2022-08-23 13:38:00
ትምህርት ቤቶች ሳይንሳዊ እውቀት የሚገበይባቸው ፣የሀገር ፍቅር የሚያድግባቸው ፣እርስ በእርስ መተሣሠብ የሚጎለብትባቸው እንዲሆኑ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ።
***
ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም(ምስራቅ ጎጃም ዞን ኮሚዩኒኬሽን): የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ የ2014 በጀት አመት እቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2015 በጀት አመት የንቅናቄና የእውቅና ፕሮግራም እንደቀጠለ ነወ።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሐም አያሌው ትምህርት ዜጎችን ለመቅረፅና የሃገር እድገት ለማፋጠን ዋነኛው ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ተናግረው ቀጣዩን ትውልድ የምናንፅበት ከመሆኑም ባሻገር ተተኪውን ትውልድ በዕውቀት ፣ በግብረ ገብነት እና በአጠቃላይ በአስተሣሠብ አንፆ ለማውጣት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።
ትምህርት አንዱ የስነ ምግባር ማነጫ ዋና መሣሪያ ቢሆንም አሁን አሁን ይህን አቅሙን አጥቷል "ከእኔ" ወጥቶ "ለእኛ" ብሎ ለሀገር የሚጨነቅ ትውልድ መፍጠር ተስኖን ቆይተናል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የትምህርት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግና በአምሮው የበለፀገ ትውልድ ለመፍጠር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የጎጃም ማህበረሰብ ከልጆቹ የሚሰስትለት አንድም ነገር የለም ያሉት አቶ አብረሐም አያሌው የዞኑን ማህበረሰብ በማሳተፍ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግ ፣ግብዓት ለማሟላትና የተማረ ምዝገባ ስራን ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት እንደሚሰራ ጨምረው ተናግረዋል ።
ዋና አስተዳዳሪው በመጨረሻም ትምህርት ቤቶች ሳይንሳዊ እውቀት የሚገበይባቸው ፣የሀገር ፍቅር የሚያድግባቸው ፣እርስ በእርስ መተሣሠብ የሚጎለብትባቸው እንዲሆኑ ከመቸውም ጊዜ በላይ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አክለው ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አቶ ሙላው አበበ እንደተናገሩት በአሁኑ ሰዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ የመጣውን አሳፋሪ የኩረጃ ተግባር ለማስወገድ ሁሉም አካል ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
በተጠናቀቀው 2014 በጀት አመት በትምህርት ተቋሙ የተሻሉ ተግባራት የተፈፀሙ ቢሆንም በትምህርት ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ስብራትና የትምህርት ጥራት ችግር በመኖሩ መምህራን፣ ወላጆች፣ ተማሪዎችና አጋር አካላት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ያሉት አቶ መላው በ2015በጀት አመት ችግሮች እንዳይደገሙ ከወዲሁ በተማሪዎች ምዝገባ፣ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ትግበራና የመጽሐፍ ስርጭት እንዲሁም ቀጣይ በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተና ትኩረት
ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ አቶ ጌታሁን ፈንቴ በበኩላቸው በተያዘው 2015 በጀት አመት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግና የግብዓት ችግርን ለመቅረፍ ከማህበሰቡና ከሚመለከታቸው አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በመጭው መስከረም 2015 አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል የሚወስዱ ተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከ3.2 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በመመደብ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ተማሪዎችን ለፈተና ዝግጁ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በ2014 በጀት አመት የነበሩ ችግሮችን በመለየት በ2015 የትምህርት ዘመን እንዳይደገሙ በማድረግ ዘርፉን ስኬታማ በማድረግ መምሪያውን በክልል ደረጃ ቀዳሚ ለማድረግ እንደሚሰራ አቶ ጌተሁን ፈንቴ ተናግረዋል።
7.9K views10:38