2021-02-18 14:29:01
"የሱማሊኛ ቋንቋን ለማሳደግ እየተሠራ ነው" የሶማሌ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ አቶ ሙሐመድ የሱፍ ሮብሌ
ቋንቋው የሕዝቦችን ባህል እና አብሮነት ትስስር ከፍ ማድረግ እንዲችል የመገናኛ ብዙኃን እና የፌደራል ተቋማት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡት ተጠይቋል፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) በ80ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በአዲስ ከፀደቁት አምስት የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋዎች አንዱ ነው- የሱማሊኛ ቋንቋ፡፡
የሱማሊኛ ቋንቋ ተጨማሪ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ሆኖ መምጣት ፋይዳው የጎላ ነው ያሉት የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ትምህርት መምህሩ ከማል ሀሽ ለተግባራዊነቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድርሻ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ለሱማሊኛ ቋንቋ እድገት እንዲሠሩም ጠይቀዋል፡፡
የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ የሥነ ቋንቋ ጥናትና ባህሪ በሚል በሱማሊኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል በማደራጀት ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርስቲው ተወካይ ፕሬዝዳንት አቶ ሳላህ ሁሴን ናቸው፡፡ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም የሱማሊኛ ቋንቋን እንዲሰጡ በትብብር እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህም የሱማሊኛ ቋንቋን ከማሳደግ በላይ ያለውን ግንኙነት ከፍ ለማድረግ ዋጋው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚናገረው የሱማሊኛ ቋንቋ ለኢትዮጵያ ሌላ ተጨማሪ ጥቅም ነው ያሉት የሶማሌ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ አቶ ሙሐመድ የሱፍ ሮብሌ "የሱማሊኛ ቋንቋን ለማሳደግ በክልሉ መንግሥት እየተሠራ" ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለስኬቱም አብረው እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡
የሱማሊኛ ቋንቋ ከክልሉ አልፎ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች እንዲነገር፣ የሕዝቦችን የባህል እና የአብሮነት ትስስር ከፍ ማድረግ እንዲቻል የመገናኛ ብዙኃን እና የፌደራል ተቋማት በትኩረት እንዲሠሩ ተጠይቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
5.1K viewsማሜ, 11:29