Get Mystery Box with random crypto!

ለድሬዳዋ ፖሊስ የጦር መሣሪያን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር የሚያስችል ሲስተም ሶፍትዌር ተረከበ *** | Ethiopian Press Agency/አማርኛ /

ለድሬዳዋ ፖሊስ የጦር መሣሪያን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር የሚያስችል ሲስተም ሶፍትዌር ተረከበ
*****
(ኢ ፕ ድ)

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የጦር መሣሪያን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር የሚያችል ሲስተም ሶፍትዌር በማበልፀግ ለድሬዳዋ ፖሊስ አስረክበዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የኢትዩጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የፖሊስ ሥራ የሚሳለጠው በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ ሲሰራ መሆኑን ጠቁመው ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ምስጋና አቅርበዋል።

የፖሊስን ተቋም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስታጠቅ የፖሊስን ስራ ቀላል ከማድረጉም በላይ ትክክለኛ የሆነ መረጃ ለማግኘት ወሳኝ በመሆኑ በቀጣይ ፖሊስን የሚያዘምኑ ስራዎች ለመስራት በስትራቴጂክ እቅዱ ላይ በግልጽ የተቀመጡ ግቦችን ወደ ታች በማውረድ ስራዎች በትጋት ይሠራሉ ብለዋል፡፡

በቀጣይ ቴክኖሎጂዎቹን በማስፋት በሁሉም የፖሊስ ተቋማት ተደራሽ የሚሆኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዲቻል የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ኮሚሽነር ጀነራል ገልጸዋል፡፡

ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት የተስማሙበት ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የፖሊስ ተልዕኮዎችን ቀላልና ቀልጣፋ ማድረግ የሚያስችለውን ሲስተም በማበልጸግ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘመናዊ የወንጀል ምርመራውን ለማዘመን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተጠርጣሪውን ሰብአዊ መብት በጠበቀ አኳሃን ስራዎችን መሰራት መጀመራቸውንና የድሬዳዋ ፖሊስ ወደ ድሬዳዋ ከተማ የሚገባ ማንኛውም ሰው መረጃ ቀድሞ እንዲደርሰው የሚያስችልና የሰውን ህይወትና ንብረት እያወደመ ያለውን የትራፊክ አደጋ በቀላሉ መረጃን ለመሰብሰብ የሚያግዙ ሲስተም ሶፍትዌሮችን መዘርጋቱን የሚበረታታ ተግባር ነው ብለዋል።

ሌሎች ከተሞችም የከተማዋን ተሞክሮ በመቅሰም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች ለሀገሪቱ የሚጠቅሙ ጥናትና ምርምሮችን እያደረጉ የፀጥታ መዋቅሩን ሥራን እንዲያጠናክሩ ኮሚሽነር ጀነራሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ስራዎችን ሊያቀሉ የሚችሉ ሶፍትዌሮችን አበልጽጎ መስጠት በመቻሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የድሬዳዋ ፖሊስ በከተማው ያለውን የጦር መሣሪያ መቆጣጠርና ማስተዳደር እንዲችል መደረጉ፣ እየተበራከተ የመጣውን የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችል ሲስተም ሶፍትዌር መጠቀም መጀመራቸው የወንጀል መከላከል ሥራውን ቀላል ከማድረጉም ባሻገር ህገወጦችን በቀላሉ በቁጥጥር ሥር አውሎ ለህግ ለማቅረብ ድርሻው ከፍተኛ እንደሆነ ጨምረው ተናግረዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የድሬዳዋ እና የፌደራል ፖሊስ አመራር እና አባላት፤ የድሬዳዋ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት የየቀጠናው አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