2023-02-27 15:02:16
ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በ2015 ዓ.ም ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች ገለጻ አደረገ
========================
የካቲት 20/2015 ዓ.ም (ትምህርት ቢሮ) ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በ2015 ዓ.ም ትምህርት ሚኒሲቴር ባወጣው መመሪያ መሰረት ውጤታቸው 50 በመቶና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡ ቁጥራቸው ከአንድ ሽህ በላይ የሆኑ ተማሪዎችን መቀበሉን አስታወቀ፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) እንዳሉት ባለፉት አመታት በነበረው የትምህርት ስርዓት ጥሩ ብቃት ያላቸውና በራሳቸው ሰርተው የመጡ ተማሪዎች እንዳሉ ሁሉ አላማ የሌላቸውና በኩረጃ ጭምር የገቡ እንደነበሩም አይዘነጋም ብለዋል፡፡
በዚህ አመት የገቡ ተማሪዎች ግን በእውቀታቸውና በችሎታቸው እንደ ወርቅ የነጠሩና በአግባቡ ተመዝነው የመጡ ስለሆኑ ዩኒቨርሲቲያችን እነሱን ለማስተማር የሚችሉ በእውቀታቸው፣ በክህሎታቸውና በስነ- ምግባራቸው የበቁ መምህራንን አዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የትምህርት ስርዓቱን ችግር ለመቅረፍ በትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮው አመት የሚጀመረውን የመውጫ ፈተና አሁን ለገቡት ተማሪዎችም ጊዜውን ጠብቆ ስለሚሰጥ እሱንም ከወዲሁ ታሳቢ በማድረግ እራሳቸውን እንዲያበቁና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩም የዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የስራ ክፍሎች ለተማሪዎች የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል፡፡ እነዚህ የስራ ክፍሎች የተማሪዎች አገልግሎት፣ የስነ ምግባርና ስብዕና ግንባታ፣ የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች፣የላይብሪና ዶክመንቴሽን፣የረጅስትራርና አሉሙናይ፣የጋራ ኮርሶች ማስተባበሪያ፣የግቢጥበቃና ደህንነት ዳይሬክተሮችና ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ ለተማሪዎቹ የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች እንዲሁም ህግና ደንቦቻቸውን አበራርተዋል፡፡
በመጨረሻም የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ደረጀ አንዳርጌ (ዶ/ር) እንደተናገሩት በዚህ አመት ለገቡ አዲስ ተማሪዎች የሚያስተምሩ መምህራንን ስንመድብ ባለፉት አመታት ከነበሩት አሰራሮች ለየት ያለና ጥንቃቄ የተሞላበት ነው ብለዋል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም በዘንደሮው አመት የገቡት ተማሪዎች እስካሁን ስናስተናግዳቸው ከነበሩት ተማሪዎች በእውቀታቸው የተሻሉ ስለሆኑ በእውቀትም ሆነ በስነ- ምግባር እነሱን የሚመጥኑ መምህራንን መድበናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
2. በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን
1.7K views12:02