎቹ አስሩ (ሌሊቶች) በዊትሮቹ ፈልጓት” ብለዋል። [ቡኻሪይና ሙስሊም]
ይህ ማለት ግን ከነጭራሹ በሸፍዕ ለሊቶችም (22፣ 24፣ 26፣ 28፣ 30) አትሆንም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ነብዩ ﷺ “ከረመዷን የመጨረሻዎቹ አስሮች ውስጥ ፈልጓት። ዘጠኝ ሲቀረው፣ ሰባት ሲቀረው፣ አምስት ሲቀረው” ብለዋልና። ወሩ 29 ቀን ከሆነ 9፣ 7፣ 5 ሲቀር ዊትር የሚሆኑት ከመጨረሻ ወደ ኋላ ሲቆጠር ነው። ከመጀመሪያ ለሚቆጥር ግን ዊትር ሳይሆን ሸፍዕ ቁጥር ነው የሚሆኑት። ይህም ሸፍዕ ሌሊቶችም ላይ የመሆን እድል እንዳለ ያስረዳናል። ቢሆንም ግን “ከ(መጨረሻው አስር) በዊትሩ ፈልጓት” ስላሉ ዊትሩ ላይ ይበልጥ ማተኮር ይገባል።
4. በለይለተል ቀድር ምን ይጠበቅብናል?
ዒባዳ ማብዛት። ነብዩ ﷺ “ለይለተል ቀድር አምኖና አስቦ የቆመ ሰው ያለፈ ወንጀሉ ይታበስለታል” ይላሉ። [ቡኻሪና ሙስሊም] እናም በዚች ሌሊት ታላቅነትና መደንገግ አምኖ፣ ከዚያም ለታይታ፣ ለጉራና መሰል አላፊ ኒያ ሳይሆን አጅሩን ከአላህ በማሰብ እንደ ሶላት፣ ዱዓእ፣ ቁርኣን መቅራት፣.. የፈፀመ ሰው ወንጀሉ ይታበስለታል ማለት ነው።
5. ምልክቶቿ
1. “በዚያን ቀን ማለዳ ላይ ፀሀይዋ ነጭ ሆና ጨረር ሳይኖራት ትወጣለች።” [ሙስሊም]
2. በዚያን ሌሊት ዝናብ ሊዘንብ ይችላል። [ቡኻሪና ሙስሊም]
3. ቀጣዩ ቀን አየሩ ሞቃትም ብርዳማም ሳይሆን የተስተካከለ ይሆናል። ፀሀይዋም ደካማና ቀይ ትሆናለች። [ሶሒሑል ጃሚዕ]
እነዚህ ምልክቶች ግን አንፃራዊ ናቸው ይላሉ ሸይኹል አልባኒይ ረሒመሁላህ። በአካባቢው ባለው የአየር ሁኔታ ሊወሰን ይችላል። ስለሆነም በትክክል ለይለተል ቀድር በተከሰተበት ጊዜም እነዚህን ምልክቶች ብዙ የማያያቸው ሊኖር ይችላል።
6. ለይለተል ቀድር ለሰጋጆች ብቻ አይደለችም!
የወር አበባ ላይ፣ የወሊድ ደም ላይ ያሉ፣ መንገደኞች፣ … የዚች ሌሊት ትሩፋት አያልፋቸውም። ማስረጃው ጠቅላይ ነውና። ባይሆን ከሶላት ውጭ ባሉ ዒባዳዎች ላይ ሊበራቱ ይገባል። በዚያች ሌሊት ዱዓእ ማብዛት ጥሩ ነው። እንዲያውም ሱፍያኑ ሠውሪይ ረሒመሁላህ “በሌሊቷ ከሶላት ይልቅ ዱዓእ እኔ ዘንድ የተወደደ ነው” ይላሉ።
7. ለይለተል ቀድር በአይን ትታያለች?
አንዳንዶች በረመዷን የመጨረሻው አስር ሌሊት ላይ እግራቸውን ዘርግተው፣ እያወሩ ሰማይ ሰማይ ያንጋጥጣሉ። የሚጠባበቁት ተወርዋሪ ኮከብ ነው። እሱን ሲያዩ “አኑረን አክብረን” ብለው ይንጫጫሉ። ይሄ ባዶ እምነት ነው። ለይለተል ቀድር አላህ በአንዳንድ ባሮቹ ቀልብ ላይ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ የመረጋጋት ወይም የመለየት ስሜት ከማሳደሩ ውጭ በአይን የሚታይ ነገር አይደለም። የሚታየው ምልክቶቿ እንጂ እራሷ አይደለችም። ሰዎች የሚጠበቅባቸውን ከተወጡ ሌሊቱ ለይለተል ቀድር መሆኑን ባያውቁ እንኳን ትሩፋቷን አያጡም።
8. ለይለተል ቀድር እንደሆነ ውስጡ ያደረ ሰው ምን ያድርግ?
በተለይ ደግሞ ሌሊቱ ለይለተል ቀድር እንደሚሆን ውስጣችንን ከተሰማን ይበልጥ ልናተኩርበት የሚገባን ዱዓእ “አሏሁመ ኢነከ ዐፉውዉን ቱሒቡል ዐፍወ ፈዕፉ ዐኒ” (“ጌታዬ ሆይ! አንተ በርግጥም ይቅር ባይ ነህ። ይቅር ማለትን ትወዳለህ። ስለሆነም ከኔ ይቅር በለኝ” የሚለው ነው። [አልባኒይ ሶሒሕ ብለውታል] ስለዚህ ዋናው ትኩረታችን የአላህን ይቅርታ ለማግኘት ይሁን።
9. ግን ለምን አላህ ለይለተል ቀድርን ስውር አደረጋት?
ዑለማዎች እንደሚሉት ታላላቅ ትሩፋቶች በሚገኝባቸው የረመዷን የመጨረሻ ሌሊቶች ሙስሊሞች በዒባዳ ይበራቱና ይጠናከሩ ዘንድ ነው አላህ ይቺን ሌሊት ስውር ያደረጋት። እናም ለይለተል ቀድርን እንዳታመልጣቸው ሲጣጣሩ ለይተው ቢያውቋት ሊኖራቸው ከሚገባው በበለጠ ለዒባዳ ይተጋሉ። በዚህም ይበልጥ ይጠቀማሉ። ለይተው ቢያውቋት ግን እሷ ብቻ ላይ አነጣጥረው ሌሎቹ ሌሊቶች ላይ ይዘናጉ ነበር። እናም መሰወሯ ነብዩ ﷺ እንዳሉት ለኛ ኸይር ነው። [ቡኻሪይ]
=
(ኢብኑ ሙነወር፣ ሰኔ 29/2007)
የቴሌግራም ቻናል :-
https://t.me/IbnuMunewor
18.6K views11:44