2023-04-23 17:28:17
የአፍሪካ አገራት በሰሜን ኢትዮጵያ አጋጥሞ የነበረው ችግር ከተፈታበት መንገድ ትምህርት ሊወስዱ ይገባል
- ኡሁሩ ኬኒያታ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት
*****
(ኢ ፕ ድ)
በግጭት ውስጥ ያሉ የአፍሪካ አገራት በሰሜን ኢትዮጵያ አጋጥሞ የነበረው ችግር ከተፈታበት መንገድ ትምህርት ሊወስዱ እንደሚገባ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ተናገሩ።
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በመንግስትና ህወሃት የሰላም ስምምነት የመጣውን ውጤት ተከትሎ “ጦርነት ይብቃ ሰላምን እናጽና” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ወዳጅነት ፓርክ የእውቅና እና ምስጋና መርሃ ግብር በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተከናወነው ስራ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ኩራት ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
የዛሬው እለት የኢትዮጵያውያን ቀን ነው ያሉት ኡሁሩ ኬንያታ "ለሰላም ጥረት ያደረጋችሁ ሁሉ እና መላ ኢትዮጵያዊያን እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚፈለገው ሰላም እውን ሆኗል፤ በመሆኑም በግጭት ውስጥ ያሉ የአፍሪካ አገራት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ችግር ከተፈታበት መንገድ ትምህርት በመውሰድ ሰላም ማምጣት አላባቸው ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
አፍሪካ ለራሷ ችግር በራስ መፍትሄ ማምጣት እንደምትችል በተግባር አሳይታለች ያሉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ የመጣው ሰላም ለመላ አፍሪካዊያን ጥሩ ተምሳሌት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ነው ያሉት።
መጪው ጊዜ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና አጠቃላይ ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና እውን እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር፣ የአፍሪካ ሀብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳፋኪ ማሃማት እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
1.2K views14:28