2023-05-11 14:07:56
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በመጭው ሐምሌ ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡
==================
ግንቦት 3/2015 ዓ.ም /ትምህርት ቢሮ/ በመጭው ሐምሌ ወር ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራ እያከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ማተብ ታፈረ /ዶ/ር/ ዛሬ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል 215590 ተማሪዎች በ574 አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ መጠናቀቁን የተናገሩት ቢሮ ኃላፊው ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከአመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ያለፈው ዓመት የተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ መሆኑን ዉጤቱ ተተንትኖ ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ መግባባት መደረሱን ያወሱት ኃላፊው በጋራ በመስራት ከችግሩ ለመውጣት የቤት ስራችንን የምንሰራበት ጊዜው አሁን እንደሆነ አክለው ገልፀዋል፡፡
ወላጆች በተማሪዎች መማር ክትትልና ተሳትፎ ከወትሮው በተለየ የተሻለ መሆኑ፣ መምህራን የትምህርት ይዘቱን በጊዜው እንዲሸፈንናለተማሪዎችን ወርክሽቶች በመስራት እንዲሁም ተማሪዎች በጥናታቸው ላይ በቁጭት መስራታቸው በቀጣይ ውጤታማ ለመሆን ያግዛል ተብሏል፡፡
በክልል ደረጃ ለተማሪዎች ሞዴል ፈተና እየተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ቢሮ ኃላፊው በመጭው ሰኔ መጨረሻ ፈተናው ይሰጣል፡፡ ይህም ለተማሪዎች ዝግጅት እንደሚያግዛቸው ተጠቅሷል፡፡
ባለፈው ፈተና የታዩ የተማሪዎች የስነ ምግባር ችግር በዚህ ዓመትም እንዳይደገሙ ተከታታይ የሆኑ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ወደ ፈተና ማዕከል የሚመጣ ተማሪ የስነ ምግባር ጉድለት ከታየበት የሚመለከተው አካል የማይታገስ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለዚህም ወላጆች ጭምር ሃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው ነው የተገለፀው፡፡
በፈተና ወቅት በተማሪዎች የስነ ምግባር ጉድለት እንዳይኖር ወላጆችና መላው ማህበረሰብም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቢሮ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
2. በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን
10.0K views11:07