2023-04-23 17:49:48
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች አፍሪካዊት ሀገር ብቻ ሳትሆን በሰላም ረገድም አርዓያነትን ያረጋገጠችበት አጋጣሚ ነው
- የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር
********
(ኢ ፕ ድ)
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች አፍሪካዊት ሀገር ብቻ ሳትሆን በሰላም ረገድም አርዓያነትን ያረጋገጠችበት አጋጣሚ መሆኑን የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ተናገሩ።
በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት የተፈታበት መንገድ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍትሄ መቅረፍ እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
"ጦርነት ይብቃ፤ ሰላምን እናጽና" በሚል መሪ ሀሳብ በመንግስት እና በሕወሃት መካከል በፕሪቶሪያ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ቁልፍ ሚና ለተወጡ አካላት የዕውቅና እና የምስጋና መርሐግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የተደረሰው የሰላም ስምምነት የተፈረመው ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ሲሆን ቀጥሎም በስምምነቱ ትግበራ አፈጻጸም ላይ ወታደራዊ አመራሮች በኬኒያ ናይሮቢ ከተማ ስምምነት ፈርመው ወደ ተግባር ተግብቶ፤ የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ መደረጉ ይታወቃል።
የዕለቱ መርሐግብርም የተደረሰውን የሰላም ሂደት ለማጽናት ያለመ ነው።
በመርሐግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የተደረሰው የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያውያን ድል ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካዊያን የሁላችንም ኩራት ነው ብለዋል።
የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት የመንግስትና የሕወሃት አመራሮች ወደ ሰላም ለመምጣት ቁርጠኛ አቋም ማሳየታቸውን አስታውሰው፤ አፍሪካ ሕብረትን እና ሂደቱ እንዲሳካ ሚና የተወጡ አካላትን አመስግነዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ዕውን መሆን የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካን ዕውን ለማድረግ ለተያዘው ግብ ስኬት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሰላም ስምምነቱ ዘላቂ ትግበራ ሁሉም ጥረት ማድረግ አለበት ብለዋል።
የሰላም ስምምነቱ ስኬት ወረቀት ላይ መፈረሙ ሳይሆን በተግባር መሬት ላይ ያለው ትግበራ መሆኑን ያወሱት ሚኒስትሯ፤ የድሕረ ሰላም ስምምነት ትግበራው ባደረጉት ክትትል በትግራይ ክልል የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ እየተተገበረ መሆኑን ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።
በቀጣይም ትግበራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለመከላከያ ሰራዊትና ለሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ስምምነቱ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አንድነት ለማምጣት የተገባ ቃል በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ወገኖች በቁርጠኝነት እንዲሰሩም አሳስበዋል።
መሰል የሰላም ሂደቶች አፍሪካ በ2063 አጀንዳ የበለጸገች፣ ሰላሟ የተረጋገጠ፣ አካታች እና ዘላቂ ልማት የተረጋገጠባት አህጉር የማድረግ ግብ እንዲሳካ ሁነኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች ሀገር ብቻ ሳትሆን ችግሮችን በሰላም በመፍታት ለአፍሪካ አርዓያነቷን ያረጋገጠችበት አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተቀረው የአፍሪካ ክፍል የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አህጉር መፍጠር፣ ሰብዓዊ መብት መከበር፣ የዜጎችን ነጻነትና ብልጽግና ዕውን ማድረግ እንዲቻል በጋራ መስራት እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
1.2K views14:49