2022-08-25 12:22:40
ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትን ሙሉ በሙሉ ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣትና ባለፈው የትምህርት ዘመንም የደረሰውን የትምህርት ብክነትን ለማካካስ በ2015 ዓ.ም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር አሳሰበ፡፡
ኮምቦልቻ-ነሐሴ 18/2014 (ደቡብ ወሎ ኮሙኒኬሽን)
በደቡብ ወሎ ዞን በ2014 ዓ.ም በአጠቃላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ለመማር ከተመዘገቡት ከ389 ሽህ 355 ተማሪዎች ውስጥ 361 ሽህ960 ተማሪዎች ለፈተና ተቀምጠዋል። 27 ሽህ395 ተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡ ለፈተና ከተቀመጡት ውስጥ ደግሞ 26 ሽህ 252 የሚሆኑት ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን የማለፊያ ውጤት ባለማምጣታቸው ከክፍል ክፍል አልተዛወሩም፡፡
በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ 102 ሽህ 321 ተማሪዎች ለመማር ተመዝግበው 16 ሽህ 992 የሚሆኑት ፈተና ላይ አልተቀመጡም፡፡ ለፈተና ከተቀመጡት ውስጥ ደግሞ 12 ሽህ 992 የሚሆኑት ከክፍል ክፍል አልተዛወሩም፡፡
በ1ኛ ደረጃም ሆነ በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየቀነሰ መምጣቱን የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ መረጃ ያመላክታል፡፡
ለ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን 442 ሽህ 596 ተማሪዎችን በአጠቃላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መዝግቦ ለማስተማር ዕቅድ ተይዟል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 92 ሽህ 90 የሚሆኑት ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት ናቸው፡፡ 133 ሽህ 601 ተማሪዎችን ደግሞ በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መዝግቦ ለማስተማር የዞኑ ምህርት መምሪያ ዕቅድ ይዟል፡፡
በ2014 ዓ.ም የተከሰተውን የትምህርት ብክነት ወደነበረበት ለመመለስ እንዲያስችለውም የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ የዞኑን አጠቃላይ አመራሮች ጨምሮ ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የዕቅድ ትውውቅና የተማሪዎች ምዝገባ ንቅናቄ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ደረጀ አማረ ከጦርነቱ በኋላ ተማሪዎች ከያሉበት በማሰባሰብ ወደ ትምህረት ገበታ እንዲመጡ በማድረግና የትምህርት ቁሳቁስና ግብዓት በሌለበት ሁኔታ የመማር ማስተማሩን ሥራ በአጭር ጊዜ በማስጀመር ዓመቱን ሙሉ ለማስተማር መምህራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ያደረጉት ጥረት የሚመሰገን ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ይሁንና በ2014 ዓ.ም ጦርነቱ ካሳደረው ተጽዕኖ ጋር በተያያዘና በሌሎችም ምክንያቶች መማር የሚገባቸው ተማሪዎች አለመመዝገባቸው እንዳለ ሆኖ አቋራጭ ተማሪዎች እንዲሁም የደጋሚ ተማሪዎች ምጣኔ ከሚጠበቀው በላይ በመሆኑ ቀላል የማይባል የትምህርት ብክነት ደርሷል ብለዋል፡፡
በ2015 ዓ.ም ከባለፈው የትምህርት ዘመን የነበረውን ችግር በመቅረፍ በትምህርት ዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑ መምሪያ ኃላፊው አንስተዋል፡፡ ከነዚህም ዋናው በሕዝብ ንቅናቄ የሚፈፀመው የተማሪዎች ምዝገባ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ዕቅዱን ተገንዝበው የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በዚህም ከነሐሴ 26/2014 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ለአምስት ቀናት የተማሪዎችን ምዝገባ ለማጠናቀቅ የታቀደ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባም ነው መምሪያ ኃላፊው ደረጀ አማረ ያስገነዘቡት፡፡
የመሃል ሳይንት ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ እንዳለ ተመስገን እና የደሴ ዙሪያ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ ጀማል ኢብራሂም ለ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በሽፋንና በትምህርት ጥራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ሥራውን በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ም/ አስተዳዳሪ ተስፋ ዳኛው በጦርነቱ በተለይም በትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት የደረሰ ቢሆንም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የትምህርት ባለሙያዎችና መምህራን የደረሰውን የሥነ ልቦና ጫና ተቋቁመው ፈጥኖ ትምህርት እንዲጀመር በማድረግ የትምህርት ዘመኑን ማጠናቀቅ መቻል ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም የደረሰውን የትምህርት ብክነት ለማካካስ ለ2015 ዓ.ም ለመማር ማስተማር ስኬታማነት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከተማሪዎች ምዝገባ ጀምሮ በአጠቃላይ በትምህርት ሥራ ውስጥ ግብዓት በማሟላትና በሌሎች ተግባራት የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት ይገባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም በአጠቃላይ ትምህርት መቅደላ፣ መሃል ሳይንትና ተንታ ወረዳዎች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን በመያዝ እውቅና ተችሯቸዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ጃማ፣ ቦረናና ደላንታ ወረዳዎች ዝቅተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
10.3K views09:22