2021-02-17 16:37:05
የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ትግበራ ላይ ሊሠራ ይገባል ተባለ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ድረ ገጽ አጠቃቀም ላይ ሰዎችን በብሄራቸው፣ በቆዳ ቀለማቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በጾታቸው ፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው በመለየት ከሰዋዊ ክብራቸው ዝቅ በማድረግ ጥቃት ሲፈጽሙ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡
በየዕለቱ ሆነ ተብሎ የፖለቲካ ወይም የገንዘብ ፍላጎትን ለማሟላት ሐሰተኛ ዜና በማሰራጨት የግል ጥቅማቸውን ማሳካት ግባቸውን ባደረጉ ሰዎች ሀገርም ሕዝብም ዋጋ መክፈላቸውን ቀጥለዋል፡፡እነዚህ ሐሰተኛ መረጃዎችም ለበርካታ ጥፋቶች መንስዔ ሆነዋል፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ሆነ ብለው አልያም በስህተት የሚያሰሯጯቸው መረጃዎች በሌሎች ተጠቃሚዎች ላይ በተለያየ መንገድ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ተጠቃሚዎችም ቢሆን መረጃዎችን ሚዛን ላይ አስቀምጦ ትክክለኛነቱን ፈትሾ መጠቀም ላይ አልተሠራም ሲሉ ከአብመድ ጋር ቆይታ የነበራቸው ወጣቶች ምልከታቸውን አንስተዋል፡፡
ወጣት ያለምወርቅ አየለ እንደምትለው የሚለቀቁ መረጃዎች መልከ ብዙ መሆናቸውን መገንዘብ ይጠይቃል ብላለች፡፡ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ትግበራ ላይ ሊሠራ እንደሚገባ አንስታለች፡፡
ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር የመጣው አሰፋ አለምነው ከእውነታ የራቁ የሐሰት መረጃ በመልቀቅ ሀገርና ሕዝብን አደጋ ላይ የሚጥሉ መልዕክቶችን መቆጣጠር ካልተቻል ውጤታቸው የከፋ ነው ብሏል፡፡
አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እና የግል ተወዳጅነትን እና የራስን አስተሳሳብ በሌሎች ለይ ለመጫን የሚደረግ ጥረት ዋጋ እንዳያስከፍል ግንዛቤን ማሳደግ እና የሕግ ማዕቀፉን ሥራ ላይ ማዋል ይገባል ነው ያለው፡፡ በጎ ተጽእኖ የፈጠሩትን፣ መልካም የሠራን፣ ታሪክን እና እውነታን ያሳወቀን ማበረታትት ይገባል ብሏል፡፡
ወጣት ኤርሚያስ ወንድሙ በበኩሉ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚ እንዴትና ለምን መጠቀም እንዳለበት ካለው ግንዛቤ ማነስ የተነሳ የተለጠፉ መረጃዎችን ሁሉ እውነት ነው ብሎ መቀበል እና መልዕክቶችን ማጋራት አብዝቶ ይታያል፤ ይህም ግለሰቦችን ለልዩ ልዩ ችግሮች እየዳረገ ነው ብሏል፡፡ ለዚህ መፍትሄው ደግሞ ምክንያታዊ እና በሀሳብ የሚሞግት ትውልድ መፍጠር ላይ ሊሠራ እንደሚገባ ተናግሯል፡፡
የተማሩና ብዙ ተከታይ ያላቸው ሰዎች ሲያጠፉ እና ሌሎችን ለአደጋ የሚጥሉ ሀሳቦችን ሲያራምዱ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ሥራ ላይ ሊውል ይገባል ብሏል፡፡
ወጣት ጽዮን ተሾመ በበኩሏ መረጃዎችን ከማጋራታችን እና ሀሳቦችን የራስ ከማድረጋችን በፊት የመረጃ ምንጮችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ቀዳሚው ተግባር ሊሆን ይገባል ብላለች፡፡
የአዲስ አበባ የወጣቶች በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ጋር በመተባበር "ወጣትነት በማኅበራዊ ሚዲያ ለመልካም ኢትዮጵያዊነት" በሚል መሪ መልዕክት በአዲስ አበባ 11ዱም ክፍለ ከተማ ለተውጣጡ 200 ለሚደርሱ ወጣቶች የማኅበራዊ ትስስር ገጽ አጠቃቀምን በተመለከተ ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡
የአዲስ አበባ የወጣቶች በጎፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኀላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች አጠቃቀም ዙሪያ የወጣቶች የሰለጠነ እይታን ማስቀደም በመረጃ ይዘትና በግንኙነት ምህዳሩ ላይ ትልቅ ቦታ አለው ብለዋል፡፡
በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ሕዝቡን ለጉዳት እንደሚዳርጉ መገንዘብ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
"የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በተለይ ከፊታችን ላለበትን ትልቅ ሀገራዊ ምርጫ በበጎ ዓላማ በመጠቀም፣ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ለማሳደግ፣ በቅንነትንና ኢትዮጵያዊ ስብዕናን በተላበሰ መልኩ መጠቀም ከቻልን የነገዋን ኢትዮጵያ ዛሬ ሠርተን ለቀጣይ ትውልድ ለማስረከብ ያግዛል" ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን - ከአዲስአበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
8.8K viewsማሜ, 13:37