2021-02-15 17:32:03
በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ449 ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) የትራፊክ አደጋ በሀገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ ለዚህ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዩች መካከልም ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ቀዳሚ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
አቶ ሙሉቀን ገዳሙ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪና በጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኮሜርሻል የጥበቃ አገልግሎት ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፔዳ ቅርንጫፍ የጥበቃ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ አቶ ሙሉቀን ከቀናት በፊት በመስሪያ ቤታቸው በር ላይ በደረሰው አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ እሳቸውና ባልደረባቸው ከሞት ተርፈዋል፡፡ በዕለቱ የሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም የሥነ ልቦና ጫና እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡
ከደቡብ ክልል ዲላ ለትምህርት በመምጣት ላለፉት ሶስት ወራቶች በባሕር ዳር ከተማ ኑሮዋን እንዳደረገች የነገረችን ወጣት ሽቱ ከማል ደግሞ በከተማዋ ምቹና ሰፊ መንገዶች መኖራቸውን ጠቅሳለች፡፡ ይሁን እንጅ ከመንገዶች ምቹነት የተነሳ አሽከርካሪዎች ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከርን እንደ ልምድ መቁጠራቸው ለትራፊክ አደጋ ምክንያት ሆኗል ነው ያለችው፡፡
በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት መምሪያ የትራፊክና ስታስቲክስ ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር ሰጠኝ አለሙ የትራፊክ አደጋ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራትም አንድ ሺህ እንድ መቶ ሃያ አንድ የትራፊክ አደጋ መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ በዚህም
• 449 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል
• 461 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት
• 487 ሰዎች ደግሞ ለቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል
• ከ28 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረትም ወድሟል፡፡
ለአደጋዎች መከሰትም ከ29 በላይ የትራፊክ አደጋ መንስኤዎች ተለይተዋል፡፡ ይሁን እንጅ በቀዳሚነት ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር ብቻ 234 አደጋ ደርሷል፡፡
ለእግረኞች ቅድሚያ ባለመስጠትም 206 አደጋዎች ደርሰዋል፡፡
ይህ ደግሞ ከምንም በላይ የአሽከርካሪዎችን የማሽከርከር ብቃትና ሥነ ባህሪ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን ምክትል ኢንስፔክተር ሰጠኝ አለሙ ገልፀዋል፡፡
አደጋውን ለመቀነስም ተደጋጋሚ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ቢከናወንም አጥጋቢ ውጤት አለመገኘቱን ነው ያስረዱት፡፡ አደጋው እየተባባሰ በመምጣቱም የጋራ መፍትሔ እንደሚሻ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ብናየው ይርሳው (ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተማሪ)
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
9.1K viewsማሜ, 14:32