2023-02-28 17:01:46
የሴት ተማሪዎች የንጽሕና መጠበቂያ ክፍልና የንጹህ መጠጥ ውኃ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።
===================================================
የካቲት 21/2015 (ትምህርት ቢሮ) በባሕር ዳር መሰናዶ ትምህርት ቤት የሴት ተማሪዎች መጸዳጃ ቤት፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ እና ውኃ ማጣሪያ ተገንብቶ ለአገልግት ክፍት ኾኗል፡፡
የባሕር ዳር መሠናዶ ትምህር ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ትዕይንት አባተ ሴት ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ ውስጥ ባለው መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም እንደሚቸገሩ ተናግራለች፡፡
በርካታ ሴት ተማሪዎች የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ይዘው መጥተው መቀየሪያ ቦታ በማጣት ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደቤታቸው ይኼዱ ነበር ፤ ባስ ሲልም ትምህርታቸውን ያቋርጡ እንደነበር ተናግራለች፡፡
የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ መሰረት ብነግረው እሷን ጨምሮ ኹሉም ሴት ተማሪዎች በወር አበባቸው ወቅት የትምህርት ክፍለ ጊዜያቸውን አቋርጠው ወደ ቤታቸው ይሄዱ እንደነበር ተናግራለች፡፡ ይህም በሴት ተማሪዎች የትምህርት ውጤት ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ተናግራለች፡፡
ተማሪ መሠረት አሁን የተሠራው መፀዳጃ ቤት ብቻ ሳይኾን የገላ መታጠቢያ እና የንጽሕና መጠበቂያ ክፍል ያለው በመኾኑ ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ይረዳል ብላለች፡፡
የባሕር ዳር መሠናዶ ትምህርት ቤት መምህሩ ቁምላቸው አይተንፍሱ በትምህርት ቤቱ በተለይ ሴት ተማሪዎች በወር አበባ ወቅት ትምህርታቸውን አቋርጠው ይሄዱ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ አሁን የተገነቡ የመጸዳጃ ቤቶች፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት የሴት ተማሪዎችን ችግር ይቀርፋል ነው ያሉት።
በትምህርት ቤቱ የነበረው የውኃ መሥመር ያረጀ እና የሚቆራረጥ በመኾኑ ሲያነቡ ለመዋል የሚመጡ ተማሪዎች ይቸገሩ እንደነበረ ጠቅሰዋል፡፡ አሁን 60 ሺህ ሊትር ውኃ የሚይዝ ታንከር መገንባቱንም አንስተዋል፡፡ ውኃው ለመጠጥ እና ለመታጠቢያ ተብሎ የተከፈለ በመኾኑ ተማሪዎች ለይተው እንዲጠቀሙም ተናግረዋል፡፡
ከዓባይ ባንክ ጋር በጋራ በመኾን ነዉ ስፕላሽ ኢንተርናሽናል ለትምህርት ቤቱ አገልግሎት መስጫውን የገነቡት። የስፕላሽ ኢንተርናሽናል የባሕርዳር አካባቢ ተወካይ መኮንን አዲሱ ተቋሙ ትምህርት ቤቶች የተሻሻለ መጸዳጃ ቤት፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ምቹ የኾነ የንጽሕና መጠበቂያ ቦታ እንዲኖር አጥብቆ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
አቶ መኮንን ስፕላሽ ኢንተርናሽናል በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በ16 ትምህርት ቤቶች ላይ ደረጃውን የጠበቀ የሴቶች መጸዳጃ ቤት፣የእጅ መታጠቢያ፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ውኃውን አጣርቶ የማቅረብ ሥራ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ከሰኔ 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም የሚቆይ ሲኾን በ54 ትምህርት ቤቶች ላይ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን በ3 ትምህርት ቤቶች ላይ ሠርቶ ማጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ ለሥራው ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም አንስተዋል፡፡
የዓባይ ባንክ የባሕር ዳር ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ ሲሳይ ጸጋዬ ባንኩ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን ለመወጣት እየሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ለሥራው 8 መቶ 50 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን እና ይህን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ስፕላሽ ኢንተርናሽናል ከአባይ ባንክ ጋር በመተባበር በባሕር ዳር መሰናዶ ትምህርት ቤት ያስገነባውን የሴቶች መጸዳጃ ቤት እና ንጹህ የመጠጥ ውኃ ማጣሪያ ግንባታ አጠናቆ ለትምህርት ቤቱ ማስረከቡን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
2. በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን
1.1K views14:01