2023-08-27 21:37:55
የአሽዐሪያ ፅንፈኝነት፣ ፈኽሩ ራዚ እንደ ናሙና
~
ፈኽሩ ራዚ (606 ሂ.)፦ የኢብኑ ኹዘይማን ኪታቡ ተውሒድ “በእውነት እርሱ የሺርክ መፅሀፍ ነው” ይላል። [ተፍሲሩ ራዚ፡ 27/582] የሚገርመው የሰለፎችን ዐቂዳ የሚያፀናውን ኪታብ በዚህ መልኩ በሺርክ የሚወነጅለው ራዚ “السر المكتوم في مخاطبة النجوم” የተሰኘ ወደ ከዋክብት አምልኮና ወደ ድግምት የሚጣራ ኪታብ የፃፈ መሆኑ ነው። በዚህ እጅግ ሰቅጣጭ ኪታብ የተደናገጡ አድራቂዎቹ “ይሄ ኪታብ የሱ ስራ አይደለም” ብለው በከንቱ ሊሟገቱ ሞክረው ነበር። ግና ራሱ ራዚ “መጧሊቡል ዓሊያ” በተሰኘው ኪታቡ ላይ የዚህን የድግምት ኪታብ ስምና የራሱ መሆኑን ጠቅሶት መገኘቱና ወደዚህ ሺርክ መጣራቱ ለመከላከል እንዳይመች አድርጎታል። [ገፅ፡ 199፣ 200፣ 210፣ 216፣ 219-222] ይሄ ግልፅ የሆነ ከኢስላም መውጣት ነው። ያለው ቀዳዳ “ምናልባት ሳይቶብት አይቀርም” የሚለው የአንዳንዶች ግምት ነው።
በሚገርም ሁኔታ ራዚ ወደ ቀብር አምልኮ ሲጣራ የአርስቶትል ባልደረቦች የሆነ ጥናት በከበዳቸው ቁጥር ወደ ቀብሩ ሄደው ሲመራመሩ ይገለጥላቸው ነበር ብሎ እንደ ማጠናከሪያ መጥቀሱ ነው። [አልመጧሊብ፡ 243] ሱብሓነላህ! በዚህ ደረጃ ያለ ሰው ነው እንግዲህ የአኢማዎች ኢማም የሆኑትን ኢብኑ ኹዘይማን የሚወርፈው።
ይሄ ብቻም አይደለም። የአላህን ከዐርሹ በላይ መሆን ከሚያስተባብሉ አሽዐሪዮችና ማቱሪዲያዎች ውስጥ የሱና ሰዎችን ብቻ ሳይሆን አልፈው ቁርኣንና ሐዲሥን ጭምር በተሽቢህ (ፈጣሪን ከፍጡር ጋር በማመሳሰል) በግልፅ እስከ መክሰስ ደርሰዋል። ከነዚህ ደፋሮች ውስጥ አንዱ ይሄው ፈኽሩ ራዚ ነው። በመረጃ ነው የማወራው። ይሄውና ንግግሩ፡-
أن الأخبار المذكورة في باب التشبيه بلغت مبلغاً كثيراً في العدد، وبلغت مبلغاً عظيماً في تقوية التشبيه، وإثبات أن إله العالم يجري مجرى إنسان كبير الجثة عظيم الأعضاء! وخرجت عن أن تكون قابلة للتأويل
“በማመሳሰል ርእስ ላይ የተጠቀሱት ዘገባዎች በቁጥር ብዙ መጠን ደርሰዋል። ማመሳሰልን በማጠንከርና የአለሙ አምላክ ግዙፍ ክፍሎች ያሉት ትልቅ አካል እንደሆነ በማፅደቅ ላይ ከባድ ደረጃ ደርሰዋል። ተእዊልን (ቁልመማን) የሚያስተናግዱ ከመሆንም አልፈዋል።” [አልመጧሊቡል ዓሊያ፡ 9/213]
ንግግሩን በጥሞና አስተውሉት። ሸሪዐዊ ማስረጃዎችን በ“ማመሳሰል” መክሰሱን ተውት። አሽዐሪያ ሰፈር የተለመደ በሽታ ነው። ሰውየውም የአላህን መገለጫዎች (ሲፋት) የሚያፀድቁ ማስረጃዎችን ነው ማመሳሰልን ይሰጣሉ፣ ማመሳሰልን ያጠናክራሉ የሚለው። ነገር ግን የአላህን ሲፋት የሚገልፁ የሸሪዐ ማስረጃዎች ከመብዛታቸው የተነሳ ለቁልመማ እንኳን እንደፈተኗቸው ማመኑን አስምሩበት። (ከመቆልመም ባይመለሱም።) በዚህ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የቁርኣንና የሐዲሥ ማስረጃዎችን ገፍተው ከጣሉ በኋላ ነው እንግዲህ ራሳቸውን የተውሒድ ሰዎች አድርገው የሚያቀርቡት። ደግሞም እወቁ! የዛሬዎቹ አሕባሾች ዑለማዎችን ማkፈር ከቀደሙት የጥፋት አስተማሪዎቻቸው የቀዱት ልክፍት እንጂ አዲስ ነገር አይደለም።
የሆነ ሆኖ ራዚ የኋላ ኋላ በከባባድ የዐቂዳ ጉዳዮች ላይ ግራ መጋባቱን ደጋግሞ ይገልፅ ነበር። እድሜውን የፈጀበትን የዒልመል ከላም ፍልስፋና ጥሎ “የአሮጊቶችን መንገድ አጥብቆ የያዘ እርሱ ነው የሚድነው!” ሲል እንደነበር ኢብኑ ከሢር እና ሌሎች አኢማዎች ገልፀዋል። [አልቢዳያ ወኒሃያ፡ 17/12]
Ibnu Munewor
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor
13.9K viewsedited 18:37