2023-06-06 20:07:22
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በሚቀጥለው ዓመት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ይካሄዳል-ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
******
(ኢ ፕ ድ)
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በሚቀጥለው ዓመት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
የዝግጅት ምዕራፍ አካል የሆኑትን የተሳታፊ መረጣና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ የ2015 በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት ለመጨረስ እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች ልየታን በሚያካሂድበት ወቅት ግልፅነት፣ አካታችነት፣ ፍትሐዊ ውክልና፣ አዳዲስ ከዋኞችና ተባባሪዎች እንዲሁም በቂ ጊዜ ታሳቢ እንደሚደረጉ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፣ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የእድሮች ማህበራት ጥምረት፣ የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የወረዳ (ልዩ ወረዳ) አስተዳደር ተወካዮች በተሳታፊ ልየታ ተባባሪነት ተመርጠዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተመረጡ ሲሆን እነሱም፤ እራሳቸውን የሚገልፁበት ዋና መተዳደሪያ ያላቸው ሰዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ዕድሮች፣ የማህበረሰብ መሪዎች /አባቶች/ እናቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ መምህራን፣ የእጅ ባለሙያዎች፣ የንግድ ማህበረሰብ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዝግጅት ምዕራፍ ማጠናቀቂያ የሆኑት የአጀንዳ መሰብሰብና የተሳታፊዎች ልየታ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በየአካባቢው ተፈናቅለው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በያሉበት የመጠለያ ስፍራ እንደ 10ኛ ባለድርሻ አካል የራሳቸውን ተወካዮች የሚያመጡበትን አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በድሬዳዋ፣ በሀረሪ፣ በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሚቀጥሉት 10 ቀናት በነዚህ አካባቢዎች የተጀመረው የልየታና የማሰባሰብ ስራ ይጠናቀቃል ነው ያሉት።
ዜጎች በየትኛውም መንገድ አልተወከልንም ብለው ካሰቡ አጀንዳዎቻቸውን ለኮሚሽኑ በአካል፣ በፖስታ፣ በስልክ፣ በበይነ መረብ የሚያስገቡበት አሰራር መዘርጋቱንም ተናግረዋል።
ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የምክክር ዝግጅቶችን ለማከናወን የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከየአካባቢው አስተዳደሮች ጋር ውይይት በማድረግ በጋራ ለመስራት መግባባት መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።
ኮሚሽኑ በተንቀሳቀሰባቸው አካባቢዎች ህዝቡ ሰላም እንደሚፈልግ እና ጥያቄዎቹንም በውይይት የመፍታት ፅኑ አቋም እንዳለው ተረድተናል ነው ያሉት።
ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም በምክክሩ አስፈላጊነትና አካሄድ ላይ ውይይት አድርጎ ወደ ስራ ለመግባት ደብዳቤ ተፅፎ ምላሽ እየተጠባበቅን ነው ብለዋል።
በመሆኑም ትግራይ ክልልን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች በሚገኙ ወረዳዎች የተሳታፊዎች ልየታና አጀንዳ የማሰባሰብና የመረጣ ስራ አስቸጋሪ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀር የ2015 በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።
ይህን በስኬት በማጠናቀቅ በሚቀጥለው ዓመት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሀገራዊ ምክክሩን ለማካሄድ ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል ከየወረዳዎች 50 ሰዎችን በተሳታፊነት እንደሚልክ ጠቅሰው በሀገራዊ ምክክሩ እስከ 700 ሺህ ኢትዮጵያውያን በቀጥታ ሊሳተፉ እንደሚችሉም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ደረጃ ለሚደረጉ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎች ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ሁለት ሁለት ተወካዮችን ይመርጣሉ ብለዋል፡፡
የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም ለኮሚሽኑ እያደረጉ ያሉትን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
1.1K views17:07