2023-03-31 13:50:08
"የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ምዝገባ በሁሉም ትምህርት ቤቶች በበይነ መረብ ብቻ ይካሔዳል"የአብክመ ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን
----------------------------//-----------------------
የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ምዝገባ ከመጋቢት 20/2015 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 15/2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡ በክልሉ ከ288 ሺህ በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የመልቀቂያ ፈተና ምዝገባ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ምዝገባ በትምሕርት ቤቶች በበይነ መረብ ብቻ ይካሄዳል ያሉት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን፤ ምዝገባውን በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተደርገዋል ብለዋል፡፡
የአስፈታኝ ትምህርት ቤቶች ርእሳነ መምህራን እና የአይሲቲ ባለሙያዎች በቂ ሥልጠናዎችን እየወሰዱ እንደሆነም በተለይም ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
የተፈታኝ ተማሪዎች ትክክለኛ ቁጥር የሚታወቀው ከምዝገባ በኋላ ነው ያሉት የጽሕፈት ቤት ኅላፊው በመደበኛ የትምሕርት መርሐ ግብር ከ177 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየወሰዱ ነው ተብሏል፡፡ በማታው መርሐ ግብር 1 ሺህ 867 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እየወሰዱ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በትምህርት ዓመቱ በግል ትምህርት ቤቶች ከ48 ሺህ በላይ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው፡፡ በክልሉ 127 ዐይነ ስውራን ተማሪዎች አሉ ያሉት አቶ ጌታቸው ቢያዝን በአጠቃላይ በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከ288 ሺህ በላይ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ምዝገባ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ምዝገባ በትምሕርት ቤቶች ውስጥ በበይነ መረብ ብቻ እንደሚካሄድ የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ ተማሪዎች በአካል በመገኘት ምዝገባቸውን ያደርጋሉ ብለዋል፡፡ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን በድጋሚ የሚወስዱ ተፈታኞች ምዝገባም በተመረጡ ትምህርት ቤቶች እንደሚካሄድ ነግረውናል፡፡ ድጋሜ ተፈታኞች ከዚህ ቀደም የተፈተኑበትን የትምህርት ማስረጃ በመያዝ በአካል መገኘት አለባቸው ብለዋል፡፡ በምዝገባ ወቅት ሁሉም ተማሪዎች ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ መያዝ አለባቸው፡፡
በዘንድሮው ዓመት የፈተና ምዝገባ ያለፉት ዓመታት ችግሮች እንዳይደገሙ በቂ ጥንቃቄ ይደረጋል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የመብራት እና የኢንተርኔት ችግሮች እንዳይፈጠሩ ወረዳዎች ከትምሕርት ጽሕፈት ቤቶች ጋር በቅርበት ይሠራሉ ብለዋል፡፡ በምዝገባ ሂደቱ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆች እና የትምሕርት ባለድርሻ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል። ምዝገባውን ያላካሄደ ተማሪ ፈተናውን አይወስድም ነው ያሉት፡፡
የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) ውስጥ የሚሰጥ ይሆናል። የፈተና ጊዜ በቀጣይ የሚገለጽ ነው ተብሏል፡፡
መረጃው የአሚኮ ነው
811 views10:50