Get Mystery Box with random crypto!

“ጥንብ ነችና ተዋት!” ~ ዘረኝነት በነብዩ ﷺ አንደበት “ጥንብ” እንደሆነ ተገልጿል። ጥንብ ላይ | Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)

“ጥንብ ነችና ተዋት!”
~
ዘረኝነት በነብዩ ﷺ አንደበት “ጥንብ” እንደሆነ ተገልጿል። ጥንብ ላይ የሚያንዣብበው ጥንብ አንሳ ነው! ሰው ሁን። ከጥንብ ራቅ። በተቅዋ ከፍ በል። “ከናተ በላጫችሁ ይበልጥ አላህን የሚፈራው ነው” ብሎናል ጌታችን። [ሑጁራት፡ 13] ሐበሻው፣ ጥቁሩ፣ ባሪያው ቢላል፤ ከዐረቡ፣ ከቁረይሺዩ፣ ከነብዩ ﷺ አጎት አቡ ለሀብ የበለጠው በተቀዋው እንጂ በምንም አልነበረም። ሞኝ አትሁን። ከእምነትህ ዘርህን አታስቀድም። አታይምንዴ አላህ ዐረቡን፣ ቁረይሺዩን፣ የነብዩን ﷺ አጎት አቡ ለሀብን ከሀበሻው ጥቁር ባሪያ በታች ሲያደርገው?! መቼም አቡ ለሀብን የሚያወግዝ አንድ የቁርኣን ምእራፍ እንደወረደ የምትዘነጋው አይመስለኝም። ቢላል ግን በኢማኑ ስንቶች የሚቋምጡበትን ማእረግ ነው የታደለው። የነብዩ ﷺ ቅርብ ሰው ነበር። የነብዩ ﷺ ሙአዚን መሆን ምንኛ መታደል ነው?! እርግጠኛ ነኝ ዛሬም ድረስ ቢላል በሙስሊሞች ልቦና ውስጥ ያለው ቦታ ታላቅ እንደሆነ እስክነግርህ አትጠብቀኝም።
የትኛውንም ቋንቋ ስለተናገርክ ከማንም በላይ አይደለህም። ከየትኛውም ብሄር ስለመጣህም ከማንም በታች አይደለህም። ከሁሉ በፊት አንተ ለራስህ ትክክለኛ ቦታህን ስጥ። ሰዎች ስለሰቀሉህ አትሰቀልም። ሰዎች ስላወረዱህም አትወርድም። ለሆሳሱ ሁሉ ስላንተ እየመሰለህ አትሳቀቅ። ለቃላት መጥፎ ትርጉም እየሰጠህ አትሸማቀቅ። በትንሽ በትልቁ ውስጥህ አይደፍርስ። ጥቂት ከጠረጠርክ ሸይጧን ብዙ ያመሳስልብሃል። በዘሩ ሊኮፈስብህም የሚሻ ካለ፣ በማንነትህ ሊንቅህ ከዳዳው በተቅዋ ብለጠው። እሱ ጥንብ ቢያነሳ አንተም ጥንብ ታነሳለህንዴ?!
ሀላፊነት ይሰማህ። ቂል የዘረኝነት እሳት ሲያቀጣጥል አንተ ጋዝ አታርከፍክፍ። ቂል ትከተላለህንዴ? የአረሕማን ባሪያዎች ማለት ቂሎች በቂልኛ ሲያናግሯቸው በነገር ሲተነኩሷቸው ነገር እንዲበርድ የሚያደርጉ፣ ሠላም እንዲሰፍን የሚጥሩ ናቸው። ታዲያ አንተ የማን ባሪያ ነህና?! እርግጠኛ ነኝ “የሸይጧን ነኝ” አትለኝም! የዘረኛ ዘረኝነት ዘረኛ አያድርግህ። የጥንብ አንሳው ጥንብ ማንሳት ጥንብ እንደማያስነሳህ ሁሉ። ሞኝ አትሁን! የሱ ዘረኝነት ላንተ ይቅርታ አይሆንም፡፡ እሱን ሸይጧን ቢጋልበው አንተም ጀርባህን ትሰጣለህ እንዴ? ግን የሸይጧን ፈረስ የሆነ ሰው ምንኛ አስቀያሚ ነው?!
