2021-02-13 15:46:53
በአማራ ክልል እያደገ የመጣውን የከተሞች ቁጥር የሚመጥን አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ እና የተጠሪ መሥሪያ ቤቶች የ2013 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም በደብረታቦር ከተማ ተገምግሟል፡፡
የክልሉ ከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት እና የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ተግባራት ተካተው በተገመገሙበት በዚሁ መድረክ ከታዳጊ እስከ ሜትሮፖሊታንት የአማራ ክልል ከተሞች 660 መድረሳቸውና የሕዝቡም ቁጥር በፍጥነት እያደገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ እያደገ የመጣውን የከተሞች ቁጥር የሚመጥን አገልግሎት መስጠት እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
ለከተሞች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ማቅረብና መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠር፣ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ማድረግ፣ የከተማ መሰረተ ልማት ማስፋፋትና ህገወጥ መሬት ወረራን መከላከል ዋና ዋናዎቹ ተግባራት ሆነው እንደተፈጸሙ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ በዘርፉ የሚታየውን ሌብነት ከመታገል አንፃር በየደረጃው ምንጮችን በመለየትና ወደ ሌብነት ተግባር የገቡ የሥራ ኀላፊዎችንም ሆነ ባለሙያዎችን ለማረም የሚደረገው ጥረት መሻሻሉ በስኬትነት ተነስቷል፡፡
በአንጻሩ የዘርፉ አገልግሎት አሰጣጥ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ መሆኑ፣ ተገልጋዮችም በተቋሙ ላይ ሙሉ እርካታና አመኔታ አለመፍጠራቸው፣ ባለድርሻ አካላትን አለማሳተፍና የራስን ችግር ወደሌላ አካል የማሻገር አመለካከት በእጥረትነት ተመላክቷል፡፡
በቀረበው ሪፖርት ሠራተኞች ውይይት አድርገውበታል፡፡ በአካባቢ ልማት ላይ የኅብረተሰብ ተሳትፎ፣ ከተሞች በማዘጋጃ ቤት የአገልግሎት ደረጃዎችን መተግበርና የመሬት ሃብት ቆጠራ መከናወን ጥሩ አፈጻጸም ከታየባቸው ተግባሮች ውስጥ መሆናቸው ተነስቷል፡፡
ህገወጥ ይዞታዎችን የመለየትና የማፍረስ፣ ለልማት ተነሺዎች ትክ ቦታ የመስጠትና ካሳ የመክፈል፣ የሊዝ አፈጻጸምን ኦዲት የማድረግ፣ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ የመስጠት፣ የመንግሥት ቤቶችን የኪራይ ዋጋ የማሻሻልና ሌሎች ተግባራት በግማሽ በጀት ዓመቱ ዝቅተኛ አፈጻጸም ከተስተዋለባቸው ተግባራት መካከል ተጠቅሰዋል፡፡
የበጀት፣ የቁሳቁስ፣ የባለሙያ እጥረትና ከአጋር አካላት ጋር ተናቦ በመሥራት የነበሩ እጥረቶች ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን ዋና ዋና ምክንያቶች ተብለዋል፡፡ በቀጣይም የከተማ ፕላን ሥራዎች ለዝርፊያ የሚጋልጡ ስለሆኑ በጥንቃቄ እንዲመሩና እንዲሠሩ፣ የከተሞችን አቅም ለማሳደግ ሲባል የሚጫን የተጋነነ የቤት ዋጋ ግመታ በስመ ንብረት ዝውውር ላይ እንቅፋት ስለሆነ ለማስተካከል ሊሠራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ለከተማ መኖሪያ ቤት ፈላጊዎች ከዚህ ቀደም 13 ሽህ የሚደርስ ቦታ የተሰጠ ቢሆንም አሁንም ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ለመመለስ ጠንክሮ መሥራት እንደሚጠይቅ ተነስቷል፡፡
ሁሉም የዘርፉ ተቋማትና የሥራ ክፍሎች በቀሪ ጊዜያት እቅዶቻቸውን መርምረውና አሻሽለው የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ እንዲሠሩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የቢሮው የ10 ዓመት መሪ እቅድም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ - ከደብረታቦር
ፎቶ፡- ከአማራ ክልል ከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
5.8K viewsማሜ, 12:46