2021-01-31 12:10:11
የአዲስ አበባ አማራ ወጣቶች ማኅበር 7ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
ባሕር ዳር፡ ጥር 23/2013 ዓ.ም (አብመድ) የማኅበሩ ሰብሳቢ ወጣት ዓባይነህ አስማረ በጉባዔው ላይ እንደገለጸው ማኅበሩ ባለፉት ዓመታት የነበሩበትን አግላይ እሳቤዎች ተቋቁሞ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፤ የተሳሳቱ ትርክቶችን ሞግቷል፤ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖችም ድጋፍ በማድረግ አማራነትን በተግባር አሳይቷል።
ማኅበሩ የተዛቡ ትርክቶችን ለማረም እየሠራ ቢሆንም አሁንም ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች በአማራነታቸው እየተገደሉ መሆኑ በእጅጉ አሳዛኝ ነው ብሏል ወጣት ዓባይነህ፡፡ “መፍትሄ እንዲሰጠውም አጥብቀን እንሰራለን፤ በአማራነት ለአማራነት በከፍታና በተደራጀ መንገድ መቆም አለብን” ብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኀላፊ አቶ አብረሃም ታደሰ የአዲስ አበባ አማራ ወጣቶች ማኅበር በከተማዋ በጎ ፈቃድ ሥራዎችን በመምራትና የአማራ ወጣቶችን አደራጅቶ በማንቀሳቀስ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ቢሮውም ለማኅበሩ ሥራዎች ውጤታማነት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። ማኅበሩ ለበለጠ ጥንካሬ መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር ዓባይ የአማራ ወጣቶች ማኅበር ለተመሰረተበት ዓላማ ስኬት የሠራቸው ሥራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ተናግረዋል። አቶ ዣንጥራር ዓባይ ማኅበሩ በጎ ማድረግን እሴታቸው ያደረጉ ወጣቶች የተሰባሰቡበት ነው፤ በተደራጀና ጨዋነት በተሞላበት መንገድ በአዲስ አበባ ለሚሠሩት ሥራ ከተማ አስተዳደሩ ዕውቅና ይሰጣል ብለዋል።
ማኅበሩ ከየትኛው የፖለቲካ ፓርቲ ነፃ ሆኖ በምክንያታዊነት ላይ የቆመና ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚታገል መሆን እንዳለበት አቶ ዣንጥራር ዓባይ አሳስበዋል።
“በመርህ ሞጋች በመሆንም ትግል ማድረግ አለበት፤ ከቆመለት ዓላማ ሳይዛነፍ ለተመሰረተለት የሕዝብ ጥቅም መሥራት ይገባዋል፤ ከተማ አስተዳደሩም ከጎኑ ነው” ብለዋል። በመድረኩ የታሪክ ተመራማሪዎቹ መምህር ታየ ቦጋለና ጋዜጠኛ ታዲዮስ ታንቱን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ አባላት ታድመዋል። https://www.facebook.com/AmharaMassMediaAgencyAMMA/photos/pcb.1469624993212490/1469623793212610/
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ታደለ - ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
7.2K viewsማሜ, 09:10