Get Mystery Box with random crypto!

በሱጁደ ቲላዋ ላይ ኢማሙ ምን ላይ እንዳለ ያላወቀ ሰው ምን ያድርግ? ~ በቁርኣን ውስጥ በሶላት ው | Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)

በሱጁደ ቲላዋ ላይ ኢማሙ ምን ላይ እንዳለ ያላወቀ ሰው ምን ያድርግ?
~
በቁርኣን ውስጥ በሶላት ውስጥም ይሁን ከሶላት ውጭ በሚቅቀሩ ጊዜ ሱጁድ የሚወረድባቸው 15 አንቀፆች አሉ። በርግጥ ሱጁዱ ግዴታ አይደለም። ነገር ግን ኢማሙ ሱጁድ ከወረደ መከተሉ ግዴታ ነው።
በሶላት ውስጥ ኢማሙ እነዚህን አንቀፆች ቀርቶ ተክቢራ ሲያደርግ እሱን በእይታ መከታተል የማይችሉ ሰዎች (በተለይም ሌላ ክፍል ውስጥ የሚሆኑ ሴቶች) ኢማሙ ሩኩዕ ላይ ይሁን ወይም ሱጁድ ላይ ይሁን ለመለየት የሚቸገሩበት ጊዜ አለ። በዚህን ጊዜ ምን ያድርጉ?

1ኛ፦ ኢማሙ ሱጁድ ወርዶ ሳለ ተከታዩ ሩኩዕ ከመሰለው

1.1. ኢማሙ ሱጁድ ወርዷል። ተከታዩ ግን ሩኩዕ መስሎት እንዳጎነበሰ ከሩኩዕ ሳይነሳ ኢማሙ ሱጁድ ላይ መሆኑን ካወቀ ኢማሙን ይከተላል። ወደ ሱጁድ ይወርዳል።
1.2. ኢማሙ ሱጁድ ላይ እንደነበር ያወቀው ከተነሳ በኋላ ከሆነ ኢማሙን ተከትሎ ያጠናቅቃል። ሱጁዱ ግዴታ ስላልሆነ ምንም ማድረግ አይጠበቅም።

2ኛ፦ ኢማሙ ሩኩዕ ላይ ሆኖ ሳለ ተከታዩ ሱጁድ ከወረደስ?

2.1. ኢማሙ ሩኩዕ ላይ እንደነበር ካወቀ ተከታዩ ከሱጁድ ተነስቶ ቀጥ ብሎ ከቆመ በኋላ አጠር አድርጎ ሩኩዑን በመፈፀም ይከተለዋል። ሆን ተብሎ የተፈፀመ ስህተት ስላልሆነ ምንም ማድረግ አይጠበቅበትም።
2.2. ተመልሶ ሩኩዑን ሳያስገኝ ከቀረ ግን ሩኩዕ የጎደለው አንዱ ረከዐ ስለማይቆጠር መጨረሻ ላይ አንድ ረከዐ ይጨምራል።

ከዚህ ሁሉ ግን ኢማም የሆነ ሰው የተከታዮቹን ሁኔታ ከግምት ቢያስገባ ጥሩ ነው። የኢማሙን ተግባር ማየት የማይችሉ በመሆናቸው የተነሳ ሰዎች ሊሳሳቱ እንደሚችሉ ከገመተ ወይ ሱጁድ በሌላባቸው አንቀፆች ቢብቃቃ ወይ ደግሞ ሱጁደ ቲላዋውን ቢተወው የተሻለ ነው። ወሏሁ አዕለም።
=
የቴሌግራም ቻናል
t.me/IbnuMunewor