2021-02-16 12:37:27
“የጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ከሶስት ወራት በኋላ ወደ ሙከራ ምርት ሊሸጋገር ነው” ስኳር ኮሮፖሬሽን
ባሕር ዳር፡ የካቲት 09/2013 ዓ.ም (አብመድ) በግንባታ ሂደት ላይ የነበረው የጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ከሶስት ወራት በኋላ ወደ ሙከራ ምርት እምንደሚሸጋገር ስኳር ኮሮፖሬሽን አስታወቀ፡፡
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ግንባታው ተጓቷል የተባለለት የጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ፣ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ቀሪ የግንባታ ሂደቶችን አልፎ የፊታችን ግንቦት ወደ ሙከራ ምርት እንደሚገባ ኮርፖሬሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አይችሉህም እንደገለፁት በኮርፖሬሽኑ የተካሄደውን የለውጥ ሥራ ተከትሎ የተጀመሩትን የስኳር ፋብሪካዎች ለመጨረስ ነባሮችን ደግሞ የማምረት አቅም ለማሳደግ ግብ ተጥሎ ሲሰራ ነበር ብለዋል፡፡
የስኳር አቅርቦትን ለማሳደግ በተደረገ ጥረት ሀገራዊ የስኳር ምርት በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በ2012 ወደ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ከሰም፤አርጆ ዴዴሳ፤ኦሞ ቁጥር ሁለትና ሶስት የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ በመግባታቸው የስኳር አቅርቦት እጥረትን መቀነስ እንደተቻለም ነው አቶ ጋሻው የገለፁት፡፡
በግንባታ ላይ ያለው ኦሞ ቁጥር አንድ የስኳር ፕሮጀክት የግንባታ አፈጻጸሙ 83 በመቶ ፤ አሞ ቁጥር 5 ደግሞ ግንባታው 27 በመቶ መድረሱም ተመልክቷል፡፡
በፀጥታ ችግር ምክንያት ግንባታው የዘገየው የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ 93 በመቶ፤ ምዕራፍ ሁለት ግንባታ ደግሞ 85 በመቶ ደርሷል ተብሏል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የስኳር ምርትን ለማሳደግ በስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፤ የነባር የስኳር አምራች ማሽኖችን ብልሽት በመጠገን፤ በቂ የሸንኮር አገዳ አቅርቦት እንዲሁም የመፍጨትና ስኳር የማምረት አቅማቸውን ማሳደግ መቻሉን የስኳር ኮርፖሬሽን ማስታወቁን የዘገበው ኢብኮ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
6.9K viewsማሜ, 09:37