እናም እልሃለሁ ዘረኛው በቆሻሻ ዘረኝነት ውስጥ ሲዋኝ ብታየው ከቻልክ “አላህን ፍራ” በለው። በጥንብ እየተጨማለቀ እንደሆነም አስረዳው። ካልሆነልህ እሱ የያዘውን ጥንብ ለመንጠቅ እንዳትሞክር፤ ወይም ጥንብ ላይ እንዳትሻማ። ዘረኝነትን በዘረኝነት እንዳትመልስ ማለቴ ነው። ሸይጧን ከፊት ሲስብህ፣ ከኋላም ሲገፋህ ዝም ብለህ አትነዳ። “አላህን ፍራ” ማለት ካቃተህ አላህን መፍራት ግን አያቅትህ። ሂሳብ ስራ። ፈሪ ሁን! አዎ! አንድየውን፣ ሁሉን አዋቂ፣ ሁሉን ተመልካች፣ የፍርዱ ቀን ዳኛ… የሆነውን ጌታ የምትፈራ ሁን። አስተውል! “ፈሪ” እባላለሁ ብለህ አትጨነቅ። የፈራሀው አላህን እንጂ ሰው አይደለም! ቀድሞ ነገር አላህን እንደሚፈራ ሰው ጀግና አለና ወይ? በጭራሽ! ነብዩስ ﷺ “ጀግና ማለት በንዴት ጊዜ ቁጣውን የሚቆጣጠር ነው” አላሉምንዴ? ታዲያ ትእዛዛቸውን እናክብራ! ወዳጅ ያምፃልንዴ?!
የሌላውን ብሄር፣ ቋንቋ፣… ከማንቋሸሽ ራቅ። በሌላው ብሄር ላይ ከመሳለቅ ከመቀለድ ተጠንቀቅ። በሌላው ላይ ሲቀለድም አትሳቅ። ለራስህ የማትወደውን ነገር በሌላው ላይ አታድርግ። ይሄ ብዙዎቻችን የተለከፍንበት ገዳይ በሽታ ነው አላህ የጠበቀው ሲቀር። ምናልባት አንተ ስለራስህ ደንታ ቢስ ሆነህ ሊሆን ይችላል። ግን ሁሉ እንዳንተ እንዳልሆነ አትርሳ።
አትጠራጠር! ዘረኝነት የጃሂሊያ ስራ የመሀይሞች መታወቂያ እንደሆነ ታማኙ የአላህ መልእተኛ ነግረውሃል። ልብ በል! በምትናገረው ቋንቋ ከማንም በታች እንዳልሆንክ ሁሉ ከማንም በላይም አይደለህም! ከፍም ዝቅም የሚያደርግህ ስራህ እንጂ ዘርህ አይደለም። “ስራው ያስቀረውን ዘሩ አያስቀድመውም!” አይደል ያሉን ነብያችን ﷺ? ነብዩኮ ልጃቸው እንኳ “የነብይ ልጅ ነኝ” ብላ እንዳትሸወድ ይልቁንም በርትታ ሰርታ እራሷን እንድታተርፍ ነው አደራ ያሏት። ከፍ ማለት ከፈለግክ በኢስላም ከፍ በል፣ በተውሒድ ከፍ በል፣ በሱና ከፍ በል። ከዚህ በራቅክ ቁጥር እየወረደክ፣ እየዘቀጥክ፣ ቁልቁል እየተምዘገዝግክ እንደሆነ ነጋሪ እስኪነግርህ አትጠብቅ።
ጥሪየ ማንነትህን እንድትጥል፣ ማንም በመታወቂያህ ሲረማመድ ዝም እንድትል አይደለም። ይልቁንም ጥሪየ አላህን እንድትፈራ ሚዛንህ እንድትጠብቅ ብቻ ነው። እናም የራስህን አስጠብቅ፣ ከሌሎች አትድረስ። ዘርህን ከእምነትህ ያስቀደምክ እለት ግን አትጠራጠር ታመሃል፡፡ እንዲህ እየገዘገዘህ ህመሙ ካልተሰማህማ ጭራሽ ቫይረሱ አናትህ ላይ ወጥቷል፡፡ ጓደኛህ ይህን ህመምህን እያየ፣ ጥምብ ስታጨማልቅ እየተመለከተህ ዝም ካለህ፤ ወይ እንደ ተናካሽ ውሻ ያገኘኸውን ስለምትነክስ ፈርቶሃል፣ ወይ ደግሞ እሱም እንዳንተው ጥንብ አንሳ ነው ማለት ነው!
አደራ ግን እኔ ይሄን ሁሉ ስለቀልቅ ከችግሩ ነፃ ነኝ እያልኩ አይደለም፡፡ እኔ ቀርቶ ስንት ታላላቆች የሚወድቁበት ችግር እኮ ነው፡፡ ቀድሞ ነገር ታላቅ ሰው ማለት ፍፁም የማይሳሳት ነውንዴ? ከስህተቱ የሚመለስ ነው እንጂ!!! እናም ቫይረሱ ጋር ላለመድረስ ስንሳሳትም ለመመለስ እንጣር፡፡ እንዲህም እንበል፡ “አላሁመ ኣቲ ነፍሲ ተቅዋሃ፣ ወዘኪሃ አንተ ኸይሩ መን ዘካሃ፣ አንተ ወሊዩሃ ወመውላሃ!” “ጌታዬ ሆይ አንተ ለነፍሴ ተቅዋዋን ስጣት፡፡ አጥራትም፤ አንተ ከሚያጠራት ሁሉ በላጭ ነህና፡፡ አንተ ረዳቷም ተንከባካቢዋም ነህ”
=
ኢብኑ ሙነወር
(ሚያዚያ 15/2009)
የቴሌግራም ቻናል :-
https://t.me/IbnuMunewor