2022-12-27 14:05:08
እየተባባሰ የመጣው የአሰሪና ሰራተኛ አለመግባባት…
በሀገራችን በአሰሪዎችና በሰራተኞቻቸው በሚፈጠር አለመግባባትና ሌሎች ምክንያቶች አሰቃቂ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ይስተዋላል ለአብነትም ከወራት በፊት አንዲት ሰራተኛ ሁለት ህጻንትን በአሰቃቂ ሁኔታ ገላ ፍርድ ቤትም የሞት ቅጣት እንደወሰነባት መገለጹ ይታወሳል።
በተጨማሪም የቤት ሰራተኛቸውን ገድለው በሳጥን ለመቅበር ጥረት ሲያደርጉ በአካባቢው ህብረተሰብ ትብብር በቁጥጥር ስር ውለው በ25 ዓመት ጽኑ እስራት የተቀጡት አሰሪዎች ደግሞ ሌላው በሚዲያው ቀረበ ማሳያ ነው፡፡
የፍትህ ሚንስቴር ዛሬ ባወጣው መረጃ ደግሞ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 አስኮ አዲስ ሰፈር ሊዝ መንደር አበቡ ሙላቴ የተባለችው ግለሰብ ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም የወር ደመወዝ አልተከፈለኝም በሚል ቂም ተነሳስታ አሰሪዋን መግደሏን ይገልጻል።
ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤትም በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንድትቀጣ እንዲሁም ማህበራዊ መብቶቹ ለዘወትር እንዲሻሩ መወሰኑን የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በስራ አጋጣሚ ሰዎች በመካከላቸው በሚያስሩት ውል መሰረት አንዱ አሰሪ ሌላው ደግሞ ሰራተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ አሰሪዎች በሰራተኞች መብት እና ደህንነት ላይ አደጋ የሚጥሉ ድርጊቶችን የመፈጸም ስልጣን የላቸውም።
የቤት ሰራተኞችም ደግሞ በሚንከባከቧቸው ህጻናት እና በሚጠብቁት ንብረት ላይ በሚያስከትሉት ማንኛውም ጉዳት ሀላፊነት እና ተጠያቂነት እንዳለባቸው ተጠቅሷል።
ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የወንጀል ህጉ እንደ ወንጀሉ ክብደት ከቀላል እስራት እስከ ሞት ሊያስቀጣ የሚችል የወንጀል ተጠያቂነትን ሊያስከትል እንደሚችል በማወቅ ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ እንደሚኖርበት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ፍትህ ሚንስቴር ከሰሞኑ ያወጣው መግለጫ ያመላክታል፡፡
@tikvahethmagazine
25.3K viewsedited 11:05